Saturday, 21 March 2020 12:47

አለም በኮሮና ሳቢያ ቀውስ ውስጥ ገብታለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 አለም በቅርብ ዘመናት ታሪኳ ገጥሟት በማያውቀው “ኮሮና” የተሰኘ አስከፊ የጥፋት ማዕበል መመታቷን፣ ነጋ ጠባ ከዳር እስከ ዳር በሚያጥለቀልቃትና ልትገታው አቅም ባጣችለት ገዳይ ወረርሽኝ ክፉኛ መፈተኗን ቀጥላለች፡፡
ከቻይና የተነሳውና ቀስ በቀስ መላውን አለም ማዳረሱን የቀጠለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፤ ቀናት አልፈው ቀናት ቢተኩም፣ ሳምንታት ቢፈራረቁም ይህ ነው የሚባል ልጓም ሳይገኝለት በፍጥነት መስፋፋቱንና በርካቶችን መቅሰፉን ተያይዞታል፡፡
አሁን ኮሮና የጤና ጉዳይ ከመሆን አልፎ የሰውን ልጅ በህልውና ስጋት ውስጥ የከተተ፣ መንግስታት፣ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጡት አንገብጋቢ ጥያቄ ሆኖ እረፍት የነሳ፣ መላውን አለም ክፉኛ እየፈተነ የሚገኝ የጤናም፣ የኢኮኖሚም፣ የፖለቲካም፣ የሁሉም ነገር ጉዳይ ሆኗል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ኮሮና ቫይረስ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ በአለም ዙሪያ በሚገኙ 176 አገራትና ግዛቶች ውስጥ ከ230 ሺህ 715 በላይ ሰዎችን ያጠቃ ሲሆን፣ ከ9 ሺህ 390 በላይ የሚሆኑትንም ለህልፈተ ህይወት ደርጓል፡፡
ቫይረሱ የተቀሰቀሰባት ቻይና እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ 80 ሺህ 928 ያህል ዜጎቿ በኮሮና የተጠቁባት ሲሆን ከ3 ሺህ 245 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ለሞት ተዳርገውባታል፡፡
በአውሮፓ ኮሮና እጅግ ከፍተኛውን ጥፋት ባደረሰባት ጣሊያን፣ 35 ሺህ 713 ሰዎች ተጠቅተው፣ 2 ሺህ 978 ሰዎች ሲሞቱ፣ በኢራን 18 ሺህ 407 ሰዎች ተጠቅተው፣ 1 ሺህ 284 ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የከፋው ጥፋት የሚጠብቃት አፍሪካ
የአለም የጤና ድርጅት በሳምንቱ መጨረሻ ባወጣው መግለጫ፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተቀረው አለም በባሰ መልኩ በአፍሪካ አገራት ላይ የከፋ ጥፋት ያስከትላል ተብሎ እንደሚጠበቅ በመጠቆም፣ አገራቱ በከፍተኛ ቁርጠኝነት ቫይረሱን ለመዋጋት እንዲነሱ አስጠንቅቋል፡፡
ከእስያና ከአውሮፓ ጋር ሲነጻጸር በአፍሪካ ቀሰስተኛ ስርጭት እንዳለው የተነገረለት ኮሮና፤ እስከ ትናንት በስቲያ በ34 የአፍሪካ አገራት ከ600 በላይ ሰዎችን ማጥቃቱንና 17 ሰዎችን መግደሉን የዘገበው ሮይተርስ፣ በሲዲሲ የአፍሪካ ሃላፊ ጆን ኬንጋሶን ግን የኮሮና ምርመራን ለማምለጥ የሚደበቁና የሚሸሹ አፍሪካውያን ቁጥር እየተበራከተ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ፣ አህጉሪቱ የከፋውን ጥፋት ታስተናግዳለች ብለው እንደሚሰጉ መናገራቸውን ገልጧል::
በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ከተጠቁባቸው አገራት መካከል በግብጽ 196፣ በደቡብ አፍሪካ 116፣ በአልጀሪያ 72 መጠቃታቸውን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል::

ሃኪሞች እና ኮሮና
በጣሊያን ወረርሽኙን ለመከላከልና ዜጎችን ከሞት ለመታደግ ደፋ ቀና ሲሉ በቫይረሱ የሚያዙ ሃኪሞች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት በእጅጉ እየጨመረ መሆኑንና እስካሁንም ከ2 ሺህ 629 በላይ የአገሪቱ ሃኪሞች በቫይረሱ መያዛቸውን አልጀዚራ ዘግቧል:: የአሜሪካ ሜዲካል አሶሴሽን በበኩሉ በቻይና በኮሮና ቫይረስ ከተጠቁት ሰዎች መካከል 3.8 በመቶ የሚሆኑት የህክምና ባለሙያዎች መሆናቸውን ሰሞኑን ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በቡልጋሪያ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁስና የህክምና መሳሪያዎች ሳይሟሉልን የኮሮና ህክምና እንድንሰጥ ተገድደናል ያሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው የህክምና ዶክተሮችና የጤና ባለሙያዎች በገዛ ፈቃዳቸው ስራቸውን መልቀቃቸው ተዘግቧል፡፡

መንግስታት በገፍ በጀት እየመደቡ ነው
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢኮኖሚውን ለመደገፍ 1 ትሪሊዮን ዶላር መመደባቸው የተነገረ ሲሆን፣ የካናዳ መንግስት በኮሮና ለተጎዱ ቤተሰቦችና የንግድ ተቋማት የ18.6 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን ባለፈው ረቡዕ ይፋ አድርጓል፡፡
እንግሊዝ በኮሮና ሳቢያ ለኪሳራ የመዳረግ አደጋ ያንዣበበባቸውን የንግድ ኩባንያዎች ለመታደግ 400 ቢሊዮን ዶላር የመደበች ሲሆን፣ ጀርመን በበኩሏ፤ አነስተኛ ነጋዴዎችን ለመደገፍና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት የሚውል 40 ቢሊዮን ዩሮ መመደቧን አስታውቀዋለች፡፡
ኢኮኖሚያቸውን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ሊከሰት ከሚችል ቀውስ ለመታደግ ከፍተኛ ድጎማና በጀት ከመደቡ የአለማችን አገራት መካከል 56 ቢሊዮን ዶላር የመደበቺው አውስትራሊያ አንዷ ስትሆን የደቡብ ኮርያው ፕሬዚደንት ሙን ጄ ኢን በበኩላቸው፤ ለተመሳሳይ ተግባር 39 ቢሊዮን ዶላር መመደባቸውን ከትናንት በስቲያ አስታውቀዋል፡፡

ጭር ያሉ ከተሞች
ባለፈው ረቡዕ ብቻ በአንድ ቀን 475 ሰዎች በኮሮና የተጠቁባትና አስከሬን በወጉ ለመቅበር የማይቻልበት ሁኔታ ላይ የደረሰችው ጣሊያን፤ ለአንድ ሳምንት የቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላልተወሰነ ጊዜ ለማራዘም ማሰቧን የዘገበው ቢቢሲ፣ በየቤታቸው ተዘግተው የሰነበቱ ዜጎች በቤታቸው መቆየታቸው የአገሪቱ ከተሞችም ጭው ጭር ብለው መቀጠላቸው እንደማይቀር አመልክቷል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በመላ አገሪቱ መደበኛ እንቅስቃሴዎች ለ15 ቀናት ያህል እንዲቋረጡ ያደረገው የፈረንሳይ መንግስት፣ ቀነ ገደቡን ሊያራዝም እንደሚችል መግለጹ ተነግሯል፡፡
የመሬት ውስጥ ባቡር አገልግሎትን ያቋረጠችው የእንግሊዟ መዲና ለንደን ከትናንት ጀምሮ ትምህርት ቤቶችን የዘጋች ሲሆን፣ ከሞላ ጎደል የዘጋችው ጀርመንም፤ ሆቴሎችን እና የህዝብ መሰብሰቢያ አዳራሾችን የኮሮና ታማሚዎችን ማከሚያ ሆስፒታል አድርጋ ለመጠቀም ማሰቧ ተነግሯል፡፡

የከፋ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ
የኮሮና ቫይረስ በአለማቀፍ ደረጃ ሊያስከትለው የሚችለው ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ እንደሚሆንና አጠቃላዩ አለማቀፍ ምርት በ30 በመቶ ያህል ሊቀንስ እንደሚችል መነገሩን የዘገበው ብሉምበርግ፣ አለም 26 ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ የኢኮኖሚ ማነቃቂያ በጀት እንደሚያስፈልጋት ገልጧል፡፡
ጄ ፒ ሞርጋን የተባለው ተቋም ኢኮኖሚስቶች ያወጡትን ጥናት ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው፤ ኮሮና ቫይረስ የቻይናን የሩብ አመት ኢኮኖሚ በ40 በመቶ፣ የአሜሪካን የቀጣዩ አመት ኢኮኖሚ ደግሞ በ14 በመቶ ይቀንሰዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ባንኮች በከፋ የፋይናንስ እጥረት ውስጥ እንደገቡ የተነገረ ሲሆን፣ የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪውም የከፋ ቀውስ ያጋጥማቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ ዘርፎች አንዱ መሆኑን ከሰሞኑ የወጡ ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡ በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ስራቸውን ያቋረጡት ታዋቂዎቹ የመኪና አምራቾች ቶዮታ፣ ኒሳን ሞተርስና ሆንዳ ሞተርስ በተናጠል በሳምንቱ መጀመሪያ በሰጡት መግለጫ፤ በሰሜን አሜሪካ ፋብሪካዎቻቸውን ለተወሰነ ጊዜ እንደሚዘጉ ያስታወቁ ሲሆን፣ ፎርድ፣ ጄኔራል ሞተርስና ፊያት በበኩላቸው፤ በአሜሪካ የሚገኙ መገጣጠሚያዎቻቸውን እንዲሁም በካናዳና በሜክሲኮ ያሏቸውን ፋብሪካዎች እንደሚዘጉ አስታውቀዋል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው የአክሲዮን ገበያ ቀውስ ሳቢያ ባለፈው የካቲት ወር ብቻ የአለማችን 20 እጅግ ባለጸጋ ቢሊየነሮች ሃብት በድምሩ በ293 ቢሊዮን ዶላር መቀነሱን ፎርብስ መጽሄት ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡
በአውሮፓና አሜሪካ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ከፍተኛ በተባለ መጠን ፋብሪካዎች መዘጋታቸውን የዘገበው ብሉምበርግ፣ ኩባንያዎች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ምርታቸውን ማቋረጣቸውንና ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጋቸውን አመልክቷል፡፡

ኮሮና ወደ ቻይና ዞሮ እየገባ ነው
ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተቀሰቀሰባትና የዚህ ሁሉ መነሻ በሆነችው የቻይናዋ ዉሃን ግዛት፣ ኮሮና ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ከትናንት በስቲያ አንድም ሰው በቫይረሱ አለመያዙ ይፋ ቢደረግም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከወራት እልህ አስጨራሽ ትግልና ርብርብ በኋላ የወረርሽኙን ስርጭት በመግታት ረገድ ተጨባጭ ስኬት ማስመዝገቧ በሚነገርላት ቻይና ርዕሰ መዲና ቤጂንግ፤ ባለፈው ረቡዕ ከሌላ አገራት ቫይረሱን ይዘው የመጡ 21 ሰዎች መገኘታቸውንና አገሪቱ ሌላ ፈተና እንደተደቀነባት ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
 
ባለጸጎች እጃቸውን እየዘረጉ ነው
የኮሮና ወረርሽኝ ተስፋፍቶ መቀጠሉን ተከትሎ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ወረርሽኙን ለመግታትና ለተለያዩ የምርምርና የህክምና ስራዎች የገንዘብና የሌሎች ድጋፎችን የሚያደርጉ  ባለጸጎች ቁጥር መጨመሩን ፎርብስ መጽሄት ዘግቧል፡፡
የቅንጦት ዕቃዎች አምራች ኩባንያ ባለቤት የሆኑት በርናርድ አርኖልት፣ 3 የሽቶ አምራች ፋብሪካዎቻቸው መደበኛ ስራቸውን አቋርጠው የቫይረስ መከላከያ ኬሜካል በማምረት በነጻ እንዲያከፋፍሉ ያደረጉ ሲሆን፣ የሚዲያው ዘርፍ ቢሊየነር ማይክል ብሉምበርግ በበኩላቸው፤ ወረርሽኙን ለመግታት የሚውል የ40 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የማይክሮሶፍቱ መስራች አሜሪካዊው ቢሊየነር ቢል ጌትስ በፋውንዴሽናቸው በኩል 100 ሚሊዮን ዶላር ያበረከቱ ሲሆን፣ ሌላው የቴክኖሎጂው ዘርፍ ባለጸጋ ማይክል ዴል ደግሞ ለኮሮና ህክምና ቁሳቁስ መግዣ የ284 ሺህ ዶላር ልገሳ ማድረጋቸው ተዘግቧል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ፣. በገንዘብና በአይነት እጅግ ከፍተኛ ድጋፍ ካደረጉ ሌሎች የአለማችን ቢሊየነሮች መካከልም 14 ሚሊዮን ዶላር የለገሱትና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቁሳቁሶችን ለመስጠት ቃል የገቡት የቻይናው አሊባባ ኩባንያ መስራች ጃክ ማ፣ 100 ሚሊዮን ዶላር የለገሰው የፌስቡኩ ማርክ ዙክበርግ ይገኙበታል፡፡

25 ሚሊዮን ሰዎች ከስራ ሊፈናቀሉ ይችላሉ
አለማቀፉ የሰራተኞች ድርጅት አይኤልኦ ባለፈው ረቡዕ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚለው፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አንዳች መላ ካልተገኘለት በቀር በመላው አለም 25 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ከስራ ገበታቸው ሊያፈናቅል ይችላል ተብሎ ይሰጋል፡፡
የአለማችን ሰራተኞች በኮሮና ሳቢያ ገቢያቸው በድምሩ 3.4 ትሪሊዮን ዶላር ያህል ሊቀንስ እንደሚችል የጠቆመው የተቋሙ መረጃ፣ መንግስታትና ተቋማት ቫይረሱ በሰራተኞች ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት ለመቀነስ መስራት እንዳለባቸው አመልክቷል፡፡

በቻይና ፍቺ ጨምሯል
በቻይና ከኮሮና ስጋት ጋር በተያያዘ ዜጎች እንቅስቃሴያቸውን ገትተው በቤታቸው ለረጅም ቀናት እንዲቆዩ የሚያስገድድ መመሪያ መውጣቱን ተከትሎ፣ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የፍቺ ጥያቄ የሚያቀርቡ ባለትዳሮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ የተነገረ ሲሆን፣ ይህም የመጣው ባለትዳሮች ለተራዘመ ጊዜ አብረው ሲቆዩ በመሰለቻቸታቸው ወይም ግጭቶች በመፈጠራቸው ሳቢያ ሊሆን እንደሚችል ተዘግቧል፡፡
በደቡብ ምዕራባዊቷ የቻይና ዳዙ ግዛት ባለፉት ሶስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ300 በላይ ጥንዶች ትዳራቸውን በፍቺ ለማፍረስ ለሚመለከተው የመንግስት አካል ጥያቄ ማቅረባቸውንና ይህም ከኮሮና በፊት ከነበረው በእጅጉ እንደሚበልጥ የዘገበው ዘ ቴሌግራም፣ የግዛቲቷ ባለስልጣናትም በተለይ ወጣት ባለትዳሮች ከትዳር አጋራቸው ጋር ለረጅም ጊዜ በአንድ ላይ ሲቆዩ የመሰላቸትና ጸብ የመቀስቀስ ዕድላቸው ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ሊሆን መቻሉን እንደተናገሩ አመልክቷል፡፡
ሻንዚ በተባለችው ሌላ የአገሪቱ ግዛት በሚገኝ ከተማ ውስጥም በአንድ ቀን ብቻ 14 ባለትዳሮች የፍቺ ጥያቄ ይዘው መምጣታቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

በኮሮና የተጠቁ ፖለቲከኞችና ዝነኞች
ከሰሞኑ በኮሮና ቫይረስ ከተጠቁ የአለማችን ታዋቂ ፖለቲከኞችና ዝነኞች መካከል በአውሮፓ ህብረት ዋና የብሬግዚት አደራዳሪ የሆኑት ሚሼል ባርኒየር አንዱ መሆናቸው ተዘግቧል:: የብራዚል የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትር ቤኔቶ አልቢኩሪ፣ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ኦግስቶ ሄሌኖ፣ በጀርመን የእስራኤል አምባሳደር ጄርሚ ኢሳካሮፍ፣ የአውስትራሊያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፒተር ዱቶን፣ የፈረንሳይ የባህል ሚኒስትር ፍራንክ ሬስተር እና የፖላንድ የአካባቢ ሚኒስትር ሚካል ዎስ በሳምንቱ በኮሮና ከተያዙ ፖለቲከኞች መካከል ይገኙበታል፡፡
ታዋቂው የአፍሮ ጃዝ ድምጻዊና የሳክስፎን ተጫዋች ማኑ ዲባንጎ በኮሮና ተይዞ ባለፈው ረቡዕ ፈረንሳይ ውስጥ ወደሚገኝ ሆስፒታል መግባቱ የተነገረ ሲሆን፣ በተለያዩ አገራት በስፖርቱ ዘርፍ የሚታወቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዝነኞችም በኮሮና መጠቃታቸው ተዘግቧል፡፡
ከዚህ ቀደም በቫይረሱ ከተያዙ ዝነኞች መካከል የሆሊውዱ የፊልም አክተር ቶም ሃንክስና ባለቤቱ፣ የፊልም ተዋናይትና ድምጻዊት ሪታ ዊልሰን፣ እንግሊዛዊው የፊልም ተዋናይና ድምጻዊ ኢድሪስ ኢባ እና የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዱ ባለቤት ሶፊ ግሪጎሪ ትሩዱ ይገኙበታል፡፡

Read 14084 times