Saturday, 21 March 2020 12:37

ተቃዋሚዎች ‹‹ብልፅግና ፓርቲ›› ከፍተኛ ገንዘብ ማሰባሰቡ ስጋት እንደማይሆንባቸው ገለፁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  ምርጫ ቦርድ ገንዘብ አሠባሰብን በተመለከተ ለፓርቲዎች ግልጽ መመሪያ ማዘጋጀት አለበት

          ብልፅግና ፓርቲ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ራሱን በሃብትና በገንዘብ ማበልፀጉ ስጋት እንደማይሆንባቸው የገለፁ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ የፓርቲው ገንዘብና ድጋፍ የማሰባሰብ ሂደት የምርጫውን ውጤት እንደማይወስነው ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 5 ቀን 2012 በሚሊኒየም አዳራሽ ብልፅግና ባካሄደው የሀብት ማሰባሰብ እንቅስቃሴ፤ 1.5 ቢሊዮን ብር ከባለሀብት ደጋፊዎች ማግኘቱን ፓርቲው ያስታወቀ ሲሆን ከ2ሺህ በላይ ግመሎች፣ ሰንጋዎችና ፍየሎችም ማሰባሰብ መቻሉን አስታውቋል፡፡
ፓርቲው ያሰባሰበውን ሃብት ለቀጣይ ምርጫ ቅስቀሳ ማካሄጃ ያውለዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በዕለቱ ከተሰበሰበው ገንዘብ 100 ሚሊዮን ብር ያህሉን ለኮሮና መከላከያ ማበርከቱን መግለፁ አይዘነጋም፡፡
ከወራት በፊት በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል ባዘጋጀው የራት ፕሮግራም ፓርቲያቸው ጠቀም ያለ ሀብት  ማሰባሰቡን የገለፁት የኢዜማ የሕዝብ ግንኙት ሃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ፤  እንዲህ ያሉ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች ለፓርቲዎች የምርጫ እንቅስቃሴ በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የገንዘብ ማሰባሰብ ሂደት ግን ዜጎች ኋላ ችግር ይገጥመናል ከሚል ስጋት ወጥተው  በነፃነት ያበረከቱት መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል አቶ ናትናኤል፡፡
ዜጎች በተፅዕኖ ጫና ገንዘባቸውን የሚሰጡ ከሆነ ግን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት አያስችልም፣ በዚህ ረገድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለፓርቲያቸው ድጋፍ የሚያሰባስቡበት መንገድ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፤ ድርጊቱም መቆም አለበት ብለዋል፡፡
ብሄራዊ ምርጫ ቦርድም ገንዘብ ማሰባሰብን በተመለከተ ግልጽ መመሪያ ማዘጋጀት እንዳለበት አቶ ናትናኤል ገልፀዋል፡፡ የብልፅግና ፓርቲ ሀብት ምናልባት ለሕዝቡ ሃሳብን ለማድረስ አቅም ሊሆነው ይችላል፤ ነገር ግን የምርጫውን ውጤት ከወዲሁ የሚወስን አይሆንም ሲሉም አስረድተዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የኦፌኮ፣ መኢአድና ኢዴፓ አመራሮችም የኢዜማን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ እስካሁን የተጠናከረ የገንዘብ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ አለማከናወናቸውን የገለፁት ፓርቲዎቹ፤ ምርጫው ላይ ገንዘብ ጉልበት ቢኖረውም የምርጫውን ውጤት ለህዝብ የማቅረብ የፖለቲካ ፕሮግራም ሀሳብ እንደሚወስነው ተናግረዋል፡፡   


Read 11940 times