Saturday, 22 February 2020 11:06

የጠፋችው ሽልንግ!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ
Rate this item
(3 votes)

        ከልጅነት ማስታወሻ!
                  
           ስድስት ወይም ሰባት አመቴ ነበር መሰለኝ:: አንድ እሁድ ከቤታችን ማንም አልነበረም:: ስለዚህ በጧት ሰራተኛችን የእማዬን የእድር ደብተር አስያዘችኝና እንድከፍል ላከችኝ:: ‹ስትመለስ ምን የመሰለ ጨጨብሳ እሰራልሃለሁ› ስትለኝ ቁምጣዬን በቀጫጭን እግሮቼ ሻጥ ሻጥ አድርጌ በረርኩ፡፡ ስመለስ የምበላውን ቁርስ በማሰብ በየመንገዱ የማገኛቸውን ልጆች ሳላዋራ ሮጥኩ:: የእድር ቤቱን አውቀዋለሁና ቀጥ ብዬ ገባሁ፡፡ ሁለት ሽማግሌዎች አንድ ጠረጴዛ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ አንደኛው የፍቃደ አባት ናቸው፡፡ ሁለተኛው ግን የእኛ ሰፈር አይደሉም፡፡ አላውቃቸውም:: ቤቱ ከቆርቆሮ የተሰራ ሲሆን ውስጡ ስገባ ብዙ ቀዳዳዎች ስላሉት በጣም ብዙ የብርሃን ክሮች (ሰበዞች) ተዘረጋግተው አየሁ:: በነዚያ የብርሃን ሰበዞች ውስጥ ደግሞ የሚንሳፈፉ ደቃቅ አቧራዎች ይደንሳሉ፡፡ በየጥጋጥጉ ተደራርበው የተደረደሩ ወንበሮችና ብረትድስቶች፣ ዕቃ የታጨቁ ጆንያዎች፣ በገመድ ተቀጣጥለው የተሰቀሉ ኩባያዎች፣ትላልቅ ትሪዎችና ሽቅብ የተደረደሩ የፕላስቲክ ሳህኖች  ….  ከዚያ ደግሞ…
‹‹…ማነህ ማሞ! ምን ታፈጣለህ!? ወዲህ በል ደብተሩን!?…›› አሉኝ ሽማግሌው ሰውዬ፡፡ ደንግጬ በእጄ የያዝኳትን ቀይ ደብተር አቀበልኳቸው፡፡ በአይኔ ዙሪያዬን ከማየት ግን ልታቀብ አልቻልኩም…
‹‹የማን ነው!?›› ሲሉ ጠየቁኝ፡፡
‹‹የ’ማዬ ነው!›› አልኩ ፈጠን ብዬ፡፡
‹‹…ሃሃሃ … ቂላቂል! እማዬ ማናት!? … ደሞ ጥብቆህን ከፍ አድርገህ ታጠቅ!…›› የብርጭቆ ቂጥ የመሰለ መነፅራቸውን ዝቅ እያደረጉ አስተዋሉኝ፡፡ መነጽሩ እጄታው ስለተሰበረ በጨርቅ ተጠምጥሟል፡፡ ‹በጫማ ማሰሪያ ክር ቢያስሩት ይሻላል!› ብዬ ልናገር ፈለግኩና ፈራሁ፡፡ ደግሞ መነፅሩ ገርሞኝ ሲያበቃ ለካንስ እማዬንም የማያውቅ አለና ስል ድጋሚ ተደመምኩ፡፡ የእኔ እናት ከሁሉም የምትበልጥ ደግና ቆንጆ ናት፡፡ ቁምጣዬን ወደላይ እየጎተትኩ ፈገግ አልኩ፡፡ (ከፊት ለፊት ለሽንት ማስተንፈሻ የተከፈተልኝ ስንጥቅ በዚፕ አይዘጋም፡፡ መጀመሪያ በአንዲት አዝራር የሚዘጋ የነበረ ቢሆንም አዝራሯን በቁማር ስለተበላሁ ነቅዬ (በጥሼ) ሰጥቻለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ዝቅ ያለ ቁምጣዬን ከፍ ሳደርግ ትንጥዬ ወሸላዬ በቀዳዳው እየሾለከች ታስቸግረኛለች፡፡ ጎረቤታችን እትዬ አመዘነች አንዳንዴ እንዲሀ ስሆን ሲያዩኝ ‹‹ ጌታመሳይ ይቺን ምላስህን ሰብስብ፡፡›› ይሉኛል፡፡ መጀመሪያ ሰሞን አይገባኝም ነበር፡፡)  
‹‹...አንተ ሞኝ ደግሞ ቀዳዳህን አትሠፋምንዴ; ሲሉ አምባረቁብኝ ሽማግሌው፡፡ (ፈገግ ብዬ በፍጥነት ጥብቆዬን ሰበሰብኩ፡፡)
‹‹…የአለሜ ልጅ አይደለህም ወይ!?..›› አሉኝ የፍቃደ አባት፡፡  
‹‹አይደለሁም የእማዬ ልጅ ነኝ!›› ሳቅሁ:: አያውቁኝም ማለት ነው፡፡ አለሜ ደግሞ ማናት? … የእኔ እናት ስሟ በእርግጠኛነት እማዬ ነው፡፡
ሁለቱም ሰዎች ፅሁፍ ማንበብ ይቸገራሉ:: ያመጣነውን ብር ይቀበሉና ፊርማ የሚመስል ፅሁፍ ከደብተሩ ሰንጠረዦች አንዷ ላይ አስቀምጠው ይመልሳሉ፡፡ ሁሉም ሰው ቀይ የእድር ደብተር ይሰጣቸዋል:: የሚነበብ ሲኖር የሚያነብላቸው ፍቃደ ነው፡፡ ልጃቸው ታላቄ ቢሆንም ጓደኛዬ ነበር፡፡ እሱ 3ኛ ክፍል ደርሷል፡፡ እኔ ደግሞ ቄስ ትምህርት ቤት ገብቼ  አ . ቡ . ጊ . ዳ …. እያልኩ እውላለሁ፡፡ በርግጥ ፀሎተ ሃይማኖት ጀምሬያለሁ፡፡
‹‹ኸረግ ይህ ደብተር የእድሩ ደብተር አልመሰለኝም፡፡ መጣፊያ ቦታው ሁሉ ተሞንጭሮበታል!›› ሽማግሌው ከጎናቸው ላሉት የእኛ ሰፈር ሰው አቀበሏቸው፡፡
‹‹የአለሜ ልጅ ነው ግድየለም፡፡ ራሱ ፊደል እየተለማመደበት ይሆናል፡፡ እናቱ ብታይ ትቀጣዋለች፤ ቆይ እንነግራታለን፡፡ ለመሆኑ ገንዘቡስ የታል?!›› አሉኝ የፍቃደ አባት፡፡ ከቁምጣዬ ኪስ ጨበጥ አድርጌ አወጣሁና ሰጠኋቸው፡፡ ተጨባብጦ የነበሩ 2 ብሮች ነበሩ፡፡
‹‹ሽልንጉስ!? ሳንቲሙን ወዲህ በል!?...›› ሽማግሌው አፈጠጡብኝ፡፡   
‹‹የተሰጠኝ ይኸው ነው!›› አልኩ ደንግጬ:: ኪሴን ብዳብስ አጣሁ፡፡ ሳንቲሟስ!? የት አደረኳት!? በእጄ ይዣት ነበር፡፡ ብሩን ኪሴ ከተትኩ፡፡ እምባዬ መጣ:: ወየው ጉዴ!? …
‹‹ማን ነው የላከህ!?››
‹‹ቡርቴ ናት!››
‹‹ደግሞ ቡርቴ ማናት!? እንዲያው ህጻናት እየላኩ ይጫወቱብናል አይደል እንዴ!? ስሟን መዝግብልኝ ቆይ ለሚቀጥለው ጉባኤ መቅጣት አለብን፡፡ ይኼኔ ፓስቲውን ገምጦባት ይሆናል --- እንጂማ ይቺን ብቻ አይሰጡህም!›› ሁለቱም ያፈጡብኝ ጀመር፡፡
‹‹እንዴ! ኸረ ማርያምን አልበላሁም!›› ላለቅስ እሩብ ጉዳይ ላይ ቆምኩ፡፡
‹‹ወዲያ! ዱርዬ ጦጣ!…›› ሽማግሌው አፈጠጡብኝ፡፡
‹ዱርዬ አይደለሁ! ምን ቸገረኝ!› ስል አሰብኩ፡፡
እምባዬ መጣብኝ፡፡ ባለፈው አጎቴ በሰጠኝ ገንዘብ ከጓደኞቼ ጋር ሆነን ፓስቲ በልተን በሳማ ቂጥ ቂጤን ተለብልቤያለሁ፡፡ እንብላበት ብሎ የለመነኝ ፍቃደ ነበር፤ እርሱ ግን አልተገረፈም፡፡ ከዚያ ወዲህ በሁሴን ሻይ ቤት አጠገብ ሳልፍ ራሱ የተገረፍኳትን አስታውሳለሁ፡፡ እንዲያውም ለማለፍ እፈራለሁ፡፡
ሌላ ቀን ደግሞ አባቴ ከናስር ሱቅ 3ኪሎ ስኳር ገዝቶ ቤት አድርስ አለኝ፡፡ ልክ እትዬ እልፌ ቤት አጠገብ ስደርስ ጓደኞቼ ሜዳው ላይ ኳስ እየተጫወቱ ነበር፡፡ እኔ ትንሽና ቀጫጫ ስለሆንኩና ጉልበትም ስለሌለኝ ብዙ ግዜ አያስገቡኝም፡፡ እየተንከረፈፍኩ ሜዳውን ሳቋርጥ በአንድ ጊዜ ከበቡኝ፡፡ ከዚያም ትንሽ ትንሽ ስጠን እያሉ ለመኑኝ:: አድርሰህ ስትመለስ እናስገባሃለን ሲሉ ቃል ገቡልኝ፡፡ ትንሽ አሰብኩበትና አንድ አንድ ግዜ ብቻ ዝገኑ አልኳቸው፡፡ ሁሉም ተሰልፎ ይዘግን ጀመር፡፡ 13 ህጻናት መዳፋቸው እስከሚችል አፈሱ፡፡ ሜዳው በአንድ ጊዜ በደስታ በሚንጫጩና መዳፋቸውን በሚልሱ ህጻናት ተሞላ፡፡ ዝንቦቹም በየህጻናቱ አፍና መዳፍ ላይ ተሰብስበው በዓል ሆነላቸው፡፡ ግማሾቹም ድጋሚ እየተሰለፉ ሳያታልሉኝ አልቀሩም፡፡ ብቻ መጨረሻ ላይ የተረፈችውን ይዤ እየበረርኩ እቤት ለቡርቴ ሰጠኋትና እኔ ወደ ሜዳ ለመሄድ ቁምጣዬን እቀይር ጀመር፡፡ ምን ዋጋ አለው! ለካንስ እንዲያ ህጻናቱ ሲራኮቱበት ያዩት ጎረቤታችን፤ ለእማዬ ነግረዋት ኖሮ ራቁቴን እንደቆምኩ መጣችብኝ፡፡
አለንጋዋን ይዛ ካለሁበት ገባችና የመኝታ ቤቱን በር ቀስ አድርጋ ዘጋችው፡፡ ጥፋቴ ወዲያውኑ ፍንትው ብሎ ተገለጠልኝ:: የማይታወቅ መስሎኝ ነበር፡፡ እናቴ ወደ እኔ ስትራመድ ሽንቴን ፊርርር … እንዳደረኩ ይታወሰኛል፡፡ ኡኡኡኡ! እማይዬ በናትሽ! ስወድሽ! አድኑኝ! በማርያም! በገብርኤል!!….. ማን ሰምቶ፡፡ ሌላ ግዜ በዝምታ የምታወቀው ልጅ አለንጋ ሲመጣብኝ ግን ኡኡታዬ ሌላ ቀበሌ ይሰማል፡፡
ቡርቴ ብቻ ‹ወይኔ ልጄን!› እያለች ስታለቅስ ይሰማኛል፡፡ ራቁቴን! እንደ እሳት የሚለበልብ አለንጋ … ቂጤ ቀያይ መስመር እስኪሰራ … የእማዬን እግር ድብን አድርጌ እይዝና እጠመጠምባታለሁ … ማሪኝ እማይዬ እላለሁ!
እና ዛሬም ሊያስገርፉኝ ነውን!? እኔ አልበላሁበትም፡፡ እነዚህ ሽማግሌ ሰዎች ግን ከቁጣ፣ ከስድብና ለእማዬ ከመናገር በስተቀር ምንም አያውቁም ስል አሰብኩ፡፡ ብርር ብዬ ከእድር ቤቱ ወጣሁና ወደ ቤቴ ፈጠንኩ፡፡
‹‹አንተ ማነህ … ማሞ…›› እያሉ ሲጣሩ እንዳልሰማ ሆኜ ወደ ቤቴ ሮጥኩ፡፡
ቡርቴን አገኘኋትና ‹‹ሽልንግ አምጣ አሉኝ!›› አልኳት እምባ እየተናነቀኝ፡፡
‹‹የሰጠሁህኮ 2 ብር ከሃምሳ! ነው፡፡ አንተ ልበ-ቢስ!›› አለች እየሳቀች፡፡
‹‹ኪሴ አድርጌ ነበር፡፡ ወሰድኩና ሰጠኋቸው፡፡ ሳንቲም ግን የለውም::›› ተሳቀቅኩ፡፡ እምባዬም ዱብዱብ ይል ጀመር፡፡ ብድግ አድርጋ እቅፍ አደረገችኝና ‹አይዞህ› አለችኝ፡፡
ቀስ ብላም ‹‹በእጅህ ነበር የሰጠሁህ፤ ከዚያ የት ከተትከው?!››
‹‹ብሩን እዚህ…›› ኪሴን እያሳየኋት:: ‹‹ሳንቲሙን…›› ሳግ ይተናነቀኛል፡፡  ‹‹ሳንቲሙን አፌ ውስጥ አድርጌው ነበር፡፡ ከዚያ ጠፋብኝ…!››
ከት ብላ ትስቅ ጀመር፡፡ ‹‹አይዞህ የኔ ቡችላ! ሁለተኛ ሳንቲም አፍ ውስጥ አይከተትም እሺ! …. ደግሞ ከዛሬ ጀምሮ ካካ ሽንት ቤት አትቀመጥም፡፡ እዚያ ጓሮ ጌሾው አጠገብ ትቀመጣለህ፡፡ እናገኛታለን፡፡ አሁን እንካ ክፈላቸውና ቶሎ ተመለስ፡፡ ቁርሱ ደርሷል፡፡ ደግሞ እንዳትጥል እሺ! ››
እምባዬን እየጠረግሁ ሃምሳ ሳንቲሜን ጨብጬ እንደ ወፍ በረርኩ፡፡ እናም ከዚያ አሮጌ እድር ቤት ስደርስ በኩራት አውጥቼ ሰጠኋቸው፡፡ ‹‹አይ ጎበዝ ልጅ ኖሯል፡፡ ጨዋ ነው! ጎበዝ!…›› አሉኝ ሽማግሌው፡፡ ኩራት ተሰማኝ፡፡ እኮ አላጠፋሁትም!፡፡ ዝም ብለው ይሳደባሉንጂ! ለማለት ፈልጌ ነበር፡፡
እንደ ወፍ በርሬም ወደ ቤቴ ተመለስኩ:: ከዚያም የሚጣፍጥ ጨጨብሳዬን በወተት ግጥም አድርጌ በላሁ፡፡… ጥግብ ካልኩ በኋላ ዕቃ ቤት ቡርቴጋ ሄድኩና ሆዴን እያሻሸሁ … ‹‹ቡርትዬ ነገም እኔ ነኝ የምከፍልልሽ እሺ?!›› አልኳት፡፡  
‹‹እሺ የኔ ቡችላ!›› እየሳቀች አንስታ ታቅፈኛለች፡፡ እናም ወዲያው ታወዛውዘኝ ትጀምራለች፡፡ ቆይ ደሞ የረሳሁትን ሳልነግራት፤ ‹እዚያ እድር ቤት እማዬን አያውቋትምኮ!› ሳልላት፡፡ ‹ጎበዝ ልጅ!› አሉኝ ሳልላት፡፡ ‹ጨዋ ነው!› አሉኝ ሳልላት ….  እኔን የሚያክል የ6 ዓመት ጎረምሳ (በርግጥ በጣም ቀጫጫ ነኝ!) አቅፋኝ እየዘፋፈነች፤ ዘፈኗም ከሩቅ እንደሚመጣ የሚያባባ እንጉርጉሮ እየተሰማኝ … ከገደል እንደሚወርድ ፏፏቴ በጆሮዬ እየፈሰሰ … ድክም ይለኛል….
… የማሙዬ እናት …
ቶሎ ነይለት ….    ምናምን  … ደግሞ … ቆየት ብላ ሌላ ዘፈን …  
… ህፃኑ ማሙዬ በደህና ሰንብት
እገዛልሃለሁ ስመለስ ብስኩት
ብስኩት አደባባይ ሁለት ዛፎች አሉ
እነሱን የነካ ልብ ይሰውራሉ …..
…ምናምን ምናምን እያለች ….. አለም ጣፋጭ ትሆናለች ….  እንቅልፌንም በጠዋቱ ተመልሼ ድብን እላለሁ፡፡
ማታ ላይ ሽንት ቤት እሔዳለሁ ስላት፣ ከጌሾው ስር ታስቀምጠኛለች …. ሳር ቅጠሉን እየቀነጣጠስኩ ሪፖርቴን ስጨርስ፣ ሃምሳ ሳንቲሟ አዲስ የታጠበች መስላ ከዚያ ተቀምጣለች፡፡ ከየት መጣች? እጠራታለሁ … ቡርቴ … ቡርትዬ!…

Read 1743 times