Saturday, 14 March 2020 11:06

“ኢትዮጵያን እንድናስቀድም እየተነገረን ነው ያደግነው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

    የ24 ዓመት ወጣት ናት፡፡ በቻይና ጄጃንግ ኖርማል ዩኒቨርሲቲ፣ በኢንተርናሽናል ትሬድና ኢኮኖሚክስ፣ ዘንድሮ የአራተኛ ዓመት ተመራቂ ተማሪ ናት፡፡ በቻይና ከትምህርቷ ጎን ለጎን፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድና በቻይና ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር፣ የአገሯን ባህል፣ ታሪክና ቱሪዝም ለማስተዋወቅ በእጅጉ ትታትራለች፤ የዛሬዋ እንግዳችን ወጣት ማህሌት ዘለቀ ረዲ፡፡ በአሁኑ ወቅት ለእረፍት አዲስ አበባ የምትገኝ ቢሆንም፣ በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ተጠምዳለች፡፡ በሴቶች ስነ ተዋልዶ ጤናና በወር አበባ ምንነት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለልጃገረዶች ለመስጠት ባለፈው ሳምንት በሂልተን
ሆቴል ‹‹I care›› ‹‹እኔንም ያገባኛል›› የተሰኘ የንቅናቄ ፕሮግራም በይፋ አስተዋውቃለች፡፡ ‹‹ሴቶችና ልጃገረዶች ድጋፍ - ኢትዮጵያ›› የተሰኘው አገር
በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅትም፣ በአሜሪካ ኤምባሲ በተከናወነ ሥነሥርዓት፣ ወጣት ማህሌት ዘለቀን ዓለም አቀፍ እንደራሴ አድርጎ ሾሟታል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ወጣቷ ‹‹Power Period›› ከተባለው የአሜሪካ ድርጅት ጋር ስለምታደርገው እንቅስቃሴ፣ በዳግማዊ ምኒልክ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ስለጀመረችው ንቅናቄና በወደፊት ራዕይዋ ዙሪያ አነጋግራታለች፡፡


          እንዴት ነው ቻይናን ለትምህርት የመረጥሻት? ዕድሉንስ እንዴት አገኘሽ?
የመጀመሪያው ነገር፣ ንግድና ኢኮኖሚ ነበር መማር የምፈልገው፡፡ ይህንን ትምህርት የምማር ከሆነ፣ የት ነው መሄድና መማር ያለብኝ? ብዬ ማሰብ ጀመርኩኝ፡፡ ከዚያም ቻይናን በብዙ ነገር ተመራጭ ሆና አገኘኋት:: አንደኛ፤ በዚህ የትምህርት ዘርፍ ቻይና ግንባር ቀደም አገር ናት፤ ሁለተኛ አብዛኛው ዕቃ የሚገባው ከቻይና ነው፡፡ በዓለም ትልቁን ኢኮኖሚ የምታንቀሳቅስም አገር ናት፡፡ በነዚህ ምክንያቶች ቻይናን ከመረጥኩ በኋላ ዩኒቨርሲቲ በኦንላይን መፈለግ ጀመርኩኝ:: ከዚያም ጄጃንግ ኖርማል ዩኒቨርሲቲን አገኘሁና አመለከትኩኝ፡፡ እነሱም ተቀበሉኝ::
ነፃ የትምህርት ዕድል አገኘሽ ወይስ እየከፈልሽ ነው?
ነፃ የትምህርት ዕድል አላገኘሁም፤ እየከፈልኩ ነው የምማረው፡፡
ቻይናን እንዴት አገኘሻት? ምግቡን፣ ቋንቋውን… መልመድ አልከበደሽም?
ወደ ቻይና የሄድኩት በ2016 ነው፡፡ እዚያ አራት ዓመት ቆይቻለሁ፡፡ መጀመሪያ ላይ ቋንቋም ችግር ነበር፤ እነሱ በራሳቸው ቋንቋ እንጂ እንግሊዝኛ አይናገሩም፤ ቢሆንም ሰዎቹ ቀና ስለሆኑ ቋንቋውንም እንግድነቱንም ተቋቁሜ ቀጥያለሁ፡፡
ቻይና ለትምህርት ብትሄጅም ከኢትዮጵያ አየር መንገድና በቻይና ከሚገኘው የቆንስላ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር፣ የኢትዮጵያን ባህል ታሪክና ቱሪዝም በማስተዋወቅ ሥራ ላይም ተሳትፈሻል፡፡ እስኪ ስለ እሱ አጫውቺን?
በዩኒቨርሲቲው ውስጥ አገራችንን የምናስተዋውቅባቸው የተለያዩ ሲምፖዚየሞች ይዘጋጃሉ፡፡ ሌሎቹም አገራቸውን ያስተዋውቃሉ፡፡ እኔም ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሜ፣ ለምን አገሬን አላስተዋውቅም ብዬ አሰብኩኝና የኢትዮጵያ አየር መንገድና ቆንስላ ጽ/ቤታችን ሲምፖዚየሙን ሲካፈሉ አናገርኳቸው። እነሱም ፈቃደኛ ሆነው ተቀበሉኝ:: ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚሳተፍባቸው የተለያዩ ሲምፖዚየሞች ላይ የኢትዮጵያን ባህል፣ ቱሪዝምና ታሪክ ማስተዋወቅ ጀመርኩኝ ማለት ነው፡፡
ባለፈው አርብ የካቲት 27 ቀን በሂልተን ሆቴል ‹‹እኔም ያገባኛል›› (I care) የተሰኘውን ንቅናቄሽን ይፋ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የመጡ ሴት ኃላፊ ቻይና ለስራ በሄዱ ጊዜ የሰራሽውን እንዳዩ በመጥቀስ በተሰብሳቢ ፊት አድንቀውሻል፡፡ ምን ተሰማሽ?
በእርግጥ፣ በቀደም፣ ግለሰቧ ይገኛሉ ብዬም ሆነ፣ አድናቆታቸውን በዚያ መልኩ ይገልፁልኛል ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡ ምንድን ነው መሰለሽ… እሳቸውና የሥራ አጋሮቻቸው ለስልጠና ቻይና በመጡ ጊዜ ተቀብያቸዋለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ፣ ከእኛ አገር፣ ለተለያዩ ስራዎችም ሆነ ስልጠና ወደ ቻይና ይሄዳሉ፡፡ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ብቻ ሳይሆኑ ባለሀብቶችና ሌሎችም ለጉብኝት ይሄዳሉ፡፡ በአብዛኛው እኔን ነው የሚያገኙት:: ሲመጡ ደግሞ ስለኔ ሰምተው ነው የሚመጡት፡፡ “እሷ ካገኘቻችሁ ኢትዮጵያ እንዳላችሁ ያህል ነው የሚሰማችሁ” ተብሎ ይነገራቸዋል:: እኔም በቻይና የምኖረው ኢትዮጵያ እንደምኖረው አይነት ስለሆነ፣ በእንግድነት መጥተው ግራ እንዳይገባቸውና እንግድነት እንዳይሰማቸው፣ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን  መስተንግዶ ሁሉ አደርግላቸዋለሁ::
“ኢትዮጵያ እንደምኖረው ነው የምኖረው” ስትይ ከምን አንፃር ነው?
ኢትዮጵያ ያለው ነገር ሁሉ እዛም አለ:: ለምሳሌ አለባበስና አመጋገብን ጨምሮ ሁሉም ነገር አለ፡፡ በበዓል ቀናትም አገሬ ላይ የሚደረጉትን በሙሉ አደርጋለሁ፡፡ ከጠላና ከጠጅ በስተቀር ምንም አይጎድልም:: በበዓላት ጊዜ ሁሉንም ሰብስቤ አብረን እናከብራለን፡፡ እዛም የኢትዮጵያ ተወካይ ስለሆንኩኝ ይህን አደርጋለሁ፡፡ ወደ ቻይና የሚመጡት ይሄ ተነግሯቸው ስለሆነ አገር አስጎበኛቸዋለሁ፣ አጠገባቸው ሰው እንዳለና እንግዳ እንዳልሆኑ እንዲሰማቸው የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ:: የሚመጣውን ሁሉና ኢትዮጵያዊን አስተናግዳለሁ፤ አስጎበኛለሁ፤ መመቻቸት ያለባቸውን ጉዳዮች አመቻቻለሁ፡፡ አንዳንዶቹን እዚህ መጥቼ ሳያቸውና ሳገኛቸው፣ ትልልቅ ሥልጣንና ሀላፊነት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡  
እነዚህ የምታደርጊያቸው እንቅስቃሴዎች በሙሉ ጊዜም ጉልበትም የሚጠይቁ ናቸው፤ የትምህርት ጊዜሽ አይጋፉብሽም? ለትምህርት ነው የሄድሽው ብዬ ነው?
እውነት ለመናገር ከላይ የገለፅኩልሽን ነገሮች የምሰራው በትርፍ ሰዓት ነው:: ከትምህርት ውጭ ባለው ጊዜዬ በበጎ ፈቃደኝነትም እሰራለሁ፡፡ በትምህርት ቤታችንም የሚካሄዱ ትልልቅ ጉባዔዎችም አሉ፡፡ ባለፈው ጊዜ፣ የዓለም ባንክ ያዘጋጀው አንድ ጉባኤ፣ በእኛ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ነበር የተካሄደው፡፡ ከኢትዮጵያም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዲኖችና የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ተጠሪ ተገኝተው ነበር፡፡ እነሱን በበጎ ፈቃደኝነት ተቀብዬ ያስተናገድኳቸው እኔ ነበርኩ፡፡ የሚሄዱበት ቦታ ሲኖርና ሲንቀሳቀሱም አግዛቸው ነበር::  በቋንቋም ሆነ በሁሉ ነገር ከጎናቸው ሆኜ  ሳስተናግዳቸው ነበር፡፡ ይሄ ዩኒቨርሲቲዬም የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ከትምህርት ሰዓት ውጭ የማግዛቸው ሰዎች አሉ፡፡ የምንማረውም በፕሮግራም ነው፡፡ ትርፍ ሰዓቴን፤ በእንዲህ አይነት ቁም ነገር ላይ ማሳለፌ ደግሞ በእጅጉ ያስደስተኛል፡፡
በ24 ዓመት ዕድሜ ከአገር ወጥቶ መማር እንዲሁም አገርን ባህልንና ታሪክን ማስተዋወቅ-ወዘተ-- አልከበደሽም?
አልከበደኝም፤ አይከብደኝም፡፡ ለምን መሰለሽ… እኔ የማስበው እንዲህ አይነት ፀጋ ተሰጥቶኛል ብዬ ነው፡፡ ስለዚህ ከባድ ነገር ተሸክሜያለሁ የሚል ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡ ሁሉንም ነገር ደስ ብሎኝ ነው የማደርገው፡፡ አሁንም የምንቀሳቀስበት የስነ ተዋልዶ ጤናና የወር አበባ ምንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዬን ሳከናውን ደስ እያለኝ ነው፡፡ ስለ አገሬ ባህል፣ እሴትና ታሪኳ ስናገር አይደክመኝም፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድም በየዓመቱ አብሬያቸው እየሄድኩ እንድሰራ የሚፈልጉበትም ዋናው ምክንያት ይሄው ነው፡፡
በወጣትነት ዕድሜሽ ለአገርሽ ታሪክ፣ ባህልና ፍቅር፤ ጥልቅ ስሜት ያደረብሽ እንዴት ነው? ከአስተዳደግሽ ጋር ግንኙነት አለው?
እኛ ቤት አምስት ልጆች አለን፡፡ እኔ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ፡፡ ከሁሉ ነገር ኢትዮጵያ የምትባለው አገራችን እንደምትቀድም ተነግሮን ነው ያደግነው። በምንም ሁኔታ ላይ አገራችንን ማስቀደም እንዳለብን ይነገረን ነበር፡፡ በዚህ ትውልድ ላይ ክፍተት አለ ለተባለው፣ የኔ ትወልድ ተጠያቂ አይደለም፤ ሊሆንም አይገባም፡፡ በዋናነት ተጠያቂው ከእኛ በፊት የነበረው ትውልድና ሚዲያው ነው፡፡ መገናኛ ብዙሃን በይበልጥ እኛ ወደ ምዕራቡ ዓለም የምንሳብበትን ነገር ነው፤ የሚያሳዩንና የሚሰብኩን፡፡ የምንወቀሰው ደግሞ እኛ ወጣቶች ነን፡፡  በጅምላ ከሚወቀሰው ወጣት መካከል ግን በዙሪያዬ ወርቅ የሆኑ፣ ለአገራቸውና ለትውልዳቸው ቀን ተሌት የሚተጉ አሉ፡፡ በቀደም ሂልተን ሆቴልም እንዳየሻቸው፣ ራሳቸውን ለአገራቸው እስከ መስጠት የሚደርሱ ናቸው። ሚዲያው ግን የሚዘግበው የምዕራቡን ነገር እንጂ የአገራችንን ባህል፣ ታሪክና ማንነት አጉልቶ በማሳየቱ በኩል ክፍተት አለ፡፡ ወጣቱ ለአገሩ የሚሰራውንና የሚያደርገውን ሚዲያው በምሳሌነት አያቀርብም፡፡ ሃና ሀይሉ የተባለች የአነቃቂ ንግግር ባለሙያና የ”ራይዝ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ” መስራች፣ አንድ የምትለው አባባል አለ፡- ‹‹ድንጋይ ሰብስቦ ቤት የሚገነባውን ሳይሆን፤ ድንጋይ ሰብስቦ መንገድ የሚዘጋውን ነው ሚዲያው የሚዘግበው›› የሚል፡፡ እውነትም ደግሞ ባህሉን የሚደግፍና የሚያስተዋውቀውን ወጣት ትኩረት ነፍጎ፣ ወደ ምዕራቡ ዓለም መሄድ፣ እንደ አገር አዋጭ አይደለም:: ከዘፈኖቻችንና ከግጥሞቻችን ጀምሮ ብትመለከች፣ በምዕራባዊያኑ ተጽዕኖ ስር የወደቀ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የአገራችን የሚዲያ ተጽዕኖ ውጤት ነው ባይ ነኝ፡፡ በሌላ በኩል፤ ታናናሾቼ ባህላቸውን አላወቁም ብዬ እነሱን አልወቅስም፤ እኔ ካላስተማርኳቸው ከየት ያውቃሉ፡፡ እኔ ቤተሰቦቼ፤ ስለ አገር ፍቅርና ክብር፣ ስለ ባህልና ታሪክ እየነገሩኝ በማደጌ የዛሬ ማንነቴን ይዤአለሁ፡፡
በቅርቡ ‹‹ሴቶችና ልጃገረዶች ድጋፍ - ኢትዮጵያ›› የተሰኘው አገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅት፤ በአሜሪካ ኤምባሲ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ላይ ዓለም አቀፍ እንደራሴ አድርጎ መርጦሻል፡፡ እንዴት ተመረጥሽ?
ከዚህ ድርጅት ጋር የተገናኘነው በአጋጣሚ ነው፡። ለጓኛዬ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፓናል ላዘጋጅ እየተሯሯጥኩ ነበር፡፡
ምን አይነት ፓናል?
የስነ ተዋልዶ ጤና ትምህርትና የወር አበባ ምንነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ፓናል ነበር፡፡ ፓናሉን አሜሪካ ከሚገኝ ‹‹Power Period›› ከሚባል ኢኒሼቲቭ ጋር ነበር የማዘጋጀው። ምክንያቱም የዚህ ኢንሼቲቭ የኢትዮጵያ ተወካይም ነኝ፡፡ ታዲያ ይህንን ዝግጅት እውን ለማድረግ ስሯሯጥ ነው ጓደኛዬ ‹‹የሴቶችና ልጃገረዶች ድጋፍ - ኢትዮጵያ”ን ያገናኘችኝ፡፡ ተገናኝተን ስንነጋገር፣ የእነሱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ፣ ከእኔ ጋር ተመሳሳይና አንድ ዓይነት ነው:: ስለዚህ እኔም ብቻዬን ከምሰራ፣ ከዚህ ድርጅት ጋር ብተባበር ሥራዬ ይበልጥ ውጤታማ ይሆናል በሚል በደንብ ተወያይተን፣(ሀሳቤንና ህልሜን ነግሬአቸው) በደንብ ተግባባን፡፡ ከዚያ በኋላ ፓናሉን አሜሪካ ኤምባሲ ማድረግ እንደምችል ነገሩኝ፤ እዛ አዘጋጁልኝ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድርጅቱ ጋር ብዙ ነገሮችን ሰርተናል:: በአጭር ጊዜ ያደረግኩትን እንቅስቃሴ ሲመለከቱ ‹‹ይቺ ልጅ አቅም አላት፤ ዓለም አቀፍ እንደራሴ አድርገን ብንሾማት በደንብ ልትሰራ ትችላለች›› ብለው የፓናል ውይይቱ ዕለት፣ በአሜሪካ ኤምባሲ፣ ሰርፕራይዝ ነው ያደረጉኝ፡፡ አሁንም ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች እያደረግን ነው፡፡
በወይዘሮ ሙሉ ዓለም ታምሬ የተመሰረተው ‹‹ሴቶችና ልጃገረዶች ድጋፍ - ኢትዮጵያ››፤ ሴቶችና ወጣቶች፤ ከጥቃት፣ ከሥራ አጥነትና ከገቢ ጠባቂነት ተላቅቀው፣ አቅምና ችሎታቸውን ተጠቅመው፣ ህልማቸውን እውን እንዲያደርጉ ከተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር የሚሰራ አገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው፡፡ ከዚህ ድርጅት ጋር መሥራት ምን ስሜት ይሰጣል? በሌላ በኩል፤ ትምህርትሽን አልጨረስሽም፤ እንዴት አጣጥመሽ ለመሥራት ነው ያሰብሽው?
ትምህርቴን እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ዘንድሮ እጨርሳለሁ፤ የመጣሁት ለእረፍትና አንዳንድ ሥራዎችን አከናውኜ ለመመለስ ነበር፡፡ ነገር ግን ኮሮና ቫይረስ በመቀስቀሱ ምክንያት፣ የእረፍት ጊዜዬን አራዝሜ እዚሁ ለመቆየት ተገድጃለሁ፡፡ መቆየቴ ግን ለበጎ እንደሆነ ተሰምቶኛል፡፡ ሥራዬን በአግባቡና በቅልጥፍና እየሰራሁ ነው፡፡  የበሽታው ሁኔታ ሲሻሻል ወደ ትምህርቴ እመለሳለሁ:: ስመለስ ግን ስራው የሚቆም አይደለም:: ምክንያቱም ዓለም አቀፍ እንደራሴ እንደመሆኔ፣ በሄድኩበት በደረስኩበት ሁሉ ሥራዬን እሰራለሁ፤”ሴቶችና ልጃገረዶች ድጋፍ - ኢትዮጵያ”ን ወክዬ መሥራት ያለብኝን ሁሉ ከመስራት የሚያግደኝ ነገር አይኖርም፤ እነሱም ዓለም አቀፍ እንደራሴ አድርገው የሾሙኝ፣ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡
በአምባሳደርነትሽ በዋናነት የምታከናውኛቸው ተግባራት ምንድን ናቸው?
በዋናነት የስነ ተዋልዶ ጤናና የወር አበባ ምንነት ግንዛቤን ለወጣቶችና ልጃገረዶች ማሳወቅና ማስገንዘብ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ‹‹ሴቶችና ልጃገረዶች ድጋፍ - ኢትዮጵያ››፤ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ለልጃገረዶች በማቅረብ ድጋፍ ያደርጋል:: አሁን ግን ቁሳቁሱን ከመለገስ ባለፈ ንጽህና አጠባበቁን፣ የሥነ ተዋልዶ ጤናን ጉዳይ፣ የወር አበባ አመጣጥና አካሄድን --- በተመለከተ ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎችና መሰል ጉዳዮችም ግንዛቤ እንፍጠር፣ እናስተምር ብለን፣ በስፋት እየሰራን ነው፡፡ ለወደፊቱ ከተለያዩ ዓለማት የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን እያሰባሰብን ነው፤ ሴቶች በቋሚነት እየመጡ የንፅህና መጠበቂያዎቹን እንዲወስዱ ማለት ነው:: ቁሳቁሶቹን ከአሜሪካ፣ ከኖርዌይና ከተለያዩ አገራት ነው የምንሰበስበው፡፡ በተለያዩ አለማት ያሉ ኢትዮጵያዊያን ‹‹እኔም ያገባኛል›› ብለው እየተንቀሳቀሱ ነው ያሉት:: ዕቃዎቹን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመነጋገር፣ ከቀረጥ ነፃ ሆነው እንዲገቡ ሁኔታዎችን እያመቻቸን ነው፡፡ በአገር ውስጥም ብዙ ደጋፊዎች እያፈራን ነው፡፡ ቀደም ሲል ድርጅቱም እኛም ያለ ደጋፊ፣. ከኪሳችን እያወጣን ነበር የምንሰራው፡፡ ‹‹እኔም ያገባኛል›› የሚባለው እንቅስቃሴ ከተጀመረ በኋላ ግን የተለያዩ ባለሀብቶች ድጋፍ ማድረግ ጀምረዋል፡፡
በሒልተን ሆቴል ድርጅቱ ለባለድርሻ አካላት አጠቃላይ ፕሮጀክቶቹንና የአንቺን ‹‹እኔንም ያገባኛል›› ንቅናቄ ባስተዋወቀበት ጊዜ፣ አንድ አርክቴክቸራል ዲዛይን አብራችሁ አሳይታችሁ ነበር ምንድን ነው?
አንድ የሕንፃ ዲዛይን አሳይተናል፤ ሁለት ዓላማ ነው ያለው፡፡ እግዚአብሄር ይፈቅዳል፤ እውን ይሆናል ብለን አምነን ነው ዲዛይኑን ያሰራነው፡፡ አንደኛው የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ሁሌ ከውጭ እየጠየቅን ከምናመጣ እዚህ አገር ውስጥ በስፋት እየተመረተ፣ ለምንደግፋቸው ወጣቶችና ልጃገረዶች በዘላቂነት እንዲዳረስ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው ለእህቶቻችን የሥራ ዕድል መፍጠር ሲሆን እዚሁ ሕንፃ ላይ የሴቶችና የወጣቶች ማዕከል በመክፈት፣ ሴቶችና ልጃገረዶች በራስ መተማመን እንዲያዳብሩ፣ እሴቶቻቸውን እንዲያውቁና እንዲጠብቁ፣ በሥነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ እውቀታቸው እንዲሰፋ፣ በወር አበባ ምንነትና ንፅህና አጠባበቅ ዙሪያ፣ እኛ ለታናናሾቻችን የምናስተምርበት፣ ከታላላቆቻችን ከእናቶቻችን የምንማርበትና ራሳችንን በአስተሳሰብ የምንገነባበት ማዕከል ነው የሚሆነው፡፡ ዲዛይኑን እንዳየሽው አልቋል፡፡
የመጀመሪያ ንቅናቄሽን ለመከወን በዳግማዊ ምኒልክ አፀደ ሕፃናትና አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ ማዕከል ገንብተሻል:: ከት/ቤቱ ጋር ያላችሁ ስምምነትና ቀጣይ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
ዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤትን በቅድሚያ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም ሀሳቡን ይዘን ስንሄድ በጣም ቅን በሆነ መንፈስ፣ በሚያበረታታ መልኩ ነው የተቀበለን፡፡ የራሱ የሥነ ተዋልዶ ጤና ክበብም አለው:: አንድ ክፍል ሰጥተውን ሥራ ጀምረናል:: በዚህ ክፍል አራት ዋና ዋና ተግባራት ይከናወናሉ፡፡ እኛም ለስራችን እንዲያመችና ለእይታም ማራኪ እንዲሆን በጥሩ ሁኔታ እያዘጋጀነው ነው፡፡ አንደኛው፤ ተማሪዎች የወር አበባቸው በሚመጣ ጊዜ ህመም ሲሰማቸው፣ መጥተው የሚያርፉበት አነስተኛ ክሊኒክ ይኖረዋል፡፡ ሁለተኛው፤ በሥነ ተዋልዶ ጤናና በወር አበባ ምንነት ላይ ሥልጠና የምንሰጥበትም ክፍል ነው:: እዚህ ከሥልጠናና ከግንዛቤ ማስጨበጥ በተጨማሪ ልጃገረዶቹ የሥነ ልቦና ድጋፍም ያገኛሉ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ፤ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ያለ ችግር መጥተው፣ ወስደው የሚጠቀሙበት ኮርነርም አለው:: አራተኛው ቤተ መጻህፍትም አለው:: ለሥልጠና ሲመጡ፣ አረፍ ሲሉም ሆነ በእረፍት ሰዓት እንዲያነቡ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡ ከት/ቤቱም የሥነ ተዋልዶ ጤና ክበብ ጋር በነዚህ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ነው የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረምነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የት/ቤቱን ርዕሰ መምህርት ወ/ሮ ዝማም ደስታንና ባልደረቦቻቸውን ከልብ እመሰግናለሁ፡፡ በነገራችን ላይ እኛን በበጎ ፈቃደኝነት ለማገዝ የሕክምና ዶክተሮች፣ ነርሶች፣ የሕግ ባለሙያዎችና የሥነ ልቦና እውቀት ያላቸው ሰዎች እየተመዘገቡ ይገኛሉ፤ ይሄ በጣም የሚያበረታታ ነው፡፡
ሥልጠናውን መቼ ልትጀምሩ ነው?
ከአንድ ሳምንት በኋላ እንጀምራለን፡፡ እንደነገርኩሽ፤ ሥልጠናውን በተለያየ መልኩ የሚሰጡልን በጎ ፈቃደኞች እየተመዘገቡ ነው፡፡ የሥልጠናውን ሂደት በተመለከተም ከተማሪዎቹ ጋር እየተወያየን ነው፤ክፍሎቹን የማሳመርና ማራኪ የማድረጉን ስራም እየጨረስን ነው ያለነው፡፡
አንቺ ለቤትሽ የመጀመሪያ ልጅ ነሽ፤ ፊደል የቆጠረና በገቢም የተሻለ ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደግሽው፤ እናም የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ችግርም ሆነ በዚህ ጉዳይ መሸማቀቅ ደርሶብሽ ያደግሽ አትመስይኝም፤ ታዲያ በዚህ ችግር እንዴት ‹‹እኔንም ያገባኛል›› ልትይ ቻልሽ?
ከራሴ ተሞክሮ ተነስቼ ልንገርሽ፡፡ እኔ የወር አበባ ማየት የጀመርኩት በ11 ዓመቴ ነው፡፡ በዛን ሰዓት ስለ ወር አበባ ምንነት አላውቅም፡፡ እናቴ ደግሞ የመጨረሻ እህቴን ወልዳ አራስ ቤት ነበረች፡፡ እንግዶች ነበሩ፤ እቤት ሄጄ እግሬን ከፍቼ ለእናቴ አሳየኋት:: “ያለማቋረጥ እየደማሁ ነው፤ የሆነ ውስጤ የተበላሸ ነገር አለ” ነው ያልኳት፤ ለእናቴ፡፡ እሷም ስለ ሁኔታው በደንብ አስረድታኝ፣ ወንድሜ ሞዴስ እንዲገዛልኝ ላከችው፡፡ ከዚያም እንዴት ንፅህናዬን እንደምጠብቅ ነገረችኝ፡፡ ይሁን እንጂ ት/ቤት ውስጥ እሳቀቅ ነበር፡፡ ቦርሳዬ አጠገብ አንድ ሰው አይደርስም፡፡
ቦርሳዬን ከከፈቱብኝ አለቅሳለሁ፤ ምክንያቱም ሞዴሱን ካዩት ባለጌ ይሉኛል በሚል፡፡ ተሳስቼ “ሄዳችሁ ሞዴስ ግዙልኝ” አልልም ነበር፤ ራሴ ሄጄ ድምፄን ቀንሼ ነው ባለ ሱቋን የምጠይቃት:: አንድ ጊዜ አስተማሪያችን ቦርሳ ይፈትሻል፤ ሊፒስቲክ ቻፒስቲክና ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ ነገሮችን ይዘን እንዳንገኝ ነው፤ በሥነ ምግባር ብልሹ እንዳንሆን በየጊዜው ቦርሳ ይፈትሻሉ፡፡ ያው የግል ትምህርት ቤትም ስለነበር የምማረው በብዙ ቁጥጥር ነበር፡፡ ከዚያ ከቦርሳዬ ሞዴሱን አውጥቶ ‹‹ምንድን ነው ይሄ ነገር?›› ይላል፤ እኔ በጣም ተሳቀቅኩኝ፡፡ በቃ ተማሪዎቹ ሁሉ ባለጌ እንደሆንኩኝ አወቁ አልኩኝ:: ቤት ገብቼ ለእናቴ እያለቀስኩ ነገርኳት፡፡ “ዛሬ ሂሳብ መምህራችን ቦርሳዬ ውስጥ ሞዴስ አግኝቶ፣ ተማሪዎቹ አዩብኝ፤ በጣም ነው የከፋኝ” አልኳት። እናቴ ደግሞ “አንቺ የወር አበባ ስላየሽ ባለጌ አይደለሽም፤ ሙሉ ሴት እንጂ:: አንቺ ክፍል ውስጥ ካሉ ሴቶች በአንድ እርምጃ ከፍ ብለሻል” ብላ ሙሉነቴን አሳየችኝ፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ ለእህቶቼም፣ ለአክስት አጎቴ ልጆችም፣ ሱቅ ሄጄ ሞዴስ የምገዛው እኔ ሆንኩኝ፡፡ በጋዜጣና በፌስታል አላሳሽገውም፤ ምክንያቱም ሞዴስ ሙሉ ሴቶች የሚጠቀሙበት እቃ ነው፡፡ ፓንትም ስገዛ አላስጠቀልልም፤ ምክንያቱም ተፈጥሯዊና አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ማድረግ የሚፈሩና የሚያፍሩ ሴቶች አሉ፡፡ ግንዛቤ ስለሌላቸው እንጂ የሚያሳፍሩ ነገሮች አይደሉም:: እኔ ነፃነት እየተሰማኝ ሌሎቹ ለምን ይሸማቀቃሉ? ብዬ መድረኮችን መፈለግ ጀመርኩኝ፡፡ በተለይ ግንዛቤ ላይ የሚሰሩ ፕላትፎርሞችን እንዴት ነው ማግኘት የምችለው በሚለው ዙሪያ ተጠመድኩኝ፡፡ ቻይና በሄድኩ በመጀመሪያው ዓመት ፕላት ፎርም ፍለጋ ጀምሬ አንድ ዓመት ፈጀብኝ:: ከዚያ በኋላ የአሜሪካውን የ‹‹Power Period›› አግኝቼ አገኘኋቸው፡፡ የኢትዮጵያ ተወካይ አድርጉኝ፤ እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ለመስራት ዝግጁ ነኝ፤ እኛም አገር እንደ ነውር የሚቆጠር ነው አልኳቸው፤ ተወካይ አደረጉኝ፡፡ እኛ አገር ነውር የሚባለውን በአደባባይ እንተገብራለን፤ ነውር ያልሆነውን እንደብቃለን፡፡
ለምሳሌ በእኔ እምነት ዘረኝነት ነውር ነው፤ አደባባይ አውጥተን ግን እንባላለን፤ አንዱ አንዱን በዘሩ ይገፋል:: የወር አበባ ግን ነውር ሳይሆን የተፈጥሮ ፀጋ ነው፤ ተገለባብጧል፤ ይሄን ደግሞ ቦታ ቦታውን ለማስያዝና ነውር የሆነው ነውር፤ የተፈጥሮ ፀጋ የሆነው የተፈጥሮ ፀጋ እንዲባል ልስራ ስላቸው በደስታ ነው የተቀበሉኝ፡፡ አሁን ራሱ ‹‹ጋይድ ቱ ፔሬድ›› የሚሰኝ አንድ ቡክሌት ልከውልኛል፤ የወር አበባ አጠቃላይ መመሪያ ነው፤ ለወር አበባ የደረሰች ሴት እንዴት በሥነ ልቦናም በሁሉም ተዘጋጅታ መቀበል እንዳለባት፣ መየት የጀመረችም እንዴት አድርጋ ንፅህናዋን ጠብቃ ማቀፍ እንዳለባት የሚያሳይ ነው፡፡ ይህንን ለአገራችን ሴቶችና ልጃገረዶች በአራት ቋንቋ ማለትም በአማርኛ፣ በትግርኛ፣ በሶማሊኛና በኦሮሚኛ ተርጉመን ለማሰራጨት ሥራ ጀምረናል፡፡ ከዚያ በተለያዩ ክልሎች ተበትኖ ተግባር ላይ ይውላል፡፡
ከቤተሰብ ልዩ ድጋፍ ያላቸው ልጆች በተለያየ መልኩ ጎልተው ይወጣሉ፤ ማህበረሰብን በማገልገልም ግንባር ቀደም ናቸው ይባላል፡፡ የታናሽሽ ታናሽ ወንድምሽ ሙሴ ዘለቀ፤ ‹‹ገፅታ›› የተሰኘ መተግበሪያ ሰርቶ እዚሁ ጋዜጣ ላይ እንግዳ ሆኖ ነበር፡፡ በዚህ በኩል ያንቺ ቤተሰብ የሚያደርግልሽን ድጋፍ ንገሪኝ?
እቤት ውስጥ እኔም ሆንኩ ታናናሾቼ ያመንንበትን ነገር እንድንሰራ ሙሉ ነፃነት አለን፡፡ ይህንን ነገር አባቴ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ ያወቀው ሌሎቹ እንዳወቁት፣ አሜሪካ ኤምባሲ አምባሳደር አድርገው ሲሾሙኝ ነው፡፡ “አንድ ፓናል ውይይት አለ፤ መጥተህ ታደም” ብዬ ነው የጋበዝኩት፤ እስካመንበት ድረስ ከጫና ይልቅ እኛን ወደ ማበረታታትና መደገፍ ነው የሚመጣው፡፡ እናታችንም ደጋፊያችን ናት፤ዋናው ነገር እኛ እንመንበት እንጂ ከዚያ ወዴት ያስኬደናል በሚለው ላይ ያማክሩናል ይደግፉናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
በ”ሴቶችና ልጃገረዶች ድጋፍ- ኢትዮጵያ” ውስጥ አብረው ለመስራት ‹‹የእናት ቃል››፣ ‹‹የኔ ኢትዮጵያ››፣ ‹‹ራይዝ ኢትዮጵያ››፣ ‹‹ሰከንድ ቻንስ ፎር ቤተር ቱሞሮው›› ከተሰኙ ኢንሼቲቮች ጋር ተፈራርማችኋል፤ እንዴት ነው በጋራ ልትሰሩ ያቀዳችሁት?
የኢንሼቲቮቹ መስራቾች በአብዛኛው ወጣቶች ናቸው፤እኔም ደግሞ እንደ ‹‹ሴቶችና ልጃገረዶች ድጋፍ ኢትዮጵያ›› አለም አቀፍ እንደራሴነቴ፣ ሴቶችና ልጃገረዶችን እስከ ከፍተኛ ትምህርት ደርሰው ከህልማቸው እንዳይገናኙ የሚያደርጓቸውን መሰናክሎች በተወሰነ መልኩ ለመቅረፍ ነው የምንሰራው፡፡ ሁሉም አብረውን የሚሰሩ ወጣቶች ትልልቅ ራዕይ አላቸው፤ተነጋግረን መግባባት እንችላለን፡፡ ለታናናሽ እህቶቻችን የተሻለ የመፍትሄ ሀሳብ እናመነጫለን ብለን እናስባለን፡፡ ሁላችንም ማህበረሰብ ተኮር ስራዎች ስለምንሰራ ለውጥ እናመጣለን፡፡ በመጨረሻም አምባሳደር አድርጎ የመረጠኝ ድርጅት፣ በስራው ከ50 ሺህ በላይ ሴቶችን መድረስ ችሏል፡፡
በቀጣይ በመላው አገሪቱ ያሉ ሴቶችና ልጃገረዶች፣ በወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ጉድለት፣ በፆታዊ ትንኮሳ፣ በሥራ አጥነትና በመሰል መሰናክሎች ከፍተኛ ትምህርት ከመድረስ እንዳይሰናከሉ፣ ወጥ የሆነ አቅም ያለው ተደራሽ ሥራ መስራት እንፈልጋለን፡፡ ሴቶች በወር አበባቸው፣ በተፈጥሮ ፀጋቸው የሚኮሩ እንጂ የሚሸማቀቁበት አስተሳሰብ ጠፍቶ እስካይ ድረስ መስራት የኔ ሕልም ነው፡፡

Read 4448 times