Sunday, 23 February 2020 00:00

‹‹የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥያቄዎች ለማስመለስ ጥረት እያደረግን ነው››

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  - ቤተ ክርስቲያኗ ቦታዎችን በወረራ አትይዝም
  - ከሁሉም የእምነት ተቋማት በጋራ ለመስራት እቅድ አለን


          በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሰማዕተ ጽድቅ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ስም በሚንቀሳቀሰው ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን መብትና ጥቅም አስከባሪ ማኅበር (ጴጥሮሳውያን ኅብረት) የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት መረጃ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ግርማ ተክሉ፤ ኅብረቱ የቤተ ክርስቲያኗን መብትና ጥቅም ለማስከበር እያደረገ ባለው ጥረት ዙሪያ እንዲሁም በቅርቡ በአዲስ አበባ በተለምዶ 24 ቀበሌ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ
ለሁለት ወጣቶች ሕይወት መጥፋት ምክንያት በሆነው ክስተት ዙሪያ ተከታዩን ቃለ ምልልስ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር አድርገዋል፡፡ እነሆ፡-


          ‹‹ጴጥሮሳውያን ሕብረት›› ማን ነው? ለምን ዓላማ ነው የተቋቋመው?
ኅብረቱ፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፣ በማኅበረ ቅዱሳን፣ በመንፈሳውያን ማኅበራት፣ በነገረ መለኰት ኮሌጆች፣ በአድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች የጋራ ጥምረት የተቋቋመ ነው፡፡ በኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች አንድነት፣ የቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀመዛሙርት፣ የሰዋሰው ብርሃን ቅ/ጳውሎስ መ/ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት፣ የነገረ መለኮት ምሩቃን ማሕበር፣ ማሕበረ ቅዱሳን፣ የወጣቶችና ጐልማሶች መንፈሳዊ ማሕበራት ሕብረት፣ የሰልስቱ ምዕት የመንፈሳዊ ማሕበራት ሕብረት፣ የአዕላፋት ድምጽ የካህናት እና የምዕመናን ሕብረት፣ የፈለገ ባኮስ የሰባክያንና የዘማሪያን ሕብረት፣ የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች ተወካይ ናቸው፡፡
ዓላማው፣ በአሁን ሰዓት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰባት ያለውን ፈተናዎች በማሰብ፣ መብቷንና ክብሯን በተለያየ መልኩ ለማስከበር ነው፡፡ በሕብረት ሆነን የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥቅምና መብት ለማስከበር ነው የተቋቋምነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም ለዚህ እንቅስቃሴያችን ዕውቅና ሰጥቶናል፡፡
ሕብረቱ ከተመሠረተ ወዲህ ምን አይነት እንቅስቃሴዎች አድርጓል? ምንስ ተጨባጭ ውጤት አግኝቷል?
ሕብረቱ ከተቋቋመ በኋላ በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ፣ በካህናቶቿ እና በምዕመኖቿ ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችንና ተጽእኖዎችን ለይቶ በማውጣትና በመከታተል ችግሩ ሕጋዊ፣ አስተዳደራዊ እና ፀጥታዊ እልባት የሚያገኝበትን ሁኔታ ለማፈላለግ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ለእነዚህ ችግሮች መንግሥት እልባት እንዲሰጥ ጥረት አድርገናል፡፡ በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ እስከ ክልል ፕሬዚዳንትና እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ ጥያቄያችን አቅርበን የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲሰጥ ጥረት አድርገናል፡፡ ነገር ግን አገሪቱ አሁን ባለችበት አስቸጋሪ የፖለቲካ አንጻር የታሰበውን ያህል ውጤት ባናመጣም፣ መብቷንና ጥቅሟን በማስከበር ረገድ ግን የቻልነውን ያህል ተጉዘናል፡፡
በተለይ ከአዲስ አበባ አስተዳደሩ ጋር በጋራ በመስራት የቤተ ክርስቲያኒቱ ይዞታዎች የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱን በሀሰት ትርክት የሚወነጅሉ፣ ስሟንና ክብሯን በሚዲያ የሚያጠለሹ አካላትን ከድርጊታቸው ለማስቆም እንቅስቃሴ እያደረግን ነው:: በቅርቡ ለብሮድካስት ባለስልጣን ይሄን አስመልክቶ ቅሬታ አቅርበናል፡፡ በተለይ በኦኤምኤን ላይ ቅሬታችንን አቅርበን ምላሽ እየተጠባበቅን ነው፡፡ እነዚህንና ሌሎች የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር በሚያስጠብቁ ሥራዎች ላይ ለወደፊትም እንቅስቃሴአችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡
በቅርቡ በአዲስ አበባ በተለምዶ ወረዳ 24 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ያጋጠመውና ለሁለት ወጣቶች ሞት ምክንያት የሆነውን ነገር፣ ከስረ መሠረቱ መርምራችሁት ከሆነ፣ የደረሳችሁበትን ቢያስረዱን?
አካባቢው ላይ የተከሰተው ችግር አንዳንዶች እንደሚሉት፣ የቅርብ ጊዜ አይደለም፡፡ እዚያ አካባቢ ላይ፣ ቀደም ሲል፣ የኢትዮጵያ፣ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ምንም አይነት ቤተ ክርስቲያን የላትም፡፡ የአጥቢያው ምዕመን ማልዶ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ከፈለገ ወይ ወደ ቅዱስ ዑራኤል፣ ቦሌ መድኃኒዓለም አሊያም መገናኛ አካባቢ ወዳለው ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ነው የሚሄደው፡፡ በእነዚህ ቦታዎች መካከል ደግሞ ከፍተኛ ርቀት አለ፡፡ አረጋውያንና ህፃናት እንዲሁም አቅመ ደካሞች ወደ እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ለመሄድ በእጅጉ ይቸገራሉ፡፡ የሰርክ ጸሎት እና ፕሮግራም፣ የጠዋት ኪዳን የመሳሰሉትን የእምነት ሥርዓታት ለመፈፀም ይቸገራሉ፡፡ ከዚህ አንፃር በአካባቢው የአምልኮ ቦታ የማግኘት ጥያቄ የከረመ ነው፡፡ ከ1998 ዓ.ም አንስቶ የአምልኮ ቦታ ጥያቄው ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክፍለ ከተማ ቀርቧል፡፡ በኋላም በ2008 ዓ.ም ምዕመናኑ ለቅዱስ ፓትሪያሪኩ ጥያቄ አቅርበው፣ ቅዱስ ፓትሪያሪኩም መስከረም 2009 ዓ.ም ለአዲስ አበባ አስተዳደር ጥያቄውን በደብዳቤ አቅርበዋል፡፡ ለጥያቄው አስረጅ የሆኑ ከ50 ገጽ በላይ መጠየቂያ ሰነድ ነበር፣ ለከተማ አስተዳደሩ የደረሰው፡፡ ነገር ግን እስካሁን ምላሽ ሊሰጥበት አልቻለም:: ምዕመናንም ጥያቄያቸውን አላቋረጡም ነበር፡፡
በኮሚቴ ነው የሚንቀሳቀሱት?  
አዎ፤ በተደራጀ መልኩ ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ከ7ሺህ በላይ ሰዎች የፈረሙበትና አጠቃላይ ጥያቄውን የሚያስረዳ ሰነድ ነው፣ ወደ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ያመጡት፡፡ የተደራጀ የምዕመናን ሕብረት አላቸው፡፡ በዚያ መልኩ ነው ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ የቆዩት፡፡ ግን ምላሽ አላገኙም፡፡
አስተዳደሩ ጥያቄውን ተቀብሎ ዝም ነው ያለው ወይስ ታገሱ ምላሽ እንሰጣለን ነው ያለው?
ምንም አይነት የተሰጠ ምላሽ የለም:: ይሄ ጥያቄ በአዲሱ የከተማ አስተዳደር፣ ከሌሎች ጥያቄዎች ጋር አብሮ ይመለሳል ተብሎ ሲታሰብ የነበረ ነው፡፡ በዚህ መሃል ነው የሰሞኑ ችግር የተፈጠረው፡፡ በኛ በኩል ለከተማ አስተዳደሩ ከ131 በላይ ጥያቄዎች ቀርበው የተመለሱት 31 ናቸው:: እነዚህ 131 ቦታዎች፣ አብያተ ክርስቲያናት ታንጾባቸው ነገር ግን የይዞታ ማረጋገጫ ያልተሰጠባቸው ናቸው፡፡ ጥያቄዎቹ፣ በይፋ ለከተማ አስተዳደሩ የቀረቡ ናቸው፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ከቀረቡ በኋላ ደግሞ በልዩ ልዩ ምክንያት መረጃውን ሳያገኙ የዘገዩ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጥያቄውን አምጥተው አሁን ከጠቅላይ ለከተማ አስተዳደሩ የቀረቡ ጥያቄዎች ከ150 በላይ ሆነዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 31 ያህሉ ፈጣን ምላሽ አግኝተዋል ማለት ነው፡፡ ሌሎቹ ጥያቄዎችም የከተማ አስተዳደሩ አብሮ አያይዞ እንዲመልስ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ለጥያቄዎቹ በሙሉ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ለምን ተቸገረ?
ሁለት ምክንያቶች አሉ፡፡ 1ኛ፤ መመሪያ ቁጥር ሁለት የሚባል ጥቅምት 2004 የወጣ አለ፡፡ ይሄ መመሪያ፤ የሃይማኖት ተቋማት ለሚኖራቸው የይዞታ ማረጋገጫ ጥያቄ፣ ምላሽ ለመስጠት የወጣ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ መመሪያ ውስጥ በዝርዝር ማየት የሚቻለው፣ ከአዋጅ 47/67 በፊት የነበሩ ቦታዎች እንዲሁም ከአዋጅ 47/67 በኋላ እስከ 1988 እንዲሁም ከ1988 እስከ 1998 መስከረም ድረስ በዚህ መመሪያ፤ አብያተ ክርስቲያናት ገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ያሉትን የእምነት ተቋማት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲያገኙ ይደነግጋል፡፡ ከዚያ በኋላ ያሉትን ግን መመሪያው አይሸንፍም፡፡ እስከ 1998 ያሉትን ብቻ ነው ይሄ መመሪያ የሚሸፍነው፡፡ ከ1998 በኋላ ስላሉትና በልዩ ልዩ መልኩ የተያዙትን ቦታዎች ግን አይሸፍንም፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ብቻ ሳይሆን የሌሎች አብያተ እምነቶችም ጉዳይ በዚሁ መመሪያ መሠረት፤ ከ1998 ወዲህ የተያዙት አይሸፈኑም፡፡ በዚህም ሳቢያ የይዞታ ካርታ መስጠትን አስቸጋሪ እንዳደረገው ተረድተናል፡፡ የመመሪያ ክፍተት ስላለ ከ1998 ወዲህ ያሉትን ለማስተናገድ የመመሪያ መሻሻል ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው መስተንግዶው የዘገየው፡፡
አሁን ደግሞ ሌላ መመሪያ በ2010 ወጥቷል፡፡ ይሄ መመሪያ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት የማምለኪያ ቦታ ፈቃድ አሰጣጥን የሚደነግግ ነው፡፡ የእምነት ተቋማት ቦታ ከመንግሥት ጠይቀው የሚያገኙበትን ሥርዓት የሚዘረጋ ነው፤ መስፈርቶችም አሉት፡፡ ከ2 ሺህ እስከ 4 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ እንደሚሰጣቸው ያስቀምጣል - መመሪያው፡፡
መስፈርቶቹ ምንድን ናቸው?
መመሪያው ከሚያስቀምጣቸው መስፈርቶች መካከል አንደኛ፣ የሚሰጠው ቦታ ቅይጥ የመኖሪያ ቦታ አቀማመጥ ውስጥ ያለ ሆኖ፣ የመዳረሻ መንገዱ ስፋት ቢያንስ 15 ሜትር ስፋት መሆን ይኖርበታል፤ ይላል:: ሁለተኛ፤ የተጠየቀው ቦታ በአካባቢው ካለው ነባር የአምልኮ ቦታ በሁሉም አቅጣጫ ቢያንስ ሶስት ኪሎ ሜትር የሚርቅ መሆን አለበት፤ ይላል፡፡ በተለያየ የሃይማኖት ተቋማት መካከል ሊኖር የሚገባው የቦታ ርቀት ቢያንስ 5 መቶ ሜትር ሊሆን ይገባዋል፤ ይላል፡፡ ለአምልኮ ቦታ የሚጠየቀው አካባቢ፣ በሁሉም አቅጣጫ በ1.5 ኪ.ሜትር ራዲየስ ወረዳ ውስጥ የተመዘገበና ቢያንስ 7 ሺህ ምዕመን የሚኖር መሆን አለበት፤ ይላል፡፡ እንግዲህ በዚህ መመሪያ መሠረት፤ የ24ቱ ጉዳይ ሲታይ ሁሉንም የመመሪያውን መስፈርቶች ያሟላ ነው። በዚህ መመሪያ  መሠረት፣ ምዕአመናኑ የእምነት ቦታ የማግኘት መብት አላቸው፡፡ የከተማው አስተዳደር ግን ሊያስተናግደው አልቻለም። መመሪያው በሚያዘው መሰረት፣ የምእመናኑን ጥያቄውን ከመመለስ ይልቅ ወደ ጎን በመግፋት፣ የከተማ አስተዳደሩ የሄደበት መንገድ ዋጋ አስከፍሏል፡፡
እንዴት?
አስቀድሜ እንዳልኩት፤ እነዚህ አካላት ጥያቄ አቅርበው ምላሽ ሲያጡ ዝም ብለው አልተቀመጡም፡፡ ከወረዳው እስከ ክፍለ ከተማው የቦታ ጥቆማ ሲያደርጉ ቆይተዋል:: ጥያቄውንም ለሚመለከታቸው አካላት አቅርበዋል፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም፣ የምዕመናንን ጥያቄ መሠረት በማድረግ፣ ጥያቄውን ለወረዳ 4 አቅርቧል፡፡ ነገር ግን ደብዳቤውን እንኳ የወረዳው አመራሮች አንቀበልም፤ ብለው ነው የመለሷቸው። ሕጋዊውን ጥያቄ ነው አንቀበልም ያሉት፡፡ ጥያቄዎች ደግሞ ከወረዳ ነው የሚጀምሩት:: በሕጋዊ መልኩ ለቀረበ ጥያቄ ወረዳው ሕጋዊ መልስ ነበር መስጠት የነበረበት፡፡ ከዚህ በፊትም አስቀድሜ እንዳስረዳሁት፣ እስከ ከተማ አስተዳደሩ የደረሰ ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ አልተሰጠም፡፡ በዚህ መሀል የዚህን ቦታ ማስተር ፕላኑን በማሻሻል፣ ለሌላ የእምነት ተቋም ሊሰጥ እንቅስቃሴ እየደረገ መሆኑን የአካባቢው ምዕመናን ይረዳሉ:: በዚህ መሀል የአካባቢው ሰው የራሱን እንቅስቃሴ አደረገ ማለት ነው፡፡
በሀይል ቦታውን መያዝ ተገቢ ነው?
በሕገ ወጥ መልኩ ቦታን መያዝ ተገቢ አይደለም፡፡ ይሄ ጥርጥር የለውም፡፡ ሕገ ወጥነትን ቤተ ክርስቲያን አትደግፍም:: ነገር ግን ያለውን እውነት ስንመለከት፣ አስተዳደሩ በተገቢው መንገድ ሕግንና መመሪያ በሚፈቅደው አግባብ ምላሽ በወቅቱ ባለመስጠቱ የተፈጠረ ችግር ነው። ትልቁ ኃላፊነት ያለው መንግሥት ጋር ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ እውነት መጥቀስ እፈልጋለሁ:: የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በአዲስ አበባ ውስጥ ያሏት አብያተ ቤተ ክርስቲያናት በተለይ ከ20 ዓመት ወዲህ ያለውን ብንመለከት፣ ከየትኛውም የመንግሥት ተቋማት የተሰጡ አይደሉም፡፡ መንግሥት የሃይማኖት ተቋማትን በሙሉ በፍትሃዊነት በእኩልነት ሊያገለግልበት መመሪያ ያዘጋጀው ከ2004 ዓ.ም በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በፊት የሃይማኖት ተቋማትን የመሬት ጥያቄ የሚያስተናግድበት መመሪያ አልነበረውም፡፡ መመሪያው ከወጣ በኋላም እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ፣ መንግሥት ለየትኛውም የእምነት ተቋማት ለሙስሊም፣ ለክርስቲያንም ሆነ ለፕሮቴስታንት ሰጥቶ አያውቅም፡፡ መመሪያው 2010 ከወጣ በኋላም ቢሆን መንግሥት ለየትኛውም የእምነት ተቋም ሕጋዊ ቦታ ሰጥቶ አያውቅም፡፡ መንግሥት ያወጣቸውን መመሪያዎች ቢተገብር ኖሮ፣ በየትኛውም የእምነት ተቋም ዘንድ የፈለገውን ቦታ በወረራ ለመያዝ ዝንባሌ አይታይም ነበር፡፡ ችግሩን የፈጠረው የመንግሥት ክፍተት ነው እንላለን፡፡ መንግሥት፣ ‹‹እዚህ ቦታ ለዚህ እምነት ተቋም ይሄን ያህል ቦታ ሰጥቻለሁ›› ለሚለው መረጃ ማቅረብ አይቻልም:: በአመዛኙ አብያተ ክርስቲያናት ሲገነቡ የነበረው፤ በግለሰቦች በሚሰጥ የስጦታ ቦታ ላይ፣ በኑዛዜ፣ በውርስና በግዥ ነው:: በሕጋዊ መንገድ ከመንግሥት በራሳቸው ቦታ ማግኘት ሳይቻል ሲቀር፣ የእምነት ተቋማት ቦታ ወደ መያዝ ይሄዳሉ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት በእኩልነት የማግኘት መብታቸው ስለሚነካ፣ በዘፈቀደ በመኖሪያ ቤት በመሳሰለው ጭምር ይመሠረታሉ:: ለዚህ ሁሉ ትርምስ መነሻው የከተማ አስተዳደሩ መመሪያዎቹን አለመተግበሩ ነው፡፡
የ24ቱ ቦታ ለሌላ የእምነት ተቋም ሊሰጥ ነው፤ የሚለው ማስረጃ አለው?
አለ፡፡ ደብዳቤው እጃችን ላይ ይገኛል:: በግል ነው ቦታውን ከአንድ ወር በፊት ጥያቄ ላቀረበ አካል ሊሰጡት ያሰቡት፡፡ አስቀድሞ ጥያቄውን ላቀረቡት ምእመናን ቢሰጡ ኖሮ (ሌላም ቦታ ሊሆን ይችላል) ችግሩ ባልተፈጠረ ነበር፡፡ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ቦታው ቢሰጣቸው እኮ የሚቃወም የለም፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ ከምእመናን የቀረበ ጥያቄ ሳይስተናገድ፣ ከወር በፊት ጥያቄ ላቀረበ አካል ለመስጠት መዘጋጀት ተገቢ አይደለም፡፡ በዚህ የተነሳ የሁለት ንጹሃን ወጣቶች ደም በግፍ ፈሷል:: ይሄ ያሳዝናል:: አሁንም መፍትሄው የማህበረሰቡን ጥያቄ መመለስ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያኗ፣ ‹‹የገበሬውን ቦታ እየወረረች ነው›› የሚል ወቀሳም ይሰነዘራል?
ይሄ ፍጹም ስህተት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ቦታዎችን በወረራ አልያዘችም፡፡ በስጦታ፣ በኑዛዜ፣ በግዥ ነው ቦታዎችን እያገኘች ያለችው:: ይልቅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ ‹‹የገበሬ ልጅ ነን›› የሚሉና የአካባቢው ልጆች ያልሆኑ ግለሰቦች፣ ‹‹ቤተ ክርስቲያን ቦታችንን ወረረች እያሉ በደል እያደረሱባት ነው ያለው፡፡ በቦሌ እና በየካ ክፍላተ ከተማ ቢኬድ፣ በሀሰት ምስክርነት፤ “የገበሬ ልጅ›› እየተባሉ የቤተ ክርስቲያን ቦታን ተቀራምተዋል፡፡ ‹‹ቦታው የኛ ነው፤ ያለአግባብ ነው የተወሰደብን›› እያሉ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ጫናና በደል እየፈፀሙ ነው ያሉት፡፡ እንደውም አሁን ቤተ ክርስቲያን ካሏት ምዕመናን አንፃር፣ ያላት የአብያተ ክርስቲያናት ቁጥር እጅግ ጥቂት ነው:: ያንሳታል፤ መጨመር አለበት፡፡
የአብያተ ክርስቲያናትን ጉዳይ በተመለከተ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ምን አይነት ውይይት እያደረጋችሁ ነው?
እውነት ለመናገር፣ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር፣ በፊት ከነበረው ይልቅ አሁን በተለይ ከክቡር ም/ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ ጋር በቅርበት እየሰራን ነው ያለነው፡፡ ሁለት ሀሳቦችን አቅርበንላቸዋል፡፡ 1ኛው፣ 1998 ዓ.ም ላይ የቆመው መመሪያ ተሻሽሎ ወጥቶ፣ ከዚያ በኋላ የታነፁ የትኛውም የእምነት ተቋማትን በሚጠቅም መልኩ አካትቶ፣ ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ እንዲሰራ ጠይቀናል:: ከሁሉም አብያተ እምነቶች፣ እስልምና፣ ኦርቶዶክስና ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ጋር በጋራ ሆነን፣ በዚህ መመሪያ ላይ ሀሳብ ሰጥተን፣ የመመሪያውን መጽደቅ እየጠበቅን ነው፡፡ ይሄ መመሪያ ብዙ ጥያቄዎችን ይመልሳል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ሁለተኛው፤ ለከተማ አስተዳደሩ ያቀረብነው ሀሳብ፣ ሁሉም አብያተ እምነቶች፣ የወጣውን መመሪያ ለማክበር የምንመራበት የጋራ ፖሊሲ ቢኖረን፤ ብለን ተነጋግረናል፡፡ ‹‹የእስልምና እምነት ተከታዮች ቦታ ሲቸገሩ ይሰጣቸው›› የሚል ኦርቶዶክሳዊ፣ ‹‹ኦሮቶዶክሶች ሲቸገሩ ይሰጣቸው›› የሚል ፕሮቴስታንት መኖር አለበት፤ በሚል ቀና መንፈስ፤ ከሁሉም አብያተ እምነቶች የተውጣጣ አንድ አካል ተቋቁሞ፣ ለመንግሥትም የፖሊሲ ግብአት ሰጥተን አብረን ተጣጥመን የምንሄድበት አንድ የጋራ ፕሮጀክት ይኑረን፤ ብለን ለክቡር ም/ከንቲባው ሀሳብ አቅርበናል፡፡ እርሳቸውም ሀሳቡን ወደውት ወደሚመለከተው አካል መርተውታል፡፡ በሌላ በኩል፣ 2010 ዓ.ም የወጣው መመሪያም ተተግብሮ፣ በምደባ የአብያተ እምነቶች የቦታ ጥያቄ እንዲስተናገድም ተወያይተናል፡፡ ከንቲባው እነዚህን ሁሉ በቀናነት ተቀብለው እያስተናገዱን ነው ያሉት፡፡
የ24ቱ ጉዳይ በዚህ ውስጥ ያለ ነው?
የ24ቱ ጉዳይ የሞራልም ጉዳይ አለው:: መሥዋዕትነት የተከፈለበት ነው:: ወንድሞች የሕይወት ዋጋ የከፈሉበት ነው፡፡ አዛውንቶች፣ ወጣቶች የእምነት ቦታ እንዲሰጣቸው ዛሬም እየጠየቁ ነው:: ጥያቄው አልቆመም፤ ነገም ይጠየቃል:: ስለዚህ የከተማ አስተዳደሩ ይሄን መመለስ አለበት፡፡ ጥያቄው ደግሞ ሁሉንም የመመሪያ መስፈርት አሟልቷል፡፡ መስፈርቱ ይደግፋቸዋል፡፡ መንግሥት ሰክኖ፣ ራሱን አይቶ፣ ለጥያቄው ምላሽ መስጠት አለበት:: ወረዳው እና ክፍለ ከተማው ተባባሪዎች ስላልነበሩ ነው፣ የከተማ አስተዳደሩ ቦታው ለሌላ አካል እንዲሰጥ የወሰነው እንጂ፣ የከተማ አስተዳደሩ አውቆ ያደረገው አልነበረም፡፡
ከንቲባው አያውቁትም እያሉኝ ነው?
ቦታው አሁን ይሰጥ ለተባለው አካል መፈቀዱን ያውቃሉ፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ግን ቦታው ላይ ጥያቄ እንዳላቸው ያውቃሉ፤ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ምክንያቱም እሳቸው የቤተ ክርስቲያናችንን ጥያቄ ለማስመለስ በምናደርገው ጥረት ውስጥ እጅግ ተባባሪና ደጋፊ እንደሆኑ አውቃለሁ:: ወረዳው እና ክፍለ ከተማው ስለ ቦታው ማስረዳት ነበረባቸው፡፡ ሸክሙ ያለው በወረዳው እና በክፍለ ከተማው አካላት ላይ ነው፡፡ ከንቲባው የተፈጠረውን የተወሳሰበ ችግር የተረዱት፣ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ነው፡፡
 የባሕረ ጥምቀተ ባህር ቦታዎችም ጥያቄ ይነሳባቸዋል?
አዎ፤ ነገር ግን የከተማ አስተዳደሩ ቀድሞ ምላሽ እየሰጠ ነው፡፡ የባሕረ ጥምቀት ይዞታዎቹን በቤተ ክርስቲያን ይዞታ ሥር እናደርጋለን፤ ብለው ከንቲባው ቃል ገብተው፣ ወዲያው ተፈፃሚ እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡ 71 ቦታዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ 6ቱ በኦሮሚያ ክልል ስር የሚገኙ ናቸው፡፡ ጥቂት የማይባሉት በአርሶ አደር ይዞታ፣ በአረንጓዴ ቦታ ሥር ናቸው፡፡ ነገር ግን የ35 የጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎችን ካርታ፣ ከጥምቀት ወዲህ የከተማ አስተዳደሩ አስረክቦናል፡፡ ሌሎቹም በሂደት ላይ ናቸው፡፡ እንቅስቃሴያችን ብዙ ውጤት ሊያመጣ የሚችል መሆኑን ህዝበ ክርስቲያኑ እንዲገነዘብልን እፈልጋለሁ:: ከሁሉም የእምነት ተቋማት ጋራ ደግሞ በጋራ እንሠራለን፤ ለመሥራትም እቅድ አለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ ትብብራችን የበለጠ አጠናክረን በጋራ እንድንሠራ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

Read 3730 times