Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 07 July 2012 09:18

ምን ያህል የዲግሪ ምሩቃን የኮብልስቶን ሰራተኞች?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው ዘንድሮ የሚመረቁ ተማሪዎች የመመረቂያ ልብስ (ጋውን) ለመውሰድ ሰሞኑን በግቢው ውስጥ ውር ውር ሲሉ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ተመራቂዎች በራሳቸው ላይ ጣል የሚያደርጉት ቀልድ መረር ያለ ነው፡፡ “እንኳን ወደ ስራ ፈትነት አለም ተቀላቀልክ” “እንግሊዝኛ ተናጋሪ ኮብልስቶን ሰራተኛ” ወዘተ ዓይነት ወትሮ ያልተለመደ በራስ ላይ ቀልድ የበዛ ይመስላል - በዩኒቨርስቲው ግቢ፡፡ ለነገሩ እንዲህ ያለው ቀልድ የተጀመረው በቅርቡ ነው - በኢቴቪ፡፡ በድግሪና በዲፕሎም እንዲሁም በማስተርስ ደረጃ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ከዩኒቨርስቲዎች የተመረቁ ተማሪዎች ከመንግስት ስራ ጠባቂዎች ሳይሆኑ በኮብልስቶንና በእርሻ ስራ እንደተሰማሩ የሚያሳዩ ፕሮግራሞች በቲቪ መስኮት እየቀረቡ ነው፡፡በእርግጥ አንድ ሰው በዓለም ላይ የመጨረሻውን ከፍተኛ ትምህርት ተምሮም ኮብልስቶን አነጥፋለሁ ካለ መብቱ ነው የግድ በተማርክበት ትልቅ የትምህርት ዘርፍ መስራት አለብህ ተብሎ ግዳጅ አይጣልበትም፡፡

ነገር ግን የተማረ የሰው ሀይል እጥረት ባለበት እንደ ኢትዮጲያ ባለ አገር በከፍተኛ የትምህርት ደረጃ በድግሪና በማስተርስ የተመረቁ ዜጎች ስራ ባለማግኘታቸው ብቻ ምንም አይነት የትምህርት ዝግጅት ሳያስፈልገው በተወሰኑ ቀናቶች ስልጠና ሊሰራ በሚችል ሙያ ላይ እየተሰማሩ እንደሆነ እየተሰማ ነው፡፡

በትምህርት አስተዳደርና አመራር ከዩኒቨርስቲ ኦፍ አሪዞና ሁለተኛ ድግሪያቸውን ያገኙት የአንድነት ፓርቲ ዋና ፀሃፊ አቶ አስራት ጣሴ በሰጡት አስተያየት፤“አንድ ከዩኒቨርሲቲ የወጣ ሰው ለምን ኮብልስቶን ሰራተኛ ሆነ ተብሎ በወንጀል አይጠየቅም፡፡ ግን ከትምህርት አላማዎች  አንፃር ሲታይ ችግር እንዳለ ያሳያል፡፡” ብለዋል፡፡  በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከለፉት 15 ዓመታት ጀምሮ በማስተማር ላይ የሚገኙት ዶ/ር ጉዲና መረራ በበኩላቸው፤ “አንድ ሰው ችግር ከገጠመው ምንም ነገር ሰርቶ ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን እንደዚህ ያለው ነገር ለሌላው የህብረተሰብ ክፍል እጅግ ተስፋ አስቆራጭ ነው” በማለት ኢቴቪ መንግስትን ለማስደሰት ብሎ የሚሰራቸውን ፕሮግራሞች ተችተዋል - የሚኮራበት ሳይሆን የሚታፈርበት እንደሆነ በመግለፅ፡፡ ሁለቱ ምሁራን ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው በኮብልስቶን ላይ ስለተሰማሩና በበሬ ወደማረስ ስለገቡ ባለድግሪ ዜጎች፤ ስለአገሪቱ የትምህርት ፖሊሲና ስለመጪው ጊዜ የተናገሩትን  እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

“ኢትዮጲያ በበሬ ጠምዶ የሚያርስ አላጣችም”

ትምህርት ዋና አላማው እውቀትን ማግኛ፤ ችሎታን ማዳበሪያ ፤ ክህሎትን ማበልፀጊያ ብሎም የባህርይ ለውጥ ማስገኛ ነው፡፡ ስለ ትምህርት መናገር ማለት ስለአንድ አገር ሁለንተናዊ ሁኔታ መናገር ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው ስራ ማፍቀሩና የፈለገውን ስራ መስራቱ በራሱ ጤናማ እና የመብት ጉዳይ ነው፡፡አንድ ከዩኒቨርሲቲ  የወጣ ሰው ለምን ኮብልስቶን ሰራተኛ ሆነ ተብሎ በወንጀል አይጠየቅም፡፡ ግን ከትምህርት አላማዎች  አንፃር ሲታይ ችግር እንዳለ ያሳያል፡፡ እንደ ኢትዮጲያ ያለ ደሀ አገር በተማረ የሰው ሀይል፤ በሀብት እና በጊዜ የምትቀልድበት ሁኔታ የለም፡፡ የተማሩ ዜጎችን ለማፍራት የወጣው ወጪ በተለይ በዚህ ደሀ አገር አቅም ቢሰላ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በተማሪዎቹ ላይ የፈሰሰው ሀብት በተገቢው ቦታ ውሎ ማየት የግድ ነው፡፡ ስለዚህ የሰሞኑ ፕሮግራሞች እንደ ብርቅ ወይም እንደውጤታማነት ሊነገሩ የሚገቡ ሳይሆን በተቃራኒው በሚያሳዝን ሁኔታ የትምህርት ስርአቱ መዳከሙንና ውጤተቢስነቱን የሚያመላክት ነው፡፡ እራሱ መንግስተ ባወጣው የትምህርት ስትራቴጂ፤ ትምህርት ከምርምር ጋር ለልማታዊ እድገት አጋ በሆነ መልኩ ከተግባር ጋር የተያያዘ መሆን አለበት ይላል፡፡ ይህ የስትራቴጂው ክፍል አንድ፤ ሰው በሰለጠነበት መስክ የሚጠበቅበትን እንዲያበረክት እንደሚጠበቅ የሚያሳይ ነው፡፡

ዲግሪ ተማሪ ኮብልስቶን ስራ ላይ መሰማራቱ ከዚህ ስትራቴጂ ጋር የሚፃረር ነው፡፡

ከትምህርት ፖሊሲው ጋር ጉዳዩን ስናየው የትምህርት ፓሊሲው ገፅ አራት ላይ እንደተቀመጠው፤ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚገቡ ተማሪዎች መማር የሚፈልጉትንና ሙያው የሚጠይቀውን የትምህርት ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ለማረጋገጥ በሚያመለክቱባቸው ተቋሞች የመግቢያ ፈተና ይወስዳሉ፡፡ ይህ አግባብ ሊሰለጥኑበት የሚፈልጉትን ሙያ ለማግኘት ሲሉ ተማሪዎች ተግተውና በተቻለ መጠን ወደ ሚፈልጉት ሙያ ስለሚያደሉ ዩኒቨርሲቲ በሚገቡበት ወቅት ውጤታማ ይሆናሉ ይላል፡፡ በተግባር ግን በተቃራኒው ነው የሚሰራው፡፡ ተማሪዎች ወደ ሚፈልጉት ዩኒቨርሲቲ ሄደው ፈተና ወስደው አይደለም የሚገቡት፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር በመደባቸው የትምህርት ዘርፍ እንዲሰለጥኑ ይገደዳሉ፡፡ ተማሪዎች መጀመሪያውኑ ከፍላጎታቸው ተነጥለው ነው እንዲማሩ የሚደረገው፡፡እንደ ኢትዮጲያ ባለ አገር የሰዉን ሁሉ ፍላጎት ማሳካት ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን ለምሳሌ ባለፈው ስርአት ለጂፒኤ ትልቅ ቦታ ይሰጥ ነበር፡፡

እጅግ በጣም ጥሩ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች በየደረጃው የፍላጎታቸውን እንዲማሩ እድል ይሰጣቸው ነበር፡፡ አራት ነጥብ ያመጣ ተማሪ የመጀመሪያ ምርጫውን ያገኛል፡፡ ይህ አሰራር ችሎታዎች እና ዝንባሌዎች እንዳይባክኑ ያደርጋል፡፡ ህክምና 150 ቦታ ኖሮት ከፍተኛ ነጥብ ያመጡ 151 ተማሪዎች ህክምናን የመጀመሪያ ምርጫቸው ቢያደርጉ አንዱ ተማሪ ብቻ ነው በሁለተኛ ምርጫው እንዲመደብ የሚደረገው፡፡ ስለዚህ በተነፃፃሪ ተማሪዎች የፈለጉትን ትምህርት የመማር እድል ነበራቸው፡፡

ሌላው 70/30 ነው፡፡ ፕሮግራሙን በመርህ ደረጃ ስናየው ጥሩ ይመስላል፡፡ ዝግጅቱ አለ ወይ? ዩኒቨርሲቲዎች ለዚህ ፕሮግራም የተሟላ ዝግጅት አላቸው? መምህራን በበቂ አሉ ወይ? ተማሪዎች በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቆይታቸው ዝንባሌያቸው ግምት ውስጥ ገብቷል ወይ? የአስረኛ ክፍል ውጤታቸውስ ታይቷል? ምላሽ የሚፈልጉ ነገር ግን ያልተመለሱ ብዙ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ተማሪው ያለፍላጎቱ ወይም ዝንባሌው ወዳልሆነ ትምህርት መመደቡም በ|ሁዋላ ውጤቱ ተምሮ ኮብልስቶን እና በሬ ጠምዶ እርሻ ይሆናል፡፡ኢትዮጲያ በበሬ ጠምዶ የሚያርስ አላጣችም፡፡ የዲግሪ እና የማስተርስ ምሩቃንን በሬ አስጠምዳ የምታሳርስበት ወይም ኮብልስቶን የምታስፈልጥበት ደረጃ ላይ አልደረሰችም፡፡ የተማረ የሰው ሀይሏን ለኮብልስቶን የምታውለው እኮ ኢኮኖሚዋ የተማረ የሰው ሀይል መሳብ ስላልቻለ ነው፡፡ ይህ የኢኮኖሚውን ያለማደግ የሚያሳይ ነው፡፡ ለተከታታይ ስምንት አመታት በአስራአንድ በመቶ ያደገ ኢኮኖሚ እንዴት ለተማሩ ዜጎቹ ስራ መስጠት አቃተው? ኢኮኖሚው የተባለውን ያህል ላለማደጉ ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡ሌላው መታየት ያለበት ስራ ፈጠራን ከዚህ ጋር ማምታታት ተገቢ አይደለም፡፡ ስራ ፈጠራ እውቀትን መሰረት ያደረገ የቴክኖሎጂ ሽግግር ነው፡፡ እንዲያውም የስራ ፈጠራ አለመኖሩንም ጭምር ያሳየ ነው፡፡ የሰሞኑ ፕሮፓጋንዳ የትምህርት ስርአቱ ቀውስ ውስጥ መግባቱን የሚያመላክት ነው፡፡

የኮብልስቶንም ሆነ የእርሻ ስራ የተከበሩ ስራዎች ናቸው፡፡ በነዚህ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ሰዎች ነገ ተምረው የያዙትን ሙያ በተሻለ መንገድ በመስራት ወይም ወደ ሌላ ስራ ተሰማርተው ለመሻሻል የሚያስቡ ናቸው፡፡

የሰሞኑ ፕሮፓጋንዳ የተማሩትን ሞራል የሚገድል፤ ተምረው ማደግ የሚፈልጉትን ህልም የሚያቀጭጭ፤ የወላጅን እና የመምህራንን ድካም መና የሚያስቀር በመሆኑ የሚመለከታቸው ሀላፊዎች የትምህርት ስርአቱን እንዲፈትሹ የሚያደርግ ነው፡፡

(የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ዋና ፀሀፊ አቶ አስራት ጣሴ)

“ዲግሪ ይዞ ኮብልስቶን እየፈለጠ ነው የሚሉትን ነገር  ቢተዉ ይሻላቸዋል”

አንድ ሰው ችግር ከገጠመው ምንም ነገር ሰርቶ ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን እንደዚህ አይነት ነገሮችን አጉልቶ ማውጣት ተገቢ አይደለም፡፡ እነዚህ እየተሰራጩ ያሉ ፕሮግራሞችም መንግስትን ለማስደሰት በሚል ካልሆነ በስተቀር ለሌላው የህብረተሰብ ክፍል መልእክቱ እጅግ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ አንድ ከአስራአምስት አመት በላይ በትምህርት ላይ ያሳለፈ ሰው ምንም አይነት ትምህርት በማይጠይቅ እና ብዙ ስልጠና በማይፈልግ ሙያ ተሰማራ ብሎ እንደ ገድል ማውራት ውሉ የጠፋበት ነገር እንዳለ ያሳያል፡፡ አንድ የማስተርስ ወይም የዲግሪ  ምሩቅ ተመልሶ ልክ እንደ ቅድም አያቶቹ በበሬ ወይም እንደነሱ በሬ ማግኘት ካቃተው በራሱ ጫንቃ ተሸክሞ ለማረስ ለምን በትምህርት ጊዜውን ያጠፋል፡፡ የትም ሳይሄድ ለትምህርት ያባከነውን ጊዜ ሳያባክን መስራት የሚችለውን፤ ዲግሪ ይዞ እየሰራው ነው ብሎ መናገር  መንግስት ውሉ እንደጠፋው ያሳያል፡፡

የሰለጠነ የሰው ሀይል እጥረት አለ በሚባልባት አፍሪካ የሰለጠነ የሰው ሀይል ወደ ውጪ ይሰደዳል ወይም እንደ ኢትዮጲያ አዲስ ግኝት ድንጋይ ይፈልጣል፡፡ ይህ የአህጉሪቱ አያአዎ ነው፡፡ ያለውን ስራ ካድሬው ይቀራመታል ፤የተሻለ የትምህርት ስልጠና ያለውና ስራ ፈጣሪው ስደት ይሄዳል፤ ስለዚህ አማረልን ብለው ዲግሪ ይዞ ኮብልስቶን እየፈለጠ ነው የሚሉትን ነገር  ቢተዉ ይሻላቸዋል፡፡ የፕሮፓጋንዳ ጋጋታውን ትተው ከውጪ የሚያመጡትን ገንዘብ ለዜጎች ጥቅም እንዲውል ሊያደርጉት ይገባል፡፡ እንደው ኮብልስቶን ስንት አመት ስራ ይፈጥራል? ሀያ አመት አስተምረን ድንጋይ እያስፈለጥን ነው ማለታቸውን ሊያፍሩበት ይገባል፡፡ መደበቅ ያለባቸውን ነውር እንዴት ለፕሮፓጋንዳ አሰቡት!

(ዶክተር መረራ ጉዲና፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር)

 

 

Read 2291 times Last modified on Saturday, 07 July 2012 09:32