Monday, 09 March 2020 00:00

“ለኢትዮጵያውያን የአስተሳሰብ ክትባት ያስፈልጋቸዋል”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

• ደቡብ ኮሪያ ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ፍቅርና አክብሮት አላት
  • አሁን ኢትዮጵያ ያላት መሪ የትም ዓለም ላይ አይገኝም
  • ተስፋ መቁረጥ ለወጣቶች ህይወት ዋና እንቅፋት ነው
  • ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ህይወቴ ፍፃሜ መኖር እፈልጋለሁ

        ፒል ሃዩን ናም (ናሆም) ይባላሉ:: ደቡብ ኮሪያዊ ናቸው፡፡  ተወልደው ያደጉትና የተማሩት በደቡብ ኮሪያ ዋና ከተማ ሴኦል ውስጥ ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስና በስነ-ልቦና ትምህርት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ አለም አቀፉን የወጣቶች ህብረት (International Youth Fellowship) በበጐ ፈቃደኝነት ተቀላቅለው ማገልገል የጀመሩት ገና በወጣትነታቸው፣ የኮሌጅ ተማሪ ሳሉ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም የህብረቱ የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ:: አማርኛን አቀላጥፈው መናገርና መፃፍ የሚችሉት እኒህ የኢትዮጵያ ወዳጅ፤ “እስከ ዕለተ ሞቴ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር እፈልጋለሁ” ይላሉ፡፡
 ለመሆኑ ፒል ሃዩን ናም እንዴት ወደ ኢትዮጵያ መጡ? ዓለም አቀፉ የወጣቶች ማህበር (“IYF”) ምንድን ነው የሚሰራው? የእሳቸውስ ሚና ምንድን ነው? የአስተሳሰብ ክትባት ምንድን ነው? ምንስ ይፈይዳል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከእኚህ ደቡብ ኮሪያዊ የሥነ ልቦና ምሁር ጋር   ስለ ደቡብ ኮሪያና ኢትዮጵያ ወዳጅነት፣ ደቡብ ኮሪያ በአስተሳሰብ ለውጥ እንዴት የብልጽግና  ማማ ላይ እንደወጣች፣ በዚህ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዴት አገርንና ህዝብን መለወጥ እንደሚቻልና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በስፋት አነጋግራቸዋለች:: እነሆ፡-


             እንዴት ነው ዓለም አቀፉን የተማሪዎች ህብረት የተቀላቀሉት?
IYFን የተቀላቀልኩት ገና የ20 ዓመት ወጣትና የኮሌጅ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ነው:: በIYF ውስጥ ከሚገኙትና ከሚከናወኑት ፕሮግራሞች መካከል በጐ ፈቃደኛ በመሆን ወደ ውጭ አገር፣ በተለይም ወደ ታዳጊ አገር በመሄድ፣ ለአንድ አመት የማገልገል ፕሮግራም አንዱ ነው፡፡ እኔም ለዚህ አገልግሎት ተመዝግቤ ስጠባበቅ ቆይቼ፣ ኢትዮጵያን መርጩ ስለነበር፣ ለአንድ ዓመት ወደዚህ አገር መጥቼ፣ በጐዳና ተዳዳሪ ልጆችና በወላጅ አልባ ህፃናት ዙሪያ ስሰራና እነሱን ስረዳ ቆይቼ ወደ አገሬ ተመልሼ ሄድኩኝ፡፡ ትምህርቴንም ቀጠልኩኝ፡፡ ከዚያም በIYF ውስጥ ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩኝ:: ነገር ግን ኮሪያ ሆኜ ከምሰራ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ የIYF የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ኃላፊ ሆኜ ለመስራት ወሰንኩኝ፡፡ በዚህ ውሳኔዬ በመጽናትም ከ15 ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ፣ እስከ ዛሬ ድረስ ካንትሪ ዳይሬክተር በመሆን እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡
ማህበሩ (IYF) ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 15 ዓመታት ያደረጋቸው እንቅስቃሴዎችና ያስመዘገባቸው ውጤቶች ምንድን ናቸው?
ወደ ኢትዮጵያ ከመጣሁ በኋላ በጣም በብዛት እየሰራን ያለነው በወጣቶች ላይ ነው፡፡ በተለይ ግንዛቤ በማስጨበጥ በኩል በርካታ ስራዎችን ሰርተናል፤ እየሰራንም ነው፡፡ ለምሳሌ በአፍሪካ አገራት በተለይም በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት በፍጥነት እየጨመረ መጥቷል፡፡ ነገር ግን ችግሩ ምንድነው ካልሽኝ… የወጣቶች ፍላጐት ከአገር ዕድገትና ሁኔታ በጣም በእጥፍ እያደገ መምጣቱ ነው፡፡ ይሄ ከሆነ ደግሞ እንኳን በማደግ ላይ ሆና፣ በጣም ብታድግ እንኳን አገራቸው የወጣቶቹን ፍላጐት ሙሉ ለሙሉ ልታሟላ አትችልም:: ወጣቶች ፍላጐታቸው ካልተሟላ ደግሞ በደስታና በሰላም አይኖሩም፡፡ መቃወምን ተስፋ መቁረጥን ስራቸው ያደርጋሉ:: ይህ እንዳይከሰት ለወጣቱ ሰፊ የሆነ የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ “Mindset Education” ማለቴ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ወጣቶችን ከአስተሳሰብ መዛባት እንዲሁም ከአለመርካት ችግር የሚያላቅቅና በደስታ እንዲኖሩ የሚያደርግ ስልጠና ነው እየሰጠን ያለነው፡፡
በጃንዋሪ 2020 ዓ.ም አጋማሽ ላይ በሸራተን ሆቴል ከኢፌዲሪ ትምህርት ማኒስቴር፣ ከክልልና ከዞን ትምህርት ቢሮዎች ጋር የአስተሳሰብ ለውጥ ትምህርት ለመስጠት ስምምነት ተፈራርማችሁ ነበር፡፡ እስኪ ስለዚህ ጉዳይ ትንሽ ያብራሩልኝ…
በመጀመሪያ ድርጅታችን IYF የዛሬ አራት ዓመት ከትምህርት ሚኒስቴርና ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር፣ ከአንድ ወር በፊት ደግሞ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተፈራርመን ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከ150ሺህ በላይ ወጣቶችን አሰልጥነናል፡፡ ከዋናው ስልጠና በፊት ትንሽ ስልጠና ነበር የሰጠነው፡፡ ለምሳሌ የሰዓት አጠቃቀም ስልጠና ሰጠናቸው፡፡ ሰዓትን ማክበርና በአግባቡ መጠቀም ከአስተሳሰብና ከአዕምሮ ጋር የተያያዘ ነገር ስለሆነ ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ቤተሰቦቻቸውን፣ አስተማሪዎቻቸውንና በዙሪያቸው ያሉትን ሰዎችም እንዲያከብሩ አሰለጠናቸው፡፡ ከትምህርቶቹ መካከል አንዱ “የአስተሳሰብ ክትባት” ይባላል፡፡ አንድ ልጅ ሲወለድ ብዙ ክትባቶችን ይከተባል አይደል?! ክትባት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ የተወለደውን ልጅ ሊይዙት ከሚችሉ በሽታዎች የሚታደግ ነው:: የአስተሳሰብ ክትባትም ተመሳሳይ ጥቅም አለው:: ለምሳሌ በዚህ ዓለም ላይ ስንኖር፣ በደስታ ህይወታችንን ለመምራት ትክክለኛ ግንኙነት ያስፈልገናል፡፡ ትክክለኛ ግንኙነት የሚፈጠረው በአስተሳሰብ ክትባት ነው፡፡
የአስተሳሰብ ክትባት ትክክለኛ ግንኙነት ይፈጥራል ሲባል እንዴት እንደሆነ ሊያብራሩልን ይችላሉ?
ምን መሰለሽ… ከቤተሰቦቻችን ከትዳር አጋሮቻችን፣ ከጐረቤቶቻችን፣ ከስራ ባልደረቦቻችን፣ ከጓደኞቻችንና ከዘመዶቻችን ጋር ያለን ግንኙነት ጤናማና ትክክለኛ መሆን አለበት፡፡ ይህን ትክክለኛና ጤናማ ግንኙነት ለመመስረት፣ የአስተሳሰብ ክትባት ያስፈልጋል:: ለምሳሌ፡- አንድ ወንድ ሚስቱን “አንቺ የእኔ ሚስት በመሆንሽ እኔ እድለኛ፣ ደስተኛና ከሁሉም ወንድ በላይ  ነኝ” ማለት አለበት፡፡ ሴቷም ባሏን “አንተ የኔ ባል በመሆንህ የተመረጥኩና ዕድለኛ ነኝ” ማለት አለባት፡፡ የስራ ባልደረባንም ቢሆን “አንተ (አንቺ) የስራ ባልደረባዬ ስለሆንክ (ስለሆንሽ) እና አብረን ስለምንሰራ ደስተኛ ነኝ፤ ዕድለኛም ነኝ” ማለት ያስፈልጋል:: ሰዎች እንዲህ በየቀኑ መልካም ቃላት ከተቀያየሩ፣ ከባቢው ሁሉ ጤናማ መንፈስ ይኖረዋል፡፡
ሰራተኞችም ለተቋማቸው አመራሮች “እርስዎ የእኛ አሰሪ በመሆንዎ፣ ድርጅቱን በቀናነት ስለሚመሩ እናመሰግናለን፤ ደስተኞች ነን” ብለው አድናቆታቸውን ሲገልፁ፤ ያ መሪ የበለጠ ጥሩ፣ ቀናና ከስሩ ያሉትን ሰራተኞችም ሆነ ስራውን የሚወድ ታታሪና ቀና እየሆነ ይሄዳል:: ይሄ በሰዎች መካከል ጤናማ ግንኙነት የሚፈጥር፣ ከጭቅጭቅና ከክርክር ነፃ የሆነ የስራና የህይወት ከባቢ እውን ያደርጋል:: ይሄ የአስተሳሰብ ክትባት ይባላል:: ነገር ግን ሴቶች “አንተ የኔ ባል ለመሆን አትመጥንም፣ ወርሃዊ ደሞዝህ ትንሽ ነው፤ አንተን በማግባቴ ደስተኛ አይደለሁም” ካሉና እሱም እንደዛው የሚል ከሆነ፣ የተበላሸ ግንኙነት ውስጥ ነን ማለት ነው:: ከዚህ ለመውጣት ደግሞ ለሰውነታችን ብቻ ሳይሆን፣ ለአስተሳሰባችንም ክትባት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡
በስልጠናው የመጣውን የአስተሳሰብ ለውጥና የሥራችሁን ውጤት የምትመዝኑበት መንገድ ምንድን ነው?
እንዳልኩሽ ለተከታታይ ዓመታት ስልጠናዎችን ስንሰጥ ቆይተናል፡፡ አሁንም እየሰጠን ነው፡፡ በዚህ ስልጠና  በተለይ ወጣቶች ተስፋ እንዳይቆርጡ፣ ነገን አሻግረው እንዲያዩ እየሰራን ነው፡፡ ተስፋ መቁረጥ ለወጣቶች ዋና እንቅፋት ነው፡፡ እኔ ስልጠና ስሰጣቸው ሀገሬን ደቡብ ኮሪያን በምሳሌነት እያነሳሁ እነግራቸዋለሁ፡፡ ከ70 ዓመት በፊት አንድ ኮሪያ ነበር የነበረው:: ከዚያ በኋላ በተነሳው የእርስ በእርስ ጦርነት ለሁለት ተከፈለች፤ ደቡብና ሰሜን ተባለ፡፡ በጦርነቱ ኮሪያ በጣም ፈርሳለች፤ ወድማለችም፤ በወንድማማቾች መካከል በተነሳ ጦርነት የኮሪያ ታሪክም ልማትም ፈርሶ ትልቅ ሀዘን ላይ ነበርን፡፡ ህዝቡም ትልቅ ስቃይ ውስጥ ነበር፡፡ በወቅቱ የውጭ አገር መገናኛ ብዙኃን መጥተው ሁኔታውን አይተው ሲመለሱ፤ ኮሪያ የምትባል አገር ታሪክ ሆና ትቀራለች እንጂ ዳግም አገር ሆና አትመለስም ብለው ነበር፡፡ እኛ ሀዘናችንን ገታ አድርገን፣ ወደ አስተሳሰብ ለውጥ አተኩረን አስተሳሰባችንን ቀየርን፡፡
የደቡብ ኮሪያ የቆዳ ስፋት ከኢትዮጵያ አንፃር ብትመለከቻት፣ 1/12ኛ የሆነች፣ በጣም ትንሽ አገር ናት፡፡ ከቆዳ ስፋቷ 70 በመቶው ተራራማና ምቹ ያልሆነ ቦታ ነው፡፡ የደቡብ ኮሪያን ምድር የትም ሄደሽ ብትቆፍሪ፣ ከድንጋይ ውጭ ምንም ማዕድን አታገኝም፡፡ በወቅቱ የነበረው የሀገሪቱ መሪ፣ የነዳጅ ድፍድፍ ለማግኘት ሞክረው ነበር፤ ነገር ግን አንድም ጠብታ ነዳጅ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ማዕድንም ነዳጅም የለም ብሎ እጅ አጣጥፎ ከመቀመጥ ወደ አስተሳሰብ ለውጥ አተኩሮ፣ መጀመሪያ ራሱ መሪው አስተሳሰቡን ቀየረ፡፡ ምን አለ? “በደቡብ ኮሪያ ማዕድናት ባይኖሩም፣ የቡና ተክል ባይኖርም፣ ነዳጅ ባይገኝም… እኛ ግን  እነዚህን ምርቶች ለውጭ ገበያ መላክ አንችልም ወይ? እንችላለን::” እንዴት ይቻላል? የሚለውን ተመልከቺ፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ በቡና ምርት ከሚታወቁት አገራት አንዷ ናት፡፡ የይርጋ ጨፌ፣ የሲዳሞ፣ የጅማ ቡና አላት፡፡ ምርጥ ምርጥ ቡናዎች አሏት:: ደቡብ ኮሪያ እነዚህን ቡናዎች  ከኢትዮጵያ ወሰደችና ዕሴት ጨምራ፣ ወደ ሌላ አገር መላክ ጀመረች:: ልብ በይ፤ በአሁኑ ሰዓት ደቡብ ኮሪያ ወደ ውጭ አገር ቡና በመላክ ከዓለም ሶስተኛ ናት፡፡ አምራቿ ኢትዮጵያ ግን ስድስተኛ ናት፡፡ ቅድም እንዳልኩሽ፤ በደቡብ ኮሪያ አንድ ጠብታ ነዳጅ ተቆፍሮ አልተገኘም፤ ነገር ግን አስተሳሰብ ስለተቀየረ የነዳጅ ኬሚካል እቃዎችን ወደ ውጭ መላክ ችለናል፡፡ እንዴት ካልሽኝ? የነዳጅ ድፍድፍ ከአረብ አገራት በማስመጣትና በማጣራት፣ ወደ ውጭ አገራት መላክ ጀመረች፡፡ አሁን ላይ ደቡብ ኮሪያ የነዳጅ ኬሚካል እቃዎችን ወደ ውጭ በመላክ ከዓለም አንደኛ መሆን ትችላለች፡፡ ይሄ ሁሉ የመጣው በአስተሳሰብ ለውጥ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ቡና አምራች ናት፤ ትልልቅ ወንዞች አሏት፤ ጥሩ የአየር ንብረት አላት፣ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችና ብዙ የህዝብ ቁጥር አላት፡፡ ነገር ግን እስካሁን ደሃ ከሚባሉ አገሮች አንዷ ናት፡፡ እንደ ደቡብ ኮሪያ የአስተሳሰብ ለውጥ ብናመጣ፣ የት ልንደርስ እንደምንችል ሊያሳዩን ይችላሎ?
በጣም ጥሩ፡፡ ኢትዮጵያ በጣም በጣም የተባረከች አገር እንደሆነች እርግጠኛ ሆኜ መመስከር እችላለሁ፡፡ ላለፉት 15 ዓመታት አይቻለሁ፡፡ ህዝቡ ሰው የሚያከብርና ስነ ሥርዓት ያለው ነው፡፡ ነገር ግን ወጣቶቹ በዚህ ጊዜ ቶሎ ቶሎ ተስፋ ይቆርጣሉ:: “እኔ በጣም ደሃ ነኝ፤ ቤተሰቤ ድሃ ነው፤ ድሃ ቤተሰብ ስላለብኝ ምንም ማድረግ አልችልም” በማለት ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ አንዳንዶቹ እንደውም ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቁ በኋላ “ምን ላድርግ? ሀገሬ ለኔ ምን ታደርግልኛለች?” እያሉ ተስፋ ይቆርጣሉ:: ቅድም ስለ ሀገሬ ነግሬሽ ነበር፡፡ ሀገሬ ምንም አልነበራትም፤ ሁኔታዎች ተስፋ አስቆራጭ ቢሆኑም፣ ተስፋ ሳትቆርጥ አስተሳሰብ በመቀየሯ፣ ትልቅ ኢኮኖሚ በመምራት ከዓለም 11ኛ አገር ናት፡፡ የደቡብ ኮሪያ ህዝብ ደግሞ በብልጽግና የሚኖር ህዝብ ሆኗል፡፡ ይሄ የሆነው የተፈጥሮ ሀብት ስለነበራቸው አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ግን ብዙ ነገር አላት:: እንዳልሽው ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር አላት:: የራሷ ቋንቋም አላት፤ በጣም አስገራሚ የሆነ ባህል ባለቤትም ናት፤ ነገር ግን ለውጥ እንድታመጣና እንድትበለጽግ ቀደም ብዬ የነገርኩሽ የአስተሳሰብ ክትባት የግድ ያስፈልጋታል፡፡ “አንተ የኔ መሪ ስለሆንክ… አንቺ የኔ የስራ ባልደረባዬ ስለሆንሽ እድለኛ ነኝ፤ ደስተኛም ነኝ” እያሉ እየተግባቡ የሚሰሩ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በእርግጠኝነት ለውጥ ይመጣል፡፡ በአፍሪካ አንደኛ፣ በዓለም ደግሞ በጣም የበለፀገችና በደረጃ የምትቀመጥ አገር መሆን እንደምትችል አልጠራጠርም፡፡
ስለዚህ “IYF” በዚህ አገር እየሰጠ ያለው ስልጠና፣ ይህን የአስተሳሰብ ለውጥ ከማምጣት አንፃር አስተዋጽኦው ምን ያህል ነው?     
በበኩላችን የኢትዮጵያ ወጣት ምንም አይነት ፈተና ቢገጥመው፣ ተስፋ እንዳይቆርጥና ችግሮችን በጽናት እንዲጋፈጥ ነው የምናሰለጥነው፡፡ ጠንካራ አመለካከት ያለው ሰው ተስፋ አይቆርጥም፡፡ ተስፋ ለማይቆርጥና ፈተናን በጽናት ለሚጋፈጥ ሁሌም መንገድ አለ:: ይህን እንመክራቸዋለን፤ እናሰለጥናለን:: በእርግጠኝነት በወጣቱ ላይ ለውጥ እያየን ነው፣ ቀላል የሚባል አስተዋጽኦ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በደቡብ ኮሪያ ጠንካራና ጥሩ የሆኑ ተሞክሮዎች አሉ:: እነዛን ልምዶችና ተሞክሮዎች በማምጣት ጭምር ነው የምንደግፋቸው:: በጆሮ ሰምተው እንዲያልፉ ብቻ ሳይሆን ወደ ተግባር ገብተው፣ ለሀገራቸው እንዲሰሩና በደስታ እንዲኖሩ ነው እየጣርን ያለነው፡፡
በተለይ ከሁለት ዓመት በፊት በመቀሌ የመላው አፍሪካ የዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ውድድር ተካሂዶ ነበር፡፡ እኛም ከመቀሌ ከተማና ከዩኒቨርስቲው ጋር ስምምነት ተፈራርመን፣ 1500 የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በጐ ፈቃደኛ ተማሪዎችን ለ1 ዓመት አሰልጥነን ነበር፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ለበጐ ፈቃደኝነት ተመዝግበው ነበር፡፡ ከዚያ አንድ ሁለት ጊዜ ወርክሾፖችና ሥልጠናዎች ተካሂደው ነበር፡፡ አንድ ቀን ታዲያ አንዱ ተማሪ “እኛ አሁን በጐ ፈቃደኞች ሆነን እየሰራን ነው፤ ዩኒቨርስቲያችን ለእኛ ምን ይሰጠናል? ምንስ ይከፍለናል?” ብሎ ትንሽ ብጥብጥ አስነስቶ ነበር፡፡ ከዚያ “IYF” ለአንድ አመት በየወሩ በአስተሳሰብና በተያያዥ ጉዳዮች ሥልጠና በመስጠት ምሳሌዎችን በማቅረብ፣ በጐ ፈቃደኝነት ምን ማለት እንደሆነ ስለ አላማው ስናሰለጥናቸው፣ የበጐ ፈቃደኝነት ምንነት ገባቸውና 1500ዎቹ እየተግባቡ መጡ:: እስካሁን መቀሌ ዩኒቨርስቲና ስፖርት ኮሚሽን “IYF” ን ያመሰግናሉ፡፡ ይሄ አንድ የለውጥ ማሳያ ነው፡፡
በ2020 የመጀመሪያ ወር ላይ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተፈራርማችሁ ነበር አይደለም?
አዎ ተፈራርመናል፡፡ ለኢትዮጵያ ብልጽግናና ዕድገት 10ሺህ በጐ ፈቃደኞች መዘጋጀታቸውን ሰምተናል፡፡ የሰላም ሚኒስትሯ ለ“IYF” መስራች ለዶ/ር ኦክሱ ፓርክም ለእኛም ነግረውናል:: ስለዚህ የመጀመሪያው ዙር ስልጠና በማርች ወር ከኮሪያ በመጡ አሰልጣኞች ይጀመራል ማለት ነው፡፡ በየክልሉ ለሚገኙ አመራሮችም ሰራተኞችም ስልጠና እየሰጠን ነው፡፡ እዚሁ ስልጠና ከመስጠት ባለፈ አመራሮችን ወደ ደቡብ ኮሪያ ጋብዘን ወስደን፣ ብዙ ጥሩ ተመክሮዎችን አይተው ወደ ክልላቸውና ወደ ከተማቸው በመመለስ ለውጥ ለማምጣት እየሰሩ ነው፡፡ ይህም ራሱን የቻለ ለውጥ ያመጣል፡፡
አገራችሁ በወቅቱ የነበሩት መሪያችሁ ጀነራል ፕሬዚዳንት ፓርክ ባመጡት የአስተሳሰብ ለውጥ ለዛሬው የዕድገት የዕድገት ደረጃ መድረሷ ይነገራል፡፡ ከእኛ አገር መሪዎችሽ ምን ይጠበቃል?
እውነት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ጀነራል ፕሬዚዳንት ፓርክ ከአሁኑ የኢትዮጵያ መሪ ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር በእጅጉ ይመሳሰላሉ፡፡
እስኪ ምን እንደሚያመሳስላቸው ያብራሩልኝ…?
አገር መውደዳቸው፣ ለአንድነት መትጋታቸው፣ ለለውጥ የሚለፉት ነገር ያመሳስላቸዋል፡፡ ነገር ግን አንድ የሚለይ ነገር አለ፡፡ የጀነራል ፓርክ አላማ አንድና አንድ ነበር፤ አገሪቱን ማበልፀግ፤ ስለዚህ ፓርክ ከከተማው እስከ ገጠሩ ያለውን የኮሪያን ህዝብ በአንድ ዓላማ፣ በአንድ ልብ አሰልፈው ነበር የብልጽግና ጉዞ የጀመሩት:: ዶ/ር ዐቢይ እንደ ፓርክ ለአገራቸው ብልጽግናና ዕድገት ይለፋሉ፤ ይደክማሉ ነገር ግን የእርሳቸው አስተሳሰብ ከከተማ እስከ ገጠር ላለው ለሁሉም ብሔረሰብ እንዲዳረስ ሁኔታዎች መመቻቸት አለባቸው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ይህን ማድረግ ከቻሉ ኢትዮጵያ በፍጥነት ታድጋለች፤ የሰላም አገር ትሆናለች:: ቅድም እንደነገርኩሽ፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ የአስተሳሰብ ክትባት ያስፈልገዋል፡፡ አሁን እንደማየው፤ እዚህ አገር አንዱ ብሔር ከሌላው ይጣላል:: ይሄ ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት እንዲጠፋ፣ የአስተሳሰብ ክትባት የግድ ያስፈልጋል፡፡ ከመሪዎቻችሁ የሚጠበቀው የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥቶ፣ ህዝቡን ከላይ እስከ ታች በአንድ ላይ ለለውጥና ብልጽግና ማሰለፍ ነው፡፡
ጀነራል ፕሬዚዳንት ፓርክ ያደረጉት ይህንኑ ነው፡፡ “የአንተ ብሔር መኖር ለእኔ ውበት ነው፤ እድለኛ ነኝ፡፡ አብረን ለአገራችን እንሰራለን እንለወጣለን፡፡ ልዩነታችን በጣም የሚያምር ውበት ነው” መባባልና ተደጋግፎ መሄድ፣ መሪውን መደገፍና ማገዝ ነው፤ ለብልጽግናና ለእድገት መፍትሔው፡፡ አሁን ያለው የኢትዮጵያ መሪ፣ በየትኛውም ዓለም የማይገኝ፣ ጥሩ አስተሳሰብ ያለው መሪ ነው፡፡ አንደኛ ወጣት ነው፣ ሁለተኛ ለራሱ ሳይሆን ለአገሩ ነው የሚደክመው፡፡ ስለዚህ ሊታገዝ ሊደገፍ ይገባዋል፤ አግዙት፤ ከዚያ ከደቡብ ኮሪያም በላይ ለመበልፀግና በደስታ ለመኖር ሰፊ ዕድል አላችሁ፤ መሪያችሁን በአግባቡ ተጠቀሙበት፡፡
ኢትዮጵያና ኮሪያ በደምና በአጥንት የተሳሰረ ወዳጅነት አላቸው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ደቡብ ኮሪያ ሲሄድ፣ ከሌላ አገር ዜጋ በተለየ ክብር አቀባበል ይደረግለታል ይባላል፡፡ እውነት ነው?
እውነት ነው፡፡ የምሬን ነው፤ እኛ ደቡብ ኮሪያዊያን የኢትዮጵያ ትልቅ ውለታ አለብን፤ ምንም ብናደርግላችሁ አንረካም፡፡ ኢትዮጵያን እንደ አንድ የአፍሪካ አገር ብቻ አይደለም የምናያት፤ ሁለታችንም ከላይ እንዳልሽው የደም ትስስር ያለን ሀገሮችና ህዝቦች ነን፡፡ እንደሚታወቀው፤ እኛ የእርስ በርስ ጦርነት ወስጥ በገባን ጊዜ፣ የኢትዮጵያ ጀግኖች ዘማቾች ወደ እኛ መጥተው ነበር:: በጣም ጀግኖች ናቸው፤ ኢትዮጵያዊኑ ዘማቾች አንዴም ተሸንፈው አያውቁም፡፡ ሁሉንም ውጊያ በማሸነፍ ነው ያጠናቀቁት:: ሌላው በጣም የሚገርመኝ፣ በውጊያ ወቅት አንድ ኢትዮጵያዊ ወታደር ተመትቶ ቢወድቅ ትተውት ሄደው አያውቁም፤ “ጓደኛችንን ጥለን አንሄድም፤ አብረን እንሞታለን ነው” የሚሉት፡፡ በጦርነቱ ወቅት አንድም ኢትዮጵያዊ ምርኮኛ እንዳልነበረ ታሪክ ይናገራል፡፡ ይሄ ትክክለኛ ታሪክ ነው:: እናም ከኢትዮጵያ ከፍተኛ እርዳታና ድጋፍ የተነሳ፣ ደቡብ ኮሪያ አሁን ራሷን የቻለች፣ የበለፀገች ሰላማዊ አገር ለመሆን በቅታለች:: እኛም እዚህ መጥተን ስንሰራ ስናገለግል፣ ውለታችንን ተመጣጣኝ ባይሆንም እየከፈልን እንደሆነ ይሰማናል፡፡
እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ የኮሪያ ዘማቾችን የሚያስታውስ ፓርክና የአካባቢ ስም ተሰይሟል:: ደቡብ ኮሪያም አንድ መታሰቢያ ሀውልት እንዳለ እሰማለሁ፡፡ እስኪ ስለሱ ይንገሩኝ?     
በደቡብ ኮሪያ “ቹንቻን” የምትባል ከተማ አለች፡፡ በዚህች ከተማ ውስጥ በጦርነቱ ጊዜ ህይወታቸውን የገበሩ ዘማቾች አሉ፡፡ ለነዚህ ዘማቾች ሀውልት ተሰርቷል፡፡ በሀውልቱ ለይ ስማቸው ተጽፎ ተቀምጧል፡፡ ከ6 ወር በፊት ከወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዳገቶ ኩምቢና ሌሎች የዞኑ አመራሮች ጋር አብረን ሄደን ነበር፤ ሀውልቱን ጐብኝተው እየተገረሙና እየተደነቁ ተመልክቼአለሁ፡፡
እርስዎ አማርኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ፤ ይጽፋሉም፡፡ አሁንም ቃለ ምልልሱን በአማርኛ ነው እያደረግን ያለነው፡፡ በአንፃሩ 20 እና 30 ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ የኖሩ ሌሎች የውጭ ዜጐች ለመግባቢያ የሚሆኑትን ቃላት እንኳን አይናገሩም:: የእርስዎ ምንድን ነው ምስጢሩ? ወይስ ይሄም ከአስተሳሰብ ለውጥ ጋር ይገናኛል?
እኔም ብዙ የውጭ አገር ዜጐችን እዚሁ አገኛለሁ፡፡ አንዳንዶች አማርኛ ቋንቋን ሊማሩና ሊያጠኑ ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን የአማርኛ ፊደሎችን ገና እንዳዩአቸው ተስፋ ይቆርጣሉ:: ከዚያ ይተውታል፡፡ ቀደም ብዬ እንዳልኩሽ፤ በቀላሉ ተስፋ መቁረጥና አለመጋፈጥ የብዙ ነገር ማነቆ ነው፡፡ እኔ ግን በ“IYF” የአስተሳሰብ ለውጥ ጠቃሚነትን ስለወሰድኩ ተስፋ አልቆረጥኩም፡፡ በዚያ ላይ እኔ የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ የምሰራው፣ በዋና ዋና ከተማ ብቻ ሳይሆን እስከ ታችኛው ገጠር ድረስ እየሄድኩ ነው:: ከእነሱ ጋር ለመግባባትና ለመቀራረብ የግድ ቋንቋ መልመድ ነበረብኝ፡፡ በእርግጥ ገና እንደመጣሁ ይከብደኛል ብዬ አስቤ ነበር:: ነገር ግን ይሄ የኔ ደካማ አስተሳሰብ ነበር፡፡ ከተሞከረ የማይቻል ነገር የለም፤ ሞክሬያለሁ ተጋፍጫለሁ፤ ገና ይቀረኛል:: ብዙዎች ጐበዝ ነህ፤ ትችላለህ ይሉኛል፤ አንቺን ጨምሮ፤ እኔ ግን ገና አልረካሁም፡፡ በእርግጥ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን ዜና በየቀኑ እየሰማሁ ነው፤ እያወራሁ ነው፣ እያነበብኩ ነው፤ በአማርኛም እየፃፍኩ ነው፡፡
እዚህ ከእነቤተሰብዎ ነው የሚኖሩት?
አዎ ከእነ ቤተሰቤ ነው የምኖረው፤ ባለቤቴም ልጆቼም አማርኛ ይናገራሉ፡፡ ይሰማሉም:: ከኮሪያ ምግብ ይልቅ እንጀራና ጥብስ ይመርጣሉ፡፡ የኮሪያና የኢትዮጵያ ምግብ እኩል ቢቀርብ፣ እንጀራ ላይ ነው ቀድመው የሚሰፍሩት፡፡ አራቱም ልጆቼ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የተወለዱት፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ማህበራዊ ኑሮው የተሳሰረና ከጐረቤት ጋርም ቁርኝቱ የጠበቀ ነው፡፡ እርስዎ ማህበራዊ ግንኙነት ላይ እንዴት ነዎት? ለቅሶ ሰርግ ይሄዳሉ?
ለቅሶም ሰርግም እሄዳለሁ፤ እንደ ኢትዮጵያዊ ነው የምኖረው፡፡ ገና ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣሁ አንድ ነገር አጋጥሞኝ ነበር፡፡ ገና አማርኛ መማር እንደጀመርኩ ሰሞን የተከሰተ ነው:: አንድ የተዋዋቅኩት ኢትዮጵያዊ ጓደኛዬ ዘመድ ሞቶ ቀብር ስነሥርዓት ላይ ተገኘሁ፡፡ በዛን ጊዜ የኢትዮጵያን ባህል አላውቅም ነበረ:: የማጽናኛ ቃላትን ተጠቅሜ ለምሳሌ “ምጽ አይዞህ እግዚአብሔር ያጽናህ፤ በርታ” ማለት ነበረብኝ፤ እኔ ግን ምንም አላውቅም::
ከዚያ ምን አልኩት መሰለሽ… ቀረብ ብዬ፤ “እግዚአብሔር ይባርክህ አመሰግናለሁ” ብዬው ሄድኩኝ፡፡ ከዚያ ይህን ስል አጠገቤ ሆኖ የሰማ ኢትዮጵያዊ “ናሆም ምን ነካህ? እንዴት እንዴት እንደዚህ ትላለህ ለቅሶ ላይ?” አለኝ፤ እንዴት ስለው “ለቅሶ ላይ እንደዚህ አይባልም” ሲለኝ፤ “ግዴለም እሱ ይረዳኛል፤ ይገባዋል ሌላ ጊዜ አስተካክለሁ” አልኩት፡፡ አሁን ላይ ሳስበው ያስቀኛል፡፡
ኢትዮጵያዊያን የለቅሶ ስነስርዓት ያከብራሉ:: ለቅሶ ስሄድ “እግዜር ያጽናህ፤ አይዞህ በርታ” እላለሁ፡፡ ሰርግ ከሄድኩም “እንኳን ደስ አላችሁ፤ መልካም ጋብቻ” እላለሁ ባህሉንም ምግቡንም አሁን አውቄያለሁ:: ምግብ መጀመሪያ እንጀራ በጣም ከብዶኝ ነበር፡፡ አሁን ላይ በየቀኑ ምሳ እንጀራ በሽሮ፣ በጐመን፣ ክትፎ ጥብስ እበላለሁ:: ሚጥሚጣም እወዳለሁም፤ ምክንያቱም ደቡብ ኮሪያዊያን የሚያቃጥሉ ነገሮችንና ብዙ ቅመማ ቅመሞችን እንመገባለን::
እስኪ ወደ “IYF” እንመለስ… በስንት የዓለም አገራት ይንቀሳቀሳል?
በመላው አፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ በጠቅላላ በ90 ሀገራት ነው የሚሰራው:: ኢትዮጵያም ውስጥ በመቀሌ፣ በሀዋሳ፣ በሀዲያ ሾኔ፣ ከኔ ቀጥሎ ቻይናዊ፣ ኬኒያዊና ሌሎችም ዳይሬክተሮች እየሰሩ ነው:: አሁን ላይ ኢትዮጵያዊያንን እያሰለጠኑ ይገኛሉ፡፡ እነሱ በብቃት እንደኛ ሰልጥነው ሀላፊነቱን ከኛ ይረከባሉ፤ እኛ ከጀርባ ሆነን እንደግፋቸዋለን:: እንግዲህ አይዋይኤፍ እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም ነው የተመሰረተው:: የተመሰረተበት ምክንያት ደግሞ ኮሪያ በጣም እየበለፀገች በመጣች ቁጥር አንድ ማህበራዊ ችግር ተከሰተ። አንዱና ዋነኛው ችግር የወጣቶች ችግር ነው። ደቡብ ኮሪያ የሳምሰንግና ኤልጂ አምራች እንደመሆኗ ትንንሽ ልጆች ስማርት ስልክ በቀላሉ ይጠቀማሉ፡፡ በየ6 ወሩ አዳዲስ ሞዴሎች ይቀያይራሉ፡፡ አገራችን በኢንተርኔት ፍጥነት ከዓለም አንደኛ ናት፡፡ ሁሉንም ነገር በቀላሉ እየተጠቀሙ ይኖራሉ፤ ነገር ግን ደስተኛ አይደሉም፤ አያመሰግኑምም:: ፍላጎታቸው ገደብ እያጣ መጣ፤ እርካታ የላቸውም:: ስለሌላቸው አይደለም፤ የጎደላቸው ነገር የለም፤ ሆኖም በደቡብ ኮሪያ በየ34 ደቂቃው አንድ ሰው ራሱን ያጠፋል። ይሄ የኢኮኖሚ ችግር ሳይሆን የአስተሳሰብ ችግር ነው።
ከ60 እና 70 ዓመት በፊት የነበሩ አያቶቻችን “ለልጆቻችን ድህነትን አናወርስም” ብለው በትጋት ሰርተው ከድህነት ነፃ አደረጉን:: አሁን ላይ ያሉት ወጣቶች እንክብካቤና ቅንጦት ከመብዛቱ የተነሳ ፍላጎታቸው እየናረ፣ አስተሳሰባቸው እየተዛባ ሄደ፡፡ ሥራ መስራት አይፈልጉም:: ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው እንኳን ፈተና ያለው ሥራ መስራት አይፈልጉም፡፡ በዚህ ችግር የተነሳ ነው ለወጣቱ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት መስራቹ ማህበሩን የመሰረቱት፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ህብረት ከደቡብ ኮሪያ አልፎ ለመላው ዓለም የተረፈው፡፡ በአይዋይ ኤፍ ካሰለጠኑት ውስጥ አንዱ እኔ ነኝ እኔ በበለፀገች አገር ተወልጄ አድጌያለሁ የጎደለኝ ነገር አልነበረኝም።
ሆኖም የሶስት ዓመት ሕጻን እያለሁ ወላጆቼ ስለተፋቱ እድለኛ አይደለሁም ብዬ ተስፋ ቆርጨ ነበር። “አልማርም አያስፈልገኝም” ብዬ ከዱርዬዎች ጋር መንደር ውስጥ እየተዘዋወርኩ እሰርቅ እጠጣና አጨስ ነበር። ተስፋ ከመቁረጤና ከአስተሳሰቤ ጉድለት የተነሳ ነው። ወላጆቻቸው ተፋትተው ያደጉ ተቋቁመው ትልቅ ደረጃ የደረሱ በመላው ዓለም ብዙ ወጣቶች አሉ፡፡ ልክ በ19 ዓመቴ ኮሌጅ ልገባ ስል IYFን አገኘሁ ሕይወቴ ተቀየረ:: የሌሎችን ሕይወት ለመወጥ እየተጋሁ ነው፤ እየለወጥኩም ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ መቼ መቆየት ይፈልጋሉ?
እስከ ሕይወቴ ፍፃሜ መቆየት እፈልጋለሁ፡፡

Read 5654 times