Saturday, 29 February 2020 11:04

በአባይ ግድብ ጉዳይ ኢትዮጵያውያን የጋራ አቋም እንዲይዙ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

      በአባይ ጉዳይ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ አቋም እንዲይዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በዋሺንግተን ዲሲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በበኩላቸው፤ በድርድሩ የአሜሪካንን ለግብጽ መወገን በመቃወም ሠላማዊ ሠልፍ አድርገዋል፡፡
የአባይ ጉዳይ የሀገር ደህንነት ጉዳይ መሆኑን የገለፀው ኢዜማ፤ በጉዳዩ ላይ እውቀቱና ብቃቱ ያላቸው ምሁራንና የፖለቲካ ሃይሎች ተወያይተው የጋራ ሀገራዊ አቋም ሊይዙበት ይገባል ብሏል፡፡
የአባይ ግድብ ጉዳይ በየትኛውም መመዘኛ በመንግስትም ሆነ በሌሎች የፖለቲካ ሀይሎች የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆን እንደማይገባውም ኢዜማ አሳስቧል፡፡
“ግድቡ የሀገር ጥቅም፤ የሀገር ደህንነት ጉዳይ ነው፤ በእንዲህ ያለ የሀገር ደህንነት ጉዳይ የፖለቲካ ጨዋታ መጫወት ኃላፊነት የጐደለው ነው” ያሉት የኢዜማ መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፤ “የአባይ ግድብ ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡
“ግድቡ ሀገራዊ አጀንዳ እንደመሆኑም፣ የፖለቲካ ሃይሎች በጉዳዩ ላይ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ሳይገቡ ለጋራ ሀገራዊ ጥቅም ተመሳሳይ አቋም መያዝ አለባቸው” ብለዋል - ፕ/ር ብርሃኑ፡፡
መንግስትም በጉዳዩ ላይ ብቃቱና እውቀቱ ያላቸውን ኢትዮጵያውያን አሰባስቦ በቂ ምክክር መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ “የፖለቲካ ሃይሎችም በጉዳዩ ላይ ተመካክረው የጋራ አቋም መያዝ አለባቸው፤ አባይን በተመለከተም የፖለቲካ ሃይሎች በጊዜያዊ ጥቅም የተሠላ አቋም ሊይዙ አይገባም” ብለዋል - መሪው፡፡
ህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በበኩሉ፤ “በኢትዮጵያ ህልውናና ሉአላዊነት ላይ የባዕዳንን ጣልቃ ገብነት አምርረን እንቃወማለን” በማለት ባወጣው መግለጫው፤ በግድቡ ዙሪያ ሲካሄድ የነበረው ድርድር በሶስተኛ ወገን ተፅዕኖ ስር መውደቁ አግባብ አይደለም ብሏል፡፡
በሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት የተካሄደው ድርድር፣ ሉአላዊነታችንን በሚጋፋና ዘላቂ ጥቅማችንን በሚጐዳ መልኩ፣ አገራችንን ወደማትፈልገው ስምምነት እየተገፋች ነው ያለው ህብር ኢትዮጵያ፤ ይህን የሶስተኛ አገራት አድሎአዊ ተፅዕኖ ያረፈበትንና በመሠረታዊ ደረጃ የኢትዮጵያውያንን ጥቅም ያላስጠበቀ ሰነድ መንግስት ሊፈርም አይገባም ብሏል፡፡
ከድርድሩ አውድ ውስጥ የሶስተኛ አገሮች ጣልቃ ገብነት እንዲወገድ፣ ይህ መሆን ካልቻለም ድርድሩ ለጊዜው እንዲቋረጥ፣ እንዲሁም መንግስት ለህዝብ የድርድሩን ሰነድ በተመለከተ ግልጽና በቂ መረጃ እንዲሰጥ ህብረቱ ጠይቋል፡፡
ከህብር ኢትዮጵያ ጋር “አብሮነት” የሚል ትብብር የመሠረቱት ኢሃን እና ኢዴፓም ተመሳሳይ አቋም መያዛቸው ይታወቃል፡፡
ባለፈው ረቡዕ እና ሐሙስ ድርድር ራሱን ያገለለው የኢትዮጵያ መንግስት፤ በግድቡ ጉዳዩ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቴን ሳላጠናቅቅ ወደ ድርድር መድረኩ አልመለስም ብሏል፡፡   
በተመሳሳይ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲም በታላቁ የህዳሴ ግድብ ውይይት፣ ብሔራዊ ጥቅማችን ለድርድር ሊቀርብ አይገባም ብሏል፡፡ ፓርቲው በጉዳዩ ላይ ባወጣው የአቋም መግለጫው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በግድቡ ጉዳይ የጋራ አቋም እንዲያዝ ጠይቆ፤ መንግስት የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም በሚገባ እንዲያስጠብቅ፣ ከግድቡ ግንባታ ጋር ተያይዞ ያሉ የቴክኒክና የፕሮጀክት አስተዳደር ችግሮችም በአፋጣኝ ተቀርፈው በተከለሰው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ግድቡ ስራው ተጠናቆ የሃይል ማመንጨት ስራውን በተያዘለት ጊዜ እንዲጀምርም ጠይቋል - ፓርቲው፡፡

Read 12270 times