Saturday, 07 March 2020 12:25

13 የፖለቲካ ድርጅቶች ጥምረት ለመፍጠር ምክክር ይዘዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

  ባልደራስ፣ አብን፣ ኦነግ፣ ኦፌኮ ይገኙበታል
              ትብብር፣ ባልደራስ፣ አብን እና ኦፌኮን ጨምሮ 13 የፖለቲካ ድርጅቶች በቀጣዩ ምርጫ ተጣምረው ለመወዳደር የሚያስችላቸውን ምክክር እያደረጉ መሆኑ ታውቋል፡፡
በሶስት የፖለቲካ ድርጅቶች ማለትም ህብር ኢትዮጵያ፣ ኢዴፓ፣ ኢሃን የተመሠረተውን “ትብብር”ን እንዲሁም ባልደራስ፣ አብን፣ ኦፌኮ እና ኦነግን ጨምሮ 13ቱ ሀገር አቀፍና ብሔር ተኮር ድርጅቶች ውይይት እያደረጉ ያሉት ህብረ ብሔራዊ ፌደራላዊ ጥምረት ለመመስረት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የህብር ኢትዮጵያ ም/ሊቀመንበር አበራ በቀለ ከአዲስ አድማስ ማብራሪያ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ ፓርቲዎቹ ገና በንግግር ላይ መሆናቸውንና በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ተጨባጭ ውጤት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
ጥምረቱን ለመፍጠር ያሰቡት 13 የፖለቲካ ድርጅቶች መላ የሀገሪቱን አካባቢዎች ይወክላሉ ተብሎ የሚታሰብ፣ ብሔር ተኮርና ህብረብሔራዊ ሃይሎች መሆናቸውንም አስረድተዋል - አቶ አበራ፡፡
ፓርቲዎቹ ጥምረት ከፈጠሩ በኋላም በጋራ ማኒፌስቶ እና የመወዳደሪያ ምልክት  እየተናበቡ፣ እጩዎችን በማቅረብ ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ አበራ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
ፓርቲዎቹ ጥምረት ለመፍጠር እያደረጉ ያለውንና የደረሱበትን ሁኔታም በመጪው ሣምንት ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

Read 13437 times