Print this page
Saturday, 29 February 2020 11:39

የአቶ ሣሙኤል ታፈሰ ስኬታማነት 10 ሚስጥሮች

Written by  ብርሃኑ ሰሙ Email - ethmolla2013@gmail.com
Rate this item
(3 votes)

    አባት ከጓደኛቸውና አንድ ልጃቸው ጋር ቤተ ክርስቲያን ደርሰው ሲመለሱ፣ ቁርስ ለመብላት ወደ ሆቴል ጎራ ይላሉ፡፡ ልጃቸው በአካል እንጂ በመንፈስ አብሯቸው እንዳልሆነ የተረዱት አባት፣ “ቀልብህን የወሰደ ምን ጉዳይ ተፈጠረ?” የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡለት፤ ሞባይል ስልኩን መሰረቁን ነገራቸው፡፡ ይህን የሰሙት አባት ሞባይላቸውን አንስተው ወደ ልጃቸው ስልክ ሲደውሉ፣ ከወዲያኛው ጫፍ  ‹‹ማን ልበል?›› የሚል ምላሽ ያገኛሉ፡፡ ስማቸውን ነግረው፣ የጠፋው ስልክ የልጃው መሆኑን ነገሩት፡፡
‹‹የልጅህ ነው እንዴ? እኔ’ኮ ያንተ መስሎኝ!›› የሚል ቀልድ አዘል መልስ ሲሰጣቸው፤ ‹‹ከእኔማ ስልክ ልትወስድ አትችልም፤ እኔ የጨርቆስ ልጅ ነጅ፤ እሱ የቦሌ ልጅ ስለሆነ ሲንከረፈፍ አግኝተህ ነው የወሰድክበት፤ ይልቁንስ ስንት እንክፈልህ›› የሚል የእንደራደር ጥያቄ ያስከትላሉ፡፡ ለመደራደር ፈቃደኛ መሆኑን ያመለከተው የሞባይል መንታፊ ያቀረበው ጥያቄ አስደማሚ ነበር፡፡ ‹‹እኔ ከእናንተ ብር አልፈልግም፤ ሰንሻይን ብር እንዲሰጠኝ ሳይሆን ሥራ እንዲሰጠኝ ነው የምፈልገው›› አለ፡፡
ከላይ የቀረበው ‹‹ተግባር (እኔና ሰንሻይን ከትናንት እስከ ዛሬ)›› በሚል ርዕስ የአቶ ሣሙኤል ታፈሰን የሕይወትና የሥራ ታሪክ በሚያስቃኘው መጽሐፍ ውስጥ፤ የባለ ታሪኩ ጓደኛ አቶ ግዛቸው ፍስሃ ከሰጡት ምስክርነት የተወሰደ አንድ ገጠመኝ ነው፡፡ ድርድሩ በምን ተቋጨ? የሚለውን ለአንባቢያን ልተወውና ሞባይላቸው በመንታፊዎች በቀላሉ ሊሰረቅ የማይችለው ጨርቆስና የመንደሯ ነዋሪዎች፤ በአቶ ሣሙኤል ታፈሰ የልጅነትና የወጣትነት ዘመን ምን ይመስሉ እንደነበር ባለታሪኩ ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ፡-
‹‹ውልደቴም እድገቴም ጨርቆስ ነው፡፡ጨርቆስ የተረብ፣ የጫወታና የመፈተኛ አካባቢ ናት፡፡ ቧልትና ቀልድ የሚፈጠርባት ብቻ ሳትሆን በራስ ላይም መቀለድና በድህነት ላይ መሳለቅ የሚችል ማኅበረ-ሰብ የሚገኝባት ናት:: አራዳነት በየሰው ልብ ውስጥ አለ፡፡ ቺስታነት ብርቅ አይደለም፡፡ የጨርቆስ ሰው ‹ተቀለደብኝ› ብሎ ቡጢ አይሰነዝርም፡፡ ይልቁንስ ያንን ቀልድ አስፍቶና አሳድጎ ከጓደኞቹ መሃል ተገኝቶ ለመተረክ ይሽቀዳደማል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ የገቢው መጠን አነስተኛ የሆነ ሕዝብ ከሚኖርባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ ጨርቆስ ነው፡፡››
አነስተኛ ገቢ ካለው ቤተሰብ የተወለደው ልጅ ሣሙኤል፤ የ6ኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተናን በጥሩ ውጤት አልፎ 7ኛ ክፍል እንደገባ፣ ወላጅ አባቱ 200 ብር ወርሃዊ ደሞዝ ከሚያገኙበት የቅጥር ሥራ በጡረታ ሲሰናበቱ፤ የቤት እመቤት የነበሩት ወላጅ እናታቸውና የሣሙኤል ታናናሾች ችግር ጥርሱን አግጥጦ ሲመጣ ተመለከቱ፡፡ ለትምህርት ቤት በወር የሚከፍለውን  7 ብር አለማግኘት ለሚያስከትለው ውርደት እጅ መስጠት እንደሌለበት ውስጡን ያሳመነው ብላቴና፣ ለመፍትሔው እያሰበ በእግሩ ተንቀሳቀሰ፡፡
ከጨርቆስ በቅርብ ርቀት ወደሚገኘው አዲስ አበባ ስታዲየም እግር ኳስ ለመመልከት የሚመጡ ተመልካቾች፤ ለማንበብ፣ ለፀሐይና አቧራ መከላከያነት የሚይዙትን ጋዜጣ፣ ብዙዎቹ እዚያው ጥለውት እንደሚወጡ ያስተዋለው ልጅ ሣሙኤል፣ ያንን ሰብስቦ በየመንደሩ ላሉ ኪዮስኮች በመሸጥ ገንዘብ ማግኘት እንደሚቻል አስተዋለ፡፡ ትምህርቱን ሳያቋርጥ ሰርቶ ገንዘብ ማግኘት ብቻ ሳይሆን፤ የራሱን የትምህርት ቤት ወርሃዊ ክፍያ ከመቻሉም ባሻገር፣ ለወላጆቹና ለታናናሽ እህት ወንድሞቹ አለኝታ መሆን እንደሚችልም ተረዳ፡፡
ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ የተጣለ ጋዜጣ ሰብስቦ መሽጡ ብቻ በቂው ስለማይሆን ተጨማሪ ገቢ ማስገኛ ሥራ ማፈላለግ ነበረበት:: ስታዲየም ውስጥ ሲጋራና ማስቲካ አዙሮ ሽጧል፡፡ መኪና በመጠበቅ ገንዘብ ለማግኘት ሞክሮ ተሳክቶለታል፡፡ በዚህ ጥረቱ ከተለያዩ ሰዎች ጋር እውቂያው እየጨመረ በመምጣቱ ስታዲየም ውሰጥ የሚሸጡ ለስላሳ መጠጦች ለአዟሪዎች ያከፋፍል ነበር፡፡ በዚህ መልኩ ለችግር እጁን ላለመስጠት ለራሱ የገባውን ቃል ማሳካት ቻለ፡፡
በትምህርቱ ገፍቶ በ12ኛ ክፍል የማትሪክ ፈተና ጥሩ ውጤት በማምጣቱ በስኮላርሽፕ ወደ ሀንጋሪ የመሄድ ዕድል ቢያገኝም በደርግ ባለስልጣናት ደባ ከጉዞው እንዲቀሩ ከተደረጉት አንዱ ሆኖ የሕይወት ፈተና መልኩን ቀይሮ ቢመጣበትም፤ ለችግር እጅ የማይሰጠው ወጣቱ ሣሙኤል፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በማታው ክፍለ ጊዜ በመመዝገብ መማሩን ቀጠለ:: ኑሮን ለማሸነፍ በተለያዩ ሥራዎች ውስጥ ሲያልፍ፣ የነፍሱን ጥሪ፣መክሊቱን ከመፈለግም አልቦዘነም፡፡
‹‹በግንባታ ሥራ ላይ ለመሰማራት ከልጅነቴ ጀምሮ ፍላጎቱ የነበረኝ ቢሆንም፣ ከአባቴ ጋር ተመሳሳይ ሥራ እየሰሩ ለቤታቸው (ነጭና ጥቁር) ቴሌቪዥን ገዝተው የነበሩት›› ጎረቤታቸው አቶ ገብሩ ሙያውን እንዲወደው በጎ ተጽዕኖ ያሳደሩበት ቀዳሚው ሰው እንደነበሩ ይገልጻል፡፡ ይህ መነሻ ሆኖት ወደ ጣራ እደሳና ቀለም ቅብ ሥራ ተሸጋገረ፡፡ እርሳቸውን በአርአያነት መከተሉ በኋለኛው ዘመን ውሳኔዎቹም ሲንጸባረቅ ይታያል፡፡ ‹‹በፍል ውሃ የተሰጠኝን (የቀለም ቅብ) ሥራ በደንብ እሰራ ስለነበር … በቋሚ ሰራተኛነት ተቀጥሬ እንድሰራ ስጠየቅ እምቢ ያልኩት፣ እንደ አቶ ገብሩ፣ በኮንትራክተርነት መስራት የተሻለ ደረጃ እንደሚያደርስ ስለታሰበኝ ነበር፡፡››
ወጣቱ ሣሙኤል ሥራዎቹና ቤተሰባዊ ኃላፊነቱ እየሰፋ ስለመጣ የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገደደ፡፡ ነፍሱ የወደደውን ሥራ ለማሳደግ ሕጋዊ ፈቃድ አውጥቶ መንቀሳቀስ ነበረበት፡፡ በ1977 ዓ.ም ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ድርጅት ተመሰረተ፡፡ ‹‹ስሙን ያወጣነው እኔና ባለቤቴ ነን፤ትርጉሙ ምንም የተለየ፣ ወይም የተወሳሰበ ሚስጥር የለውም፡፡ ሰንሻይን፣ የአስራ ሦስት ወር የጸሐይ ጸጋ የሚገኝባት ሀገር ውስጥ ያለ ድርጅት ነው፤ ለማለት ነው፡፡››
* * *
6 እህት ኩባንያዎችን በውስጡ የያዘው የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለቤትና ፕሬዚዳንት የአቶ ሣሙኤል ታፈሰ የሕይወትና ሥራ ታሪክን የያዘው ‹‹ተግባር (እኔና ሰንሻይን ከትናንት እስከ ዛሬ) / TEGBAR (my sunshine through the year)›› መጽሐፍ በአማርኛ (108 ገጽ) እና በእንግሊዝኛ (111 ገጽ) በሁለት ቋንቋዎች  የቀረበ ሲሆን በነፃ የሚታደል መጽሐፍ ነው:: እኔ ባለኝ መረጃ መሰረት፤ ኢትዮጵያዊያን የንግድና ቢዝነስ ሰዎች፣ የሕይወትና የሥራ ታሪክ በመጽሐፍ ሲቀርብ የአቶ ሣሙኤል ታፈሰ 18ኛው  ነው፡፡ አቶ ዘሙይ ተክሉ፣ አቶ አስፋው ተፈራ፣ አቶ በላይ ተክሉ፣ ቀኛዝማች ከድር ኤባም በተመሳሳይ መልኩ የሥራና የሕይወት ታሪካቸውን የያዘ መጽሐፍ በነጻ ለአንባቢያን አድለዋል፡፡
ባለቤቴና ልጆቼን ጨምሮ የሕይወትና የሥራ ታሪኬን በመጽሐፍ እንዳቀርብ የበዛ ጉትገታ ይቀርብልኝ የነበረ ቢሆንም፣ በአሜሪካን አገር ኦክላንድ ካሊፎርኒያ የሚገኘው የሊንከን ዩኒቨርስቲ የተመሰረተበትን 100ኛ ዓመት በሚያከብርበት በዚህ ዓመት (ጥር 23 ቀን 2012 ዓ.ም)  የክብር ዶክትሬት ሲሰጠኝ፣ ታሪኬን ለማሰናዳት አነሳስቶኛል የሚሉት አቶ ሣሙኤል ታፈሰ፤ ለሽልማት የተመረጡባቸው ምክንያቶች፤ ችግርን ድል ነስተው በሺህ ለሚቆጠሩ ሰዎች የሥራ ዕድል በመፍጠራቸው፤ ችግረኛ ልጆች የሚማሩባቸው ት/ቤቶችን በመገንባታቸውና በየ5 ዓመቱ ለሠራተኞቻቸው የመኖሪያ ቤቶች ሽልማት በመስጠታቸው መሆኑን በመጽሐፉ ገልጸዋል፡፡
ሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ በሦስቱም ዘርፍ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል በጥራዙ የቀረቡ ዝርዝር ማሳያዎች አሉ፡፡ ችግረኛ ልጆች ማስተማርን በተመለከተ ‹‹ … በዚህ ድርጅት ስም ትምህርት ቤቶችን መክፈት ብቻ ሳይሆን የመምህራንን ደሞዝና የአስተዳደር ወጪዎችን በመሸፈን በኦሮሚያ ክልል ነቀምት ከተማ፣ በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ፣ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን አገና ከተማ ትምህርት ቤቶችን ገንብተን፣ አነስተኛ የገቢ መጠን ላላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የነፃ የትምህርት ዕድል ለማኅበረሰቡ በማቅረብ ላይ›› እንዳሉ እና በ2014 ዓ.ም ሥራ የሚጀምረው የደብረ ብርሃን ትምህርት ቤት የሚቀበላቸውን ጨምሮ፣ አንድ ሺህ 500 ተማሪዎች በዕድሉ ተጠቃሚ እንደሆኑ፤ የዚህ በጎ አድራጎት ገቢ ምንጭም መስቀል አደባባይ አካባቢ የሚገኘው ባለ 9 ፎቅ ሕንፃ ኪራይ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ‹‹እንደ አለመታደል ሆኖ ሠራተኛ እንደ ጀግና የሚቆጠርበት ማኅበረሰብ መፍጠር አልቻልንም›› የሚለው አቋማቸውም፤ ሠራተኞችን በማመስገንና በመሸለም ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ማሳየት የፈለጉ ይመስላል፡፡
‹‹እንደ እኔ አመለካከትና የሕይወት ተሞክሮ፣ ክብደት ሰጥቼ መናገር የምፈልገው፣ የልምዶቻችን ዋና መሠረቶች፣ የሀገር ውስጥ ምሳሌዎቻችን መሆን ያለባቸው መሆኑን ነው:: በሌላ አነጋገር፤ የአንድ ግንባታ መሰረት መጀመሪያ መነሳት ያለበት ከሚገነባበት ሀገር የተፈጥሮ ጸባይ ላይ ነው፡፡ የሀገራችን የሥራ ባሕል፣ የራሳችን ባሕላዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረት ላይ ካላስቀመጥነው ከውጪ (ከሌላ ሀገር) የምናመጣው ተሞክሮ ብቻውን በራሱ አመርቂ ውጤት አያስገኝም …›› የሚሉት አቶ ሣሙኤል፤ ከራሳቸው የስራ ልምድ በመነሳት ሀገርና ሕዝብን ለመቀየር፣ በቁጭትና በትብብር ከተሰራ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ያቀረቧቸው ማሳዎች አሉ፡፡
በመንገድ ኮንስትራክሽን ዘርፍ በጉራጌ ዞን በዘቢደር ተራራ ላይ የተሰራው ‹‹ተአምር›› አንዱ ማሳያ አድርገው ያቀረቡት፣ የኢሕአዴግ ሦስተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የተሰራውን ካዩ በኋላ የሰጡትን ምስክርነት ነው፡፡‹‹ይህንን መንገድ አሰርቶ እውን ለማድረግ ብዙ ጥረት ብናደርግም አልሆነልንም ነበር፡፡ ለውጭ ኮንትራክተር ለመስጠትም ሙከራ አድርገን ነበር፡፡ ሆኖም ግን እኔ በሀገር ውስጥ ሙያተኞች እዚህ ደረጃ ሊደርስ ይችላል ብዬ አልገመትኩም ነበር፡፡ ለዚህ በመብቃተችን ትልቅ ኩራት አሳድሮብኛል››
ሌላኛው ማሳያቸው ከሆቴል ዘርፍ ጋር በተያያዘ በአገራችን ማምጣት የተቻለው ለውጥ ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ለአፍሪካ መሪዎች አትመጥንም›› በሚል የሊቢያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሙሐመድ ጋዳፊ፤ በአገራችን ላይ የሰነዘሩት ነቀፌታ ያስቆጣቸው ኢትዮጵያዊያን ባለስልጣናትና ባለሀብቶች መክረው፣ ለውጥ ካመጡበት የአገልግሎት መስጫ ተቋማት አንዱ፣ የሆቴል ዘርፍ መሆኑን፣ ሰንሻይን ማሪዮት ሆቴልን የገነባው ከዚሁ ጋር በተያያዘ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
አቶ ሣሙኤል ታፈሰ ከ1976 እስከ 2010 ዓ.ም የተገለገሉባቸው አጀንዳዎች ተሰንደው መቀመጣቸውን የሚያመለክተውን ጨምሮ በርካታ ፎቶግራፎችን የያዘው ‹‹ተግባር (እኔና ሰንሻይን ከትላንት እስከ ዛሬ)›› መጽሐፍ፤ ባለታሪኩ ሃይማኖት ላይ ስላላቸው ጠንካራ አቋም፤ በምንም ደረጃ ቢገኝ ለሰው ልጅ ስላላቸው ክብር፤ ቁጭትን፣ ጸጸትን፣ ንዴትን በመቀነስና በመቆጣጠር ጤንነትን ከተለያዩ በሽታዎች መከላከልና ዕድሜንም ማራዘም እንደሚቻል ማመናቸው፤ አጥንት (የቅቅልና ቀይ ወጥ) መጋጥን ጨምሮ የሚያታግል ነገር አለመውደዳቸው … ስለመሳሰሉት ባሕርያትና ተፈጥሯቸው፣ ከተለያዩ አካላት የተሰጡ ምስክርነቶችም ቀርበዋል - በመጽሐፉ፡፡
አሁን 6 ሺህ ያህል ሠራተኞች ያሉት ሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ፤ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፎ ነው ለዛሬ የደረሰው ይላሉ - አቶ ሣሙኤል፡፡ ‹‹ከባለስልጣናት ጋር ተወዳጅቶ ነው የከበረው›› በሚል ሀሰተኛ ክስ ተንገላተው፤ ጉዳዩ እስኪጣራ ተብሎ ለወራት ሥራቸው ታግዶ ነበር፡፡ ከችግሮች ከታደጉን ውስጥ ቀዳሚዋ ባለቤቴ ናት ሲሉም ያመሰግኗቸዋል:: ‹‹ባለቤቴ ደንብ በመተላለፍ ስማችን እንዲነሳ አትፈልግም:: ከሕጉ፣ ከመመሪያው መውጣትን ትቃወማለች፡፡
በየቀኑ ከሚያስጠይቀን፣ ከሚያስከስሰንና ስማችንን ከሚያጠፋ ነገር በመራቅ፣ ለልጆቻችንም ሆነ በቅርብና በሩቅ ለሚያውቁን ሰዎች በተለይ ለወጣቶች ምሳሌ እንድንሆን ነው የምትፈልገው››
የአቶ ሣሙኤል ታፈሰ የሕይወትና የሥራ ታሪክ የያዘው መጽሐፍ፤ የታተመበት ሀገርና ማተሚያ ቤትን አያመለክትም፣ ዓለም አቀፍ ተከታታይ የመጽሐፍ ቁጥር (ISBN) አልተሰጠውም፣ በገጽ 74 የአቶ ሣሙኤል ታፈሰን ስዕል የሳለው ባለሙያ ሥም አልተገለጸም፣ ከዚህም ባሻገር መጽሐፉ አሁን ከቀረበበት መጠን በሰፋ መልኩ ተስፋፍቶ ሊቀርብ ይችል እንደነበር ያልተብራሩ ብዙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ባለታሪኩ ከሕይወት የተማርኳቸው ነገሮች ብለው የዘረዘሯቸውን 10 ቀመሮች፤ በተለይ የሕይወትና የሥራ ታሪካቸውን በመጽሐፍ ሰንደው የሚያቀርቡ የንግድ/ቢዝነስ ሰዎች ቢከተሉት ጥሩ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ የአቶ ሣሙኤል ታፈሰ ስኬታማነት 10 ሚስጥሮች፤ ቀጠሮ ማክበር፣ ዛሬ የሚያልቅ ሥራን አለማሳደር፣ የሚያውቁትና የሚችሉትን ሥራ ማስቀደም፣ ስልክን ጨምሮ የመረጃ ምንጮችን በሚገባ መጠቀም፣ ሥራን በጠዋት መጀመር፣ ከአቅም በላይ የሆነ ሥራን አለመሞከር፣ ኢንቨስትመንትን በአቅምና በእውቀት መጀመር፣ ሞትን ተቀምጦ አለመጠበቅ፣ ሥራን ለሥራ ባልደረባ ማጋራት፣ አልሳካ ያለ ጉዳይን ደጋግሞ መሞከር ናቸው፡፡

Read 3636 times