የድል በር
ተፅፎ ባይታይም
አቅጣጫ ሚጠቁም ጉልህ ማሳሰቢያ
ለጀግና መውጪያው ነው የፈሪዎች መግቢያ
***
የላጤ ሐገር
ከአቅመ አዳም ልንገባ ደጁ ተሰልፈን
ሃያ አመት ከሞላን ሃያ አመት አለፈን
***
ለፓርቲዎቻችን
ከአምስት አመት እንቅልፍ ድንገት ስትነሱ
ህዝቡ ቀድሞ ነቅቷል እንዳትቀሰቅሱ
***
ታራሚ
የኔና ያንቺ ነገር ግራ ነው ለዳኛ
አብረን መቆም ሳንችል አብረን የምንተኛ
***
ጊዜ የሰጠው
ጊዜን ጊዜ ሲወልድ ቀን እየበረረ
ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ከሰበረ
ይሄ ሁሉ አለት ለም አፈር ሆኖ እንዳይ
ቅል አርገኝ አምላኬ ለሀገሬ ድንጋይ
ከሙሉቀን ሰ.
፪ሺህ፲፪
Published in
የግጥም ጥግ