Saturday, 14 March 2020 11:06

ሻይ በሰላም መጠጣት

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

  “ታዲያላችሁ…አንዳንድ ቀን በቃ ምንም ነገር ሳትሰሙና ሳታዩ መዋል ትፈልጋላችሁ፡፡ ሬድዮና ቴሌቪዥን የለ፣ ጋዜጣ የለ፣ ፌስቡክ ምናምን ቡክ የለ! ዓለም ልትጠፋ ነው ቢባል እንኳን “ለአርባ ስምንት ሰዓታት ኖ ፌስቡክ!” አይነት ‘ሰበር ውሳኔ’ ታስተላልፋላችሁ፡፡--”
        
          እንዴት ሰነበታችሁሳ!
መቼም የችግር ወሬ እጥረት የለብንም፡፡ የምር ግን አንዳንዴ… አለ አይደል… “ምንም ነገር የማልሰማበት፣ የማላይበት የት ብሄድ ይሻላል!” የሚል ምኞት አያድርባችሁም! አሀ…በዚህ ስትሄዱ የሆነ ችግር፣ በዛ ስትሄዱ ሌላ ችግር፡፡ ቤታችሁ እኮ ችግር ከሳንቃ እስከ ጣራ ሞልቶላችኋል፡፡ ያለፈው ቀን ማታ፤ አስሩን ጨርሶ አስራ አንደኛ ዓመቱን የያዘ ጎረምሳችሁ ይመጣል…
“ዳድ…” ይላል ‘ፍሪዝ’ ለማድረግ እየሞከረ ያለውን ጸጉሩን ሳብ፣ ሳብ እያደረገ፡፡ (“አባዬ” ምናምን ከቀረ እኮ ሰነበተ፡፡)
“እህ…ደግሞ ምን ጎደለ?”
“ዳድ፣ ትምህርት ቤት ልጆች ሁሉ ይዘዋል እኮ! ለምንድነው ለእኔም የማትገዛልኝ?!”
አሁን ደግሞ ምን አይነት  ስኒከር አድርገው አይቶ ይሆን!
 “ምንድነው የምገዛልህ?!”
“ስማርት ፎን ነዋ፤ ዳድ!”
ጎሽ! ‘ጭራሽ የዛሬ ዓመት ለስኒከር ያወጣሁት ሁለት ሺህ ብር አልተተካ፤ አጅሬው ስማርት ፎን አማረው! ኮስተር ትላላችሁ፡፡
“ሌላ ጊዜ እናወራለን”
“ዳድ፣ ግን…”
“ሌላ ጊዜ አልኩህ!”
እያጉረመረመ ይሄዳል፡፡ እና የእሱ ስማርትፎን ጥያቄ፣ ሆድ እያባሳችሁ ሳለ እራት ይቀርባል፡፡ አየት ታደርጉና በሆዳችሁ… “እኔ የምለው…ወጡ ውስጥ ምስርም እንደ ሥጋ እየተፈለገች የምትገኝ ልትሆን ነው!” ምናምን ትላላችሁ፡፡ ትንፍሽ በሉና ‘ማዳም’ በሰከንድ አስራ ሦስት ጥይት የሚያርከፈከፍ ኡዚ ምናምን ነገር ልትሆንባችሁ ትችላለች፡፡ አሀ…የእናንተ ነገር አንገቷ ሲደርስስ! “ቲማቲም ተወደደ፣” “የሽንኩርት ዋጋ አልቀመስ አለ፣” ስትባሉ ምንም ሳይሰማችሁ… “ያለውን አብቃቂው፣” ስትሉ እንዳልነበር ይኸው ድራፍትና ቢራ ተወደደ ብላችሁ ንጭንጫችሁ አላስቀምጥ ብሏታል፡፡
እናላችሁ…  እራት ያልቅና የሆነ ቴሌቪዥን ፊልም ማየት ስትጀምሩ ‘ማዳም’ ወደ መኝታ ቤት ታመራለች፡፡ እግረ መንገድም ትእዛዝ ታስተላልፋለች:: “ጠዋት ሳልነሳ ከሄድክ የኩንታል ጤፍና ሀያ አምስት ኪሎ ስንዴ ገንዘብ ሳታስቀምጥ እንዳትሄድ፡፡” “አስቀምጥልኝ…” ማለት መልእክት ማስተላለፍ ነው፡፡ “ሳታስቀምጥ እንዳትሄድ…” ግን የበላይ አካል ውሳኔ አይነት ነው፡፡ እናማ… “እዚህ ቤት እኮ ከአምስት ኪሎ ቲማቲም ይልቅ ቀድሞ የሚያልቀው መቶው ኪሎው  ጤፍ ነው፣” ብላችሁ ታጉረመርሙና ማዳም ደግሞ ‘በአስፈላጊዎቹ’ ቅጽሎች ቀና እንዳትሉ አድርጋ ትረመርማችኋለች፡፡
ታዲያላችሁ…አንዳንድ ቀን በቃ ምንም ነገር ሳትሰሙና ሳታዩ መዋል ትፈልጋላችሁ፡፡ ሬድዮና ቴሌቪዥን የለ፣ ጋዜጣ የለ፣ ፌስቡክ ምናምን ቡክ የለ! ዓለም ልትጠፋ ነው ቢባል እንኳን “ለአርባ ስምንት ሰዓታት ኖ ፌስቡክ!” አይነት ‘ሰበር ውሳኔ’ ታስተላልፋላችሁ፡፡
እናማ…የሆነ ቦታ ሻያችሁን ይዛችሁ ወጪ ወራጁን ታያላችሁ፡፡ “ለካ ሌላ፣ ሌላው ነገር ላይ ሙጭጭ ብዬ ስንት ነገር አምልጦኛል! እኔ የት ሄጄ ነው ይህች ሁሉ ቆንጆ ወደዚህ ዓለም የመጣችው!” እናላችሁ…ሰዉም፣ የለበሰውም ልብስም፣ መኪናውም…ብቻ ሁሉም ነገር ይብለጨለጭባችኋል፡፡ “ለካስ ሁሉም ነገር ሲተዉት ይተዋል!” ምናምን አይነት ፍልስፍና ይሞካክራችኋል፡፡ ሻይም እንዲህ ይጥማል እንዴ! ድንገት ልክ ከሰማይ ዱብ ያለ ይመስል፣ የሆነ የምታውቁት ሰው አጠገባችሁ ከች ብሏል፡፡
 “አንተ!” ድምጹ እኮ ልክ የተፈጥሮ ‘ሜጋፎን’ ሲወለድ ጀምሮ የተገጠመለት ነው የሚመስለው፡፡ “አንተ፣ እዚህ ሀገር ላይ አለህ?” እንዴት ነው ነገሩ! ልክ እኮ ‘ፖፑሌሽን ሴንሰስ’ ምናምን የሚሉት ላይ ተዘላችሁ የታለፋችሁ ነው የሚመስለው:: የምር እኮ ይቺ “አንተ፣ እዚህ ሀገር ላይ አለህ?” የሚሏት ነገር አንዳንዴ ሰልቸት ትላለች፡፡ ኮሚክ እኮ ነው… ከትናንት ወዲያ አምስት ጃምቦ ድራፍት እንባ እንባ እያላችሁ ከፍላችሁለታል እኮ! ፈገግ ብላችሁ፣ ወይም ፈገግ ለማለት እየሞከራችሁ፣ ከአንገት እንቅስቃሴ በስተቀር መልስ አትሰጡትም፡፡
እናማ… መቼም የጉድ ዘመን ነውና ሀምሳ ምናምን ባዶ ወንበር እያለ፣ አጠገባችሁ ይቀመጣል ሳይሆን ጉብ ይላል…ልክ ሆነ የጂብራልታር አለት ይመስል ‘ጉብ’ ይላል:: ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል….ኮሚክ እኮ ነገር ነው፡፡ የሆነ ሰው ብቻውን ተቀምጦ ሻይ፣ ቡና እያለ ነው:: ስንገባ እናየውና ሰላምታ እንሰጠዋለን፡፡ እናም ሰላም ብለን መንገድ ቀጥለን፣ ሌላ ወንበር ላይ እንደ መቀመጥ  አጠገቡ ያለ ወንበር ሳብ አድርገን መቀመጥ ሳይሆን ‘ጉብ’ እንላለን፡፡ ሰውየው እዛ የመሸገው እኮ ሰው እንዳያገኘው፣ ብቸኝነቱን ፈልጎ ነው! ለተወሰኑ ሰዓታት እኛንም፣ ወሬያችንንም ሸሽቶ ነው እኮ! እና “ተቀመጥ…” “ቁጭ በይ እንጂ…”  ምናምን ሳይባሉ ሄዶ ‘ጉብ’ ማለት ድንኳን ሰበራ እንጂ ወዳጅነት አይደለም!
እናላችሁ… “አንተ፣ እዚህ ሀገር ላይ አለህ?” ያለውና ከሶስት ቀን በፊት ሁለታችሁም ታክሲ ስትጠብቁ ያገኛችሁት ሰው፣ ምንም ሳይጠይቅ፣ ከሌላ ሰው ቀጠሮ ይኖራችሁ እንደሁ ሳያረጋግጥ፣ አጠገባችሁ ወንበር ላይ ዘፍ ይላል፡፡ እና ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ኑሮ እንዴት ነው?”
ምን አገባው! የእናንተ ኑሮ እንዴት ይሁን፣ አይሁን እሱ ምን ‘ይኮነስረዋል!’ ስለ ቦተሊከኞች፣ ‘አክቲቪስት’ ስለሚባሉትና እውነትም ‘አክት’ እያደረጉ ስላሉት (ቂ…ቂ…ቂ…) መስማት የጠላችሁትን ያህል ስለ ኑሮ የሚያነሳባችሁን ሰውም አትፈልጉም፡፡ አሀ… ማዳም ያዘዘችው መቶ ኩንታሉ ጤፍ ይመጣባችኋላ! ለዳቦ ይሁን ለማን ያልታወቀው ሀያ አምስት ኪሎ ስንዴው ይመጣባችኋላ! የጎረምሳው የስማርትፎን ጥያቄ ይመጣባችኋላ!
ይኸው ‘ማዳም ሚስት’ ማታ ወደ መኝታ መሄጃችሁን ሰዓት ጠብቃ…  “ጤፍ አልቋል…” ብላ የረጨችባችሁ የሆነ ዲ.ዲ.ቲ. ነገር ሳይራገፍ ይሄ ይጨምርበታል! ቁልጭ ብላችሁ ነው ያደራችሁት፡፡ “እዚህ ቤት እኮ ከአምስት ኪሎ ቲማቲም ይልቅ ቀድሞ የሚያልቀው መቶው ኪሎው  ጤፍ ነው፣” የሚል ትንኮሳ ይሁን ‘ስታንድ አፕ ኮሜዲ’ የማይለይ ነገር ጨምራችሁበት፣ ማዳም ሚስት  ‘ከአንጀት የወጣ ስድብ’ ምን ማለት እንደሆነ በተግባር አሳይታለች፡፡  ለነገሩ እኮ ለከፋው ሰው አይባልም እነጂ፣ ሲነሳባችሁ ነው፡፡ አሀ…ልክ ነዋ! አምስት ቤተሰብ ሀምሳ ኪሎ ጤፍ በቀን ሶስቴ እየጨረገደ፣ አምስት ወር ሙሉ! (ቁርስም ፍርፍር ስለሆነ ነው፡፡)
ብቻ ሰውየው “ኑሮ እንዴት ነው?” ሲላችሁ …አለ አይደል… እነ ‘ድራኩላን’ የሚያስንቁ ሆረር ፊልሞች ይሯሯጡባችኋል::
“ምንም አይል፣” ትላላችሁ፣ ነገር ለማሳጠር፡፡ የምር ግን…“ምንም አይል” የሆነ የጆከርነት ጉልበት ያላት መልስ ነች:: “መጥፎ ነው”ም የለ፣ “ደግ ነው”ም የለ! እናማ…ከዛ ቀጥሎ እሱም ምንም ባይል ደስታችሁ ነው፡፡ የሚጠበቅባችሁ መልስ… አለ አይደል… “ምን ኑሮ አለና፡፡ በቁማችን እኮ በድን ሆነናል፣” ምናምን እንድትሉ ነው የሚፈለገው፡፡ ይሄ ነዋ ለወሬ የሚያመቸው::
“የሚገርም እኮ ነው” ይላል፡፡ ጀመረው! የጠላችሁትን፣ የሸሻችሁትን ይዞባችሁ ሊመጣ ነው፡፡ “በገዛ ሀገራችን እኮ አላስቀምጥ አሉን!” ይላል፡፡ በቃ ይቺ ‘መቅድም’ ‘መግቢያ’ ምናምን ስለምን እንደሆነ ወዲያው ይገባችኋል፡፡ እናላቸሁ…ያለው አማራጭ ወይ ሠዓታችሁን አይታችሁ “ሶሪ የሆነ ቀጠሮ ረፈድበኝ” ብላችሁ ቶሎ ‘እብስ’ ማለት፡፡ ካልሆነ ደግሞ…አለ አይደል… “ሌላ ቦታም ብሄድ ሌላው ስለሚመጣብኝ ይኸኛው እንደጀመረ ይነዝንዘኝ” ብላችሁ መቀመጥ፡፡ በተለይ ደግሞ ወሬው ፖለቲካ ሲሆን ያለው ጣጣ!
“ማንን ነው የምትደግፈው?”
ምን! “ይቺ ናት ጨዋታ!” ምናምን የምትለዋ ዜማ ምናምን ትዝ ትላችኋለች:: ደግሞ ሌላ መልማይ ተላከባችሁ እንዴ! ቆይ…ዝም ብሎ አያወራም እንዴ! ማንን ደግፉ፣ ማንን አትደግፉ የሚለውን ምን አመጣው! እናላችሁ… ከመቶ ምናምኖቹ የሆነውን ቡድን ምናምን “እንትን የሚባለውን…” ካላችሁ ከቤትም፣ ከመሥሪያ ቤትም የሸሻችኋቸው ችግሮች በሙሉ የጋራ ጥቃት ይከፍቱባችኋል፡፡
እስቲ አንዳንዴ ለጥቂት ደቂቃዎች እንኳን ሰዋችን ‘ሻይ በሰላም ይጠጣ!’ ለጭቅጭቅ እንደሁ ትደርሱብናላችሁ! የት እንዳንሄድባችሁ ነው!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 2067 times