Saturday, 14 March 2020 11:02

“የጐደር ለዛ” ወርሃዊ የኪነ-ጥበብ ዝግጅት በጐንደር ሊጀመር ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

      የጐንደር ከተማ አስተዳደር ከጐንደር ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀው “የጐንደር ለዛ” የተሰኘ ወርሃዊ የኪነጥበብ መሰናዶ ሊጀመር ነው፡፡ በዚህ መሰናዶ ለሀገርና ለማህበረሰቡ ጠቃሚ የሆኑ የሀገርን ዕሴት፣ ባህል፣ አንድነትና ትብብር የሚያጐሉ መሰናዶዎች የሚቀርቡበት ሲሆን፤ በወርሃዊ መሰናዶው አሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ ከገጠመን ቀውስ ለመወጣት አንዱ የመፍትሔ አካል ይሆናል ተብሎ እንደታመነበት የጐንደር ባህል ማዕከል ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
“የጐንደር ለዛ” ወርሃዊ መሰናዶ ታዋቂና አዋቂ ሰዎች እየተጋበዙ ያላቸውን ጠቃሚ ሃሳብ፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ፖለቲካ ከአገር አንድነት፣ መተባበር፣ መተጋገዝና ህብረት አንፃር በመቃኘት የሚያቀርቡበት እንደሚሆን የባህል ማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገብረማሪያም ይርጋ ተናግረዋል፡፡
እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ በወርሃዊ ዝግጅቱ በምሁራንና ታዋቂ ሰዎች በሚቀርቡ መሰናዶዎች ስለሀገር መውደድ፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት መተሳሰብ፣ ስለ ሰብአዊነት፣ ስለ ሀገር ግንባታ፣ ስለ ተስፋ፣ መቻቻልና አብሮነት በአጠቃላይ አገርና ህዝብን ከመበታተን አውጥቶ በአንድነት ስለማሻገር የሚሰበክበትና ወጣቱ ትውልድ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጣ የሚረዱ አነቃቂ ንግግሮች፣ ግጥሞች፣ ዲስኩሮች፣ ወጐችና መሰል መሰናዶዎች በሙዚቃ ታጅበው የሚቀርቡበት ነው ተብሏል፡፡
በየወሩም ከተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የሚጋበዙ ገጣሚያን የዩኒቨርስቲ ምሁራን፣ አንቂዎች፣ አርቲስቶች፣ የስነ ጽሑፍ ባለሙያዎችና ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ የተባለ ሲሆን፤ መሰናዶው ከቀጣዩ ሳምንትጀምሮ መካሄድ እንደሚጀምር አቶ ገብረማርያም ጨምረው ገልፀዋል፡፡


Read 21008 times