Saturday, 28 March 2020 12:21

አለም በጭንቅ ውስጥ ናት

Written by 
Rate this item
(5 votes)

    አለማችን ልትቋቋመው አቅም ባጣችለት፣ ነጋ ጠባ እንደ ሰደድ እሳት  በያቅጣጫው በሚስፋፋና ብዙዎችን በሚቀጥፍ “ኮሮና” የተባለ የጥፋት ማዕበል ከዳር እስከ ዳር መናጧን ቀጥላለች:: ማዕበሉ በቴክኖሎጂ ተራቀቅኩ፣ በሃብት በለጸግኩ የሚሉ ሃያላንን ሳይቀር ማጥለቅለቁን፣ መላውን የሰው ልጅ ማስጨነቁን ተያይዞታል፡፡
መላ የታጣለት የወቅቱ የአለማችን ቀዳሚ ፈተና የሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እስካለፈው ሃሙስ ተሲያት ድረስ በአለማችን 198 አገራትና ግዛቶች ውስጥ ከ550 ሺህ በላይ ሰዎችን ማጥቃቱና ከ25 ሺህ በላይ የሚሆኑትንም ለሞት መዳረጉ ተነግሯል፡፡
ከ7 ሺህ 500 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ለሞት የተዳረጉባት ጣሊያን ብዙ ሰዎች የሞቱባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ስትሆን፣ ባለፈው ረቡዕ ብቻ 738 እንዲሁም ሀሙስ በ24 ሰዓት ውስጥ ብቻ 769 ዜጎቿን በኮሮና ሳቢያ በሞት የተነጠቀችውና አጠቃላይ የሟቾቿ ቁጥር 4 ሺህ 869 የደረሰባት ስፔን በሁለተኛ፣ 3 ሺህ 287 ያህል ሰዎች የሞቱባት ቻይና ደግሞ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ፣ ኮሮና ቫይረስ በመላው አለም በፍጥነት እየተዛመተ እንደሚገኝ የጠቆሙ ሲሆን፣ የመጀመሪያዎቹ 100 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙት በ67 ቀናት መሆኑን በማስታወስ፣ ቀጣዮቹ 100 ሺህ ሰዎች በ11 ቀናት፣ ሌሎቹ 100 ሺህ ሰዎች ደግሞ በ4 ቀናት ጊዜ ውስጥ ብቻ በቫይረሱ መያዛቸውንና ይህም ቫይረሱ ምን ያህል በፍጥነት እየተስፋፋ እንደሚገኝ አመልካች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሩብ ያህሉ የአለም ህዝብ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎበታል
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እያደረሰ ያለው ጥፋት ተስፋፍቶ መቀጠሉን ተከትሎ፣ በርካታ የአለማችን አገራት መንግስታት ከቤት እንዳይወጡ መከልከልን ጨምሮ የዜጎችን እንቅስቃሴ የሚገቱ የተለያዩ ጥብቅ ትዕዛዛትን እያስተላለፉ ሲሆን፣ ከአጠቃላዩ የአለማችን ህዝብ ሩብ ያህሉ ወይም 2 ቢሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የእንቅስቃሴ ገደብ እንደተጣለባቸው ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
አገራት በዜጎቻቸው ላይ የጣሉት የእንቅስቃሴ ገደብ የተለያየ መሆኑን የዘገበው ሮይተርስ፣ ብዙዎችን ያነጋገረው ግን የህንድ መንግስት ከ1.3 ቢሊዮን የሚበልጠው የአገሪቱ ህዝብ በሙሉ ለ21 ቀናት ያህል ከቤቱ እንዳይወጣ ባለፈው ረቡዕ ያስተላለፈው ቀጭን ትዕዛዝ እንደሆነ አመልክቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ድንገተኛውን እገዳ ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በመዲናዋ ዴልሂና በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች፣ አስፈላጊ ሸቀጦችን ለመግዛት በገፍ መውጣቱንና ጭንቀት መፈጠሩን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሳምንቱ ዜጎቻቸውን ከቤት እንዳይወጡ ከከለከሉ አገራት መካከል አንዷ በሆነችው እንግሊዝ፣ 66 ሚሊዮን የሚጠጋው የአገሪቱ ህዝብ እጅግ በጣም አንገብጋቢ ለሆነ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከቤት ውጭ ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርግ የተከለከለ ሲሆን፣ እገዳውን በመተላለፍ ከቤት ውጭ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የተገኘ ዜጋ ቅጣት እንደሚጣልበት ተነግሯል፡፡
በዜጎቿ ላይ ተመሳሳይ የእንቅስቃሴ ገደብ የጣለችው ሩስያም፣ ገደቡን ጥሶ በተገኘ ሰው ላይ ከሶስት እስከ ሰባት አመት የሚደርስ የእስር ቅጣት ለመጣል ማሰቧ ተነግሯል፡፡
ዜጎቻቸው ለተወሰነ ጊዜ ከቤት እንዳይወጡ፣ እንዳይሰበሰቡና የተለመደ እንቅስቃሴያቸውን እንዲያቋርጡ ከከለከሉ የንግድ ተቋማትና መስሪያ ቤቶችም አገልግሎታቸውን አቋርጠው እንዲዘጉ ካደረጉ አገራት መካከል ጣሊያን፣ ስፔን፣ ፈረንሳይ፣ ቦሊቪያ፣ ዮርዳኖስ፣ ቱኒዝያ፣ ጀርመን፣ ደቡብ አፍሪካና ሩዋንዳ ይገኙበታል፡፡
መሰል የእንቅስቃሴ ገደቦችን በተወሰኑ ግዛቶችና አካባቢዎች ተግባራዊ ካደረጉ አገራት መካከልም አውስትራሊያ፣ ማሌዢያና ፊሊፒንስ ይጠቀሳሉ፡፡

ክትባቱ ለመቼ ይደርስ ይሆን?
የአለም የኢኮኖሚ ፎረም በመላው አለም ከ35 በላይ የሚሆኑ የምርምር ተቋማትና ኩባንያዎች ለኮሮና ቫይረስ ክትባት ለማግኘት ሌት ተቀን ደፋ ቀና እያሉ እንደሚገኙ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መረጃ ቢገልጽም፣ ተመራማሪዎች በለስ ቀንቷቸው ክትባቱን በፍጥነት ቢያገኙት እንኳን ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ለማጠናቀቅና ፍጥነቱን አረጋግጦ ለገበያ ለማቅረብ ግን ቢያንስ አንድ አመት ከመንፈቅ ሳይፈጅ አይቀርም ብሏል፡፡
ለኮሮና ክትባትና መድሃኒት የማግኘቱና ለአለም የማዳረሱ ጥረት ከላቦራቶሪ ምርምርና ከሙከራ ባለፈ ከፍተኛ ገንዘብን የሚጠይቅ ነው ያለው ተቋሙ፤ አለማቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት የኮሮና ህክምና ምርምሮችን በገንዘብ እየደገፉ ቢሆንም በስፋት አምርቶ የማሰራጨቱ ጉዳይ ግን ተጨማሪ ጊዜና በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እንደሚፈልግ  ጠቁሟል፡፡
ለሌሎች በሽታዎች ፍቱን መፍትሄ የሆኑ ክትባቶች ውጤታማ ለመሆን ከ5 እስከ 15 አመታትን እንደወሰደባቸው ያስታወሰው ተቋሙ፤ ለኮሮና ቫይረስ ክትባት የማግኘቱና በአለም ዙሪያ የማሰራጨቱ ጥረትም ከዚህ የተለየ እንደማይሆን ገልጧል፡፡

አሜሪካ - ቀጣዩዋ የጥፋት ማዕበሉ መዳረሻ
ቻይናን ክፉኛ ደቁሶ ወደ ጣሊያን የተሻገረው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በቀጣይ ከፍተኛውን ጥፋት ያደርስባታል ተብላ የምትጠበቀው የአለማችን አገር ሃያሏ አሜሪካ እንደሆነች የአለም የጤና ድርጅት ባለፈው ማክሰኞ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል::
እስከ ትናንት በስቲያ ተሲያት ድረስ ከ68 ሺህ 905 በላይ ዜጎቿ በኮሮና ቫይረስ በተጠቁባትና ከ1 ሺህ 37 በላይ የሚሆኑትም ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉባት አሜሪካ፤ ባለፈው ረቡዕ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ አደጋ ላይ የወደቀውን ኢኮኖሚ ለመደገፍ የሚውል የ2 ትሪሊዮን ዶላር በጀት አጽድቃለች፡፡
ኮሮና በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች መስፋፋቱን ተከትሎ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች ለስራ አጥነት መዳረጋቸውን የዘገበው ኒውዮርክ ታይምስ፤ ባለፉት ሳምንታት ብቻ ስራ አጥ በመሆናቸው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ለሚመለከተው የመንግስት አካል ማመልከቻ ያስገቡ አሜሪካውያን ቁጥር ከ3.5 ሚሊዮን በላይ መድረሱንም ጠቁሟል፡፡
ኒውዮርክ ታይምስ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው አንድ ዘገባው እንዳለው፣ ኬንተኪ፣ ኔቫዳ፣ ኦክላሃማና ቴክሳስን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች አንዳንድ የህክምና ዶክተሮች ለኮሮና ማስታገሻ ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉ የመድሃኒት አይነቶችን ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው በገፍ እየገዙ መከዘን እንደጀመሩ ተነግሯል፡፡

ኢኮኖሚ
ኮሮና ቫይረስ የፈጠረው የጤና ቀውስ አለማችን በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያስተናገደችው እጅግ አስከፊ የኢኮኖሚ፣ የገንዘብና የማህበራዊ መናጋት ነው ያሉት የልማትና የኢኮኖሚ ትብብር ተቋም ዋና ጸሃፊ ኤንጅል ጉሪያ፤ የአለማችን ህዝቦች የኮሮና ቫይረስ ከሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለማገገም አመታትን እንደሚፈጅባቸው መናገራቸውን ኢቢሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በወረርሽኙ ክፉኛ በተጠቁ በአገራት ውስጥ እየተከሰተ ያለው የምርት መስተጓጎል በመላው አለም ያለውን የአቅርቦት ሰንሰለት ክፉኛ እንደሚያዛባውና አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚናጋም አክለው ገልጸዋል፡፡ ኮሮና ቫይረስ በአለማችን ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ጥፋት በ2008 ከተከሰተው አለማቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ የባሰ ሊሆን እንደሚችል መነገሩንም ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ወረርሽኙ በመላው አለም በርካታ ኢንዱስትሪዎችንና ፋብሪካዎችን እንዲዘጉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰራተኞችም ስራ ፈትተው ቤት እንዲውሉ በማድረግ በኢኮኖሚው ላይ የከፋ ተጽዕኖ ማስገደዱን የጠቆመው ዘገባው፣ በአንጻሩ ደግሞ የኢንዱስትሪዎች መዘጋት የአየር ብክለትን በመቀነስ በጎ አስተዋጽኦ አድርጓል መባሉን ገልጧል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በአብዛኛው የአለም አገራት ምግቦችንና የተለያዩ ሸቀጦችን የሚገዙና የሚያጠራቅሙ ሰዎች ከመበራከታቸው፣ የአገራት የምግብ ምርቶች ኤክስፖርት ከመቀነሳቸውና ከሸቀጦች ዝውውር መስተጓጎል ጋር በተያያዘ አለማችን አስከፊ የምግብ እጥረት እንደሚከሰትባት መነገሩን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ በኮሮና ቫይረስ ክፉኛ ለተጠቁ ድሃ አገራት የ2 ቢሊዮን ዶላር ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ባለፈው ሃሙስ ማስታወቃቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የአለማችን አየር መንገዶች ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በፈረንጆች አመት 2020 ገቢያቸው ከ250 ቢሊዮን ዶላር በላይ መቀነስ እንደሚያሳይ መነገሩን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ለቀጣዩ አመት የተላለፈው የቶኪዮ ኦሎምፒክም በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር  አመልክቷል፡፡

አፍሪካ በመሰንበቻው
እስካለፈው ረቡዕ ተሲያት ድረስ ኮሮና ቫይረስ በ45 የአፍሪካ አገራት ከ2ሺህ 412 በላይ ሰዎችን ማጥቃቱና 64 የሚሆኑትን ለሞት መዳረጉ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ደቡብ አፍሪካ በ709፣ ግብጽ በ402፣ አልጀሪያ በ264 የቫይረሱ ተጠቂዎች እንደ ቅደም ተከተላቸው በአህጉሩ ብዙ ሰው የተጠቃባቸው ቀዳሚዎቹ ሶስት አገራት መሆናቸው ተነግሯል፡፡
የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅንና የጉዞ እገዳን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ እንደሚገኙ የዘገበው ኦል አፍሪካን ኒውስ፣ በርካታ አገራት በረራቸውን አቋርጠዋል ድንበራቸውንም ዘግተዋል፡፡
ሩዋንዳ፣ ኬንያ፣ ሴኔጋል፣ አይቮሪኮስትና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ጨምሮ ብዙ የአፍሪካ አገራት የሰዓት እላፊና ከቤት ያለመውጣት ገደብ በዜጎቻቸው ላይ ቢጥሉም፣ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮን የሚገፉ ድሃ ዜጎች የሚበዙባት አፍሪካ “ከቤት አትውጡ” ብላ ገደብ መጣሏ የብዙዎችን ህልውና አደጋ ላይ መጣል ነው ብለው የሚተቹ እንዳሉ ታውቋል፡፡
አፍሪካ በኮሮና ያልተጠቁ ብዙ አገራት የሚገኙባት አህጉር ስትሆን፣ እስከ ትናንት በስቲያ ተሲያት ድረስ በቫይረሱ ያልተጠቁት 9 አገራት ሴራሊዮን፣ ጊኒ ቢሳኡ፣ ኒጀር፣ ብሩንዲ፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ ቦትሱዋና፣ ምዕራብ ሰሃራና ደቡብ ሱዳን መሆናቸው ተነግሯል፡፡
ኮሮና ቫይረስ በቡርኪና ፋሶ አራት የመንግስት ሚኒስትሮችን፣ በናይጀሪያ የፕሬዚዳንቱን ዋና አማካሪ እንዳጠቃ የተዘገበ ሲሆን፣ ካሜሩናዊው ዝነኛ የሳክስፎን ተጫዋችና ድምጻዊ ማኖ ዲባንጎ በሳምንቱ መጀመሪያ በኮሮና ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት መዳረጉም ተነግሯል፡፡

ሽሚያ - ከምግብ እስከ ጦር መሳሪያ
የኮሮና ቫይረስ በስፋት መሰራጨቱንና የዜጎችን የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ መግታቱን ተከትሎ ጭንብል፣ ጓንት፣ የእጅ ማጽጃ ኬሚካሎች፣ ምግቦችና የንጽህና መጠበቂያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ሸቀጦችን በጊዜ ሸምቶ ለማስቀመጥ መሽቀዳደም አለማቀፋዊ ክስተት ሆኖ ሰንብቷል፡፡
ከሰሞኑ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ያወጧቸው ዘገባዎች ግን ለክፉ ቀን ራስን ከማዘጋጀትና ምን ይመጣ ይሆን ከሚል ስጋት የመነጨው የሸመታ ግፊያና እሽቅድድም ከላይ ከተገለጹት ምርቶች አልፎ ጠመንጃና ጥይትን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የጦር መሳሪያዎች መሻገሩን ያሳያሉ፡፡
ፎርብስ መጽሄት ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዘገባው እንዳለው፤ ሜሪላንድን ጨምሮ በአሜሪካ የተለያዩ አካባቢዎች የጠመንጃ መሸጫ መደብሮች የኮሮና ቫይረስ አገሪቱን ወደ ከፋ ቀውስ ሊያስገባትና ስርዓት አልበኝነት ሊነግስ ይችላልና ራስን መጠበቅ አይከፋም ባሉ ገዢዎች ተጨናንቀው የሰነበቱ ሲሆን፣ በሁለት ወር የሚሸጡትን የጦር መሣሪያ በአንድ ሳምንት የቸበቸቡ መደብሮች መኖራቸው ተረጋግጧል፡፡
ሮይተርስ በበኩሉ ባለፈው ረቡዕ ባወጣው ተመሳሳይ ዘገባ፣ በሃንጋሪም የኮሮና ቫይረስ የፈጠረው የሸቀጦችና የምግቦች እጥረት ህዝቡን ሊያጨካክነውና ወደ ስርዓት አልበኝነት ሊመራው ይችላል ብለው የሰጉ በርካታ ዜጎች፤ ሽጉጥና አነስተኛ ጠመንጃዎችን ጨምሮ የተለያዩ አይነት ቀላል የጦር መሳሪያዎችን በወረፋ ሲገዙ ሰንብተዋል ብሏል፡፡
በሃንጋሪ የጦር መሳሪያዎች ሽያጭ በአምስት እጥፍ ያህል ማደጉንና በአንዳንድ መሳሪያዎች ሽያጩ እስከ 15 እጥፍ ያህል እንደሚደርስ የጠቆመው ዘገባው፤ ሃንጋሪና ቼክ ሪፐብሊክን ጨምሮ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ጥብቅ በሆነባቸው የምስራቃዊ አውሮፓ አገራት ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የፍላጎት መጨመር መታየቱንም አክሎ ገልጧል፡፡

እርዳታና ድጋፎች
አለማቀፍና አህጉራዊ ተቋማት፣ ኩባንያዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ለጋሾች የኮሮና ቫይረስ እያደረሰ ያለውን ጥፋት ለመቀነስና ወረርሽኙን በቁጥጥር ስር ለማዋል ለሚደረገው አለማቀፍ ጥረት፣ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፎችን ማድረጋቸውን እንደቀጠሉ ነው፡፡ የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙክበርግ፣ ለአሜሪካ የጤና ባለሙያዎች 720 ሺህ ያህል የፊት ጭንብሎችን የለገሰ ሲሆን፣ ለአነስተኛ ተቋማትም የ100 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቋል፡፡
ፖርቹጋላዊው የአለም እግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ለአገሩ ሆስፒታሎች የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶችን የለገሰ ሲሆን፣ ሌላኛው የእግር ኳስ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ የ1 ሚሊዮን ዩሮ፣ የማንችስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ የ1 ሚሊዮን ዩሮ፣ የሜዳ ቴኒስ ሻምፒዮናው ሮጀር ፌደረር የ1 ሚሊዮን የስዊዝ ፍራንክ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ዘ ኢንዴፔንደንት ዘግቧል::
አሜሪካዊው ድምጻዊ ጄምስ ቴለር የ1 ሚሊዮን ዶላር፣ ትዊተር የ1 ሚሊዮን ዶላር፣ ኔትፍሊክስ የ1 ሚሊዮን ፓውንድ፣ ታዋቂዋ ድምጻዊት ሪሃና የ5 ሚሊዮን ዶላር፣ የቴስላው መስራች ኤለን ሙስክ የጭንብል ድጋፍ አድርገዋል፡፡
 
የወህኒ ቤቶች ጉዳይ
የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መስፋፋቱን ተከትሎ በርካታ የአለማችን አገራት ቫይረሱ ወደ ወህኒ ቤቶች እንዳይገባና ከፍተኛ ጥፋት እንዳያደርስ በመስጋት እስረኞችን መፍታትን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛሉ፡፡
ኢራን በቅርቡ 85 ሺህ እስረኞችን በጊዚያዊነት የፈታች ሲሆን አውስትራሊያና እንግሊዝ የተወሰኑ እስረኞችን ለመፍታት ማቀዳቸው ተነግሯል፡፡ በኮሎምቢያ ውስጥ በሚገኝ አንድ ግዙፍ እስር ቤት ከኮሮና ጋር በተያያዘ ስጋት እስረኞች ለማምለጥ ሲሞክሩ 23 ያህሉ መገደላቸውን የዘገበው ሮይተርስ፤ በጣሊያን ውስጥ በሚገኝ እስር ቤት ሰሞኑን በተቀሰቀሰ አመጽና ግርግር ስድስት እስረኞች ለሞት መዳረጋቸውን ገልጧል፡፡
ብራዚል ውስጥ ከሚገኙ አራት እስር ቤቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ማምለጣቸው የተነገረ ሲሆን በተለያዩ የአለማችን አገራት የእስረኞች አመጽና የማምለጥ ሙከራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ዘገባው አመልክቷል፡፡ በአሜሪካ ባለፈው ሳምንት በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ በኮሮና የተያዙ እስረኞች መገኘታቸውን ተከትሎ፣ ሎሳንጀለስና ክሌቭላንድን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞች መፈታታቸው ይታወሳል፡፡

ኡሁሩ ደመወዛቸውን በ80 በመቶ ሊቀንሱ ነው
በኬንያ የኮሮና ቫይረስ መስፋፋቱን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና ምክትላቸው ለድሃ ዜጎች መደጎሚያ በሚል ደመወዛቸውን በጊዜያዊነት በ80 በመቶ ለመቀነስ መወሰናቸውን ባለፈው ረቡዕ አስታውቀዋል፡፡ የአገሪቱ ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎችም በፈቃዳቸው ከደመወዛቸው ላይ 30 በመቶ እንዲቀነስ መወሰናቸውን ከትናንት በስቲያ ባወጡት መግለጫ ማስታወቃቸውን ኦልአፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡

የወንዶች በኮሮና የመሞት ዕድል ከፍ ያለ ነው
ኮሮና ቫይረስ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ለህልፈተ ህይወት በተዳረጉ ሰዎች ላይ በተደረገ ጥናት ከሴቶች ይልቅ ወንዶች በኮሮና የመሞት ዕድላቸው ከፍ ያለ እንደሆነ የሚያመላክት ውጤት መገኘቱን ዘ ጋርዲያን ከሰሞኑ ዘግቧል፡፡
በቻይና በተደረገ ጥናት በአገሪቱ የወንዶች በኮሮና የመሞት ዕድል 2.8 በመቶ፣ በሴቶች ደግሞ 1.7 በመቶ ያህል እንደሆነ መረጋገጡን ያስታወሰው ዘገባው፤ በፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኢራን፣ ጣሊያን፣ ደቡብ ኮርያና ስፔን የተደረጉ ሌሎች ጥናቶችም ኮሮና ከሴቶች ይልቅ ወንዶችን የመግደል አዝማሚያ እንዳለው ማረጋገጣቸውን አመልክቷል፡፡
በጣሊያን እስካሁን ድረስ በኮሮና ቫይረስ ለሞት ከተዳረጉት መካከል 71 በመቶው ወንዶች መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ በስፔንም በቫይረሱ ለሞት የተዳረጉ ወንዶች ከሴቶች በሁለት እጥፍ ያህል እንደሚበልጡ መረጋገጡን ገልጧል፡፡
 
“ከመለያ ቦታ ያመለጠ በስቅላት መቀጣት አለበት!”
የቺቺኒያው መሪ
በሩሲያ የቺቺኒያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ራምዛን ካዲሮቭ፣ በአገሪቱ በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥሮ ከገባበት መለያ ቦታ አምልጦ የወጣና ቫይረሱን ወደ ሌሎች ሰዎች ያስተላለፈ ሰው በስቅላት መቀጣት አለበት ሲሉ መናገራቸውን ኒውስ ዊክ ዘግቧል፡፡
ከውጭ አገራት የሚገቡ ሰዎች  ለሁለት ሳምንት ያህል ራሳቸውን ከሌላው ሰው አግልለው እንዲቆዩ ጥብቅ ትዕዛዝ ያስተላለፈችው ደቡብ ኮርያ በበኩሏ፤ ይህን መመሪያ ተላልፎ የተገኘ ሰው የሌላ አገር ዜጋ ከሆነ ወደ አገሩ እንደሚላክ፣ ዜጋ ከሆነ ደግሞ እስከ አንድ አመት የሚደርስ እስርና የ8 ሺህ 100 ዶላር የገንዘብ ቅጣት እንደሚጣልበት ከትናንት በስቲያ አስጠንቅቃለች::

ሃኪሞች  እየሞቱ ነው
አስፈላጊው የመከላከያ ቁሳቁስ ሳይሟላላቸው በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ዜጎችን በማከም ላይ እያሉ በቫይረሱ የሚጠቁና ለሞት የሚዳረጉ የህክምና ዶክተሮች ቁጥር እያደገ መምጣቱ የተነገረ ሲሆን፣ በፊሊፒንስ ዘጠኝ ዶክተሮች በዚህ ሳቢያ ለሞት መዳረጋቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በስፔን በኮሮና ቫይረስ ከተጠቁት ሰዎች መካከል 14 በመቶ ወይም ከ5 ሺህ 400 በላይ የሚሆኑት ዶክተሮችና ሌሎች የህክምና ባለሙያዎች መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፣ በፈረንሳይና ጣሊያን ከ30 በላይ የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው ለሞት መዳረጋቸውንና ሌሎች በሺህዎች የሚቆጠሩ በመለያ ቦታ እንደሚገኙም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡


Read 14470 times