Saturday, 21 March 2020 12:44

ጋዜጠኞች፤ ሙያችሁን ለማስከበር በራሳችሁ ላይ ዝመቱ!

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(0 votes)

  በዚህ ርእስ አማካይነት ሦስት መሰረታዊ ጉዳዮችን ለማንሳት አሰብኩ፡፡ የመጀመሪያው ጉዳይ ስለ ጋዜጠኛነት ምንነት (ትርጉም) እና ስለ ጋዜጦች ህትመት፣ ስለ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥንና ዲጂታል ሚዲያ ታሪካዊ ሂደት በአጭር በአጭሩ ለማቅረብ ጥረት አደርጋለሁ፡፡ በሁለተኛው፤ በሀገራችን ስለ እነዚህ ሚዲያዎች አጀማመርና አሁን እስካለው ሁኔታ ያሉኝን መረጃዎች ለማካፈል እሞክራለሁ፡፡ በመጨረሻም፤ ሦስተኛው ጉዳይ ስለ ጋዜጠኛነት የስነ ምግባር መርሆዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ካነሳሁ በኋላ በሀገራችን ያስተዋልኳቸውን ሁኔታዎች በማመላከት አጠቃልላለሁ:: በዚሁ መሰረት በዛሬዋ መጣጥፍ ስለ ጋዜጠኛነት ምንነት (ትርጉም) እና ስለ ጋዜጦች ህትመት አጀማመር፣ ስለ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥንና ዲጂታል ሚዲያ ታሪካዊ ሂደት በአጭር  ለማቅረብ ጥረት አደርጋለሁ፡፡
ከትርጉሙ እንጀምር፡፡ “ጋዜጠኛ ማለት መረጃዎችን የሚሰበስብ፣ የሚጽፍና በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች የሚያሰራጭ ሰው ነው” ይላል በዊኪፔዲያ ላይ ያገኘሁት ብያኔ (definition)፡፡ በሌላ ሰነድ ላይ ደግሞ “ጋዜጠኛነት ማለት በተጨባጭ የተፈጸመን ድርጊት፣ በጽሁፍ በማሰናዳት፣ ለህዝብ መንገር ማለት ነው” ካለ በኋላ፤ “ይህንን ስራ የሚያከናውኑ ሰዎች ደግሞ ‘ጋዜጠኛ’ ይባላሉ፡፡ የሥራ ቦታቸው በጋዜጣ፣ በመጽሄት፣ በዌብሳይት ዝግጅት ክፍል ወይም በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ጣቢያ ሊሆን ይችላል” በማለት የስራ ቦታቸውን ጭምር ያስረዳል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ትርጓሜዎች በመነሳት ጋዜጠኛ በሚያቀርበው መረጃ ህብረተሰብን ያስተምራል፣ ያነቃል፣ ያስታውሳል፣ ያስጠነቅቃል፣ ያርማል፣… ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ጋዜጠኞች ብዙውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ባለሙያዎችን በማነጋገር፣ የመረጃ ምንጮችን በማሰስ፣ ሰነዶችን በመፈተሽ፣ አንዳንድ ጊዜ እስፍራው ድረስ ሄዶ ቀጥተኛ ዘገባዎችን በማቅረብ ነው::ከዚህ በተጨማሪ ጋዜጠኞች ያገኙትን መረጃ ይተነትናሉ፡፡ ምርቱን ከግርዱ ይለያሉ፡፡ ጥሩውን ከመጥፎው ያነጻጽራሉ:: የሚጠቅመውን ከማይጠቅመው ያገናዝባሉ:: ይህንን ስራ ጥራት ባለውና አስተማማኝ በሆነ መልኩ ለመተንተን ጋዜጠኛ ምንጊዜም ያነባል፡፡ ከወቅቱ ጋር ራሱን ያበቃል፡፡
ጋዜጠኛ የሚሰራው ስራ ከሰዎች የእለት ከእለት ስራዎችና ውሳኔዎች ጋር በቀጥታም በተዘዋዋሪም የተያያዘ ነው፡፡ ስለሆነም፤ ጋዜጠኛ ስራውን ሲሰራ ከወገንተኛነት በራቀ መንፈስ ማከናወን እንዳለበት ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ “ወገንተኛነት” እንዳይኖር ከሚደረግባቸው መንገዶች አንዱ ቃለ መሀላ መፈጸም ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የህክምና ዶክተሮችና የህግ ባለሙያዎች ከተማሩበት ተቋም ሲመረቁ ቃለ ምህላ ይፈጽማሉ፡፡ እና… ጋዜጠኛስ ቃለ መሐላ ይፈጽማል? በአንዳንድ ሀገሮች ጋዜጠኞች ቃለ መሀላ እንደሚፈጽሙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ እኔ ያገኘሁት የጋዜጠኛ ቃለ መሐላ እንዲህ የሚል ነው… “በጋዜጠኛነት ሙያ አምናለሁ… ጋዜጠኛ እውነት ነው ብሎ በልቡ ያመነውንና የተቀበለውን ብቻ መጻፍ እንደሚገባው አምናለሁ፡፡ ለህዝብ ሰላምና ደህንነት ሲባል ካልሆነ በስተቀር ዜናን ማፈን ተገቢ አይደለም፣ ሊከለከል አይገባም ብዬ አምናለሁ…” በእኛስ ሀገር ብንሞክረው ምናለበት? ወደ ሌላ ጉዳይ ልለፍ፡፡
ጋዜጠኛነት በጥንት ዘመን
ጋዜጠኛነት “በዚህ ዓመት፣ በዚህ ስፍራ፣ በዚህ ሀገር ተጀመረ” የሚል ቁርጥ ያለ ጊዜ ማስቀመጥ አስቸጋሪ ነው:: የህትመት ዘገባዎች ለህዝብ መሰራጨት የጀመሩት በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ለምሳሌ በቻይና የሀን ስርወ መንግስት በነበረበት ዘመን፤ ወቅትን ጠብቀው የሚወጡ የዜና መጽሔቶች (news bulletins) ይታተሙ እንደነበርም በመስኩ ከተደረጉ ጥናቶች መገንዘብ ይቻላል፡፡ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በቬኒስ ሪፑብሊክ ተመሳሳይ ቅርጽ ያላቸው ህትመቶች እንደነበሩም የታሪክ ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡ እነዚያ ህትመቶች ግን ለመንግስት ባለስልጣናት ብቻ የሚቀርቡ እንጂ ለህዝብ የሚቀርቡ አልነበሩም፡፡ በነዚያ ህትመቶች ላይ ይቀርቡ የነበሩት ዘገባዎች፣ በዚህ ዘመን ያለው የጋዜጠኛ ዜና ዘገባዎች ዓይነት አልነበሩም፡፡
የህትመት መሣሪያዎች ቴክኖሎጂ እያደገ፤ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ፤ ዜና ይዘው የሚወጡ ጋዜጦች ህትመት በስፋት መከናወን መጀመሩም ይነገራል፡፡ የመጀመሪያው በግል ድርጅት የሚታተም ጋዜጣ በቻይና በሚንግ ስርወ መንግስት፤ እ.ኤ.አ በ1582 እንደታተመ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በአውሮፓ የመጀመሪያው ጋዜጣ ተደርጎ የሚወሰደው እ.ኤ.አ በ1605 በስትራስበርግ (ጀርመን) ጆን ካርሎስ በተባለ ሰው አዘጋጅነት “Relation aller Fürnemmen und gedenckwürdigen Historien” ተብሎ የታተመው እንደሆነ ይነገራል፡፡ “Daily Courant” በሚል ርእስ የእንግሊዝኛ እለታዊ ጋዜጣ እ.ኤ.አ ከ1702-1735 ድረስ ባልተቋረጠ ሁኔታ የታተመ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በእንግሊዝ ሀገር የጋዜጠኛነት ሙያ እየተጠናከረ መምጣቱ ይታወቃል፡፡
ከላይ በተጠቀሱት ዘመናት የሮማ ኢምፓየር፣ የእንግሊዝ ኢምፓየርና እንደ ፈረንሳይና ፕሩሲያን የመሳሰሉ ሀገሮች ጋዜጦችን ጠንከር ብለው መቆጣጠር መጀመራቸውም ይነገራል፡፡ በእነዚህ ሀገሮች ጋዜጦች የመንግስት የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ሆነው እንዲያገለግሉ ጠበቅ ያለ የቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) ሥራ ይከናወኑ ነበር፡፡ እንደ ሩሲያ ኢምፓየር ያሉ ሌሎች ሀገሮች ደግሞ እስከ 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ የጋዜጠኛ ዘገባዎች እንዳይታተሙ እገዳ ጥለው ነበር፡፡ በዚያ ወቅት የጋዜጦች ህትመትና ስርጭት የንግድ ማእከላት በነበሩት እንደ ለንደን፣ አምስተርዳምና በርሊንን በመሳሰሉ ከተሞች ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡
የዜና ዘገባ እና የ18ኛውና የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አብዮቶች
በ18ኛውና በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተለያዩ ሀገሮች የተቀሰቀሱ ህዝባዊ ንቅናቄዎችን በማጋጋልና በማጠናከር ረገድ ጋዜጦች የጎላ ሚና ተጫውተዋል፡፡ እንደ ቶማስ ፔን ያሉ ጸሐፊዎች፤ የአሜሪካ ቅኝ ገዢ በነበረቺው እንግሊዝ ላይ የቅስቀሳ ጽሁፎችን ያሰራጩ ነበር፡፡ ለቅኝ ገዢዋ እንግሊዝ ወገንተኛ የሆኑ ጸሐፍት ደግሞ በአሜሪካውያን የተጀመረውን አብዮታዊ ንቅናቄ በመቃወም ይጽፉ ነበር፡፡ በዣን ፖል ማሬት (Jean-Paul Marat) አዘጋጅነት፤ “ለ’ሚ ዱ ፑፕል” (L’Ami du peuple) በሚል ርእስ ይታተም የነበረው የፖለቲካ ጋዜጣ፤ ለፈረንሳይ አብዮት መጋጋልና ዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል በመቀስቀስ ትልቅ አስተዋጽዖ ነበረው፡፡ በዚህም ምክንያት ናፖሊዎን እ.ኤ.አ 1800 የሳንሱር ህግ እንዲያወጣ አድርጎታል፡፡ ከናፖሊዎን ህልፈት በኋላ የህትመት ሚዲያው እንደገና ገንኖ በመውጣት የፈረንሳይን የፖለቲካ ባህል በመገንባት ጠቃሚ ሚና ተጫውቷል:: እ.ኤ.አ በ1848 በመሀከለኛው የአውሮፓ ሀገራት ከአሪስቶክራቲክ መንግስታት ጋር የተደረገውን አብዮታዊ የነጻነት ትግል  ያቀጣጠሉትም በወቅቱ የነበሩ ጋዜጦች ነበሩ፡፡ አንዳንድ የህትመት ውጤቶች ደግሞ ለዘብተኛ አቋምን ያራምዱ ነበር:: ሌሎች የግራ፣ የሶሻሊስትና የኮሙኒስት ርእዮተ ዓለምን የሚያራምዱ ጋዜጦች፣ በየሀገሩ መንግስታት መጠነ ሰፊ ተጽእኖ ቢደረግባቸውም በፈረንሳይ፣ በሩሲያና በጀርመን በርካታ ተከታዮች ነበሯቸው፡፡
ወደ 20ኛው ክፍለ ዘመን እንሻገር:: በ20ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ የነበረውን ሁኔታ ስንቃኝ ለምሳሌ በቻይና እ.ኤ.አ ከ1910 በፊት በነበሩት ዓመታት ጋዜጠኛነት ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ያገለግል ነበር ተብሎ ይታመናል፡፡ እ.ኤ.አ በ1911 የቻይና ንጉሳዊ ስርዓት ሲገረሰስ፣ የቻይና ብሄርተኛነት መንፈስ ተናወጠ:: ሳንሱር እንዲቆም፣ የጋዜጠኛነት ሙያ እንዲከበር በመላ ሀገሪቱ ንቅናቄ ተቀጣጠለ:: እ.ኤ.አ በ1920ዎቹ መጨረሻ ጋዜጦች በማስታወቂያ ስራና በህትመት ስርጭት ላይ ትኩረት ያደረገ ስራ ይሰሩ ጀመር፡፡ በወቅቱ ጋዜጦቹ ፖለቲካዊ የቅስቀሳ ጋዜጠኛነትን (advocacy journalism) በጥቂቱ ያካሄዱ ቢሆንም በዚያ ወቅት የነበሩ አብዮተኞች፤ በነዚያ የጋዜጣ መልእክቶች ግፊት ይበልጥ በመነሳሳት ትግላቸውን ያጧጡፉ ነበር፡፡
በፈረንሳይ ከጦርነቱ በኋላ በፓሪስ ይታተሙ የነበሩ ጋዜጦች የህትመት ቅጂ መጠን በጣም እየቀነሰ የመጣበት ሁኔታ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት እንደ “ፓሪስ ሶር” (Paris Soir) የመሳሰሉ ጋዜጦች ከጦርነቱ በኋላ የፖለቲካ አጀንዳ ሲያጡ ስሜት ቀስቃሽ ዘገባዎችን በማቅረብ የህትመት ቅጂ መጠናቸውን ለመጨመርና ተነባቢ ለመሆን ጥረት አድርገዋል፡፡ እ.ኤ.አ 1939 የዚህ ጋዜጣ የህትመት ቅጂ መጠን 1.7 ሚሊዮን ደርሶ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩ ተወዳዳሪ ጋዜጦች፣ የዚህን ጋዜጣ ግማሽ ያህል ቅጂ ብቻ ያሳትሙ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ1900 በታላቋ ብሪታንያ የነበረው ጋዜጠኛነት ትኩረት ያደረገው ሰፊ ቁጥር ላለው አንባቢ ተደራሽ መሆንን ነበር፡፡ በዚህ ረገድ በተለይም ለወዛደሩ ተደራሽ ለመሆን ችለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የጋዜጦቹ የህትመት ቅጂ ብዛት በማደጉ ከማስታወቂያ የሚያገኙት ገቢያቸውም ሊጨምር ችሏል:: በማስታወቂያዎቹ አማካይነት የሸቀጦችን የሽያጭ ስራ አሳልጠዋል፡፡ ወደ ክፍለ ሀገሮች የሚደረጉ ገበያዎችን አቀላጥፈዋል:: በራሳቸው ገቢ መተዳደር በመቻላቸው ከፓርቲ ቁጥጥር ነፃ ለመሆን ችለዋል፡፡ በዚያ ወቅት ይታተም የነበረው “ዴይሊ ሜይል” (Daily Mail) የተሰኘው ጋዜጣ፤ በህትመት ቅጂ ብዛትና በስርጭት ተደራሽነት በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ አልነበረውም፡፡
በህንድ አገር የመጀመሪያው ጋዜጣ “Hicky’s Bengal Gazette” ተብሎ ይታወቃል፡፡ የመጀመሪያ ህትመቱም እ.ኤ.አ  ጥር 29 ቀን 1780 ገበያ ላይ ውሏል:: ይህ ጋዜጣ ከወጣ በኋላ ሌሎች ጋዜጦች ፈለጉን ተከትለው በእንግሊዝኛ ቋንቋ መታተም ጀምረው እንደነበር የታሪክ ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡ እነዚህ ጋዜጦች ይዘጋጁ የነበሩት በቅኝ ገዢዋ እንግሊዝ ዜጎች ነበር:: እ.ኤ.አ ከ1800ዎቹ ጀምሮ ግን ህንዳውያን ራሳቸው በአሳታሚነት መሳተፍ ጀመሩ:: የህትመቶቹ ትኩረትም በእንግሊዝኛ ተናጋሪ ህንዳውያን ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ትልቁ ችግር የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ነበር፡፡ በዚያ ሰፊ የህንድ ግዛት በርካታ ቋንቋዎች ይነገሩ ስለነበር ብዙሃኑን አንባቢ ለማግኘት ቋንቋ ወሳኝ ሚና ነበረው፡፡ በመጨረሻም እንግሊዝኛ በመላዋ ህንድ የሚነገር ቋንቋ  (linguafranca) በመሆኑ በእንግሊዝኛ ማተም ተመራጭ ሊሆን ቻለ፡፡
ወደ አሜሪካ እንለፍ፡፡ ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ እና የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መግቢያ ጀምሮ በአሜሪካ የመገናኛ ብዙሃን ኢምፓየር ያቆጠቆጠበት ወቅት ነበር፡፡ ዊሊያም ራንዶልፍ እና ጆሴፍ ፑሊዘር የመሳሰሉ ሰዎች የታዳሚዎችን (audience) ቁጥር ለማበራከት ይዘታቸው ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር እንዲኖረው  በማድረግ፣ የጋዜጦችን ህትመት ተቆጣጥረው፣ በማስታወቂያ አማካይነት ገቢያቸውን ለማሳደግ የመስራትን አቅጣጫ ተከትለዋል:: በዚህም መሰረት በተለይም እ.ኤ.አ በ1900 የአሜሪካ ጋዜጦች ከወገንተኛነት ርቀው የፖለቲካን ጉዳይ በጣም በትንሹ ይዘግቡ ጀመር፡፡ በዚያ ዘመን የነበሩ የአሜሪካ ጋዜጦች ጎላ ባሉ ፊደሎች የተጻፉ ስሜት ቀስቃሽ (sensationalized) ዘገባዎችን ቀዳሚ ርእስ አድርገው ይዘግቡ ነበር፡፡ የጋዜጣ ህትመትም ሙያዊ ገጽታን እየተላበሰ በመምጣቱ የስራ ዲሲፕሊን በመፍጠር ረገድ መሻሻሎች መታየታቸው ይነገራል፡፡ በዚያ ዘመን የፕሬስ ነፃነት የህግ ድጋፍ እንዲያገኝ ጥረት በመደረጉ ፕሬዝዳንት ሩዝቬልት የፓናማ ካናልን የሙስና ቅሌት ያጋለጡ ጋዜጦችን ለመክሰስ ያደረጉት ጥረት ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡ በዚያ ወቅት በነበሩ ጋዜጦች ላይ የሚቀርበው ሂስ፤ የሚዲያ ተቋማቱ ባለቤትነት በጥቂት ግለሰቦች የተያዘ በመሆኑ “ወገንተኛ ዘገባዎች ይቀርባሉ፣ የሚዲያ ባለቤቶችን ፍላጎትና ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል፣ ራስን ሳንሱር የማድረግ አሰራርን ይከተላሉ” የሚል ነበር፡፡
በአፍሪካ- አሜሪካውያን ላይ ዓይን ያወጣ አድሎና ማግለል መፈጸሙ፣ አፍሪካ-አሜሪካውያን፣ የራሳቸውን እለታዊና ሳምንታዊ ጋዜጦችን እንዲያትሙና በትልልቅ ከተሞች እንዲያሰራጩ ገፋፋቸው፡፡ በዚህም መሰረት በአሜሪካ በ19ኛው እና በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የጥቁሮች ጋዜጦች መታተም መጀመራቸው ይነገራል፡፡ እነዚያ ጋዜጦች በፖለቲካና በንግድ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አሳታሚዎቹ የጎላ ሚና ነበራቸው፡፡ በዚህ ረገድ የቺካጎ ዲፌንደር (Chicago Defender) አሳታሚ የነበረው ሮበርት ሰንግስቴክ፣ የ-ዘሪችሞንድ ፕላኔት (the Richmond Planet) ኤዲተርና የአፍሮ አሜሪካን ፕሬስ ማህበር ፕሬዝዳንት የነበረው ጆን ሚቼል ጁኔር፣ የቺካጎ ንቦች (Chicago Bee) አሳታሚ የነበረው አንቶኒ ኦቨርተን እና የፔቲስበርግ ኩሪዬር (Pittsburgh Courier) አሳታሚ የነበረው ሮበርት ሊ ቫን ጎላ ብለው የሚጠቀሱ አፍሪካ-አሜሪካውያን ፕሬስ ባለቤቶች ናቸው፡፡
ራዲዮ፣ ቴሌቪዥንና ዘመነ ዲጂታል ሚዲያ
የሬዲዮ ስርጭት ዝነኛነትን እያገኘ የመጣው እ.ኤ.አ ከ1920ዎቹ ጀምሮ ሲሆን ሰፊ የስርጭት ሽፋን ያገኘው ደግሞ እ.ኤ.አ በ1930ዎቹ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የሬዲዮ ስርጭት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ የሚባለው ግን በ2ኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነበር፡፡ በዚያ ወቅት ስለነበረው የጦርነት ሁኔታ የሚሰጡ ጋዜጣዊ መግለጫዎች (newsreels) በሬዲዮ አማካይነት ይዘገቡ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ ከ1940ዎቹ ጀምሮ በአሜሪካ የቴሌቪዥን ስርጭት መጀመሩ ይነገራል፡፡ በዚያ ወቅት ከ10 – 15 ደቂቃ ለሚሆን ጊዜ በየምሽቱ የዜና ፕሮግራም፣ አንድ ወይም ሁለት ጊዜ በቴሌቪዥን ስርጭት ይተላለፍ ነበር፡፡ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት የዜና ዘገባ መቅረብ የጀመረው ደግሞ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ አንስቶ ሲሆን፤ በተለይም የጆን ኤፍ. ኬኔዲን ግድያ በተመለከተ ዘገባዎች በተለያዩ ቻናሎች በቀጥታ ስርጭት መተላለፋቸው ይታወቃል፡፡ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ እና 70ዎቹ ከምሽት ዜናዎች በተጨማሪ፣ ጧት እና ቀትር ላይ የዜና ዘገባዎች መቅረብ ጀምረዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1980 ሲ.ኤን.ኤን (CNN) ተቋቋመ፣ የ24 ሰዓት የዜና ዘገባ ሽፋን መስጠትም ጀመረ፡፡
ባለፉት ሁለት አሰርት ዓመታት የነበረው የጋዜጠኛነት ሚናና ደረጃ እንዲሁም የብዙሃን መገናኛ አውታሮች ያሳለፏቸው የእድገት ሂደቶች፤ ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ማደግና ዜናዎችን በኢንተርኔት ከማሰራጨት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የህትመት ሚዲያን የአጠቃቀም ሁኔታ በእጅጉ ቀይሮታል፡፡ ሰዎች ጋዜጦችን ከማንበብ ይልቅ በዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልኮች አማካይነት ማንበብን የመረጡበት ሁኔታ ታይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት የዜና አውታሮች ዲጂታል ስራ የሚያከናውኑ የስራ ክፍሎቻቸውን ወደ ማጠናከር እንዲያዘነብሉ አድርጓቸዋል:: ይህ ሁኔታ ደግሞ ለህትመት ሚዲያ መክሰርና ለሰራተኞች ቅነሳ በር ከፍቷል፡፡ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎችም ላይ ቀላል የማይባል ጫና መፍጠሩ ተስተውሏል፡፡
ዘመነ ዲጂታል ሌላም ሁኔታ ፈጥሯል:: ይኸውም ተራ ዜጎች ትልቅ ሚና እንዲኖራቸው በር በመክፈቱ በኢንተርኔት አማካይነት ተግባራዊ የሚደረግ “citizen journalism” የሚባል ነገር እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት ፈጣን ዜጎች የሚያገኟቸውን መረጃዎች በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው አማካይነት እየቀረፁና እየቀዱ እንደ ዩትዩብ (YouTube) ባሉ አውታሮች ማሰራጨት ችለዋል፡፡ ዜናዎችን ከነባሮቹ የመረጃ አውታሮች ከመጠበቅ ይልቅ ይፋ ከሆኑም፣ ከማይታወቁ ምንጮችም፣ ዜናዎችን በብሎግና በማህበራዊ ሚዲያ አማካይነት በቀጥታ መስመር (online) ማግኘት የሚቻልበት አማራጭ እውን ሆኗል፡፡
በአጠቃላይ ከላይ በአጭር በአጭሩ የተጠቀሱት መረጃዎች፤ የተለያዩ ሚዲያዎችን አጀማመርና አሁን ያሉበትን ደረጃ የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ አንጋፋው ጋዜጠኛና ደራሲ በዓሉ ግርማ “ጋዜጠኛነት ላብና ደምን ይጠይቃል” ይላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ላብና ደም ሳይሆን ማይክ መጨበጥ ብቻ ሰዎችን ጋዜጠኛ እያደረጋቸው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ላብና ደም ሳይሆን በፌስቡክ ሁለት መስመር ጽሁፍ መጻፍ ብቻ ሰዎችን ጋዜጠኛ እያሰኛቸው ነው፡፡ ላብና ደምን የሚጠይቀው ጋዜጠኛነት፤ በአሁኑ ወቅት እያበበና እየጎመራ ሳይሆን እየሞቱ ካሉት ሙያዎች አንዱ እየሆነ መምጣቱ ይታየኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት በጋዜጠኛና በአስተዋዋቂ፣ በጋዜጠኛና በዲጄ፣ በጋዜጠኛና በስብሰባ አወያይ፣ በጋዜጠኛና በጥያቄና መልስ አቅራቢ፣… መካከል ያለው ልዩነት በግልጽ ተለይቶ ሊታወቅ አልቻለም፡፡ ለዚህ ሁሉ መደበላለቅና ለጋዜጠኛነት ሙያ “መዝቀጥ” ተጠያቂዎቹ፤ እውነተኛዎቹ፣ የሙያው ባለቤት የሆኑት፣ ጋዜጠኞች ራሳቸው ናቸው፡፡
የራሳቸው ሙያ ትቢያ ላይ ወድቆ ማንም ሲጫወትበት እያዩ ዝም ብለው፣ በሌላ ማህበረሰባዊ ህጸጽ ላይ መዝመት፤ በራሳቸው ዓይን ውስጥ ያለን ግንድ ትተው፣ በሌሎች ላይ ያለን ጉድፍ ለመጥረግ ደፋ ቀና ከማለት የዘለለ ትርጉም የለውም፡፡ ለማንኛውም “ጋዜጠኞች ሙያችሁን ለማስከበር በራሳችሁ ላይ ዝመቱ” ያልኩበትን ምክንያት ሳምንት እመለስበታለሁ!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻው: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 1080 times