Saturday, 22 February 2020 12:32

የልጆች ጥግ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)


       ውድ ልጆች፡- በቤት ውስጥ ሁሉም ነገር የየራሱ ቦታ አለው፡፡ ፍራፍሬ (ሙዝ፣ ብርቱካን፣ ወይን፣ ወዘተ) በቅርጫት ወይም በፍራፍሬ ቦውል ውስጥ ይቀመጣል:: የቆሸሸ ልብስ ደግሞ ቅርጫት ውስጥ ይጠራቀማል፡፡ የሕጻናት መጫዎቻዎች ተሰብስበው የሚቀመጡበት ሳጥን ወይም ካርቶን ይኖራቸዋል፡፡ ማናቸውንም ነገሮች በምትፈልጓቸው ጊዜ ብቻ  ነው አውጥታችሁ መጠቀም ያለባችሁ፡፡ ተጠቅማችሁ ስትጨርሱም… ወዲያውኑ እቦታቸው መመለስ አለባችሁ፡፡ ያለበለዚያ ግን ሌላ ጊዜ ስትፈልጓቸው በቀላሉ አታገኟቸው፡፡ አንዳንድ ነገሮች እየጠፋብችሁ የምትቸገሩት ለምን ይመስላችሁ? በትክክለኛ ቦታቸው ስለማታስቀምጧቸው ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉንም ነገር በቦታ በቦታው ማስቀመጣችሁን አትዘንጉ!  
ውድ ልጆች፡- ቤት ውስጥ የተበላሸ ወይም የተዘበራረቀ ነገር ካለ ወዲያውኑ አስተካክሉት፡፡ የሚያደናቅፍ ነገር ካያችሁ፣ ቶሎ ብላችሁ አንሱት፡፡ እናንተን ወይም ሌላ ሰው ሊጥል ይችላል፡፡ ውሃ ወይም ለስላሳ ወለሉ ላይ ከፈሰሰ ዝም ብላችሁ አትለፉት፤ አድርቁት፡፡ መሬት ላይ የወደቀ ሶፍት ወይም ወረቀት ከተመለከታችሁ አንስታችሁ የቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ ጨምሩት፡፡ እናንተ መስራት የምትችሉትን ነገር፣ ሌላ ሰው እንዲሰራላችሁ አትጠብቁ፡፡
ውድ ልጆች፡- ከት/ቤት ስትመለሱ፣ ዩኑፎርማችሁን ቀይራችሁ፣ አልጋ ላይ ወይም እዚህና እዚያ  መጣል ተገቢ አይደለም:: በትክክል አጣጥፋችሁ ማስቀመጥ  አለባችሁ:: ጫማና ካልሲያችሁንም እንደዚያው፡፡ መኝታ ቤታችሁንና የጥናት ክፍላችሁን ምንጊዜም ንፁህ አድርጉት:: ወላጆቻችሁ፤ “ክፍላችሁን አጽዱ” ብለው እስኪነግሯችሁ ድረስ አትጠብቁ፡፡ የራሳችሁን ሥራ ራሳችሁ ተወጡ፡፡
ውድ ልጆች፡- ታናናሽ ወንድሞችና እህቶቻችሁን ማጫወት፣ መምከርና ማገዝ እንጂ ማብሸቅና ማስለቀስ የለባችሁም:: ተገቢም አይደለም፡፡ የትም ቦታ ቢሆን ታላላቆቻችሁን አክብሩ፡፡ ቤተሰባችሁንም ውደዱ፡፡
እደጉ! ተመንደጉ!

Read 602 times