Saturday, 22 February 2020 11:05

በሃሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(3 votes)

  ከረዥም ዓመታት በፊት፣ ከቀናቱ በአንደኛው ዕለት፡-
“እኔ እንደሰማሁ፣ እኔ እንዳወቅሁ ማንም እንዳይሰማ፣ ማንም እንዳያውቅ…ነግሬሃለሁ” አለችኝ እናቴ፡፡
“ምንድነው ምትይው?”
“ከጓደኞችህ ጋር ትንባሆ ጠጥታችኋል?”
“እ?... ማነው ያለው?”… ተናደድኩ:: “ያለፈው አልፏል፣ እንዳይደገም ብቻ፡፡ አባትህ ከሰማ ይገድልሃል”
“ኡ! ኡ!..አገር ይያዝልኝ” ብዬ ጮህኩ::…እጄን ይዛ ወደ መኝታ ቤቴ ወሰደችኝ፡፡ ከአልጋዬ እግር ጥግ ስር ደብቄ የረሳሁዋትን ሲጋራ አውጥታ…
“ይቺ የማን ናት?” አለችኝ፡፡
…አመዴ ቡን አለ፡፡ አልፎ አልፎ እንደሚይደርጉት ከቤታችን ዝቅ ብሎ ከሚገኘው የነዳጅ ማደያ በሚያመጡት የተቃጠለ ዘይት ቤት ሲወለውሉ መኝታ ቤቴ በመግባታቸው ነበር የተጋለጥኩት፡፡
ያቺን ቀን አልረሳትም፡፡
ወዳጄ፡- ልባችን የሚያውቀውን፣ ያፈጠጠ፣ ያገጠጠ እውነት ምላሳችን ይክደዋል፡፡ ጥፋታችንን አምነን ይቅርታ ጠይቀን ከመታረም ይልቅ ሌሎችን ለመሸንገል፣ ሌሎችን አላዋቂ ለማድረግ እንዳዳለን፡፡ እየዋለ ሲያድር፣ አእምሮ ሲበስል፣ የዋሾ ነው እራሳችንን፣ አላዋቂዎቹም አኛ መሆናችን ሲገባን እንፀፀታለን፡፡ “እውነቱን ተናግሮ በመሸበት ማደር” መቻል ትልቅነት ነው!!
አንድ የድሮ ጨዋታ ነበረች፡-
ሰውየው ለንግድ የሚሆን ገንዘብ ከአንድ በጐ ሰው ይበደራል፡፡ እመልሳለሁ ባለበት ጊዜ መመለስ ስላስፈለገ ከአካባቢው ተሰወረ፡፡
በሌሎች ቦታዎች እየተዘዋወረ ሲነግድ ቆይቶ ወደነበረበት ሲመለስ አበዳሪው ከሰሰው፡፡ ሰውየው ግን በክህደቱ ፀንቶ ከክሱ የሚገላግለውን ነገር ለመሻት ዓዋቂ ፈልጐ አማከረ፡፡ “አባ ነገር” የተባለው ሰውም፣ ተከሳሹ ፍ/ቤቱን አታሎ ነፃ የሚወጣበትን መንገድ ነገረው፡፡
ለወረታውም ሰውየው ከተበደረው ገንዘብ ግማሹን ሊሰጠው ተስማሙ፡፡
በቀጠሮው ቀን ተከሳሹ ከችሎት ፊት ቆመ፡፡ እንደተመከረውም ዳኛው ለሚጠይቀው ጥያቄ ተገቢ መልስ ከመስጠት ፈንታ እንዳልገባው መስሎ እጁን እያወናጨፈ…
“አ…ባአአአ…” እያለ መንተባተብ ጀመረ፡፡
ዳኛውም ወደ ከሳሹ ዞሮ፡-
“”ይኸን የአእምሮ ጉዳተኛ እንዴት ትሞግተዋለህ?...እባክህ ተወው” አለው:: ተበዳዩም የከሰሰውን ሰው ለረዥም ጊዜ ሳያየው ከመቆየቱ ምናልባት ከጊዜ በኋላ የገጠመው እክል ይሆናል” ብሎ በማሰብ ክሱን አነሳ፡፡ አጅሬው በነፃ ተሰናበተ፡፡ ከፍ/ቤቱ ሲወጣ አማካሪው፡-
“አላልኩህም? እንደነገርኩህ ሆነ… እንኳን ደስ ያለህ” ሲለው፤ ሰውየው ምን እንዳረገ ታውቃለህ?...በኋላ ነግርሃለሁ፡፡
***
ወዳጄ፡- ባለፉት ብዙ ዓመታት በአገራችን በተለይ ደግሞ በከተሞች በሚኖረው ህዝብ ላይ የነፃነት ስሜት መቀዛቀዝና በራስ የመተማመን እንከን እንደሚታይ በግል በተደረጉ ጥናቶች ይስተዋላል፡፡ ብዙ ሰዎች በፖለቲካ፣ በእምነት፣ በትዳር፣ በማንነትና በመሳሰሉ ጉዳዮች በሙሉ ፈቃደኛነትና በግልጽነት የሚሰማቸውን መናገር ያዳግታቸዋል፡፡… ነፃነት አይሰማቸውም፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የነበረው የመንግሥት አስተዳደርና የፖለቲካ ሥርዓት ቀስ በቀስ የጫነባቸው ወይም ውስጣቸው እንዲሰርጽ ያደረገው ፍርሃትና ጥርጣሬ አስሮ ጠፍሮና ቀፍድዶ በመያዝ፣ ማወቅ የሚገባቸውን እንዳያውቁ፤ እንዳይመረመሩና እንዳይጠይቁ ስላደረጋቸው ነው፡፡… ከይቅርታ ጋራ!!
ወዳጄ፡- ጎሳን መሰረት ያደረገው አግላይ ፖለቲካና ፕሮፓጋንዳ፣ ዜጎች በግልና በቤተሰብ ጉዳዮች በሚኖራቸው ግንኙነት እንኳ ሳይቀር ተጠራጣሪና ፈሪ እንዲሆኑ ያላደረገው ሙከራ አልነበረም፡፡ የሚፈልጉትን ዓይነት ጥቅም በማቅረብም መመሪያ ተቀባይ ብቻ (Yes men!) ሆነው እንዲቀረፁ ማድረግ የሥርዓቱ ባህሪ ነበር፡፡
በየት/ቤቱ ተማሪዎች ከክፍል ክፍል የሚዘዋወሩበት ፈተናዎች ማርክ አሰጣጥና የኮሌጅ መግቢያ መመዘኛዎች ሳይቀሩ በዚሁ ‹ዜሮ ስም› ፖለቲካ የተቀኙ (infected የሆኑ) ነበሩ፡፡ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና ተቋሞች ውስጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነበር፡፡ የሰው ሀይል ዕድገት፣ ዝውውርና ቅጥርን የሚመለከቱ የውስጥና የውጭ ማስታወቂያዎች በፖለቲካ ዲዛይን ተደርገው፤ በሚስጢር ተለክተው በልክ የተሰፉ መሆናቸውን የሚያውቅ ያውቀዋል:: ፌዴራል በሚባሉት እንደ ባንክና አየር መንገድ ዓይነት መ/ቤቶችም ተመሳሳይ ውንብድና እንደሚፈፀም ማስረጃ አለ፡፡… ከይቅርታ ጋር!!
ወዳጄ፡- ዜጎች ያደረጉትን ለመመስከር፣ የሚሰማቸውን ለመናገር ከማይደፍሩዋቸው ምክንያቶች ዋነኞቹ ራሳቸውንም ሌላውንም አደጋ ላይ የመጣል ስጋት ስላለባቸው፣ እገመታለሁ፣ እገመገማለሁ፣ ከሥራ እታገዳለሁ ወዘተ ብለው ስለሚያስቡ ሲሆን የሌላውን ሰው ስሜት ለመጠበቅ ሲሉ እውነታን የሚሸሹ ምስኪኖችም አሉ፡።
ወዳጄ፡- የሌላ ሰው ስሜት ካልኩ ዘንዳ አንድ ወዳጄ ሲያጫውተኝ፡- በገጠር ከተማ ውስጥ አብረው ያደጉ ጓደኛሞች ነበሩ። አንደኛው ስራ ፍለጋ ሩቅ አገር እንደሄደ እናቱ ያርፋሉ፡፡ ‹ዝም› ማለት ‹እርም መብላት› የሆነበት ጓደኛው፤ የባልንጀራውን አድራሻ አፈላልጎ ስልክ ደወለለት አሉ፡-
‹‹አያ ጓዴ እንዴት ነህሳ?››
‹‹እኔስ ደህና ነኝ፡፡ አንተ እንጂ… ያለወትሮ መደወልህ በደህና ነው? እናቴ ደህና አይደለችም? ››
‹‹እዩት ተጠርጥር›› የሚል ነበር የደዋዩ መልስ፡፡
‹‹አሟት እንደሁ እንጂ ባይሆንም…››
‹‹እዩት ቲቀርብ›› አለ ጓደኛው፤ ሌሎች ሰዎች አጠገቡ እንዳሉ አስመስሎ፡፡
‹‹ዳር ዳር አትበል… ሞታም ከሆነ ንገረኝ ቁርጤን ልወቅ›› አለው…
‹‹አያችሁ ቲረዳ›› በማለት በለሰለሰ መንገድ አረዳው አሉ፡፡
ወዳጄ፡- የሌሎችን ሰዎች ስሜት መጠበቅ ከልብ ሲሆን የፍቅር የርህራሄና የማስተዋል    ብቃት ነው፡፡ ማስመሰል ከሆነ ግን ራስንም ሌላውንም ማታለል ይሆናል - ከይቅርታ ጋር!!
***
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- አጅሬው ፍ/ቤቱን አታሎ በነፃ ተሰናብቶ ከችሎት እንደወጣ፣ ነገር ዐዋቂ ተብየው ተከትሎት፡-
“አላልኩህም? ሃሳባችን ተሳካ፣ በል ድርሻዬን አካፍለኝ” ሲለው የአጅሬው መልስ
“ባ አ አ አ” ማለት ነበር፡፡ “ደባ ራሱን፣ ስለት ድግሡን” እንዲሉ፡፡
በነገራችን ላይ ወዳጄ “When you say” “No” make it sound “Yes” በማለት የፃፈልን ማን ነበር? ..ስሜታችን እንዳይነካ ያሰበልን? መቼም “ሆድህ” እያወቀው ለምን ታደርቀናለህ?” አትሉኝም፡፡
ሠላም!!


Read 1524 times