Saturday, 28 March 2020 11:53

የሠራውን የረሣ ዋጋውን ያገኛል! ሥራውን ያስታወሰ መዋያውን ያውቃል

Written by 
Rate this item
(12 votes)

    ከዕለታት አንድ ቀን እመት ጦጢት አንድ ዋርካ ላይ ጥፍር ተደርጋ ታሥራ፣ አላፊ አግዳሚውን “እባካችሁ ፍቱኝ ወይም አስፈቱኝ” እያለች ትለምናለች፡፡
በመጀመሪያ የመጣው አንበሳ ነው፡፡
አንበሳ - “እመት ጦጢት ምን አጥፍተሽ ነው የታሠርሽው?” ሲል ጠየቃት፡፡
ጦጢትም - “አልበላም ብዬ ነው የታሠርኩት” አለች፡፡
አንበሳም - “አንቺ እንኳን ብልጥ ነበርሽ፡፡ ምን ሆነሽ ነው ያልበላሽው? በይ ሥራሽ ያውጣሽ” አላትና ሄደ፡፡
ቀጥሎ የመጣው ነብር ነው፡፡
“እመት ጦጢት ምን አጥፍተሽ ታሠርሽ፡፡
ጦጢት - “ብይ ብባል አልበላም ብዬ ነው”
ነብር - “አንቺ ብልጥ አልነበርሺም እንዴ? አብረሽ ሌላ ጥፋት አጥፍተሽ ነው እንጂ አልበላም ስላልሽ ብቻ አትታሰሪም፡፡ በይ ሥራሽ ያውጣሽ” ብሏት አለፈ፡፡
ቀጥሎ ጦጢት አጠገብ የደረሰው ቀበሮ ነበር፡፡
ቀበሮም - “አመት ጦጢት፣ ምን አጥፍተሽ ነው የታሠርሽው?”
ጦጢት - “ከሰው ማሣ የተሰረቀ አተር ካልበላሽ ብለውኝ እምቢ ስላልኳቸው እነ ዝሆን ናቸው ያሠሩኝ!”
ቀበሮም - “አይ እመት ጦጢት፣ አንቺን እናውቅሻለን’ኮ እንዲያውም ሳትጠሪ ሰው ማሣ ገብተሽ የምትሠርፊ አይደለሽ እንዴ? ሌላ ያጠፋሽው ጥፋት ቢኖር ነው” ብሏት አለፈ፡፡
ቀጠለና ዝንጀሮ መጣ፡፡
ዝንጀሮ - “እመት ጦጢት ምን አርገሽ ነው የታሠርሺው?”
ጦጢት - “አልበላም ብዬ!”
ዝንጀሮም - “አንቺ አጭበርባሪ ነሽ፡፡ እናውቅሻለን ካገኘሽ የማንንም ሰብል አትምሪም! አንድ የሆነ ያጠፋሽው ሌላ ጥፋት ቢኖር ነው!”
ዝሆን በተራው ከጫካ ሲመለስ ጦጢት ታሥራ አየ፡፡
“እመት ጦጢት ምን ሆነሽ ታሠርሽ?”
“አልበላም ብዬ”
“ምን አልበላም ብለሽ?”
“ባቄላ”
“አሄሄሄሄ! አንቺ ባቄላ አይተሽ ዝም ብለሽ ልታልፊ? አታጭበርብሪ!” አላትና እየሳቀባት ሄደ፡፡
ቀጠለና ድኩላ መጣ፡፡
ድኩላም፤
“እመት ጦጢት ምን አጥፍተሽ ታሠርሽ?”
“ከሰው አዝመራ ገብቼ እሸት ስበላ አግኝተው፤ አሰሩኝ”
“ባለቤቱ ሲመጣ አጣርተን ነው የምናስፈታሽ!” ብሏት ሄደ፡፡
በመጨረሻ አያ ጅቦ ይመጣል፡፡
አያ ጅቦም ሌሎቹ እንደጠየቋት ጠየቃት፡፡
አያ ጅቦ- “እንዴ እመት ጦጢት! ምን ሆነሽ ነው የታሠርሺው?”
ጦጢትም - “ብዙ መንገድ መጥቼ እዚህ ስደርስ ራበኝ! “እባካችሁ መንገደኛ ነኝ፡፡ ርቦኛል” ብላቸው፤ “ዞር በይ ከዚህ አሉኝ፡፡ እነሱ ሲዘናጉልኝ ጠብቄ ልሰርቅ ስገባ ያዙኝና እንደምታየው አሠሩኝ፡፡ አሁን ግን አሳዘንኳቸውና “አስኮናኝ ነሽ! በይ ብይ አሉኝ!” እኔም ተራዬን አልበላም! አልኳቸው”
አያ ጅቦም፤
“እንደሱ ከሆነማ እኔ ስለራበኝ ባንቺ ቦታ ልታሠርና ልብላ” አላት፡፡
“በጣም ጥሩ” አለችው፡፡
አያ ጅቦም ጦጢትን ፈታትና፤ በሷ ገመድ ገባ! ጦጢትን ያሠሯት ሰዎች መጡ፡፡ በእሷ ቦታ አያ ጅቦን አገኙት፡፡ እስኪበቃው ድረስ ቅጥቅጥ አደረጉት፡፡
“እባካችሁ አይለምደኝም ልቀቁኝ!” ብሎ ለመናቸውና ለቀቁት፡፡
አያ ጅቦ እስከዛሬ ድረስ እመት ጦጢትን አያምናትም፡፡ እንዲያውም እይዛታለሁ ብሎ ብዙ ጥሯል፤ ግን አልተሳካለትም!
***
የሠራነውን ደግ እንጂ ክፉውን አንርሳ፡፡ ደግ የተሠራለት ቢረሳ፤ ክፉ የተሠራበት ምን ጊዜም በደሉን አይረሳም! የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም ይባላል፡፡ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን፤ የዚህን ግልባጭ በጥበቡ ተቀኝቶበታል፡፡ እንዲህ ሲል፡-
ትቸዋለሁ ይተዉኝ
አልነካቸውም አይንኩኝ
ብለህ ተገልለህ ርቀህ
ዕውነት ይተዉኛል ብለህ
እንዴት ተስፋ ታደርጋለህ?!
የተወጋ በቅቶት ሲተኛ፣ የወጋ መች እንቅልፍ አለው
የጅምሩን ካልጨረሰው፡፡
እና በእኔ ይሁንብህ
እንቅልፍ ነው ‘ሚያስወስድህ!
“እንቅልፍ ነው ሚያስወስድህ”
(እሳት ወይ አበባ)
የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የምንወደውን ሰላምታና መጨባበጥ እንሰዋ ዘንድ ሆነ፡፡ ኮሮና ቫይረስ ቀሳፊ ነው! ሲሆን ሲሆን ለኮሮና ብቻ ብለን ሳይሆን ስለ ንፅህናችን መቆርቆርን ባህል እናድርግ! እንዳጋጣሚ ሆኖ ኮሮና መምጣቱ “ሳይደግስ አይጣላም” እንደሚባለው ነው - A Blessing in disguise እንደማለት ሆነ ማለት ነው፡፡ እነሆ ለራስም ለሌላውም ማሰብ ያለብን አሳሳቢ ሰዓት ነው፤ ለመዘጋት ጊዜ የለም! ለእንዝህላልነት ቅጽበት የለም! የሁላችንም ሥጋት፣ የሁላችንም ፍርሃት የተከሰተበት ሰዓት ነው! ዛሬን የአሥራ አንደኛው ሰዓት ክፍልፋይ ሰኮንዶቹ ብቻ የቀሩበት አድርገን እንጨነቅ! የግል ብቻ አይደለም፤ የቡድንም ብቻ አይደለም! የህብረተሰብ ጉዳይ ነው! “የአንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል እኔ ቤት” ብለን ነበር ዱሮ፡፡
ዛሬ ግን የሁላችንንም ቤት በአንድ ጊዜ የሚያንኳኳ፣ ሁላችንም ላይ ያነጣጠረ ቀሳፊ ጊዜ መጥቷል፡፡ ራስን ብቻ ሳይሆን ዓለምን የሚያባብስ የጭንቅ ሰዓት ነው! በዚህ ሰዓት የሁላችንንም ሰቆቃ ሥራዬ ብለን የምንደማመጥበት፣ ህብረታችንን የሚያናጋ፣ ነጋችንን የሚያጨልም እጅግ አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ነን፤ እንተሳሰብ እንመካከር!
ምንም እንኳ የበሽታ ምርጫ ውስጥ የምንገባ ባይሆንም፣ የክፉም ክፉ እንዳለ ማስተዋል ሊሳነን አይገባም፡፡ ከጽንሱ አንስቶ እስከ የክፉ ገጽታ ስትጭቱ፣ የቅድመ ምርመራውና የመጣራቱ ሂደት ድረስ እጅግ አንገብጋቢ የንክኪ አደጋ መኖሩን በጥሞና እናሰላስል፡፡ ነፃ መሆን ወይም ኔጋቲቭ መሆን ምንጊዜም ከጥንቃቄ ሊገታን በጭራሽ አይገባም፡፡ አሁንም ያለን የዕለቱ መልዕክት፡-
“ጥንቃቄ!
ጥንቃቄ!!
ጥንቃቄ!!!
እናድርግ!” የሚለው ነው! የሁላችንም ያልተቆጠበ ጥረት ያስፈልጋል፡፡ ከቶውንም በእርዳታ ያገኘነውን ናሙና መውሰጃና መመርመሪያ፣ እንዲሁም መከላከያ ቁስን፤ በአግባቡ ሥራ ላይ እናውል!!
ትላንትና መነካካትን እንደፆምን፣ ዛሬ መቀራረብንም እንፁም!!!
የሠራውን የረሳ ዋጋውን ያገኛል! ሥራውን ያስታወሰ መዋያውን ያውቃል የሚባለውን ለአፍታም ቢሆን አንዘንጋ! አንዘናጋ! አንዘናጋ! ከአደጋው ይሰውረን!!!


Read 16005 times Last modified on Sunday, 10 May 2020 15:16