Saturday, 28 March 2020 11:27

የታገቱ የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያሉበትን ሁኔታ መንግስት እንዲያሳውቅ አምነስቲ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

       የታገቱ የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ያሉበትን ሁኔታ መንግስት በአስቸኳይ ለተማሪዎቹ ቤተሰቦች ግልጽ እንዲያደርግ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የጠየቀ ሲሆን የተማሪዎቹ ቤተሰቦች በበኩላቸው፤ የልጆቻቸው ጉዳይ ሰቀቀን እንደሆነባቸው መቀጠሉን ለአምነስቲ አስረድተዋል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ልጆቻቸው የታገቱባቸውን ቤተሰቦች አነጋግሮ ባጠናቀረው ሪፖርቱ፤ የተማሪዎቹ ቤተሰቦች በከፍተኛ ጭንቀትና ፍርሃት ውስጥ መሆናቸውን ተገንዝቤያለሁ፤ መንግስት በጉዳዩ ላይ ይፋዊ መረጃ ማቅረብ አለበት ብሏል፡፡ የታገቱት ተማሪዎች በቁጥር 17 መሆናቸውን የጠቆመው አምነስቲ፤ ተማሪዎቹ የታገቱት በደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ባለው የፀጥታ ችግር የተነሳ ወደ ቤተሰቦቻቸው እየተመለሱ ባለበት ሰዓት መሆኑን ከቤተሰቦቻቸው ተረድቻለሁ፤ መንግስት በምዕራብ ኦሮሚያ ኢንተርኔትም ስልክ የማቋረጥ እርምጃ መውሰዱን ተከትሎም፣ ስለአካባቢው ፍንጭ ለማግኘት እንኳ መቸገራቸውን ገልፀውልኛል ብሏል፡፡ ከታገቱት ተማሪዎች አንዷ የሆነችው የ3ኛ አመት የባዮ ቴክኖሎጂ ተማሪ ግርማነሽ የኔነህ ወላጅ አባት አቶ የኔነህ አዱኛ ለአምነስቲ በሰጡት ቃል፤ በኮሮና ስጋት ምክንያት ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ መደረጉን ስንሰማ፣ የኔም ልጅ እንድትመጣልኝ እፀልያለሁ በተስፋ እጠብቃታለሁ” ብለዋል፡፡ “ልጃችን በሠላም እንድትመለስልን እኔም ሆንኩ እናቷ ጠፋች ከተባለበት ቀን ጀምሮ እንባችን አልቆመም፤ ፀሎታችን አልተቋረጠም” ብለዋል አቶ የኔነህ - ለአምነስቲ፡፡ ተማሪዎቹ በታገቱበት የደንቢዶሎ ዩኒቨርስቲ መገኛ ምዕራብ ኦሮሚያና አካባቢው የግንኙነት አውታሮች መቋረጣቸውን ተከትሎ፣ አምነስቲ ከአካባቢው መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካለት ጠቅሶ፤ መንግስት በአፋጣኝ ተማሪዎቹ ያሉበትን ሁኔታ ለቤተሰቦቻቸው እንዲያሳውቅ ጠይቋል፡፡
ተማሪዎቹ ታግተው ቤተሰቦቻቸው በሰቀቀን ውስጥ መኖር ከጀመሩ አራተኛ ወር መቆጠሩንም አውስቷል - በሪፖርቱ፡፡

Read 1215 times