Saturday, 28 March 2020 11:39

የወር አበባና የተለያዩ የህመም ስሜቶች

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(4 votes)

ከወር አበባ ጋር በተያየዘ ሁለት ደብዳቤዎች ደርሰውናል፡፡ አንዱዋ የ14 አመት እድሜ ያላት ታዳጊ ስትሆን ሌላዋ ደግሞ ሰላሳ አመት የሞላት የአንድ ልጅ እናት ናት፡፡ የሁለቱንም ደብዳቤ አሳጥረን ለንባብ ብለነዋል፡፡  
‹‹…..እድሜዬ 14 አመት ሲሆን የመጣሁትም ከገጠር ነው፡፡ ከገጠር እንደመጣሁም የሚረዱኝ ሰዎች ከትምህርት ቤት ስላስገቡኝ ከነበርኩበት ቀጥዬ ዘንድሮ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ነኝ፡፡ እኔ ከገጠር ሆኜ አንድ ችግር ነበረብኝ:: ይኼውም በየወሩ ቢያንስ ሶስት ቀን ያህል ከትምህርት ቤት እቀራለሁ፡፡ ቤተሰቦቼ ለምን ትቀሪያለሽ ብለው ስለማያስቸግሩኝ ችግሬን ሳላዋይ ተመልሼ ከት ምህርት ቤት እገባ ነበር፡፡ አሁን ግን ከከተማ ከገባሁ አንድ አመት የሞላኝ ሲሆን ነገሮች ተለዋውጠዋል፡፡ ከትምህርት ቤት ብቀር የሚያስተዳድሩኝም ሆኑ ትምህርት ቤቱ ለምን የሚል ሆነ፡፡ በወር አንድ ጊዜ የሚመጣው የወር አበባ እራሴን በጣም እንዲያመኝ ያደርገኛል፡፡ እናም በዚህ ጊዜ ሁሉን ነገር ትቼ ካልተኛሁ በስተቀር ምንም ደስታ የለኝም፡፡ ለመማር የተጠጋሁ ባቸው ሰዎች መጀመሪያ ወደ ሕክምናው እንድሄድ ያደርጉኝ ነበር፡፡ በሁዋላ ግን ችግሩ በየወሩ ሲሆን ለምንድነው ብለው ሲጠይቁኝ ነገርኩዋቸው፡፡ በቃ የወር አበባ ከሆነ ሕመሙን መቻል ብቻ ነው የሚያዋጣው ብለው ተውኝ፡፡ ምን ይሻለኛል?››
ሰርክአለም ተሻገር
‹‹….አንድ ልጅ አለኝ፡፡ እድሜዬም 30 አመት ከስድስት ወር ነው፡፡ እኔ የምቸገረው የወር አበባዬ ሊመጣ ሲል የሚያጋጥመኝ የወገብ ሕመም ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ አልጋው ነው ወይንም ፍራሹ ነው እያልኩ እራሴን ሳጽናና ነበር:: ነገር ግን አሁን የገባኝ ነገር የወር አበባ ሊመጣ ሲሆን እንደሚያመኝ ነው፡፡ ምክንያቱም የወር አበባው መፍሰስ ሲጀምር ወገቤን ይሻለኛል፡፡ ሊመጣ አንድ ሁለት ቀን ሲቀረው ግን ተቀምጬም ሆነ ተኝቼ ወገቤን ያምመኛል:: እስከመቼ ይሆን የሚያመኝ?››
ሶስና ተክሌ
ከላይ ያነበባችሁዋቸው ከወር አበባ ጋር በተያያዘ ከሁለት የተለያዩ ሰዎች የደረሱን የህመም ስሜቶችን የሚገልጹ መልእክቶች ናቸው፡፡ ከወር አበባ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሴቶች የተለያዩ ሕመሞች ሊሰሙዋቸው እንደሚችሉ እሙን ነው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ መምጣት መሄዱን እንኩዋን በማያስታውሱበት ደረጃ በሰላም ጊዜውን ያጠናቅቃሉ፡፡ በመጀመሪያ የወር አበባ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የሚገልጸውን መረጃ እናስነብባችሁ:: ከአሁን ቀደም ያነጋገርናቸው የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስት ዶ/ር አበበ ፈጠነ ሰጥተውን የነበረ መረጃ ነው፡፡
‹‹…..የወር አበባ ማለት ከሴት ልጅ ከውስጠኛው የማህጸን ክፍል እየተቀረፈ በየወሩ የሚወጣ ከደም ጋር የተቀላቀለ የማህጸን የውስጠኛው አካል ማለት ነው፡፡ ይህ ክፍል ዋናው መሰረት ደም ቢሆንም እንደ ፕሮጄስትሮን (progesterone) ሰውነትን ከኢንፌክሽን የሚከላከሉ እንደ የነጭ የደም ሴል ዘሮች እና የመሳሰሉ ከደሙ ጋር እየተቀላቀሉ የሚወጡ ንጥረ ነገሮች አሉ:: ከደሙ ጋር እየተቀላቀሉ የሚወጡት ንጥረ ነገሮች ከውስጠኛው ማህጸን ክፍል ተቀርፎ ከሚወጣው አካል ጋር ተቀላቅሎ ሲወርድ የወር አበባ ይባላል:: ማህጸን ሶስት ክፍሎች አሉት እነርሱም ውስጠኛው የማህጸን ክፍል ኢንዶሜትርየም ማህከለኛውና ዋናው ማዮሜትር እና የማሀከ ለኛውን የሚሸፍነው የውጨኛው ክፍል ሴሮሳ ይባላል፡፡ የውስጠኛው የማህጽን ክፍል ኢንዶ ሜትር የሚበለው ክፍል ደግሞ እንደገና በሁለት ይከፈላል:: ይኼውም በጣም ከውስጥ ያለው 2/3 ኛው ክፍል ዲሲዱአስ ፈንክሽናሊስ (deciduas functionals) 1/3ኛው ደግሞ ዲሲዱአስ ፓዛሊስ (pazalis) ይባላል፡፡ ስለዚህ ዲሲዱአስ ፈንክሽናሊስ (deciduas functionals) የሚባለው በየወሩ እንደ ወር አበባ ሆኖ እየተቀረፈ ይወጣል ማለት ነው፡፡›› የወር አበባ ማለት ተፈጥሮ አዊ ሁኔታው ከላይ ያነበባችሁትን የሚመስል ሲሆን ፍሰቱን በሚመለከት ያገላበጥነው መረጃ የሚከተለውን ይገልጻል፡፡
በእርግጥ በአሁኑ ወቅት ከአንዳንድ የኑሮ፤ የአየር፤ የአመጋገብ …ወዘተ ለውጥ የተነሳ የወር አበባ መምጫው ጊዜ እስከ አስራ ሶስት አመት የማይቆይበት ሁኔታ እየተስተዋለ ቢሆንም  የወር አበባ መታየት የሚጀምረው ከአስራ ሶስት አመት ጀምሮ ባለው እድሜ ነው፡፡  አንዲት ሴት የወር አበባዋ በየወሩ መምጣት አለበት ፡፡ብዙ ጊዜ ከሃያ አንድ እስከ ሰላሳ አምስት (21-35) ባሉት ቀናት ከመጣ እና መጠኑም ከአስር (10) ሚሊ ሊትር እስከ ሰማንያ (80) ሚሊ ሊትር ከሆነ (በጠቅላላ መጥቶ እስከሚሄድ) ትክክል ነው እንላለን፡፡አነሰ እንኩዋን ቢባል በአማካይ ሰላሳ (30) ሚሊ ሊትር ነው፡፡የሚፈስበት ጊዜ ደግሞ እስከ ስምንት (1-8) ቀን ድረስ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ችግር የለውም፡፡ በአብዛኛው ግን ብዙ ሴቶች የወር አበባቸው ከሶስት እስከ አምስት (3-5) ቀን ድረስ ይፈሳል፡፡ ከዚህ ውጭ ከሆነ ግን የወር አበባን የተለያዩ ነገሮች እያስተጓጎሉት ነው ማለት ነው፡፡
የወር አበባ ቀኑን ጠብቆ መጠኑም ሳይዛባ መፍሰስ እንዲችል የግል ጥረትን ጨምሮ የህክምና አገልግሎትም ድርሻ ከፍ ያለ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት …..ብዙ ጊዜ የወር አበባ መጠን ከአስር እስከ ሰማንያ ሚሊ ሊትር በአማካይ ደግሞ ሰላሳ ሚሊ ሊትር ነው መሆን ያለበት:: በሚሊ ሊትር መለካት ከባድ ስለሆነ በቀን ምን ያህል ሞዴስ ትቀይራለች በሚለውም መገመት ይቻላል:: ለምሳሌ አንዲት ሴት በቀን ከሁለት እስከ ሶስት ሞዴስ ብትቀይር ጤነኛ ሀኔታ ነው፡፡ ነገር ግን አንዲት ሴት አስከ አስር ሞዴስ በቀን የምትቀይር ከሆነ ያ የደም መፍሰስ መብዛትን ያመለክታል፡፡
የወር አበባ በሚፈስበት ወቅት የደም የመርጋት ሁኔታ ሊታይበት አይገባም፡፡ ይህ ካጋጠመ የወር አበባ መብዛቱን ያመለክታል፡፡ ይህ ሁኔታ የደም ማነስን አስከትሎ ከደም ማነስ ጋር የተያያዙ ሌሎች ችግሮችንም ያስከትላል:: ለልብድካም እና ለኢንፌክሽኖች ሊያጋልጥ ይችላል:: የወር አበባ ጊዜውን ያለመጠበቁና የመጠን መብዛቱ የስነ-አእምሮአዊ ችግርንም ሊያመጣ ይችላል:: ለምሳሌ አንዲት ሴት ጓደኛዋ በየወሩ የወር አበባዋ በትክክል እየታያት የእሷ ግን የተዛባባት ከሆነ የስነ-እምሮአዊ ችግር ይገጥማታል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የወር አበባ መዛባት ከስሜት መቀዝቀዝ፣ ማዘን፣ ከድብርት እና ከመሳሰሉት ጋር ይያዛል፡፡ ሌላው ትዳር ላይ ላሉ ሴቶች የወር አበባቸው ወቅቱን ጠብቆ የማይመጣ ከሆነ የማርገዝ ችግርን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዥነት የሚነሳው ተደጋጋሚ ለሆነ ውርጃ እና ብሎም ለማህጸን ካንሰር የሚያልጥ መሆኑን ነው፡፡
የወር አበባ በትክክል አለመፍሰስ ለተለያዩ የጤና እክሎች ሊያጋልጥ ይችላል፡፡ የደም ማነስ፣ የልብድካም፣ የማህጸን ካንሰር፣ ተደጋጋሚ የሆነ ውርጃ… የመሳሰሉት ከተዛባ የወር አበባ ፍሰት ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ ከሚችሉ ሕመሞች መካከል ናቸው ፡፡
ለዚህ እትም የደረሱት የተለያዩ የህመም ምልክቶችና ሌሎችም ከወር አበባ ጋር በተያያዘ የሚነሱ የህመም ስሜቶች ምክንያት አላቸው ይላሉ ባለሙያዎች፡፡ ከዚህ ቀደም ለዚህ አምድ አነጋግረናቸው የነበሩት ዶ/ር አበበ ፈጠነ እንደገለጹት  በወር አበባ ጊዜ ህመም ሊኖር ይችላል፡፡ ለዚህም ምክንያት አለው፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት (estrogen) የሚባለው ሆርሞን ያዘጋጀው የማህጸን ግድግዳ በፕሮጄስተሮን (progesterone) ይደገፋል፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ እንደ ፕሮስታግላንዲን  (prostaglandin) አይነት የታለያዩ ቅመሞች ማህጸን ወስጥ ይዘጋጃሉ፡፡እንዲሁም እገርግዝና ካልተካሄደ ወደ ወሩ መጨረሻ ላይ ፕሮጄስተሮን (progesterone) እና ኤስትሮጂን (estrogen) የሚባሉ ቅመሞች ዝቅ ይላሉ:: በዚህን ጊዜ አዲስ የተሰራው የማህጸን ግድግዳ ላይ ውስጡ ያለው የደም ዝውውር ያንሳል፡፡የደም ዝውውር አነሰ ማለት ውስጡ ያለው ነገር እየሞተ ነው ማለት ነው፡፡የማህጸን የውስጥ ግድግዳው የሞተ እና እየሞተ ያለ ከሆነ ህመም ሊሰማ ይችላል፡፡ በእንግሊዝኛውም አጠራር ኤስኬሚክ (ischemic) ይባላል፡፡ አዲስ የተሰራው ዴሲዱአስ (deciduas functional)  የሚባለው ግድግዳ ላይ የደም ዝውውር ማነስ እና የምግብ እጥረት ያጋጥማል:: ስለዚህ የምግብ እጥረት እና የኦክሲጅን (oxygen) እጥረት ሲያጋጥም ኤስኬሚክ ischemic ይሆናል በዚህ ምክንያት ህመም ይፈጠራል፡፡ሁለተኛው እና ዋናው የህመም መፈጠር ምክንያት ደግሞ ፕሮስታግላንዲን (prostaglandin) የሚባለው ቅመም ማህጸን ውስጥ ያለውን ስፓይራል (spiral) የሚባለውን የደም ስር እንዲኮማተር በማድረጉ ከባድ የሆነ ህመም እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ይህን ሲያደርግ አዲስ የተሰራው ግድግዳ ላይ የደም ዝውውር እንዲቀንስ በማድረጉ  ለ ኤስኪሚክ (ischemic) ወይም ለምግብ እጥረት በማጋለጥ  ህመም እንዲሰማ ያደርጋል፡፡    ሶስተኛው የህመም ምክንያት ደግሞ ፕሮስታግለነረዲን (prostaglandin) የሚባለው ንጥረ ነገር የማህጸን ግድግዳ እንዲኮ ማተር በማድረጉ ነው፡፡ እንዲኮማተር የሚያደርግበት አንደኛው ምክንያት  የደም ዝውውሩ እንዲ ቀንስ እና ሴቲቱ  ብዙ እንዳትደማ ለማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ  በምግብ እጥረት የተ ነሳ ከውስጥ የሞተው ክፍል  ከማህጸን ውስጥ እንዲወጣ የግድ ማህጸን መጭመቅ ስላለበት  የመጭመቅ ሂደቱ ህመም እንዲሰማ በማድረጉ ነው፡፡ስለዚህ ባጠቃላይ በወር አበባ ጊዜ ሶስት መሰረታዊ ህመሞች አሉ ማለት ነው፡፡ በምግብ እጥረት ፣አየር (oxygen) እጥረት እና ሶስተ ኛው ደግሞ ማህጸኑ እራሱ ስለሚኮማተር በእነዚህ ምክንያቶች ህመም ይከስታል፡፡


Read 15869 times