Sunday, 22 March 2020 00:00

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኖቤል ሽልማትና የዶክትሬት ዲግሪያቸው

Written by  ሀብታሙ ግርማ (ruhe215@gmail.com)
Rate this item
(3 votes)

 የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊና የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መጋቢት 6 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት በሚሊኒየም አዳራሽ በተሰናዳ የብልጽግና ፓርቲ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ ያደረጉት ንግግር  አወዛጋቢ ነበር፡፡ የዚህ ጽኁፍ ጭብጥ ስብዕናን በሚነካ መልኩ በምሁራዊ እሴቶች (virtues of intellect) ጉዳይ ላይ ያነሱትን ዘለፋ አይነት ንግግር መነሻ እና እንድምታዎች መፈተሸ ነው፡፡ አንባቢ እንዲገነዘብልኝ የምፈልገው በጠቅላዩ ንግግር ላይ መልስ ለመስጠት መሞከሬ ጉዳዩ መልስ ለመስጠት የመሚመጥን ሆኖ ሳይሆን ቢያንስ በግሌ ከእርሳቸውና ከአመራራቸው ብዙ በጎ ነገሮች እጠብቅ ስለነበር ነው፡፡ ንግግራቸው የስሜት መጎዳት (ንዴት) የፈጠረብኝ ቢሆንም፣ ይህን መጣጥፍ የማሰናዳቱ መነሻ፣ በሃሳብ ለመሞገት እንጂ  የዶር አብይና ደጋፊዎቻቸውን ስብዕና ለመንካትም አይደለም፡፡ የሃሳብ ሚዛናዊነትን መጠበቅ ሙያዬም ያስገድደኛል፡፡ ከዚህ አንጻር ይህን ጽሑፍ ከማሰናዳቴ በፊት፣ ከብስጭት ስሜት ለመውጣት፣ አንድ ሁለት ቀናት የማገገሚያ ጊዜ መውሰድ ነበረብኝ፡፡ በሀተታዬ እኔ ወደምፈልገው ድምዳሜ ለመድረስ ከመፈለግ አንጻር  ስህተት እንዳልሰራ (fallacy of deductionism ይባላል) ወይም ስሜት-መር ድምዳሜ ላይ ላለመድረስ በተቻለኝ መጠን ተጠንቅቄአለሁ፡፡
ዶ/ር ዐቢይ እንደ አገር መሪና እንደ ፖለቲከኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስልጣን ከጨበጡበት ካለፉት ሁለት አመታት ገደማ ጀምሮ ንግግሮቻቸውን በትኩረት ስከታተል ቆይቻለሁ፡፡ በአብዛኛው የስልጣን ወራቶቻቸው፣ የንግግሮቻቸው ዓላማና ጭብጥ፣ አገራዊ አንድነትን ስለማምጣትና በጽኑ ተሸርሽሮ የነበረውን የመንግስት ቅቡልነት መጎዳት ለመጠገን ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራዊ አንድነትን ዓላማ ባደረጉ  ንግግሮቻቸው፤ ተጨባጭ ሀቆችን፣ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችንና ጽንሰ ሃሳባዊ ፍልስፍናዊ ድጋፎችን በማቅረባቸው፣ በአጭር ጊዜና ውስጥ በህዝብ ልብና አእምሮ እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡  
በመሰረቱ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ንግግር፤ ዓላማውን አገራዊ አንድነትና ህዝባዊ ወንድማማችነት ላይ ካደረገው፣  በቅርጽም ሆነ በአቀራረብ የተለያየ ነው:: በእኔ እምነት ዶ/ር ዐቢይን በፖለቲካዊ ንግግሮቻቸው እምብዛም የምናውቃቸው አይመስለኝም፡፡
በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት ብልጽግና ፓርቲ በያዝነው ዓመት ዕውን መሆኑን ተከትሎ ግን ፖለቲከኛውን ዐቢይን ማየት ጀምረናል፡፡ ባለፉት ሁለት ወራት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተደረጉ ትልልቅ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፎችና ስብሰባዎች ላይ ንግግር አቅርበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖለቲካ ገበያችንን ለማስተካከል የሚያደርጉትን ጥረት፤ የዚህ ትውልድ ትልቅ ፕሮጀክት የመሰረት ድንጋይ እንደሆነ ይሰማኛል:: ለዚህ መሳካትም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት እላለሁ፡፡ ነገር ግን በቅዳሜው ንግግራቸው ራሳቸው ዶ/ር ዐቢይ፣ ወደ ብሽሽቅ ፖለቲካ እየተንደረደሩ እንደሆነ ተሰምቶኛል፡፡
የዶ/ር አብይ ንግግር አንድምታ ምንድነው?
ለብልጽግና ፓርቲ ገቢ ማሰባሰቢያ በተዘጋጀው መድረክ፤ የፓርቲው ሊቀ መንበር ዶ/ር አብይ፣ ምስጋና ለማቅረብ ወደ መድረኩ የወጡ ቢመስልም፣ ባለሃብቶችን ማወደስና ምሁራንን መውቀስ ለምን እንደፈለጉ አላውቅም:: ፖለቲካዊ አላማ አለው እንዳይባል፣ የፖለቲካ ድጋፍ መሰረታቸው ነጋዴው ማህበረሰብ ሰለመሆኑ ብዙም አናውቅም::
በመሰረቱ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ፤ ነጋዴውም ሆነ ምሁራኑ፣ የአገዛዞች ፖለቲካ ተጠቂዎች እንጂ የድጋፍ መሰረቶች የነበሩበት ወቅት የለም:: ዶ/ር አብይ ነጋዴውን (ባለሃብቱን) የፓርቲያቸው የድጋፍ ማህበራዊ መሰረት ለማድረግ አስበው ቢሆን እንኳ በባለሃብቱና  በምሁራኑ መካከል የፍላጎት ተቃርኖ አይታየኝም:: በመሆኑም የፖለቲካ ባላንጣ ሊሆኑ የሚችሉበት ንድፈ ሃሳባዊ አስረጅ የለም:: እንዲያውም የዳበረ የካፒታሊዝም ስርዓት በሚከተሉ አገሮች  እንደምናየው፤ የኢኮኖሚው መሰረት የንዑስ ከበርቴው ማህበረሰብ ክፍል፣ ከምሁራን ጋር በጥምረት መስራታቸውን ነው፡፡ የካፒታሊዝም ስርዓት በሰው ልጅ ታሪክ ከታዩ የተለያዩ ስልተ-ምርት ዓይነቶች  የተሻለ ስኬታማ የሆነበት አንዱ ምክንያትም ይህ ነው፡፡
በአጠቃላይ በንድፈ ሃሳባዊም ሆነ በኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ ታሪካዊ እውነታ መነጽር አስረጅነት፣ ባለሃብቱ እና ምሁሩ ክፍል የፍላጎት ተቃርኖ የላቸውም፤ይህ በሆነበት ሁኔታ ታዲያ፣ ዶ/ር አብይ ይህን ንግግር እንዲደር ያስገደዳቸው ምክንያት ነባራዊም ሆነ ጽንሰ ሃሳባዊ እውነታ አለው ለማለት አይቻልም፡፡ ከሁሉም በላይ የዶ/ር አብይ የአመራር ፍልስፍናዊ መሰረት የሆነው የመደመር ቀመር፤ ሁሉም ሙያ/ዘርፍ ተደጋጋፊ እንደሆነ አስረግጦ ያስረዳል፡፡ ከሁሉም በላይ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር፤ የፓርቲያቸው ብልጽግና ሰብእናዊ መሰረት የሆኑትን እውነትና እውቀት የሚጻረር ነው፡፡
ዶ/ር አብይ በንግግሮቻቸው ደጋግመው እንዳወሱት፤ ፓርቲያቸው ከተፎካካሪ ፓርቲዎች አንጻር በሃሳብ መስመር ለመሞገት በቂ አማራጭ ሃሳቦች አሉት፡፡ የፓርቲያቸው የፖለቲካ መሪ ጽንሰ ሃሳብ የመደመር ፍልስፍና፣ ግቡ ደግሞ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሆነ በንግግሮቻቸው ደጋግመው አውስተዋል:: አልፎ አልፎም ቢሆን ከተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ለሚነሱባቸው ወቀሳዎችም ሆነ ተቃውሞዎች መልስ ለመስጠት እንደምታ ያለው ቃላት ወይም ሽሙጦችን ጣል ማድረጋቸው ቢስተዋልም፣ መጋቢት 6 ቀን 2012 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ እንዳደረጉት ንግግር፣ በምንም መልኩ በጎ ጎኑን ለማየት የሚያስቸግር ንግግር አልሰማሁም።
በእኔ እምነት አወዛጋቢው የዶ/ር አብይ ንግግር ሶስት መላምታዊ ገፊ ምክንያቶች አሉት፡፡
የመጀመሪያው ዶ/ር አብይ ጉምቱ የፖለቲካ ተገዳዳሪዎቻቸውን በሙያቸው (በተማሩት ትምህርት መስክ) በማስታከክ ለመሸንቆጥ ያደረጉት ሙከራ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ አንጻር የኢዜማው መሪና የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰሩ ብርሃኑ ነጋ፣ የኦፌኮ ከፍተኛ አመራሮችና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን፡- ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እና አቶ ጃዋር መሃመድ፤ የዶ/ር አብይ የቃላት ጥይት ኢላማ እንደሆኑ ይገመታል።
ሁለተኛው የዶ/ር አብይ ንግግር ገፊ ምክንያት፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ምሁራን ያስተላለፉት መልዕክት ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ አንጻር የከፍተኛ ትምህርት ቁንጮ የሆኑት ምሁራን፣ ለሃገር በቀል ዕውቀት መስፋፋት ካላቸው ጉጉት አንጻር (የምር ከሆነ) ተጨባጭ አገራዊ ችግሮች ላይ አተኩረው እንዲሰሩ ከማሳሰብ አኳያ  ሊሆን ይችላል፡፡
ሶስተኛው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምሁርነትና ምሁራዊ እሴቶች ያላቸው የተዛባ አመለካከትና የተሳሳተ ግንዛቤ ሊሆን ይችላል፡፡
የዶ/ር አብይን ንግግር ከላይ በተጠቀሱት ሶስት መላምቶች አግባብ ለመተንተን እሞክራለሁ፡፡
የአዘጋጁ ማስታወሻ፡- ሀብታሙ ግርማ፤ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆን አንባቢያን በኢ-ሜይል አድራሻቸው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ሊያገኟቸው ይችላሉ፡፡


Read 12996 times