Saturday, 14 March 2020 13:26

ኮሮና አለምን “መውረሩን” ቀጥሏል

Written by 
Rate this item
(5 votes)

     ኮሮና ቫይረስ ከቻይና ተነስቶ መላውን አለም እያዳረሰ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ካጠቃና ከ4 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለህልፈተ ህይወት ከዳረገ፣ በኩባንያዎችን እንቅስቃሴና በአገራት ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ካደረሰ፣ በየአቅጣጫው ብዙ ጥፋትን ካስከተለ በኋላ፣ መስፈርቴን አላሟላምና “ወረርሽኝ” ብዬ አልጠራውም በሚል ለወራት ሲያመነታ የቆየው የአለም የጤና ድርጅት በስተመጨረሻም “ኮሮና አለማቀፍ ስጋት የሆነ ወረርሽኝ ሆኗል!” ሲል ባለፈው ረቡዕ በይፋ አወጀ፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኮሮና ቫይረስ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ በአለም ዙሪያ በሚገኙ 125 አገራትና ግዛቶች ውስጥ 129 ሺህ 854 ሰዎችን ያጠቃ ሲሆን፣ ከ4 ሺህ 751 በላይ የሚሆኑትንም ለህልፈተ ህይወት ዳርጓል፡፡
ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተባት ቻይና ምንም እንኳን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር በሳምንቱ በእጅጉ መቀነሱን ይፋ ብታደርግም፣ እስከ ትናንት በስቲያ በአገሪቱ 80 ሺህ 796 ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸውንና 3 ሺህ 169 ሰዎች ደግሞ ለሞት መዳረጋቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡
አንድ በሽታ ወረርሽኝ ተብሎ የሚጠራው በዓለም ዙሪያ በተመሳሳይ ጊዜ በተለያዩ አገራት ሲሰራጭ መሆኑን የተናገሩት የአለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ኮሮናም በመላው አለም በስፋት እየተሰራጨ በመሆኑ ወረርሽኝ መሆኑ መታወጁንና አገራትም ከመቼውም በበለጠ የወረርሽኙን ፍጥነት ለመግታት መረባረብ እንደሚገባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከቻይና ውጭ ባሉት የአለም አገራት ባለፉት ሁለት ሳምንታት በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ13 እጥፍ ያህል ማደጉን የተናገሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ፣ አለም ወረርሽኙን ለመግታት እጅ ለእጅ ተያይዞ መስራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ጠንካራ የጉዞ እገዳዎች
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት በማሰብ በአውሮፓ ህብረት አገራት ላይ የጉዞ እገዳዎችን መጣላቸውን ባለፈው ረቡዕ ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ጉዳዩ በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
ለኮሮና ጉዳይ ተገቢውን ትኩረት አልሰጡም በሚል ሲተቹ የሰነበቱት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከእንግሊዝ በስተቀር ከ26 የአውሮፓ አገራት ወደ አገሪቱ የሚደረጉ ጉዞዎች በሙሉ ከትናንት ጀምሮ ለ30 ቀናት ያህል መታገዳቸውን ማስታወቃቸውን የዘገበው ቢቢሲ፣ የጉዞ እገዳው አሜሪካውያን ዜጎችን አይመለከትም መባሉንና ኮሮና በአሜሪካ ከ1 ሺህ 135 በላይ ሰዎችን ማጥቃቱንና 38 ሰዎችን መግደሉንም አመልክቷል፡፡
የአውሮፓ ህብረት የትራምፕን የጉዞ እገዳ በማስመልከት ባወጣው መግለጫ፣ “ኮሮና አለማቀፍ ቀውስ እንጂ የአንድ አህጉር ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ ከአንድ ወገን እርምጃ ይልቅ ትብብርን የሚሻ የጋራ ችግር ነው” ሲል የትራምፕን እርምጃ ማውገዙን የዘገበው ቢቢሲ በርካታ የአውሮፓ አገራት መሪዎችም ሌላ ቀውስ የሚያመጣ አደገኛ እርምጃ በሚል ትችታቸውን መሰንዘራቸውንም ዘግቧል፡፡
በተመሳሳይ መልኩም፣ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቶ 45 ያህል መድረሱ ያሰጋት ሳዑዲ አረቢያ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ አውሮፓ ህብረትና ሌሎች 12 የአለማችን አገራት የሚደረጉ ጉዞዎችን ከትናንት በስቲያ ያገደች ሲሆን በተጠቀሱት አገራት የሚገኙ ዜጎች በ72 ሰዓታት ውስጥ ወደአገራቸው እንዲገቡም ጥሪ አቅርባለች፡፡
የአገሪቱ መንግስት ባወጣው መግለጫ የጉዞ እገዳው ከተጣለባቸው የአውሮፓ፣ የእስያና የአፍሪካ አገራት ወደ ሳዑዲ የሚደረጉና ከሳዑዲ ወደ አገራቱ የሚደረጉ የጉዞ በረራዎች ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆሙ መወሰኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

ክፉኛ የተጎዳ ንግድና ኢኮኖሚ
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በአውሮፓ አገራት ላይ የጉዞ እገዳ መጣላቸውን ተከትሎ አሜሪካ፣ አውሮፓና እስያን ጨምሮ በአለማቀፍ የፋይናንስ ገበያዎች ላይ ያልተለመደና ከፍተኛ የአክሲዮን ዋጋ ማሽቆልቆል እንደታየ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከአውሮፓ አገራት ወደ አሜሪካ የሚገቡ የጭነት አውሮፕላን በረራዎች ጭምር የሚያግደው አነጋጋሪው የትራምፕ ውሳኔ የሁለቱን አገራት ብቻ ሳይሆን የተቀረውን አለም የንግድና ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በእጅጉ ይጎዳዋል ተብሎ መሰጋቱን የጠቆመው ዘገባው፣
የቻይና አምራች ኩባንያዎች ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ስራቸው በከፍተኛ ሁኔታ መስተጓጎሉን ያስታወቁ ሲሆን፣ በተለይ በመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ላይ የተከሰተው የሰው ሃይልና የግብዓት እጥረት በአለማቀፉ የመድሃኒት ገበያ ላይ ከፍተኛ እጥረት ሊያስክትል እንደሚችል ተሰግቷል፡፡
አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ውስጥ የሚገኙ ታላላቅ ኩባንያዎች ሰራተኞቻቸውን የመቀነስ ወይም በቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ የማድረግ አማራጭን እየተጠቀሙ ሲሆን፣ ይህ ግን በአንዳንድ አገራት እጅግ አስቸጋሪ መሆኑ ተነግሯል፡፡
የጎግል እህት ኩባንያ የሆነው አልፋቤት በአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ አገራት ውስጥ የሚገኙ ሰራተኞቹ በሙሉ እስከ ሚያዝያ ወር መጀመሪያ ድረስ ቤታቸው ውስጥ ሆነው ስራቸውን እንዲሰሩ መምከሩን የዘገበው ሲኤንቢሲ፣ ትዊተር በበኩሉ 5 ሺህ የሚደርሱ ሰራተኞቹን በተመሳሳይ ሁኔታ ቤታቸው ውስጥ ሆነው እንዲሰሩ ቀጭን ትዕዛዝ ማስተላለፉን ገልጧል፡፡
ኢኮኖሚው በቫይረሱ ሳቢያ ክፉኛ የተጎዳበት የጣሊያን መንግስት 28.3 ቢሊዮን ዶላር ድጎማ ለማድረግ ማሰቡ የተነገረ ሲሆን፣ የጀርመኖቹ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያዎች አዲዳስና ፑማ ሽያጫቸው በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንስ እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መስፋፋቱን ተከትሎ በአለም ዙሪያ የሚገኙ አየር መንገዶች በሺህዎች የሚቆጠሩ በረራዎችን መሰረዛቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ሪያንኤር፣ ኢዚጄት፣ ኖርዌጂያን ኤር፣ ብሪቲሽ ኤርዌይስና አሜሪካን ኤርላይንስ በረራቸውን በብዛት የሰረዙና ለከፍተኛ የገቢ መቀነስ የተዳረጉ አየር መንገዶች መሆናቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

የተዘጋች ጣሊያን
ከአውሮፓ አገራት መካከል ኮሮና ክፉኛ እንዳጠቃት በሚነገርላትና የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከ12 ሺህ የሟቾች ቁጥር ደግሞ 827 በደረሰባት ጣሊያን የዕለት ከዕለት የስራና የንግድ እንቅስቃሴ እየተገደበ ሲሆን፣ የአገሪቱ መንግስትም ከምግብ መደብሮችና ፋርማሲዎች በስተቀር ሁሉንም ሱቆችና የንግድ ተቋማት በመዝጋት ላይ ይገኛል፡፡
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ የሰጡትን መግለጫ ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ጂምናዚየሞች፣ ሙዚየሞችና የምሽት ክለቦች ቀደም ብለው በተዘጉባት ጣሊያን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሲባል መጠጥ ቤቶች፣ ሬስቶራንቶችና ጸጉር ቤቶችን ጨምሮ እምብዛም አንገብጋቢ ያልሆኑና መሰረታዊ ግልጋሎቶችን የማይሰጡ የንግድ ተቋማት በሙሉ ለሁለት ሳምንታት ያህል የሚዘጉ ይሆናል፡፡
በጣሊያን በኮሮና ቫይረስ ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር ባለፈው ረቡዕ በ30 በመቶ ያህል መጨመሩን ተከትሎ፣ የአገሪቱ መንግስት ዜጎች እንቅስቃሴያቸውን ገትተው በቤት ውስጥ እንዲቀመጡ ጥብቅ ማሳሰቢያ ማስተላለፉ ተነግሯል፡፡

አፍሪካ
ከሌሎች አህጉራት ጋር ሲነጻጸር ኮሮና ቫይረስ እምብዛም ጉዳት ያላደረሰው በአፍሪካ ቢሆንም፣ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ ቫይረሱ የተገኘባቸው 12 የአፍሪካ አገራት ግብጽ፣ አልጀሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቱኒዝያ፣ ሞሮኮ፣ ሴኔጋል፣ ካሜሩን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ናይጀሪያ፣ ቶጎ፣ ዶሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ኮትዲቯር መሆናቸው ተዘግቧል፡፡
ኮሮና ቫይረስ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ በተጠቀሱት አስራ ሁለት የአፍሪካ አገራት ውስጥ በድምሩ 119 ሰዎችን ማጥቃቱ የተነገረ ሲሆን፣ 60 ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባት ግብጽ በአህጉሩ በከፋ ሁኔታ ተጠቂ የሆነች ቀዳሚዋ አገር ናት፡፡
አልጀሪያ 20፣ ደቡብ አፍሪካ 13፣ ቱኒዚያ 7፣ ሞሮኮ 6፣ ሴኔጋል 4፣ ካሜሩን ቡርኪናፋሶና ናይጀሪያ እያንዳንዳቸው 2፣ ቶጎ ዲሚክራቲክ ኮንጎና ኮትዲቯር እያንዳንዳቸው 1 ሰው በኮሮና ቫይረስ እንደተጠቃባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
የመርኬል “ግምት”
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በሳምንቱ ከተሰሙትና መላውን አለም ሲያነጋግሩ ከሰነበቱት ጉዳዮች መካከል፣ የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ መርኬል “ኮሮና ቫይረስ 70 በመቶ ያህል የጀርመንን ህዝብ ሊያጠቃ ይችላል” ሲሉ ባለፈው ረቡዕ በይፋ ያሰሙት ማስጠንቀቂያ አንዱ ነው፡፡
ከጀርመን ህዝብ 70 በመቶ ያህሉ ወይም 58 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሊያዙ ይችላሉ የሚለው የአንጌላ መርኬል ማስጠንቀቂያ ብዙዎችን ሲያስደነግጥ፣ አንዳንዶችን ደግሞ “ሴትዮዋ ወይ ቁጥር ወይ ግምት አይችሉም!” ብለው እንዲሳለቁ ማድረጉን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡

በ22 አገራት ትምህርት ሙሉ
ለሙሉ ተቋርጧል
በመላው አለም በሚገኙ 22 አገራት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የመደበኛና የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ሙሉ ለሙሉ መቋረጡን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ትምህርት ሙሉ ለሙሉ ከተቋረጠባቸው የአለማችን አገራት መካከል ጣሊያን፣ ዴንማርክ፣ ካዛኪስታን እና ጃፓን እንደሚገኙበት የጠቆመው ዘገባው፣ አገራቱ ትምህርት ቤቶችንና ዩኒቨርሲቲዎችን እንዲዘጉ የወሰኑት ለተለያየ የጊዜ እርዝማኔ መሆኑንም አመልክቷል፡፡
ሌሎች 13 የአለማችን አገራት ደግሞ ቫይረሱ በተስፋፋባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የተወሰኑ ትምህርት ቤቶችን ብቻ መርጠው መዝጋታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ከእነዚህ አገራት መካከል ስፔን፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመንና ዩክሬን እንደሚጠቀሱም አክሎ ገልጧል፡፡

ከቶም ሃንክስ እስከ ፓብሎ ኤግሊሲያስ
ለስራ ጉዳይ ወደ አውስትራሊያ ጎራ ብለው የነበሩት የኦስካር ተሸላሚው የፊልም ተዋናይ ቶም ሐንክስና ባለቤቱ ሪታ ዊልሰን በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸው በምርመራ መረጋገጡን ባለፈው ረቡዕ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን በስፋት ዘግበዋል፡፡
ፎረስት ጋምፕና ሴቪንግ ፕራይቨተር ራያንን ጨምሮ በበርካታ ፊልሞቹ የሚታወቀው ቶም ሃንክስና ባለቤቱ ወደ አውስትራሊያ የተጓዙት የኤልቪስ ፕሪስሊን የሕይወት ታሪክ በፊልም ለማዘጋጀት እንደነበር የዘገበው ሆሊውድ ኒውስ፣ ሁለቱም የህመም ስሜት ሲሰማቸው ወደ አንድ ሆስፒታል መሄዳቸውና በተደረገላቸው ምርመራ በቫይረሱ መጠቃታቸው መረጋገጡን ተከትሎ ከሌሎች ሰዎች ተነጥለው እንዲቀመጡ መደረጋቸውን አመልክቷል፡፡
የስፔን የእኩልነት ሚኒስትር አይሪን ሞንቴሮ ባለፈው ረቡዕ በኮሮና መጠቃታቸው መረጋገጡን ተከትሎ የትዳር አጋራቸው የሆኑት የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፓብሎ ኤግሊሲያስም  ራሳቸውን ነጥለው እንዲቀመጡ መደረጋቸውና ሁሉም የአገሪቱ የፓርላማ አባላትና ባለስልጣናት ምርመራ እንዲያደርጉ መወሰኑን የአገሪቱ መንግስት አስታውቋል፡፡
በቫይረሱ እንደተያዙ ከተነገረላቸው ሌሎች የአለማችን ታዋቂ ሰዎች መካከል ለጣሊያኑ የእግር ኳስ ክለብ ጁቬንቱስ የሚጫወተውና በተገገለ ቦታ እንዲቀመጥ የተደረገው ዳኔል ሩጋኒ እና የእንግሊዝ የጤና ሚኒስትር ናዳኔ ዶሪስ ይጠቀሳሉ፡፡
በስፔን የአንድ ቅርጫት ኳስ ቡድን ተጫዋች በኮሮና መያዙ መረጋገጡን ተከትሎ የሪል ማድሪድ የቅርጫት ኳስና የእግር ኳስ ቡድኖች ተጫዋቾች በሙሉ ወደ ጊዚያዊ የማረፊያ ቦታ እንዲገቡ መደረጋቸውም ተነግሯል፡፡


____________________________________________

የአገሩ ስም የተጠቂዎች
ቁጥር
የሟቾች
ቁጥር
ቻይና 80,796 3,169
ጣሊያን 12,462 827
ኢራን 10,075 429
ደቡብ ኮርያ 7,869 66
ስፔን 3,003 84
ጀርመን 2,355 4
ፈረንሳይ 2,281 48
አሜሪካ 1,377 38
ስዊዘርላንድ 867 6
ኖርዌይ 713
ዲያምንድ
ፕሪንስ መርከብ
696 7
ጃፓን 643 16
ስዊድን 635 1
ዴንማርክ 615
ኒዘርላንድ 614 5
እንግሊዝ 590 10
ቤልጂየም 399 3
ኦስትሪያ 302 1
ኳታር 262
ባህሬን 195
ሲንጋፖር 178
ማሌዢያ 158
አውስትራሊያ 156 3
ሆንግ ኮንግ 130 3
ካናዳ 118 1
ፊላንድ 109
አይስላንድ 103
እስራኤል 100
ግሪክ 99 1
ቼቺያ 96
ስሎቫኒያ 89
የተባበሩት አረብ
ኤሜሬትስ
85
ኩዌት 80
ፖርቹጋል 78
ህንድ 74
ኢራቅ 71 8
ታይላንድ 70 1
ሳንማሪኖ 69 3
ብራዚል 69
ሊባኖስ 68 3
ግብጽ 67 1
ፊሊፒንስ 52 2
ፖላንድ 51 1
ታይዋን 49 1
ሮማኒያ 49
ሳዑዲ አረቢያ 45
አየርላንድ 43 1
ቬትናም 39
ኢንዶኔዢያ 34 1
ፍልስጤም 31
ሩስያ 28
ጆርጂያ 25
ብሩኒ 25
አልጀሪያ 24 1
አልባኒያ 23 1
ቺሊ 23
ኮስታ ሪካ 22
አርጀንቲና 21 1
ፓኪስታን 21
ክሮሺያ 19
ሉግዘምበርግ 19
ሰርቢያ 19
ኦማን 18
ኢኳዶር 17
ኢስቶኒያ 17
ፔሩ 17
ደቡብ አፍሪካ 17
ቡልጋሪያ 16 1
ላቲቪያ 16
ሃንጋሪ 16
ስሎቫኪያ 16
ፓናማ 14 1
ቤላሩስ 12
ሜክሲኮ 12
አዘርባጃን 11
ቦስኒያ
ሄርዘጎቪኒያ
11
ማካኦ 10
ሰሜን ሜቄዶኒያ 9
ኮሎምቢያ 9
ማልታ 9
ማልዴቪስ 8
አፍጋኒስታን 7
ቱኒዚያ 7
ቆጵሮስ 7
ሞሮኮ 6 1
ጊኒ 6
ካምቦዲያ 5
ዶሚኒካን
ሪፐብሊክ
5
ኒውዚላንድ 5
ሴኔጋል 5
ፓራጓይ 5
አርሜኒያ 4
ሊችተንስቲን 4
ሞልዶቫ 4
ሊዪቲያና 3
ባንግላዴሽ 3
ቻነል ደሴቶች 3
ኩባ 3
ማርቲሚኒክ 3
ናይጀሪያ 2
ሲሪ ላንካ 2
ቦሊቪያ 2
ቡርኪና ፋሶ 2
ካሜሮን 2
ፋኦሬ ደሴቶች 2
ሆንዱራስ 2
ጃማይካ 2
ሴንት ማርቲን 2
ጊኒ 1 1
አንዶራ 1
ዮርዳኖስ 1
ሞናኮ 1

Read 13686 times