Saturday, 21 March 2020 12:17

የኦሮሚያ ኒውስ ኔት ዎርክ ጋዜጠኞች ከእስር እንዲፈቱ ሲፒጄ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

    የተጠረጠሩበት ጉዳይ በግልጽ ሳይታወቅ ታስረው የሚገኙት የኦሮሚያ ኒውስ ኔትዎርክ (ONN) ጋዜጠኞች በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ ጠየቀ፡፡ የኦሮሚያ ኒውስ ኔትዎርክ ምክትል ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ደሱ ዱላ፣ የጣቢያው ሪፖርተር ዋቆ እና ሲጓጓዙበት የነበረ ተሽከርካሪ ሹፌር የሆነው እስማኤል መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም በቡራዩ ከተማ ሲንቀሳቀሱ ለእስር መዳረጋቸውን ሲፒጄ አስታውቋል፡፡ ጋዜጠኞቹ ከታሠሩ በኋላ መጋቢት 6 ፍ/ቤት ቀርበው የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ቀን ለፖሊስ እንደተፈቀደለትና የተጠረጠሩበት ጉዳይም በግልጽ እንደማይታወቅ ሲፒጄ በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ “ጋዜጠኞችን ለሣምንታት ያለምንም ክስ አስሮ ማቆየት የሰብአዊ መብትና የጋዜጠኞችን ተዘዋውሮ በነፃነት የመስራት መብት የሚጋፋ ድርጊት ነው” ያለው ሲፒጄ፤ “ጋዜጠኞች ማንኛውንም ፖለቲካዊ ሁኔታ በነፃነት ተዘዋውረው መዘገብ አለባቸው፤ በማንኛውም መልኩ ነፃነታቸውን የሚገደብ ተግባር የተወገዘ ነው፤ የኢትዮጵያ መንግስት በአስቸኳይ ጋዜጠኞቹን ከእስር ሊፈታ ይገባል” ብሏል፡፡ የኦሮሚያ ኒውስ ኔትዎርክ ጋዜጠኞች በቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው የሚገኙትን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራር አቶ አብዲ ረጋሣን ጠይቀው ሲወጡ ‹‹በስልካችሁ ፎቶ አንስታችኋል›› በሚል ከፖሊስ ጋር ንትርክ ውስጥ ከገቡ በኋላ ለእስር መዳረጋቸውን የሲፒጄ ሪፖርት ያስረዳል፡፡ በጉዳዩ ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻን ለማነጋገር መሞከሩንም ገልፆ፣ ሆኖም ሃላፊው ስለጉዳዩ መረጃ እንደሌላቸው እንደገለፁለት ተቋሙ አስታውቋል፡፡  

Read 1081 times