Saturday, 29 February 2020 11:06

ቀያይ መስመሮች!!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(8 votes)

  “የዓመቱ መጨረሻ ይደርሳል፡፡ ያው እንደተለመደው ስብሰባ ይጠራል፡፡ እሺ የመቶ ሀምሳ ፐርሰንቷ ነገር እንዴት ሆነች! ምን ይባላል መሰላችሁ… “በበጀት ዓመቱ በገጠሙና በተለያዩ ችግሮች ምርታችንን የማሳደግ አላማችንን ማሳካት አልተቻለም፡፡ በችግሮቹ የተነሳም የዘንድሮ ምርታችን አርባ ስምንት በመቶ ነው፡፡ ምን! አርባ ስምንት! ከመቶ ሀምሳ ወደ አርባ ስምንት! በ“እንቁልልጭ” ዓመቱን ሙሉ ያከረማችሁንስ!”
          
              እንኳን ለታላቁ የአድዋ ድል በዓል አደረሳችሁማ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ለአብዛኞቹ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዓቢይ ጾም ገብቷል፡፡ ያው አንግዲህ የጾም ነገር ያው ሥጋን አድክሞ ፈጣሪን ማስታወሻ ነው:: (ይሄንንም ‘በውስጥ ሰርኩላር’ ለውጡት አሉ! ቂ…ቂ…ቂ…) እናላችሁ… ይህ ወቅት መልካምና በጎ ተግባራት መፈጸሚያ ነው:: ደግሞላችሁ በኃይማኖታዊ እምነትም ሆነ በፖለቲካ መስመር ማስመሰል በበዛበት ዘመን፣ ጾምን በመሳሰሉ ጽናት የሚፈተንበት ነው፡፡ የይቅርታ ጊዜ ነው፣ የፈረሱ ድልድዮች መገንቢያ ወቅት ነው፡፡ (ይሄ ነገር ስብከት መሰለ እንዴ?!)
እናማ… እነ እንትና እውነት ‘ሥጋችሁን እያደከማችሁ’ ነው! አሁን የደከመ ሥጋ ለቀበቶ እንደዚህ ያስቸግራል! እውነት ለመነጋገር አብዛኞቻችን የተመጣጠነ ምግብ የሚባለውን የምናገኘው በጾም ሰሞን ሆኗል:: ልጄ በብቸኝነት ‘ሆድ ሲብሳት’ የኖረችው ‘ዶኬ’ እኮ የእነ ጎመንና ምናምን ጎረቤቶች የምታገኘው ያን ጊዜ ነው፡፡ አለ አይደል… “ምነው ጾም በመጣና የተመጣጠነ ምግብ በተመገብኩ” የሚያሰኝ ነው፡፡ አሀ….ምግቡ በተደረደረ ቁጥር “ለካስ አንቺም ነበርሽ!” ያስብለናል እኮ!
አሁን እኮ ምግብ ቤቶች ራሳቸውን እያስተዋወቁ ያሉት ቢፌአቸው ላይ፣ ስንት አይነት የጾም ምግቦች እንደሚደረድሩ በመፎከር ነው፡፡ ሀያ አይነት፣ ሠላሳ አይነት…ምን አለፋችሁ፣ ትልቅ የምግብና የምግብ ነክ ነገሮች ኤግዚቢሽን ሊመስል ምንም አይቀረውም እኮ!
“ስማ፣ ዛሬ ምሳ በእኔ ነው፡፡”
“በእውነት ለውጥ መጥቷል ማለት ነው:: በአንድ አፍ፡፡”
“እንትን ምግበ ቤት እንሂድ፡፡”
“ከጋበዝክ በደንብ ጋብዘኝ፡፡ እዛ ቤት የሚያቀርቡት የጾም ምግብ ከሁለትና ሦስት አይነት አይበልጥም፡፡”
“ታዲያ የት እንሂድ?”
“እንትን ሬስቱራንት ቢፌያቸው ጠረዼዛ ሞልቶ ሊፈስ ምንም አይቀረው፡፡”
እናላችሁ…ይቺን ሰሞን እንደ ምንም ብሎ “ለኪሱ ብዙም የማይሳሳ ጋባዥ ይጣልልኝ” ማለት ነወ፡፡ ይሄ ‘እድል’ በድጋሚ አይገኝማ!
እሺ የምግቡስ ነገር ይሁን፤ ይህ የጾም ሰሞን እኮ ከምንጊዜውም በላይ ከክፉ ተግባራት የመራቅ ጊዜ ነው፡፡ ከምንጊዜም በተሻለ መልኩ ሰብአዊነት ሊሰማን የሚገባበት ጊዜ ነው:: ደግሞላችሁ… እንደ ዘንድሮ ክፋት ጠፍሮን አያውቅም፡፡ ወንድምና ወንድም፣ አባትና ልጅ በየፍርድ ቤቱ  የምንጓተትበት ዘመን ነው፡፡ ጸሎት ስፍራ ሄደን “የእሷን ነገር ካላሰየኸኝማ!” ብለን ፈጣሪን በክፋታችን ልናነካካው የምንሞክር ነን፡፡ የምር እኮ…ፖለቲካችን  እንዲህ ጥምብርኩሱን እያጣ ያለው የፖሊሲና የእምነት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ክፋት ስለበዛ ነው፡፡ በማንነት ብቻ የተነሳ… ሌላ ሰው የሚናገረውን፣ ሌላ ሰው የሚሠራውን፣ ሌላ ሰው የሚያስበውን ሁሉ ያለ በቂና አሳማኝ ምክንያት በጥላቻ ብቻ ከመቃወምና ከማጠልሸት የባሰ ምን ክፋት አለ?! (እንደተበጫጨቀ ጂንስ የተበጫጨቀ ሀሳብ የሚባል ነገር አለ እንዴ?! ግራ ስለገባን ነው፡፡ “ሰውየው የሚናገረው እውነት ሀሳብ ነው ብሎ ነው ወይስ ገና ከእንቅልፉ አልነቃም!” እያልን ነው፡፡)
እግረ መንገድ… ይኸው የተበጫጫቀ ጂንስ ፋሽን ነው ተባለና ሰዉ ሁሉ የሚሆነውን እያጣ ነው፡፡ መጀመሪያ አካባቢ ብጨቃው በጉልበት አካባቢ ነበር፡፡ እየሰፋ፣ እየሰፋ ሄደና መስፋቱ ብቻ ዓይን ውስጥ አልከት አለ መሰለኝ እዚህም እዛም ይበጫጨቅ ገባ፡፡ በቀደም በአንድ የከተማችን ክፍል ብዙ መቶ ወጣቶች ለክፍት የሥራ ቦታ ለመመዝገብ ተሰልፈዋል፡፡ አንዲት ልጅ የለበሰችው የተበጫጨቀ ጂንስ፤ ወጣቶቹን ራሳቸውን ያስገረመ ነው፡፡ አበጫጨቁ ያልተለመደ ከመሆኑ የተነሳ› ያልተበጨቀውን የሱሪውን ስፍራ መለየቱ የሆነ አይነት ጂ.ፒ.ኤስ. ምናምን ነገር የሚያስፈልገው ነው የሚመስለው፡፡ አጠገቧ የነበሩ ሌሎች ወጣቶች የሆነ ምከር ቢጤ ነገሯት መሰለኝ ስትመናጨቅ የጉድ ነበር፡፡ ‘እንዳሰኘ መልበስ’ መብት ቢሆንም የመሥሪያ ቤቱ መዝጋቢዎች በዛ አይነት አለባበስ ሲያዩዋት፣ ሊሰማቸው የሚችለው ሰሜት ግልጽ ነው፡፡ “አሁን እውነት ይቺ ቢሮ ገብታ ሥራ ልትሠራ ነው!” ቢሉ ችሎታዋን ስለተጠራጠሩ ሳይሆን “በምን ቦታ በእንዴት አይነት መልክ መቅረብ እንደሚገባ  የማታውቅ ልጅ፤ እንዴት ለሀላፊነት ትሆናለች?” በሚል ሊሆን ይችላል፡፡
በነገራችን ላይ…የመስሪያ ቤት ነገር ከተነሳ አይቀር… አለ አይደል… ይህ ምርታችንን፣ አገልግሎታችንን በምናምን ፐርሰንት እናሳድጋለን የሚሉት ነገር ለሆነ ዓመት፣ ሁለት ዓመት ከጥቅም ውጪ ቢደረግ አሪፍ ነበር:: ትዝብት ሆኖ እየቀረ ነዋ! መጀመሪያ ላይ በሚደረገው የታሸገ ውሀ ትርኢት በሚመስል ስብሰባ ላይ ቃል ይገባል:: የተለመዱት “ሀገራችንን ወደ መካከለኛ ገቢ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት…” ምናምን የሚሉ ለተቋማት ስብሰባዎች ሁሉ ‘ኮምፐልሰሪ’ የሆኑ የሚመስሉ መግቢያዎች ይደረደራሉ:: ከዛም “በዚህ ዓመት ላይ ምርታችንን በመቶ ሀምሳ ፐርሰንት እናሳድጋለን” ምናምን ይባላል:: እግረ መንገድ የሠራተኛው ታታሪነት፣ ሥራ አክባሪነት ምናምን ሁሉ ይወሳል፡፡ መቼም እሰየው ነው፡፡ አይደለም መቶ ፐርሰንት ሀምሳና ስድሳ ፐርሰንት ማሳካት እንኳን እንደ ስኬት ጣሪያ በሚታይበት ጊዜ አይደለም በመቶ ሀምሳ ፐርሰንት ማሳደግ ማሰቡ ራሱ መልካም ነው፡፡
የዓመቱ መጨረሻ ይደርሳል፡፡ ያው እንደተለመደው ስብሰባ ይጠራል፡፡ እሺ የመቶ ሀምሳ ፐርሰንቷ ነገር እንዴት ሆነች! ምን ይባላል መሰላችሁ… “በበጀት ዓመቱ በገጠሙና በተለያዩ ችግሮች ምርታችንን የማሳደግ አላማችንን ማሳካት አልተቻለም:: በችግሮቹ የተነሳም የዘንድሮ ምርታችን አርባ ስምንት በመቶ ነው፡፡ ምን! አርባ ስምንት! ከመቶ ሀምሳ ወደ አርባ ስምንት! በ“እንቁልልጭ” ዓመቱን ሙሉ ያከረማችሁንስ!
የምር ግን...ምን አለ መሰላችሁ፡፡ ቃል መግባት፣ ባዶ ከሚባል በአንድ ጊዜ “መቶ ምናምን ፐርሰንት እንገባለን” ማለት ችግር የለም:: በኋላ ጠያቂ አይኖርማ! “መቶ ሀምሳ ፐርሰንት እያልክ ሰዉን እንቁልልጭ ስትል የከረምከውስ?” ብሎ የሚጠይቅ የለማ! እንደውም አርባ ስምንት ፐርሰንት በተባለበት መድረክ ላይ “ችግሮቻችንን አስወግደን በተከታዩ የበጀት ዓመት ምርታችንን በመቶ ምናምን ፐርሰንት ለማሳደግ…” እየተባለ ሌላ ዙር ቃል ሊገባ ይችላል፡፡ የኮሜዲው ብዛት!  
ምን አለ መሰላችሁ…እዚህ ሀገር አንድ ነገር ስንኮርጅ የምንሄድበት ጥግ የጉድ ነው:: አንድ ሰሞን ሱሪ ዝቅ ማድረግ ‘ፋሽን’ ሆነና አዛውንቱ ሁሉ ገብቶበት ነበር:: እሺ ወጣቱስ ይሁን፣ ወጣትነቱ በራሱ ፈተናው ብዙ ነውና:: እኔ የምለው… ይሄ ባለ ነጫጭ ጸጉሩ ሁሉ፣ ቀበቶ ማሰሪያውን እዛ ታች አውርዶ እንትኑን የሚያሳየው ነገር አይዘገንንም?! እድሜ የሆኑ አጥሮች ማበጀት የለበትም እንዴ! አሀ… ‘ኤቨርግሪን’ ምናምን መሆን ሱሪውን አውርዶ ማስታወቂያ ያልተነገረለት ኤግዚቢሽን ማሳየት ነው! (በዛ ሰሞን ጎንበስ ሲሉ የሆነ ነገር የታየብዎት ሰውዬ… የመዋእለ ህጻናት ስእል መለማመጃ የመሰለውን ‘ታቱውን’ እዛ ማዶ መውሰድ ምን የሚሉት ነገር ነው! እንዴ ቀያይ መሥመሮች ይከበሩ አንጂ!)
እኔ የምለው… ይሄ የ‘ታቱ’ ነገር እንዴት ነው…ማለት የአገልግሎት ሰጪዎች ችሎታና ብቃት አሳሳቢ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በቅርቡ በከተማችን አንዱ አካባቢ፣ የሆነ ወጣት፣ በንቅሳት ምክንያት በተፈጠረበት የጤና ችግር ህይወቱ ማለፉን ሰምተናል፡፡ አሳዛኝ ነው፡፡
የምር ግን… አለ አይደል…‘ታቱ’ አሁን የደረሰበት ስፍራ “ከአስራ ስምንት ዓመት በታች የተከለከለ” አይነት የሚያሰኝ ነው ይባላል:: እኔ የምለው፣ የተነቃሾቹ ድፍረት፣ የነቃሾቹ ‘ትእግስት’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ግርም እይላችሁም፡፡
ንቅሳት የሚለውን ቃል ለመጠቀም አንኳን ይተናነቃቸዋል፡፡ እንደውም ‘ታቱ’ ለሚለው ቃል ‘ንቅሳት’ የሚል ቃል መኖሩን ለማወቃቸው ራሱ ያጠያይቃል፡፡ ኮሚክ እኮ ነው፡፡ እኛ ዘንድ ከስንትና ስንት ዘመናት በፊት የነበረውን አሁን ‘ታቱ’ ተብሎ የዘመናዊነት ምልክት ሆኖ መጣና፣ ይኸው ጁኒየር የለ፣ ሲኒየር የለ፣ ፋዘር ማዘር የለ --- ህዝቤ እየተዥጎረጎረ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ የውጭ ኳስ ተጫዋች ክንዱ፣ ደረቱ ምናምኑ ‘ሪቮሊዩሽን’ ያካሄዱ ዶሮዎች የተሯሯጡበት የሚመስለው እኮ አንድም ለመታየት ነው:: እኛ ዘንድ “ኒቂሴ” “ያልተነበበ ጋዜጣ” ምናምን እንዳልተባለ፣ አሁን ‘ታቱ’ ተብሎ ሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን መግባታችንን አወጅን እላችኋለሁ፡፡ እኔ የምለው… እዚህ ሀገር ለ‘ስታንድ አፕ ኮሜዲ’ የሚሆኑ ሀሳቦችን ኤክስፖርት የማናደርግሳ!
ለሁሉ ነገሮች ባይታለፉ የሚመረጡ ቀያይ መስመሮች ቢኖሩ አሪፍ ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2195 times