Saturday, 29 February 2020 10:47

በአወዳይ ከተማ በመንግሥት ታጣቂዎች ተፈጽሟል የተባለውን ኢ ሰብዓዊ ድርጊት ፓርላማው እንዲያጣራ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

     በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን አወዳይ ከተማ ላይ ተፈጽሟል ያለውን ኢ ሰብዓዊ ድርጊት የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አጣርቶ ውሳኔ እንዲያስተላልፍበት ኦፌኮ ጠየቀ፡፡
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ለፓርላማው በጻፈው የአቤቱታ ደብዳቤው የካቲት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ለማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨውና ዜጎች እየተቀባበሉ ስለተመለከቱት በአወዳይ ከተማ ማህበረሰብ ላይ የመንግሥት የፀጥታ ሀይሎች ሲፈጽሙት የሚታየውን ጭካኔ የተሞላበት ደብደባና ግድያ ጉዳይ እንዲጣራ ነው የጠየቀው፡፡
በማህበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር የነበረው የድምጽ ምስል መረጃ በቀላሉ የምንመለከተው አይደለም ያለው ኦፌኮ ድርጊቱም እጅግ አሳዝኖኛል ብሏል፡፡
ከዚህ ቀደም ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ የፀጥታ ሀይሎች በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ ሲፈጽሙ ከሚታየው ኢ ሰብዓዊ ድርጊት ጋር ተመሳሳይ መሆኑን የጠቀሰው ኦፌኮ ም/ቤቱ እንዲህ አይነት ድርጊቶችን አጣርቶ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል፡፡
በአወዳይ ከተማ ተፈጽሟል የተባለውን ኢ ሰብዓዊ ድርጊትም ፓርላማ  አስቸኳይ ምርመራ አድርጎ እንዲወያይበትና ውሳኔ እንዲሰጥበት ኦፌኮ ጠይቋል፡፡  

Read 1150 times