Saturday, 14 March 2020 15:47

የግጥም ጥግ

Written by  ሞገስ ተከተል
Rate this item
(7 votes)

   “ሰው ነህ የሚል ማተም”
                      
   አዳም አባታችን አንደተፈጠረ ገነት ነው
የኖረው
ገነት ለመኖሩ ምክንያት የሆነው
ከፍጥረታት ሁሉ
እጅግ “የከበረ” ሰው ስለሆነ ነው።
እየሱስ በሞቱ
ፍቅሩን የገለፀው
ኤጄቶ ላውራልህ
ፋኖ ሆይ ልንገርህ
ቄሮዬ ሆይ ስማኝ
ሰዎች ለተባልነው ለኔና ላንተ ነው።
የእስልምናም ትምሀርት ተግባራቱ
ሲታይ ከነአበቃቀሉ
ሰውን ያስቀድማል ከፍጥረታት ሁሉ
ስለዚህ አዳምጠኝ
በየትም የሰፈርክ የትም የምትገኝ
አንተ ባለ መውዜር ፥ጎበዙ ቀስተኛ
፥አነተ ባለ ሜጫ
ሰው መሆንን ትተህ
ሁኔታን ሳትመጥን ሳታይ አቻችለህ
ብሄርን አካብደህ
መደብክን አንግሠህ
ጶታህን አስልቀህ
ሐይማኖትን ይዘህ
ከወገንህ ጋራ የገባህ ፍጥጫ
ብሔርን አጉልተህ ትግራዋይ ነኝ ብትል
“ነፃነት “ ገድቦ ብቻ ያስቀርሐል
ቋንቋን አስቀድመህ ኦሮሞ ነኝ
ብትል
ሌላን አስኮርፎ “ወንድም “ያሳጥሐል
በዚህም በዚያም በኩል አማራ ነኝ
ብትል
ስግብግብ አድርጎ “ክብር” ያስርብሐል
ይህ አልበቃ ብሎህ
ጠባብነት ጠልፎህ
ሰው ከሚለው ንግር ሰው ከሚለው
በላይ
የቀለም ደረጃ
የሐብት ደረጃ
የውበት ደረጃ
ምንትስ ደረጃ
እያልክ በመደርደር ዘርዝረህ ብታሳይ
እኔ አልቀበልም ከቁብም አልቆጥረው
ምክንያት ብትለኝ
እግዚያብሔር የሰጠኝ ደረጃዬ ሰው ነው
ፍጥረቴም ከገነት ፍቅሬም ከየሱስ ነው
እናም ኮሚሣሬ ወረዳ መሪዬ
ብሔሬን ሰርዘህ ከመታወቂያዬ
ምኔም ምናምኔም ሰው እንዲመስልልኝ
ክብር እንዲሰማኝ
ነፃነት እንዳገኝ
ወደ ጎጃም ሄጄ ለማለት “ቄሮ “ ነኝ
አሪሲ ተጉዤ ለማለት” ሄጎ” ነኝ
ሲዳማ ዘልቄ ለማለት “ፋኖ” ነኝ
በመታወቂያዬ “ሰው ነህ “
የሚል ማተብ አሳትመህ ስጠኝ።

Read 2916 times