Print this page
Sunday, 15 March 2020 00:00

ብቻ መንግሥት ገመዱን አጥብቆ ይያዝ!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(3 votes)

  ‹‹እንደ አሜሪካ አትቅለል›› - የሚለው አባባል የሰሞኑ የአዲስ አበባ ወጣቶች የቁጣ መግለጫ ሆኖ እያገለገለ ነው:: አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ ስትቀል የመጀመሪያዋ አይደለም። የሸጠችለትንና የኢትዮጵያ መንግሥት ገንዘቡን ሆጭ አድርጎ የከፈለበትን የጦር መሣሪያ በመቋዲሾው የኢትዮጵያ ድንበር የጀኔራል ሲአድ ባሬ ጦር  እንዲደፈር አድርጋለች፡፡ ይህ የሚዘነጋ ቅሌት አይደለም፡፡
መንግሥት ፍርጥርጥ አድርጎ መልስ ሊሰጥበት የሚገባ ነው ብዬ የማምንበትን ጥያቄ ላስቀድም፡፡ ሶስቱ አገሮች (ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን) እ.ኤ.አ በ2015 የደረሱበት የጋራ መግባባት አለ:: ባልሳሳት የዚያ ስምምነት መሠረታዊ ጉዳይ፤ በሶስትዮሽ የሚደረጉት ድርድሮች በባለሙያዎች ደረጃ ካለቀ እሰየው፣ ነገሩ ከጠበቀ በሚኒስትሮች ደረጃ እንዲታይ ይፈቅዳል፡፡ በዚህ ካልሆነም በመሪዎች መካከል በሚደረግ ውይይትና ድርድር፣ እያንዳንዱ ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ይወስናል፡፡
ግብፅ ይህን ስምምነት ረግጣ፣ አሜሪካንና የዓለም ባንክን አደራዳሪ አድርጋ ስትጋብዝ፣የኢትዮጵያ መንግሥት፣ “ይህ ከስምምነታችን ውጭ ነው” ብሎ ለምን ውድቅ አላደረገውም? “መነጋገርና መደራደር ምንም ክፋት የለውም” ብሎ የአሜሪካንን መንግሥትና የዓለም ባንክን በታዛቢነት ከተቀበለ ደግሞ፣ ለምን በታዛቢነታቸው ብቻ እንዲቆሙ ወይም እንዲፀኑ አልተደረገም? በካርቱምና በአዲስ አበባ በተደረጉ ሁለት ስብሰባዎች በታዛቢነት የቆዩት አሜሪካና የዓለም ባንክ፣ በየትኛው ስምምነትና መግባባት ወደ አደረዳሪነት አደጉ?
ከሁሉም በላይ ደግሞ ጠበቅ ረገጥ አድርጎ መጠየቅ የሚገባው፣ አሜሪካ በየትኛው ስብስባና  ስምምነት ነው የመስማሚያ ውል እንድታዘጋጅ ሥልጣን የተሰጣት? ወይስ በማን አለብኝ ገባችበት?
መንግሥት ሱዳን የአቋም ለውጥ አላደረገችም ብሎ ያቀረበው ክርክር ይዞለታል፡፡ አሜሪካ ያዘጋጀችው ውል ጥቅሟን እንደማያስጠብቅ ከመግለጧ በላይ፣ የአረብ ሊግ ሰሞኑን ባደረገው ጉባኤ፣ ግብፅን መወገኑን ትቶ፣ ጉዳዩን ለባለ ጉዳዩን እንዲተውላቸው ጠይቃለች:: ስሟም ከውሳኔው ደጋፊዎች ዝርዝር ውስጥ እንዳይካተት አድርጋለች፡፡ ይህ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው እርምጃ ነው:: ኢትዮጵያ አሜሪካ ያዘጋጀችውን ውል አልፈርምም እንዳለችው ሁሉ ሱዳንም የአለመፈረም እምቢ እንደምትደግመው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አሜሪካና የዓለም ባንክ ሊያስቀጥሉት የሚፈልጉት የ1959 የዚህ ምክንያቱ ስምምነት መፍረስ የምሥራቹ፣ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሱዳንም መሆኑ የታወቀ ነው፡፡  
የአለም ባንክ ከአስር ዓመት በፊት ግብፅ ምን ያህል የውኃ ሀብት እንዳላት አጥንቷል። ይህን ጥናት ዛሬም በከፍተኛ ሚስጥርነት ይዞት ይገኛል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ግብፅ የራሷን የውኃ ሀብት ቆጥባ በኢትዮጵያ ላይ ሸክም ሆና እንድትቀጥል፣ በሌላ አገላለፅ፤ ኢትዮጵያ በውኃ ሀብቷ ለመጠቀም ያላትን ፍላጎት ለማዳከም፣ ከተቻለም ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጥ ለማድረግ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ከግብፅና ከሱዳን ጋር በአሜሪካና በዓለም ባንክ ታዛቢነት  እየተደረገ የነበረውን ድርድር ጥሎ መውጣቱ ካስደሰታቸው ሰዎች አንዱ ነኝ:: ደግሜ ደጋግሜ “ደግ አደረገ” ብያለሁ:: ከልቤም አመስግኛለሁ፡፡
በመጀመሪያ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ግብፅ ድርድሩን አቋርጣ፣ አስራ አንድ ወር ቆይታ እንደተመለሰች ሁሉ እሱም አስራ አንድ ወር ከድርድር ነፃ የሆነ ጊዜ እንዳለው አውቆ፣ ወደ ድርድር መመለስ የሚችለው በዚህ ጊዜ ውስጥ መሆኑን ወስኖ ለሚመለከታቸው እንዲያሳውቅ አሳስባለሁ::
ወደ ድርድሩ መመለስ የሚይፈልገው ወይም የሚመለሰው አሜሪካና የዓለም ባንክ ከታዛቢነት ውጪ አንድም አይነት የአደረዳሪነት የአግባቢነት እርምጃ የማይወስዱ መሆኑን በግልጽ ካረጋገጠና መተማመኛ ከሰጡ በኋላ መሆን አለበት፡፡
በሌላው በኩል ደግሞ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የጀመሩትና ያልተገፋበት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር ሲሪል ራማፎዛ የአደራዳሪነቱን ኃላፊነት እንዲወስዱ የመገፋፋትና የማግባባት እርምጃ ነው፡፡ ግብፆች የሚመርጡት ተጨማሪ አፍሪካዊ መሪም ካላቸው ያቀርቡ ዘንድ ዕድሉ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
ምንም እንኳን የቀደሙት የኢትዮጵያ መሪዎች ተቃውሟቸውን በወቅቱ የገለፁ ቢሆንም፣ ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥትም ግብፅ የስዊዝ ካናልን አሻግራ፣ ለእስራኤል በየዓመቱ 365 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ለማቅረብ ባላት እቅድ ላይ ተቃውሞውን በይፋ ማሰማት አለበት። የትራምፕ ሴራ ማጠንጠኛ በየትም ዞሮና ተዟዙሮ፣ ለእስራኤል አንድ ዓይነት ጥቅም ማስገኘት መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ውኃ ስትለቅ፣ ግብፅ ለእሥራኤል የምትሸጠው ውኃ ታገኛለች - ተጠየቁ ይኸው ነው፡፡
ነገሩን እንዲህ እንየው፡፡ ገመዱ ጫፍ ላይ አንድ ዋጋ ያለው እቃ ታስሯል እንበል:: ገመዱ ምንም ያህል ይርዘም ገመዱን የያዘው ሰው በፈለገው ጊዜ እቃውን ወደ እርሱ ያቀርበዋል፡፡ ያለ ፈቃዱም በእጁ ያስገባዋል:: የግብፅ ጉዳይ በገመድ ከተያዘው እቃ የተለየ አይደለም፡፡ ዘግይቶም ቢሆን ኢትዮጵያ በምታስቀምጠው ሁኔታ ውስጥ መግባቷ አይቀርም፡፡ ብቻ መንግሥት ገመዱን አጥብቆ በጥንቃቄ ይያዝ፡፡
ቸር ያሰማን!     

Read 10791 times