Saturday, 21 March 2020 12:27

የዶ/ር ካትሪን 60 ዓመታት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

     እ.ኤ.አ ጥር 24 1924 ዓ.ም በአውስትራሊያ ከሲዲኒ ወጣ ባለች መንደር ተወለዱ፡፡ በተወለዱበት መንደር ተማሩ፣ ዩኒቨርሲቲ ገብተውም በሕክምና ሳይንስ ተመረቁ፡፡
በ1946 እ.ኤ.አ ከዩኒቨርሲቲ በሕክምና እንደተመረቁም በትውልድ አገራቸው አውስትራሊያ በሕክምና እስከ 1958 እ.ኤ.አ አገልግለዋል - ዶ/ር ካትሪን ግምሊን፡፡
እ.ኤ.አ በ1958 የኢትዮጵያ መንግሥት አዋላጅ ነርሶችን በልዕልተ ፀሐይ ሆስፒታል ለመቅጠር ያወጣውን አለማቀፍ ማስታወቂያ ሰምተው ወደ አዲስ አበባ መጥተው ፈተናውን አልፈው እዚሁ የቀሩት ዶ/ር ካትሪን ሃምሊን ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ላለፉት 60 ዓመታት ኢትዮጵያውያንን በፍፁም ትጋትና ቅንነት አክመዋል፤ የሴቶችን ስቃይ የቀነሱ ሁነኛ ሆስፒታል ገንብተዋል፤ የፌስቱላ ሕመም ሕክምናን በኢትዮጵያ አስተዋውቀዋል፤ ሺዎችን አክመው ከስቃይ አድነዋል፤ ከማህበራዊ መገለል ታድገዋል፡፡
ዶ/ር ካትሪን ሃምሊን ከኒውዚላንዳዊው ባለቤታቸው ዶ/ር ሬጊናልዩ ሃምቢን ጋር በመሆን ከ60 ዓመት በፊት በወጣትነታቸው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ሁለቱም ሕይወታቸውን ለኢትዮጵያውያን ዋጋ ከፍለውበታል፤ ከኢትዮጵያውያን ጋር ሀዘንና ደስታን ተካፍለው ሺዎችን በሕክምና ሙያቸው ረድተው ኖረዋል፡፡
ዶ/ካትሪንና ባለቤታቸው ወደ ኢትዮጵያ በመጡበትና ሥራ በጀመሩበት ወቅት የፌስቱላ ሕመም ተጠቂዎች ኢትዮጵያ ውስጥ መኖራቸውን ተረድተው ሙሉ ጊዜና ጉልበታቸውን እውቀታቸውን ለዚሁ በወቅቱ በዓለም ላይ ጠፍቶ ለነበረው ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የበርካቶች ስቃይ የሆነውን ፌስቱላ በማከም ለራሳቸው ቃል ይገባሉ፡፡
ወዲያውም የፌስቱላ ተጠቂዎች ወደ ማከሙ ፊታቸውን አዞሩ፡፡ ሕክምናውን በተቀጠሩበት ሆስፒታል እየሰጡ ከቆዩ በኋላ እ.ኤ.አ በ1974 ራሱን የቻለ የፌስቱላ ማዕከል የሆነ ሆስፒታል በኢትዮጵያ አቋቋሙ፡፡
ይህ ሆስፒታል በየጊዜው ማስፋፊያዎች እያደረጉ በሚሰጠው ሕክምና እስካሁን ከ45 ሺህ በላይ ሴቶች ከሕመማቸው ተፈውሰውበታል፡፡ በዚህ ተግባር ዶ/ር ካትሪንና ሆስፒታላቸውም በአለም ላይ የታወቁ የፌስቱላ እርዳታ ሰጪ ተቋማት ተብለው ክብርና ሞገስ አግኝተውበታል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በዚህ ተግባራቸው የወደር የለሽ አገልግሎት እውቅና ሰጥቷቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥትም (በዶ/ር ዐቢይ አህመድ የሚመራው) ላበረከቱት ወደር የለሽ አገልግሎት የአገሪቱን ከፍተኛ የክብር ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡
የፌስቱላ ታማሚ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ህመም ሲፈውሱ ለ60 ዓመታት የኖሩት ዶ/ር ካትሪን ሃምሊን የተፈጥሮ ግድ ሆኖ ባሰሩት ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በ96 ዓመታቸው መጋቢት 9 ቀን 2012 ዓ.ም አርፈዋል፡፡  

Read 11664 times