Saturday, 14 March 2020 11:02

ባልታቀደ እርግዝና ምክንያት የሚከሰት ድብርት

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

        ባልታቀደ እርግዝና ምክንያት ድብርት ለምን እንደሚከሰት ከሚገልጸው በጥናት የተደገፈ መረጃ በፊት የአንዲት እናት ገጠመኝን ጽሁፍ እንደሚከተለው አጠር አድርገን ለንባብ ብለናል፡፡
‹‹እኔ ልጅ መውለድ የጀመርኩት ገና የ16/አመት ታዳጊ ሆኜ ነበር፡፡ በእርግጥ ዛሬ እድሜዋ ከስድሳ ለዘለለ ሴት እንደ ደንብ ይቆጠር ነበር እንዳትሉኝ፡፡ ምክንያትም እኔ እድገቴ ገጠር ሳይሆን ከአዲስ አበባ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ:: በቃ፡፡ ሁሉም ነገር ቀርቶ ጉዞ ወደ ትዳር ሆነ፡፡ እርሳስና ደብተሩን ቁጭ አድርጌ ቢላና መክተፊያዬን ጨበጥኩ፡፡ ከዚያም በልክ በልኬ የተሰፉልኝን ቀሚሶቼን ጥዬ ከእግር እስከራሴ የባለቤቴን እናት ቀሚስ ማጥለቅ ጀመርኩ፡፡
እራሴን እንደሆንኩ ለመቀጠል ያልቻልኩበት ምክንየት ደግሞ እርግዝና ነው፡፡ እያከታ ተልኩ ልጆች ወለድኩ፡፡ ነገር ግን አንድም ጊዜ እርግዝናዬን ወድጄው አላውቅም፡፡ ሁልጊዜ ጉዋደኞቼን እና ትምህርቴን እያሰብኩ እንዳዘንኩ እና እንዳለቀስኩ እርግዝናው አልቆ ልጅ ይወለዳል፡፡ አንዳንዴም የሚኬድበት እየጠፋኝ እንጂ ልጅን ማስወረድ እቃጣ ነበር፡፡ ብቻ እስከዛሬም ድረስ የእኔ እርግዝና እኔንም ሆነ ባለቤቴን አስደስቶ አያውቅም፡፡
ባለቤቴ እርጉዝ ልሁን አልሁን ግድ የሚሰጠው ሰው አልነበረም፡፡ እናቱ የገንፎ እህል ማዘጋጃ ሲጠይቁት ነው ማርገዜንም የሚያውቀው፡፡ እኔማ ስለማፍረው ምንም አልጠይቀውም፡፡ እሱም ልጅ ልናገኝ ነው ወይንም የእኔ ሚስት አይዞሽ ብሎኝ አያውቅም፡፡ ጊዜ ካለፈ በሁዋላ እንኩዋን …አንተ እኮ አንድም ቀን በእርግዝናዬ ምክንያት ወይንም በመውለዴ ምክንያት አጽናንተኸኝ አታውቅም….ስለው… ለምን አጽናናሻለሁ… የተፈጥሮ ግዴታሽ አይደለም እንዴ …. የሚል መልስ ነበር የሰጠኝ፡፡
በእርግጥ ልጆቼ ዛሬ በጣም ያስደስቱኛል….ይረዱኛል…ቢያመኝ ያሳክሙኛል…. ከፈጣሪ በታች ካለእነሱ ምንም ደጋፊ እና ተመልካች የለኝም:: ባለቤቴም ካረፈ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን እኔ በራሴ ሕይወት የተደሰትሽበትን ቀን አምጪ ብባል መልስ የለኝም፡፡ ሁልጊዜ እርግዝና ሲከሰት እኔ እንዳዘንኩና እንደተደበርኩ ነበር ጊዜው የሚያልቀው፡፡ የማዋየው ሰው እንኩዋን የለም:: በጊዜው እንደአሁኑ በቀጥታ የእርግዝና ክትትል ስላላነበረ በስነስርአቱ እየሄድኩ አልመረመርም ነበር:: እንድሄድ የሚያበረታታኝም ሰው አልነበረም፡፡ ሁልጊዜም ለማርገዝ አስቤ ሳይሆን ሳልዘጋጅ ሳላቅድ እያረገዝኩ ሳልደሰት እየወለድኩ እነሳ ነበር፡፡ ወላድ በመሆኔ ምንያት በተለይም በባለቤቴ ቤተሰቦች በኩል ምስጋናና ሙገሳ ይቀርብልኝ የነበረ ሲሆን እኔ ደግሞ ያንን ሙገሳ በጥላቻ ሳስታውሰው የምኖረው ነው፡፡ ምክንያቱም የእነሱ ሙገሳ ሴት ልጅ ከተዳር በሁዋላ ልጅ ከመውለድና ከማሳደግ በላይ ምንም ስራ የላትም የሚል ስሜት ያዘለ ስለሆነ ነው፡፡››
ውብአለም ተጠምቀ ከኮልፌ
የወ/ሮ ውብአለም ተጠምቀ ገጠመኝ በዚያ ዘመን ለነበሩ ሰዎች አዲስ ነገር አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ብዙ ሴቶች ወደትዳር አለም ይገቡ የነበረበት እድሜ ተመሳሳይ እና ከህጻንነት እድሜ ክልል ገና ሳይወጡ ስለነበር ልጅ መውለድ የሚጀምሩትም ልጅ ወልዶ መሳም ምን ያሀል እንደሚያስደስት በማያውቁበት ደረጃ ነው፡፡ ሴቶች በታዳጊነት እድሜያቸው ገና ብዙ መማር ሲኖርባቸው እንዲሁም እራሳቸውን ወደተሸሻለው አለም የሚያስገባቸውን ግንዛቤ እና ክህሎት ጨብጠው እራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን እንዲሁም አገር ወገናቸውን እንዲጠቅሙ መንገዱን ከመክፈት ይልቅ በልጅነት እድሜያቸው እራሳቸው ወደውና ፈቅደው ሳይሆን በቤተሰብ ምርጫ እና ትዛዝ የሚገቡበት የትዳር አለም የብዙዎችን ብቃት የሚፈታተን እንደነበር የሚመሰክሩ ብዙዎች ናቸው:: ዛሬ ግን ብዙ ምርጫ ያለ ሲሆን አሁንም ግን በተመሳሳይ ችግር ውስጥ የሚወድቁ የሉም ማለት አይቻልም፡፡
በርእሱ የተጠቀሰው ሴቶች ከእቅድ ውጪ እርግዝና ሲከሰት የሚያደርጉትን የእርግዝና ክትትል እስከማወክ የሚደርስ ድብርት ወይንም ደስተኛ አለመሆን የሚከሰተው በምን ምክንያት ነው የሚለውን ወደ አማርኛ መልሰነዋል፡፡
ድብርት የሚለውን ቃል አሲስታንት ፕሮፌሰር ወንዳለ ጌትነት ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በጥናታ ቸው ምንጭ ጠቅሰው እንደገለጹት በአለም ዙሪያ በሕይወት ከሚኖርባቸው አመታት ወደ 12 ከመቶ የሚሆነው ከአቅም ማነስ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ የአለም የስነአእምሮ ጤና እ.ኤ.አ በ2012/ እንዳሳወቀው በእርግዝና ጊዜ የሚከሰተው ድብርት አካላዊና ስነልቡናዊ ጉዳትን ወይንም ምቾት ማጣትን ያስከትላል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደሚጠቁመው ድብርት እ.ኤ.አ በ2020/ ለታማሚዎቹም ሆነ አገልግሎት ለሚሰጡት በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀስ የህመም መንስኤ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ የአለም ጤና ድርጅት (WHO,2009) እንዳስነበበው ድብርት ምንም እንኩዋን የስነ ተዋልዶ እድሜ ላይ በሚገኙ አቅም በሌላቸው ሴቶች መካከል ለህመም መንስኤ የሚሆን ቢሆንም እንደስነተዋልዶ ጤና የማይቆጠር መሆኑ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል፡፡ ባደጉ አገሮች ከአስር ሴቶች አንዱዋ በዚህ ችግር እንደሚወድቁ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡
ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ይህ ድብርት በመባል የሚታወቅ ችግር በስፋት የተለመደ እና የችግሩ ስፋት ከ8 ከመቶ ወደ 40 ከመቶ ማደጉንም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡  
አለም አቀፍ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ድብርት ከወሊድ በሁዋላ ከሚከሰተው ይልቅ በእርግዝና ጊዜ የሚታዩት እጅጉን የተለመዱ እና ከፍተኛ ደረጃን የያዙ ናቸው፡፡
በእርግዝና ጊዜ የሚደርሰው የድብርት ስሜት በባለሙያ በትክክል ካልተረዳ በጽንሱ ላይ ጎጂ ተጽእኖ ሊኖረው እና ጉዳቱም ሊጨምር ይችላል፡፡
አሲስታንት ፕሮፌሰር ወንዳለ ጌትነት ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንደሚጠቁሙት ጥናቱን ለስራት ያገላበጡዋቸው 9 ጥናቶች በአርግዝና ወቅት የሚኖረው ድብርት ከ11.8 ከመቶ ወደ 31 ከመቶ ጨምሮ ይገኛል፡፡
ድብርት የተለያዩ ምክንያቶች አሉት፡፡
የመጀመሪያው እና በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው የእርግዝናው አለመታቀድ ነው፡፡
አንዲት ሴት ለማርገዝ ሳትፈልግ እርግዝና ከተከሰተ እና ወልዶ በተገቢው መንገድ ከማሳደግ ጀምሮ ሌሎች ተያያዥ የሆኑትን ነገሮች መስመር ለማስያዝ የምትቸገር ከሆነ ለድብርት ትጋለጣለች፡፡
ተያይዞም የስነልቡናና የማህበራዊ ችግሮች እንዲከሰቱ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
ጥናቱ በስተመጨረሻው እንደጠቆመው
በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት ድብርት የእናቶችና የህብረተሰብ ጤና ችግር ነው፡፡
ስለሆነም ያልታቀደ እርግዝና እንዳይከሰት ልዩ ትኩረትን በመስጠት ማህበራዊ ድጋፍ ማድረግ፤
ከእርግዝና ጋር በተገናኛ የሚደርሱ የተለያዩ ችግሮችን መፍታት፤
ሊፈጠሩ የሚችሉ ግጭቶችን እንዴት መፍታት እንደሚቻል ማሳየት ፤
ሴቶች ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ጉደቶችን ማስወገድ የሚቻልባቸውን መንገዶች መጠቆም፤
የመሳሰሉትን ለመስራት ልዩ ትኩረትን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የጥናት ወረቀቱ በስተመጨረሻው የሚከተለውን ሀሳብ አስፍሮአል፡፡
የአእምሮን ጤና ከሌሎች አስፈላጊ ከሆኑ የጤና አሰጣጥ ፕሮግራሞች ጋር በማቀናጀት በዋናነት መመልከት፤
ሁሉ አቀፍ የህክምና አገልግሎት ተግባራዊ መደረግ መቻል አለበት፡፡
በየትኛውም የጤና አገልግሎት የአእምሮ ጤናን በሚመለከት ስልጠናን በመስጠት አገልግሎቱን ማስፋፋት፤
ባልታቀደ እርግዝና ምክንያት የሚከሰተውን ድብርት ለመከላከል እንዲቻል ከእቅድ ውጭ በሆነ እርግዝና ላይ ትኩረት ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡  


Read 13493 times