Print this page
Saturday, 14 March 2020 12:55

አክራሪ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ኳራንታይን ያስፈልጋቸዋል

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(12 votes)

    ሰሞኑን ለማውቃቸውና ለማላውቃቸው አንዳንድ የአዲስ አበቤ ነዋሪዎች (የኢቴቪ “አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች” አልናፈቋችሁም?!) ድንገተኛ ጥያቄ አቀረብኩላቸው በእርግጥ ተጠያቂዎቹ ከ20 አይበልጡም፡፡ ለኔ ዓላማ ግን ከበቂ በላይ ነበሩ፡፡ ጥያቄው ደግሞ ምን መሰላችሁ? ‹‹ከኢትዮጵያ ፖለቲካና ከአደገኛው የኮሮና ቫይረስ የትኛው የበለጠ ያሰጋችኋል?›› የሚል ነው፡፡ ልብ አድርጉ! ኮሮና ቫይረስን ያወዳደርኩት ከኤችአይቪ ኤድስ ወይም ከትራፊክ አደጋ አሊያም ከካንሰር ጋር አይደለም፡፡ ከአገራችን ፖለቲካ ጋር ነው፡፡
ብዙዎቹ ተጠያቂዎች በጥያቄው በእጅጉ ተገርመዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን መልሳቸው ፈጣን ነበር፡፡ ፈጣን ብቻ ሳይሆን ተመሳሳይም ነው፡፡ (ተመካክረው ነው እንዳልል አይተዋወቁም!)
እናላችሁ… ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ከኮሮና ቫይረስ የበለጠ የሚያሰጋን ፖለቲካችን ነው›› አሉኝ በእርግጠኝነት ስሜት:: (እኔ ደሞ በፖለቲከኞቻችን አፈርኩ!) ይታያችሁ… ከቻይና እስከ ጃፓን፤ ከጣልያን እስከ ኢራን፤ ከአሜሪካ እስከ አፍሪካ… ዓለምን እያጥለቀለቀና በፍርሃት እያራደ የሚገኝ አደገኛ ቫይረስ ቢሆንም ለእኛ ግን በእጅጉ የሚያሰጋን መርዘኛው ፖለቲካችን ነው፡፡ ወዳጆቼ፤ እንዴት በሀገሬ ፖለቲከኞች አለማፈር እችላለሁ!? እኔ ብቻ አይደለሁም ማፈር ያለብኝ፡፡ ፖለቲከኞቹም በአደባባይ ደረታቸውን ነፍተው መራመድ የለባቸውም፡፡
ሙያችን ነው፣ እንጀራችን ነው፣ ልጅነታችንን ገብረንበታል”… እያሉ የሚመፃደቁበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለሕዝቡ አደገኛ ‹‹ቫይረስ›› ሆኖበታል - ከኮሮና ቫይረስ የከፋ፡፡
እኔን ጨምሮ ብዙዎች የአገሬ ሰዎች እንደ ጭራቅ እንፈራዋለን፡፡  ልብ በሉ! ፖለቲካን መድሃኒትም መከላከያም እንደሌለው ከምናውቀው አደገኛው የኮሮና ቫይረስ በላይ ያሰጋኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ቫይረሱ ዓለምን በፍጥነት እያዳረሰ ነው። ኮሮና ቫይረስ አስጊ ያልሆነበት የዓለማችን ጥግ የለም ማለት ይቻላል፡፡ አየር መንገዶች የአገር ውስጥ በረራ ሳይቀር እያቋረጡ ነው፡፡ (የኛ አየር መንገድ ምን መላ እንዳገኘ ባናውቅም!) ት/ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች እየተዘጉ ነው፡፡ በዓላትና የስፖርት ውድድሮች እየተሰረዙ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ጉዞዎች ታግደዋል፡፡ ዓለም ባንክና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ከቫይረሱ ወረርሽኝ ጋር ለሚታገሉ ታዳጊ አገራት የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል:: ቫይረሱ ሰዎችን እየገደለ ብቻ ሳይሆን የዓለምን ኢኮኖሚም እያንኮታኮተ ነው፡፡ ለኢትዮጵያም (ለጊዜው ቁጥሩ ባይታወቅም) አደገኛነቱና አስጊነቱ ከሌሎች አገራት ቢብስ እንጂ አያንስም፡፡ (ከድህነታችንና ከኋላቀርነታችን አንፃር!)
ጥያቄውን ያቀረብኩላቸው አዲስ አበቤዎች፤ ይሄን ሁሉ የማመዛዘን አቅም የሚያንሳቸው አይደሉም፡፡ አብዛኞቹ ቢያንስ አንድ ‹‹የአገር ውስጥ ድግሪ›› ያላቸው ናቸው፡፡ (በዕውቀትም በማስተዋልም አይታሙም ለማለት ነው!)
እንዲያም ሆኖ ግን… ሁሉም በእጅጉ የሚያሰጋቸው ኮሮና ቫይረስ ሳይሆን መርዘኛው ፖለቲካችን ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር… እነዚህ ሰዎች አልተሳሳቱም፡፡ ከቫይረሱ ይልቅ የምር እንቅልፍ የሚነሳን በጥላቻ የተሾምነው ኋላቀር ፖለቲካችን ነው:: ለምን ቢሉ… ተማርን የሚሉ ማስተዋል የተሳናቸው ፖለቲከኞቻችን ሥራዬ ብለው በሚቆሰቁሱት ነገር በየጊዜው ምን ያህል ዜጎች ለሞትና ለአካል ጉዳት እንደተዳረጉ አሳምረን እናውቀዋለን፡፡ በዩኒቨርሲቲዎቻችን ተማሪው እርስ በርሱ ሲገዳደል የነበረው በምን ምክንያት ነው? ተማሪዎች ሊማሩ ወጥተው የታገቱት በማንና በምንድን ነው? በመርዘኛው ፖለቲካና ፖለቲከኞቻችን ነው:: ስንትና ስንት ሕዝባችን በየጊዜው ከመኖሪያ ቀዬው የሚፈናቀለው የውጭ ወራሪ ሀይል መጥቶብን እኮ አይደለም፡፡ ለሁሉም አገራዊ ጥፋትና ቀውስ ሰበቡ መርዘኛ የጥላቻ ፖለቲካችን ነው!! እናም… በ16ኛውና 17ኛው ክ/ዘመን ላይ ቆሞ የቀረው ኋላቀር የአገራችን ፖለቲካ… ከዘመን አመጣሹ ኮሮና ቫይረስም ሆነ ከሌሎች ክፉ በሽታዎች ሁሉ የበለጠ ያሰጋናል ቢባል አንዳችም ስህተት የለውም:: መቶ ፐርሰንት ሃቅ ነው!! እኔ የኢትዮጵያ ፖለቲከኛ ብሆን ኖሮ፣ ይሄን እውነታ እንደሰማሁ ራሴን ከፖለቲካው ዓለም አገል ነበር፡፡ ሕዝብ እንደ ጭራቅ በሚፈራው ሙያ ወይም ሥራ ውስጥ መሳተፍ አልፈልግማ:: እውነቴን ነው… ሰውን ለሞት በሚዳርግ ምንም ሥራ ውስጥ መካፈል ፍላጎቴ አይደለም፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከኮሮና ቫይረስ ወይም ከኤችአይቪ/ኤድስ አሊያም ከትራፊክ አደጋ ወዘተ… የበለጠ አዳጋች ስጋት የጋረጠ ጉዳይ መሆኑን … ሳሰላስል አንድ ሃሳብ ብልጭ አለልኝ፡፡ እንግዲህ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች (በተለይ የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞቹ) በታሪክ ጉዳይ ይሁን፣ በሃብት ክፍል በሥልጣን ይሁን በምርጫ ጉዳይ… ብቻ በምንም አጀንዳ ላይ ይናገሩ ወይም ይፃፉ አንደኛውን የሕብረተሰብ ክፍል ቢያንስ ማስቆጣታቸው፣ ሲብስ ደግሞ ነፍጥ ማማዘዛቸው ሳይታለም የተፈታ ነው:: (ወዲያው ባያማዝዙ እንኳን ለወደፊቱ ቀብድ ያሲይዛሉ! ይሄን ደግሞ ሲያደርጉ ያለምንም ጭንቀትና ጥበት ነው፡፡ ሕዝብ ቢጋጭ፣ ደም ቢቀባባ፣ በቀል ቢይዝ፣ ክፉኛ ቢጠላላ… ጉዳያቸው አይደለም፡፡ (ጭራቅ በስንት ዓለሙ!) በነገራችን ላይ አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች (አክራሪዎቹን ማለቴ ነው!) በሚጠሩት ሰልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ሰዎች ጆሮአቸውና ልባቸው የሚሞላው በመጥፎና በክፉ ሃሳቦች መልዕክቶች ነው:: በጥላቻ፣ በፀፀት፣ በተጠቂነት፣ በበቀል…፣ በተበዳይነት ወዘተ በአጠቃላይ በአሉታዊ ስሜቶች! በቃ!! ይኸው ነው፤
ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ንግግር ውስጥ… የሃገር ፍቅር ስሜት፣ የመነቃቃት መንፈስ፣ የአሸናፊነት ሥነ ልቦና፣ ድል አድራጊነት፣ ደግነት፣ ወንድማማችነት፣ ወዘተ… መጎናፀፍ ጨርሶ የሚታለም አይደለም የትኛው ፓርቲ ነው ከጥላቻ ንግግር ወጥቶ ስለ አገር ብልፅግና የሚያወራው? (ያልፈጠረባቸውን!) የትኛው ፖለቲከኛ ነው ህዝቡ በሃገሩ ተስፋ ከመቁረጥ ወጥቶ ተስፋ እንዲያደርግ የሚሰብከው?! አብደዋል እንዴ? የጦቢያ ፖለቲከኞችና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸው መቼ በተስፋ ተሞልተው ያውቃሉ? ለረዥም ዘመን የሥልጣን ጉጉት ተስፋ የቆረጡ ናቸው:: ተስፋ የቆረጠ ፖለቲከኛ ለህዝብ ተስፋ ሊሆን አይችልም፡፡ (ከየት ያመጣዋል?!) ወዳጆቼ፤ “አጥፍቶ ጠፊዎች” ልንላቸው ሁሉ እንችላለን፡፡ -  (በርግጥም ከኮሮና ቫይረስ የባሱ ናቸው!)
የሚገርመው ደግሞ… ሚሊዮኖችን ከኋላ አስከትለው ጥላቻና ክፋትን የሚዘሩት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ከምርጫ ቦርድ የዕውቅና ሰርተፊኬት የሚወስዱት ለሕዝቡ ሕይወት ዋስትና ሳይገቡ ነው፡፡ እናም ከእውቅና በፊት ለሕዝቡ የሕይወት ኢንሹራንስ መግባታቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዲያቀርቡ መገደድ አለባቸው እላለሁ፡፡ እንደውም ከ10 ሺ ወይም አራት ሺ ፊርማ በፊት መቅደም ያለበት ዋናው ጉዳይ ኢንሹራንስ ነው - የህይወት ኢንሹራንስ፡- የአካል ጉዳት ኢንሹራንስ፡፡ የስደትና የቶርቸር ኢንሹራንስ ወዘተ አያችሁ አንድ ፓርቲ ለደጋፊዎቹና አባላቱ ሁሉ ኢንሹራንስ ካልገባ በቀር በቦርዱ ተመዝግቦ ዕውቅና እንደማይሰጠው በጥብቅ መደንገግ አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ቁጥር 1 ገዳይ ከሆነው የትራፊክ አደጋ ሳይቀር  ለሞት አጋላጭ ወደሆነው ምርጫ ከመግባታችን በፊት የኢንሹራንስ ጉዳይ  በፓርቲዎች የምዝገባ ሕግ ውስጥ መካተት ይገባዋል - ባይ ነኝ፡፡ ያኔ መርዘኛ የጥላቻ ቃላት እየዘሩ ዜጐችን ለሞት ከመዳረግ ይቆጠቡ ይሆናል (በገንዘባቸው ኢንሹራንስ ገብተዋላ!) እንዲያም ሆኖ ‹‹ለስልጣን ድምጽ እንጂ ህይወት አንሰጥም::” የሚለውን መፈክራችንን ሁሌም አንረሳም::
ሌላው ደግሞ ምን መሰላችሁ? ሕዝብን እርስ በርስ ከማጋጨት ውጭ የማያውቁ፣ አገር ለመበታተን ቆርጠው የተነሱ፣ ከአንደበታቸው ክፋት ብቻ የሚወጣቸው፣ ከሥልጣን ውጭ ሕይወት ያለ የማይመስላቸው፣ ለጥፋት ብቻ የቆሙ ፖለቲከኞች ተለይተው የሚቀመጡበት (ኳራንታይን) ሥፍራ በፍጥነት መዘጋጀት አለበት - በኮሮና ቫይረስ ለተያዙ ሰዎች እንደሚዘጋጀው፡፡ (ያለዚያ ማለቃችን ነው!)
ከፖለቲካ ኮሮና ቫይረስ ይጠብቀን!!


Read 5463 times