Saturday, 30 June 2012 12:58

ደም ባለመዘጋጀቱ ቀዶ ህክምና የተቋረጠባት ህፃን አረፈች

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

ከህብለሰረሰር (Spinal cord) ጋር በተያያዘ የጤና ችግር ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የገባችው ህፃን ድንቂቱ ተስፋዬ፤ ሰኞ እለት ነው ወደ ቀዶ ህክምና ክፍል የተወሰደችው፡፡ የህፃኗ ህክምና ለበርካታ ቀናት ቀጠሮ እየተያዘለት ሲስተጓጎልና ሲራዘም እንደነበር የተናገሩት ወላጅ አባቷ አቶ ተስፋዬ፤ ልጃቸው ወደ ቀዶ ህክምና ክፍል ገብታ ህክምናው ሲጀመር በከፊል እፎይታ እንደተሰማቸው ይገልፃሉ። ለቀዶ ህክምናው ሲባል፤ ህፃኗ ምግብ እንዳትበላ በሃኪም ትዕዛዝ ተሰጥቶ ስለነበር፤ ቀነ ቀጠሮው እየተስተጓጎለ ሲራዘም፤ የምግብ ክልከላውም እየተራዘመ ሲያስጨንቃቸው ቆይቷል። ሰኞ እለት ሁሉም ነገር ተዘጋጅቷል ተብሎ የተጀመረው የቀዶ ጥገና ህክምና ግን እንደገና ተስተጓጎለ፡፡

የቀዶ ህክምና ክፍል ውስጥ የህፃኗ የጀርባ ክፍል ተከፍቷል። ሁሉም ነገር በስርአት እየተከናወነ ይመስላል። በዚሁ መሃል፤ ከህፃኗ የፈሰሰውን የሚተካ ደም ሲፈለግ፤ የተገኘው ምላሽ እንግዳና አስደንጋጭ ነው - ደም የለም፡፡ ሆስፒታል ውስጥ ተተኪ ደም ሳይኖር እንዲህ አይነት የቀዶ ህክምና ጨርሶ አይካሄድም፡፡

የቀዶ ህክምናው ተቋረጠ፡፡ ሃኪሙ በቁጣ ከክፍሉ  እንዳዩዋቸው አቶ ተስፋዬ ገልፀው፤ ህክምናውን እንዳቋረጡት ነግረውኝ እዚያው ባለሁበት ጥለውኝ ሄዱ ይላሉ።

ግራ ተጋብተው የቆሙት አባት፤ ህፃን ልጃቸውን ከቀዶ ህክምና ክፍል እስኪያስወጧት ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው። ሰውነቷ በደም ተነክሯል የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ ጀርባዋ በፕላስተር ተለጣጥፎ ነበር በማለት ድንጋጤያቸውን ይገልፃሉ። ነርሶቹን ስጠይቃቸው፤ “የምናውቀው ነገር የለም፤ ሃኪሙ የህፃኗን ጀርባ እንደከፈተ ጥሏት ሄደ” ሲሉ እንደመለሱላቸው አቶ ተስፋዬ ጠቅሰዋል።

ከጅማ ዞን ጡራፈታ ወረዳ የመጣችውና  ጥቁር አንበሳ የገባችው ህፃን ድንቂቱ፤ ከጤና ችግር ጋር ነው የተወለደችው። በመጀመሪያዎቹ የእርግዝና ሳምንታት የሚከሰት ከነርቭ ጋር የተያያዘ የጀርባ እብጠት የህፃኗን ጤና እንዳቃወሰው ሃኪሙ ዶ/ር አባት ሳህሉ ገልፀዋል። የወላጆቿ አቅም አነስተኛ ስለሆነ፤ “አክሽን ፕላን ኦፍ ኢትዮጵያ” የተሰኘ የረድኤት ድርጅት የህክምናዋን ወጪ ለመሸፈን በመተባበሩ በአገር ውስጥ ካልተቻለ ወደ ውጭ አገር ወስዶ ለማሳከም ድርጅቱ ቃል ገብቶልን ነበር ብለዋል- የልጅቷ አባት ነገር ግን ህክምናውን በአገር ውስጥ ማከናወን ይቻላል ተብሎ ስለተወሰነ፤ ወደ ውጭ አገር እንድትሄድ ሳይፈቀድ ቀርቷል፡፡ በዚህ ውሳኔም ነው፤ ግንቦት 30 ቀን በጥቁር አንበሳ አልጋ እንድትይዝ ተደርጎ የቀዶ ህክምናውን መጠባበቅ የጀመረችው።

በህፃኗ ላይ ለሚካሄድ የቀዶ ህክምና ዝግጅት እንዲካሄድ ዶ/ር አባት ሳህሉ በሰጡት ትእዛዝ፤ ወላጅ አባቷ አቶ ተስፋዬ ወደ ቀይ መስቀል በመሄድ ደም ሰጥተዋል። ለልጃቸው የሚሆን ደም ለማግኘት በቅድሚያ፤ ደም መስጠት ነበረባቸው። እናም የልጃቸው የደም አይነት ታይቶ ለቀዶ ህክምናው የሚሆን ደም ወደ ሆስፒታሉ የተላከው በማግስቱ ሰኔ 1 ቀን 2004 ዓ.ም እንደነበረ አቶ ተስፋዬ ያስታውሳሉ።

የህክምናው ቀጠሮ ሲደርስ፤ በሃኪሙ ትእዛዝ ህፃኗ ምግብ እንዳትበላ አደረግን የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ የመጀመሪያ ቀጠሮ ተስተጓጉሎ ሌላ ቀጠሮ የተሰጠን ጊዜም እንዲሁ ምግብ እንዳትበላ አድርገናል። ለአራት ጊዜ ያህል ቀጠሮ እየተስተጓጎለ ተራዝሟል ይላሉ አቶ ተስፋዬ። ሰኞ ሰኔ 18 ቀን ግን ቀጠሮው አልተስተጓጎለም። ህፃኗ የቀዶ ህክምና ክፍል ውስጥ ገብታለች፤ አባቷም የህክምናውን መጠናቀቅ ይጠባበቃሉ። ግን ህክምናው ተስተጓጎለ።

በጅምር የተቋረጠውን ህክምና ያከናወኑት ዶ/ር አባት ሳህሉ፤ ህፃኗ ተደራራቢ ችግር እንደነበረባት ጠቅሰው፤ ቀዶ ህክምናው ቢጠናቀቅ ኖሮም የህፃኗ የመትረፍ እድል አነስተኛ ነበር ይላሉ፡፡ “ለቀዶ ህክምና በየጊዜው ቀጠሮ ብንይዝም በልዩ ልዩ ምክንያቶች ህክምናው ሳይከናወን ቆይቷል” የሚሉት ዶ/ር አባት ሳህሉ፤ “ሰኔ 18 ቀን ቀዶ ህክምናውን ልሰራ ገባሁ” በማለት የተፈጠረውን ችግር ይገልፃሉ።

“ቀዶ ህክምናውን ከሰራሁ በኋላ፤ ለህፃኗ ደም እንዲሰጡኝ ስጠይቅ፤ ደም የለም አሉኝ” የሚሉት ዶ/ር አባት ሳህሉ፤ “ወደ ላብራቶሪ ደውዬም ጠይቄያለሁ” ይላሉ። “ለህፃኗ የተዘጋጀ ደም ላብራቶሪ ውስጥ ተቀምጦ ነበር፤ ነገር ግን ለእሷ የተዘጋጀላትን ደም ለሌላ ድንገተኛ ታካሚ ስለተጠቀምንበት የለም ተባልኩ” ብለዋል  በዚህም እንደተናደዱ በመግለፅ። “እንደዚያ ሆኖ መስራትም ስለማይቻል፤ ሌላ ቀን ይሰራላት ብዬ ህክምናውን አቋርጬ ወጥቻለሁ። አቋርጬ የወጣሁት ህፃኗን በማይጐዳት መልኩ ነው” ብለዋል ዶ/ር አባት።

ህክምናውን ከመጀመራቸው በፊት፤ አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ መዘጋጀታቸውን ማረጋገጥ አልነበረብዎትም ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ዶ/ር አባት በሰጡት ምላሽ፤ “ደሙ መኖሩን ቀደም ብዬ ጠይቄያለሁ፤ ከልጅቷ የደም አይነት እንደሚስማማ ሰኔ 16 ቀን አረጋግጠናል። የምንፈልገው ደም አለ በሚል ሃሳብ ህክምናው ጀመርኩ” ብለዋል። “በህክምናው መሃል፤ ደም የለም ስለተባለ፤ ህክምናውን የግድ ማቆም ነበረብኝ” የሚሉት ዶ/ር አባት፤ “ህፃን ስለሆነች እያንዳንዱ የደም ጠብታ ካልተተካ ለህይወቷ አስጊ ነው፡፡ ህክምናውን ብቀጥል ኖሮ የበለጠ በመድማት አደጋ ላይ ትወድቅ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በጅምር ከቀረው የቀዶ ህክምና በኋላ የተዳከመችው ህፃን፤ መተንፈስ እያቃታት በማግስቱ ኦክስጅን ቢደረግላትም ረቡእ እለት ህይወቷ አልፏል። ለህፃኗ መሞት ዶ/ር አባት የተለያዩ ምክንያቶችን ያቀረቡ ሲሆን፤ ህፃኗ እጅግ ዘግይታ ወደ ህክምና እንድትመጣ መደረጉ አንድ ምክንያት ነው ብለዋል። ቀዶ ህክምናው በተቋረጠ ማግስት የያዛትንም የሳንባ ምች ዶ/ር አባት በምክንያትነት ጠቅሰው፤ “ለቀዶ ህክምናው ደም አለመዘጋጀቱም ለችግሩ አስተዋፅኦ ያደርጋል” ብለዋል። አንዳንድ ጊዜ ህይወትን ለማዳን ለሌላ ሰው የተዘጋጀን ደም መጠቀም ሊያስፈልግ ይችላል የሚሉት ዶ/ር አባት፤ የደም ላብራቶሪ ውስጥ ለልጅቷ የተቀመጠውን ደም ተጠቅመውበታል” ብለዋል። የተዘጋጀው ደም ለሌላ ሰው ህክምና መዋል አለመዋሉ ሳይረጋገጥ የቀዶ ጥገና ህክምናው ለምን ተጀመረ የሚለው ጥያቄ ቢኖርም፤ የቀዶ ህክምናውን ያቋረጥኩት ልጅቷን በሚጐዳት መልኩ አይደለም ይላሉ ዶ/ር አባት፡፡በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሜዲካል አገልግሎት ዳሬክተር ዶ/ር አብርሃም እንደሻው፤ ስለጉዳዩ የደረሳቸው ሪፖርት አለመኖሩን ገልፀው፤ በህክምና አገልግሎት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን የሚከታተልና እርምጃ የሚወስድ አካል ስላለ ክትትል እናደርጋለን ብለዋል፡፡የቀዶ ህክምና ከመከናወኑ በፊት በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ያለ በቂ ዝግጅት በሚከናወን ስራ ሳቢያ ለሚፈጠሩ ችግሮች ተጠያቂነት ይኖራል ብለዋል - ዶ/ር አብርሃም።

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል (በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ፋኩልቲ ዲን) ዶ/ር ደረጀ ጉልላት በበኩላቸው፤ ዶ/ር አባት ሳህሉ ከወጣት የቀዶ ጥገና ሃኪሞች መካከል አንዱ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በእውቀትና በችሎታቸው እተማመንባቸዋለሁ ብለዋል። ነገር ግን የቀዶ ህክምና ከመጀመሩ በፊት አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ መሟላታቸውንና ዝግጁ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነበረበት የሚሉት ዶ/ር ደረጀ፤ ከዚህ ቀደም የዚህ አይነት ችግር ተፈጥሮበትና አጋጥሞኝ አያውቅም ብለዋል፡፡

የህፃኗ ወላጆች ከትናንት በስቲያ የልጃቸውን አስከሬን ይዘው ወደ ጅማ ሄደዋል።

 

 

 

Read 20592 times Last modified on Saturday, 30 June 2012 13:03