Print this page
Sunday, 08 March 2020 00:00

“ማየት ማወቅ፤ አለመታየት ጨለማ ነው”

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

      “ማየት ማወቅ፤ አለመታየት ጨለማ ነው”

ከመጨረሻው እንጀምር፡፡ አዲስ አበባ የሚገኘው ፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት፣ የሁለቱን ተከሳሾች ይግባኝ መርምሮ የስር ፍ/ቤት ያሳለፈውን የአስራ አምስት ዓመት የነፍስ ወከፍ ቅጣት በማጽደቅ የመጨረሻውን ውሳኔ ሰጠ። ጠበቃው፣ እህቱና አሳዳጊዎቹ ተቃቀፉ፡፡…
***
ሰውየው ብርቱ ገበሬ ነበር፤ ከራሱ በተጨማሪ በበዓላትና በስብሰባ ሰበብ ሥራ የሚሸሹ ሰነፍ ገበሬዎችን መሬት እየተከራየ በማረስ ንብረት ያፈራል። አያድርስ ሆኖ ሁለቱ ተጎራባቾች ቀኑበት፡፡ አንደኛው የቤተ መንግስት ታጣቂ ነው:: ከዕለታት አንድ ቀን፣ ገበሬው ከገበያ ሲመለስ ሀይለኛ ዝናብ ጣለ፡፡ በተጠለለበት ጠጅ ቤት አንድ ሁለት እያለ ሲጫወት አምሽቶ፣ ወደ ቤቱ ሲመለስ ደቦኞቹ ጠብቀው ገደሉት፡፡ ገንዘቡን ዘርፈው አጋሰሶቹን ነዱበት፡፡ ሽፍታ ገደለው ተብሎ ተወራ። ነፍሰ ጡር የነበረችው ሚስቱ ጉዳዩ ወደሚመለከታቸው እየተመላለሰች ብታለቅስም ‹‹እየተከታተልን ነው›› ከሚል መደለያ ውጭ ፍትህ ማግኘት አልቻለችም፡፡ ከረፈደ በኋላ እውነቱን የነገረቻት፣ የአንደኛው ገዳይ የቀድሞ ሚስት ነበረች፡፡ በምህላና በግዝት የተቋጠረ ሚስጢር ሆኖ ቀርቷል፡፡
ቀን ሲያልፍ፣ መሬቱ ራቁቱን ሲያድር፣ የጓሮውም፣ የጓዳውም ሲነጥፍ ልጆቿን ይዛ፣ ቀዬዋን ጥላ ተሰደደች፡፡ አዲስ አበባ ከአንድ ጎዳና ጥግ ወደቀች፡፡ ወንድ ልጇ በአንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት በኩል፣ የጉዲፈቻ አሳዳጊ ቤተሰብ አግኝቶ፣ ወደ ውጭ አገር ሄደ፡፡ እህቱ ግን እናታቸው እስካረፈችበት ጊዜ ድረስ እየረዳቻት አብረው ኖሩ፡፡
***
ዛሬ ከታላቁ ዬል ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በሕግ ትምህርት ለተመረቀው ኢትዮጵያዊ ታላቅ ቀን ነው፡፡ ሱዛን እቅፍ አበባ ጀባ ስትለው፣ አሳዳጊዎቹ በቆንጆ ወረቀት የተሸፈነች ትንሽ ሳጥን ሰጡት፡፡ ወጣቱ ተመራቂ ሳጥኗ ውስጥ ምን እንዳለ ለመገመት አልተቸገረም፡፡ ቤተሰቦቹ በአንድ አጋጣሚ ‹‹የምትወዳትን የምታጨው በኛ የጋብቻ ቀለበቶች ነው›› ብለውት ነበር:: ምን ያህል እንደሚወዱት ያውቃል፡፡ ያስገረመው ነገር ሳጥኗ የተጠቀለለችበት ወረቀት ላይ ‹‹ከአምስት ዓመት በፊት እንዳትከፍተው›› ብለው መጻፋቸው ነው፡፡ ‹‹ሁሌም ልጅ የሆንኩ ይመስላቸዋል፣ ደግሞስ ሱዛን አምስት ዓመት ትጠብቀኛለች ወይ?›› ሲል አሰበ፡፡
***
ይህ ከሆነ ከ3 ዓመት በኋላ፡-
‹‹ተሸውደናል!›› አለች ሱዛን፤ አንድ ቀን በእጮኛዋ መኝታ ቤት ሲጨዋወቱ፡፡
‹‹ምን ተፈጠረ?››
ከኮሌጅ ሲመረቅ ቤተሰቦቹ የሰጡት ትንሽ ሳጥን የተጠቀለለበት ወረቀት ላይ የሰፈረውን ቀን አሳየችው፡፡
‹‹ከአምስት ዓመት በፊት እንዳትከፍተው የሚወዱህ ቤተሰቦችህ 1/4/90››
‹‹አይቼዋለሁ ባክሽ››
‹‹አፕሪል ዴይ (April the fool) መሆኑን አውቀሃል?››
‹‹እ?››… ዓይኑን ማመን አልቻለም፡፡
‹‹ወይኔ! ሰሩልን›› አለ፤ እየሳቀ፡፡
‹‹ለነገሩ ለኛ በማሰብ ነው።››
‹‹በቃ ወሬ አታብዢ፤ ቶሎ ክፈችው፡፡ ››… ተከፈተ፡፡
የተመለከቱት ነገር ‹ክው› አደረጋቸው፡፡ ምን ይሆን?
***
ወዳጄ፡- አንዳንድ ሰዎች የሚገባቸውንም፣ የማይገባቸውንም ይመኛሉ፡፡ ፍላጎት ሲበረታ መንፈስ ይታሰራል፣ መንፈስ ሲጠነክር ፍላጎት ይታሰራል። በየጊዜው ወደየቤተ እምነቶቻችን እየሄድን ‹‹ላጠፋነው ይቅር በለን›› እያልን እንማልዳለን፣ እንፀፀታለን፡፡ ነገር ግን ተመሳሳይ የሆነ ጥፋት ወይም ካሁን በፊት ካደረስነው በደል የበለጠ ጉዳት ከማድረስ አንቆጠብም፡፡ ‹‹ንስሃ ሳልገባ አይግደለኝ›› የምንለው ላጠፋነው ብቻ ሳይሆን ወደፊትም እንደምናጠፋ ውስጣችን ስለሚያውቅ ነው፡፡ ባይሆን ኖሮ በየጊዜው እየተፀፀትን፣ እየተናዘዝን፣ እየሰገድን፣ እየተጠበጠብን እያለን “ንስሃ ሳልገባ አትግደለኝ” ማለት ለምን ፈለግን?
ወዳጄ፡- በሚዲያ ከምንሰማው በተጨማሪ በቤተሰብ፣ በጎረቤትና በአካባቢያችን በየዕለቱ የሚከሰቱ አሳዛኝ አጋጣሚዎችን እያየን እንኳ አቅፈን የምንዞረው ሞት ሩቅ ያለ እየመሰለን አጀንዳ ልናስይዘው እንሞክራለን፡፡ ሞት በኛ ፍላጎትና እቅድ የሚከሰት ቢሆን፣ አሁን ለሕይወት ያለን ግምት የተለየ ይሆን እንደነበር አናስብም፡፡
ወዳጄ፡- ራስን ማጥፋት (Sucide) እንኳ በሰዎች ነፃ ፍቃድና ምርጫ (Free will) የሚፈፀም ድርጊት አይደለም፡፡ የጀርባ ምክንያት አለው፡፡ በዓይን የማይታዩ ተዋስያን ውስጣችንን ሰርስረው፣ ሰውነታችንን እንደሚያፈርሱ ሁሉ ምክንያታዊነታችንን አፈራርሰው፣ አእምሯችንን አምክነው፣ ከሕይወት የሚያፋቱን ‹መናፍስትም› አሉ፡፡
ወዳጄ፡-  መንፈስም እንደ ስጋ ሊታሰር መቻሉን አትዘንጋ፡፡ ሊቃውንቱ ከሚነግሩን ከብዙ የተለያዩ አመለካከቶች ውስጥ ለኛ አውድ (context) የምትሆን ኮሳሳ ምሳሌ እንኳን ብንጠቅስ፡- አንድ ሰው ‹‹እንዲህ ሆኜ የተፈጠርኩት ወይም እንዲህ ሆኜ የምኖረው የእግዜር፣ የአላህ ወይም የሌላ አምላክ ፈቃድ በመሆኑ ነው›› ብሎ ካመነ ሀሳቡ ታስሯል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እምነቱ ነው:: እንደሱ አስተሳሰብ ከእምነቱ ጀርባ ምንም የለም፡፡ ሌላው ብላቴና ደግሞ ለአፈጣጠሩም ሆነ ለዛሬው እሱነቱ ምክንያት የሚጠቅሰው አካባቢን፣ ቤተሰብን የፖለቲካ ሥርዓትን ወይም ሌላ ከሳይንስና ጥበብ ዘርፍ ጋር የተዛመደ ዕውቀትን ሊሆን ይችላል፡፡
ከነሱ ጀርባ ያለው ደግሞ ያልተደረሰበት እንጂ የሌለ ነገር አይደለም፡፡ ልዩነታቸው አንደኛው በተዘጋ ቤት መኖሩ፣ ሌላኛው በርና መስኮቱ በተከፈተ ቤት መገኘቱ፣ አንደኛው በመለወጥ ላይ ያለውን ዓለም ማየት ሲችል፣ ሌላኛው የሚያየው ነገር አለመኖሩ ነው፡፡
ወዳጄ፡- ማየት ማወቅ፣ አለማየት ጭለማ ነው፡፡ ሲያጠፉ መፀፀት ተገቢ ሲሆን እየተፀፀቱ ማጥፋት ግን ጉዳት አለው፡፡ የታሰረ መንፈስ በመኖርና ባለመኖር፣ በገነትና በሲዖል ኮሪደር መመላለስ አይችልም፡፡
***
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- የታሪካችን  እንብርት የተቋጠረው የወዳጃችን አሳዳጊዎች ለልጃቸው ምርቃት ባዘጋጁት ስጦታ ላይ ነው። ሱዛን በስጦታ መጠቅለያ ወረቀቱ ላይ የተጻፈውን ቀን ‹‹አፕሪል ዴይ› መሆኑን ስታውቅ ‹”ተታለናል” ብለው መሳቃቸውንና ሳጥኗን መክፈታቸውን፣ የተመለከቱት ነገር ደግሞ እንዳስደነገጣቸው ተጨዋውተናል:: በሳጥኗ ውስጥ የነበረው እናቱ በሕጻንነቱ አንገቱ ላይ አስራለት የነበረው ‹ክታብ› ነበር፡፡ አሳዳጊዎቹ ወደ አገራቸው ከመጡ በኋላ ፈተው ሲመለከቱት፣ በግዕዝና በአማርኛ የተፃፈበት የብራና ቆዳ ነበር፡፡ በቋንቋ አዋቂ ሲተረጎም፤ በግዕዝ የተፃፈው ክፉ መንፈስ የሚያርቅ ድግምት ሲሆን አማርኛው ደግሞ የቤተሰቡ ታሪክ ነው፡፡ ስለ አባቱ አሟሟት፣ ወንጀለኞቹ እነማን እንደሆኑ፣ እናቱ ፍትህ በማጣቷ የደረሰባትን በደል ይዘረዝራል፡፡ ተመሳሳይ ክታብም እህቱ ዘንድ እንደሚገኝ ያትታል። የልጁ አሳዳጊዎች በተነበበላቸውና በተረዱት ነገር መንፈሳቸው ተነካ፡፡ ከቀዬው እየተፈናቀለ፣ በስደትና በጎዳና ተበትኖ የሚኖረው የሰው ልጅ ለካ ጠጋ ብለው ካዳመጡት፣ እንደ ማንኛውም ሰው የሚያወራው ታሪክ እንዳለው በመገንዘባቸውም አንድ ነገር ለማድረግ ወሰኑ፤ ልጃቸው ለወገኖቹም ሆነ ዕርዳታውን ለሚሹ ግፍን ተሟጋች ጠበቃ እንዲሆን ማመቻቸት፡፡ ወደ ሕግ ት/ቤትም ላኩት፡፡ እንዳሰቡትም ሆነ:: ዛሬ የአባቱን ገዳዮች ጉዳይ ጨርሰው ከፍ/ቤቱ ሲወጡ፤ ሱዛን አበባ ይዛ በር ላይ ቆማ ነበር:: አሳዳጊው ፈጠን ብለው በኪሳቸው የያዙትን ትንሽ ሳጥን አቀበሉት፡፡ ሁለት የአልማዝ ቀለበቶች ነበሩ፡፡ ሁለት ሰርግ ባንድ ቀን!!  
“Justice is done! “  አለችው፡፡
“Justice delayed, justice denied” ሊላት ፈለገና ተወው፡፡
ሰላም!!       



Read 1295 times