Tuesday, 31 March 2020 00:00

“አይባልም!”

Written by  አዛኤል
Rate this item
(2 votes)

     “በአለም የሚኖረው ቋሚ ነገር ቋሚ ነገር አለመኖሩ ነው” እንዳለው ስሙን የማላስታውሰው ፈላስፋ፤ የሰው ልጅ ምድርን ግዛት ተብሎ ወይም ምድርን ግዛት አድርጎ ከተሰየመበት ጊዜ ጀምሮ ለአንድም  ጊዜ እንኳ ሲገታ የማናየው ተፈጥሮ ቢኖር ‘ለውጥ’ን ብቻ ነው፤ ለውጥ ተፈጥሯዊ ነው፤ ተፈጥሮ በለውጥ ውስጥ ትኖራለች፡፡
መሬት ስናወርደው….
1966 ዓ.ም  በጥር ወር ላይ ለመጀመሪያ ሙከራ የታተመው በኢትዮጵያውያን የዩኒቨርሲቲ መምህራን የውይይት ማህበር የተዘጋጀው ‘ተራማጅ  መዝገበ ቃላት ፤የፅንሰ-ሀሳብ ቃላት መፍቻ’ ጥራዝ፤ “ለውጥን፦ ከአንድ ነባር ሁኔታ ወደ ሌላ ሁኔታ መቀየር ነው”  ብሎ ይፈታዋል፤ እንግዲህ በለውጥ ወይም በመቀየር መርህ መሰረት፤ እንደ ማንኛውም ተፈጥሯዊ ስርዓት የመንግስት ስርዓት  መቀያየርም ግድ ነው (ለመሪዎች ባይዋጥላቸውም)፤ ሃገረ ጦቢያም የዚሁ ለውጥ ባለቤት መሆኗ አልቀረላትም፤ በየ 30 በየ 40 አመቱ ቢሆንም ፤ በርግጥ እንደ  አፍሪካ መሪዎች እሳቤ የሆድ ቁርጠትን ወደ  እግር እብጠት  መውሰድ በራሱ ለውጥ ነው፤ ለምን? ቢሉ ህመሙ  ከነበረበት ሁኔታ ወደ ሌላ ሁኔታ ተቀይሯልና፤ ለውጥ ነው! ለውጥ ነው! ካሉ አሉ ነው ……አበቃ!
ሁሉም ለውጥ የቀዶ ጥገና ያህል ጥንቃቄ ቢያሻውም ሀገረ-መንግስታዊ ለውጥ ግን ግዘፍ በነሳ መልኩ አስተውሎትን ይጠይቃል፤ የግለሰቦች ህልውና መነሻውም መቅመሻውም መድረሻውም  ቤተ መንግስት ያለው  ስነ-መንግስት ነውና፤ አንድ ደራሲ እንዳለው ልደታችንም ሞታችንም ከዚሁ ጊቢ ነው የሚመነጨው፤ ስለዚህማ ከፖለቲካዊ እሳቤ እኛ ለመራቅ ‘ፎድ’ ብንል እንኳ እነሱ ከፊት ይቀድሙናል፤ እኛ አያገባንም ብንልም እነሱ እና ስርዓታቸው ግን ካገቡን ቆይተናል፡፡  
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ…..
ታዲያ ይሄ ትቶ የማይተወን ፖለቲካ ይሉት ቁማር  እለዋወጣለሁ ይለናል፤ ሲለዋወጥ ብቻውን አይደለም፤ እኛን ለማን  ትቶ?  ዳሩ ለውጥ ከነበረው ነገር መቀየር ቢሆንም ለሰው የሚያስፈልገው ለውጥ ግን  
‘ከነበረው ሁኔታ ወደ ተሻለ ሁኔታ ‘መቀየር የምንለው ነው፤ መሻሻል የሌለው ለውጥ ለሰው ምን ይረባዋል?
ሃገረ  ላቤሪያ በሳሙኤል ዶይ፣ ኡጋንዳ በኢድ ያሚን፣ ማዕከላዊት አፍሪቃ በንጉስ ቦካሳ፣ ዚምባቡዌ በዛ.ኑ.ፒ.ኤፍ  መስራች ሮበርት ሙጋቤ፣ ሊቢያ በኮለኔል  ሙሃመድ ጋዳፊ፤ ግብፅ በሁስኒ ሙባረክ፤ አማካኝነት ህዝቦቻቸው የለውጥ ብርሃንን እናያለን ብለው እንደ ህፃን ገላ በጠዋቷ ፀሀይ የሰላም ሙቀት ቢሰማቸውም  የሁሉም  መሪዎች  “ለውጥ አመጣንልህ” ባይነት ግን የቀትር ፀሀይ ያክል አንገብግቦ አክስቶታል፤ እርግጥ ግን እነኚህ ሰዎች  ሀገራቸውን ከነበረበት ሁኔታ አላወጡትም ማለት ግን አይደለም፤ ግን ወደ ምን አይነት ለውጥ?
የአፍሪቃ መንታ ወደሚመስለኝ አፈታሪክ  ልውሰዳችሁ …….
  የእጓለ ገብረዮሃንስ  ከፍተኛ ትምህርት ዘይቤን ሳነብ ነው ያገኘሁት፤  አፈታሪኩ ወይም ሚቶሎጂው የግሪካውያን ነው፤ ይህም ‘ዳናኢዴስ’ ስለሚባሉት ሴቶች ነው፤ እነኚህ ሴቶች ለባሎቻቸው የሚገባውን  እምነት ሳይጠብቁ ቀርተው ኖሮ ሲወሰልቱ ተገኝተዋል፤ ታዲያ የጋብቻን ንፁህነት በሚጠብቁት አማልክት ዘንድ ተከሰው በደላቸው  ታውቆ እንዲቀጡ ተፈረደባቸው፤ ፍርዱም ….የተሸነቆረ ማድጋ ውሀ እንዲሞሉ ነበር፤ መቼም የማይሞላን ማድጋ የመሙላት ፍርድ፡፡
 ጥቁሩ አህጉር እያሉ ነጮቹ የሚጠሩን እኛ አፍሪቃውያንም በማን እና በምን ላይ እንደወሸምን ባላውቅም፤ ዘመናችን ሁሉ ግን የ‘ዳናኢዴስ’ ሆኖብናል፤ የተሸነቆረ ታሪክ  የማያጣን፤ ምን  ማድጋችንን ለመሙላት ብንጥር  አልሞላ የሚለን ዘላለም አንድ አይነት አዙሪት የሚያዞረን….ነን፤ የወቅቱም የሃገረ ጦቢያ ‘ለውጥ’ የማድጋው  አይነት እጣ ፈንታ የገጠመው ይመስላል፤ ህዝቡም መሪዎቹም ለሚከሰተው የማድጋ መሸንቆር ችግር ሁሉ  ሃላፊነትን ለመውሰድ ሲሸሹ መመልከት የተለመደ ሆኗል፤ ወትሮስ እርስ በእርሳቸው “ለውጡ የህዝቡ ነው”፤ “ለውጡ የነእገሌ ነው” እየተባባሉ ሲንቆለጳጰሱ ከርመውብናል፤ የለውጡን ምንጭነት ያላመነ አካል የለውጡንም ሰንኮፍ ምንጭነት አያምንም፤ ለዚህ ነው ለውጡ ‘ኑ ውጡ’ በሚሉ በየአቅጣጫው በተነሱ ጎበዞች የተሞላው፡፡
ህዝብ ከቤተ-መንግስት ሲጣረስ እንደ ማየት ክፉ ነገር የለም፤ ለውጥ ከገባው ፓርቲ ይልቅ ለውጥ  ያልገባው  ህዝብ አስፈሪ ነውና፤ እንኳን ተግባሩ ምኞቱም አይያዝም እና፤ የህዝብ የለውጥ አረዳድ ሲዛባ ፦እነሆ ምሳሌ  
ቤት እሰራ ብዬ፣ ልጅ አሳድግ ብዬ፣ ባገር እኖር ብዬ ለወታደር ዳርኋት ሚሽቴን እቴ ብዬ፤  
እያለ በወታደሩ አፈሙዝ እየተገደደ  ሃብቱን ንብረቱን ሲያጣ የነበረው ገበሬ ምሬቱን አንጎራጉሯል፤ ታዲያን  አፄ ምኒልክ ወላይታና ሲዳሞን አስገብረው ከብቱ  ላለቀበት ለሸዋ ሰው መጸወተ፤ ከዚህ በኋላ በ3ኛው  ዘመን ጥጋብ ሆነ፤ አፄ ምኒልክም “ከባላገር ደጅ የደረሰ ወታደር ብርቱ ቅጣት እቀጣዋለሁ፤ ብዙ ቢሆን ከሜዳ ሰፍሮ ስንቁን በልቶ ይደር፤ አንድ ከሆነ የእግዜር እንግዳ ነኝ ብሎ በውድ ይደር፤ ብለው አዋጅ አስነገሩ፤ በዚህ ጊዜም ባላገር ሁሉ መብቱ ተጠበቀለት፤ ለወታደር ያበላው የነበረውን ለራሱ አደረገ፤ ታዲያ አፄ ምኒልክ  በአዋጃቸው የገበሬውን መብት መልሶ በመስጠት ለውጥን ቢያውጁም፤ ጥጋብ በሆነ በአመቱ  የስናን እየሱስ  ደገኛ (የደጋ ሴት) እማይረሳውን የረሃብ ዘመን ረስታ ጠገበችና  እንዲህ አለች፤ ይሉናል አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ፡-
ጉንጬም ቅጥ አጣ ቂጤም ቅጥ አጣ
እባክህ ጌታዬ የአምናውን ቀን አምጣ፤   
ለውጡን ከመርዳት በላይ ለውጡን መረዳት ይቀድማል እና፤ የብሔር ፖለቲካው ዜጎችን እያንጓለለ፤ የዜግነት ፖለቲካው ብሔሮችን እያገለለ፤ የሃይማኖት ፖለቲካው ሌሎች  አማኞችን እያስገደለ ፤ የሃሳብ ፖለቲካው ማሰበ የጠሉ ምሁራንን እያገለገለ፤ እውነት እውነተኛ ለውጥ አለ? ማለትን ይጠይቃል፤ያጠያይቃል፤ የድብድብ ፖለቲካ ትተን የንግግር ፖለቲካ ካላሰብን፤ የሰው ሰራሽ የቲዎሪ ፖለቲካ  አቁመን የሰው ፖለቲካ ካልተለማመድን፤ ወገን……. እንደ ሰው ሳንኖር እየሱስ መምጣቱ ነው፡፡
ለሰው መቀየር በራሱ ግብ አይደለም፤ ወዴት እንደምትቀየር ማንን እና ምንን እንደምትቀይር ካላስተዋልከው ለውጥ ብቻውን የመንፈስ ነውጥን ያስከትል ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ከማሰብ ወደ አለማሰብም መሄድ ለውጥ ነውና፤ ህልው ከመሆን ወደ ሞት መጠራትም በራሱ ለውጥ ነውና፤ እኛ እኮ  ከንጉሳዊ ስርዓት ወደ ፕሬዚዳንታዊ ስርዓት መቀየር በራሱ ለውጥ ነው ያልን ጀግኖችም ነን፤ ሁሉም ለውጥ ግን ወዴት ይወስዱናል ብሎ መጠርጠር ኋላ ላይ “የት ነኝ?” ከማለት ያድናል፤ “ሳንርቅ እንጠይቅ” ብሎን የለ ገጣሚ ሙሴ፤ በመጨረሻ በተራማጅ መዝገበ ቃላት ፍቺ ላይ የተቀመጠውን የለውጥ ሙሉ አንቀፅ  አስቀምጠን እኛ እንውጣ፤ “ለውጥ፦ ከአንድ ነባር ሁኔታ ወደ ሌላ ሁኔታ መቀየር ነው፤ ለውጥ የጥራት ወይም የመጠን ሊሆን ይችላል፤ የጥራት ለውጥ መሰረታዊ ሲሆን የመጠን ለውጥ ግን ተራ ነው” -- መቀየር ብቻውን ለውጥ “አይባልም”

Read 8005 times