Saturday, 28 March 2020 16:12

የአድማስ ትውስታ

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

  ከነነዌ እስከ ባቢሎን፤ የከተማ ትሩፋትና “የማይዘልቅ ታላቅነት”?
                         

              ከተሞች፣ የሰው ልጆችን ድንቅ ተፈጥሮ የሚመሰክሩ፣ የእውቀትና የትምህርት፣ የሥራና የብልፅግና፣ የሰላምና የስልጣኔ መነሃሪያ ቢሆኑም፤... ብዙዎቹ አንጋፋ ከተሞች፣ እንደ አጀማመራቸው አልዘለቁም። ብዙዎቹ የጥንት ከተሞች፣ ዛሬ የሉም። ፈራርሰው አፈር ሆነዋል። በአሸዋ ተቀብረዋል። ተቃጥለው አመድ ሆነዋል። ብናኝ ሆነው ተበትነዋል።
ጥንታዊዎቹን እንደ ባቢሎን፣ ነነዌ፣ አሦርና ትሮይ የመሳሰሉ ከተሞችን ብቻ ሳይሆን፤ የአገራችን ከተሞችንም ማየት ይቻላል። በታሪክ እንደሚወሳው፤... ሐረር፣ ጎንደር፣ ይፋት፣ አክሱም የመሳሰሉ፣ የስልጣኔ ግስጋሴን በአርአያነት ያሳዩ ከተሞች፤ በተለያየ ጊዜ፣ ለውድቀት ተጋልጠዋል። በአመፅ የተቃጠሉ፣ በወረራ የተዳከሙ፣ ቀስ በቀስ እየተፍረከረኩ ከእይታ የጠፉ ከተሞች ብዙ ናቸው።
እንዲያውም፤ በስልጣኔ የዘለቁ ከተሞች፣ ብዙም አይገኙም። ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአለም ዙሪያ፣ ብዙዎቹ ጥንታዊ ከተሞች፣ ከምድረገፅ ጠፍተዋል። እንደምንም ከጠቅላላ ጥፋት የተረፉት ጥቂት ከተሞችም፤ ከአንድም ሁለት ሦስቴ፣ የተቃጠሉና የፈራረሱ፣ እንደገና ለማንሰራራት የሞከሩ ናቸው - አቴንስንና ሮምን ጨምሮ። አንዳንዶቹ በወረራ ነው። ሌሎቹ ደግሞ፣ በነዋሪዎች ስህተት፣ ድክመትና ጥፋት ሳቢያ።
እንዴት? እንደ ነነዌ ወይስ እንደ ባቢሎን?
ብዙ አዋቂዎች፣ ብዙ ሙያተኞችና ብዙ መልካም ሰዎች ድንቅ ታሪክ ሊሰሩ ይችላሉ። እውቀታቸውን በጽሑፍ አስፍረው፤ ስራቸውን በድንቅ ግንባታ አንጸው፣ ሰብዕናቸውን በጀግንነት ታሪክ አስመዝግበው፣ ለልጆቻቸው ያወርሳሉ። ነገር ግን፤ የስራ ውጤታቸውን ያወርሳሉ እንጂ፤ ስራን ማውረስ አይችሉም። እውቀትን፣ ሙያን፣ ብቃትን... በዘር ወይም በነዋሪነት የሚተላለፍ ውርስ አይደለም። እናም፣ ልጆች እንደ አባቶቻቸው ላይሆኑ ይችላሉ።
ቀስ በቀስ፣ መንገድ እየሳቱና እየተንሸራተቱ፣ ከእውቀት ብርሃን እየሸሹ፣ ከስራ ጎዳና እያፈነገጡ፣ ከብቃት ከፍታ እየወረዱ... ወደ ጨለማ፣ ወደ ገደል፣ ወደ ውርደት ይዘቅጣሉ።
ትንቢተ ዮናስ የተሰኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ትረካ እንደሚነግረን ከሆነ፤ “ታላቂቱ ነነዌ”፣ እንዲህ እስከ መጨረሻው ተብረክርካና ተበላሽታ እንጦሮጦስ አፋፍ ላይ አልደረሰችም። የነነዌ ሰዎች፣... ትንሽ ነው መንገድ የሳቱት። ጥፋታቸው ገና አልገነነም። ሰብዕናቸው ብዙ አልዛገም። ግን ጀማምሯቸዋል።
ይሄኔ፣ እየሩሳሌም አቅራቢ የነበረው ዮናስ፣ ትዕዛዝ ደረሰው። ወደ ነነዌ ሂድ፤... የቅጣት መዓት እንደሚወርድባቸው ንገራቸው ተባለ።
ኧረ? ፈጥኖ ተነሳ። ታዲያ፣ የዮናስ ጥድፊያ፣ ወደ ነነዌ ለማቅናት አይደለም። ከትዕዛዝ ለመሸሽ ነው። በእግር፣ በመርከብ... ለማምለጥ ሮጠ። ግን አልጋ ባልጋ አልሆነለትም። መርከቢቱ ጉዞ እንደጀመረች፣ ባሕሩ በአውሎነፋስ ተናጠ፤ በማዕበል ተናጋ። ተሳፋሪዎች፣ የቻሉትን ሁሉ ሞከሩ። የመርከቢቱን ክብደት ለመቀነስ፣ ብዙ የሸቀጥ ጭነትና እቃ እያነሱ፤ ወደ ባህር ወረወሩ። ሙከራቸው፣ ውጤት አላስገኘላቸውም። ሲጨንቃቸው ጊዜ፣ እንደየእምነታቸው፣ ለየአምላካቸው ፀለዩ። እሪ አሉ። ጮሁ። ይሄ ሁሉ ሲሆን፣ ዮናስ ደንታ አልሰጠውም።
ተጋድሞ፣ እንቅልፉን ይለጥጣል። ‘ባሕሩ የሚናወጠውና መርከቢቱ ተሰባብራ ልትበታተን የደረሰችው በኔ ምክንያት ነው’ ብሎ አምኗል። ግን፣ ከትዕዛዝ ለማምለጥ መሸሹ፣ እንደጥፋት ሊቆጠር አይገባም ባይ ነው። እናም፣ በድርጊቱ አልተፀፀተም። ተሳፋሪዎች ይህንን አውቀዋል።
ግን ዮናስን፣ ወደ ባህር ሊወረውሩት አልፈለጉም ነበር። አምላክን ለማግባት ሞከሩ። “በአንድ ሰው ጥፋት ሁላችንንም መቅጣት ተገቢ አይደለም። ንፁሃን ነን፤ የንፁሃንን ደም ማፍሰስ የለብህም” በሚሉ ሃሳቦች አምላክን ለማሳመንና ለመለማመጥ ብዙ ቢናገሩም፤ ነውጡና ቀውሱ አልተረጋጋም። በመጨረሻም፣ አማራጭ የለንም ብለው፤ ዮናስን አንስተው ወደ ባህር ወረወሩት። ወዲያውኑ ነው፤ ሁሉም ነገር የተረጋጋው።
አውሎነፋሱ በረደ፣ ማዕበሉም ረገበ። በዮናስ እጣፈንታ ቢያዝኑም፣ ከሞት በመትረፋቸው በእፎይታና በምስጋና ጉዟቸውን ቀጠሉ።
ዮናስ ግን፣ እንጦሮጦስ ወርዷል። ጨለማ ሲኦል ውስጥ ገብቶ ተዘግቶበታል - የአሳ ነባሪ ሆድ ውስጥ።
እዚያ ውስጥ ሆኖ፣ ወደ አምላክ እንደጮኸና እንደተጣራ የሚነግረን ዮናስ፣ ጩኸቱም ሰሚ እንዳገኘ ይገልጻል። አሳው፣ ዮናስን ወደ ምድር ተፋው። ታዲያ፣ ከዚያ ሁሉ ስቃይ በኋላም፣ በአቅመቢስነትና በሚስኪንነት አንገቱን አልደፋም።
እንዲያውም፤ በራሱ መልካምነት ከስቃይ እንደተላቀቀ ይጠቁማል። ከሞት አምልጦ በእፎይታ ለመተንፈስ የበቃው፣... እውነተኛና ቁምነገረኛ በመሆኑ ነው። ሌሎች ሰዎች ግን፣ በሃሰትና በከንቱነት ተዘፍቀው፣ ከጥፋት ማምለጥ ይሳናቸዋል።
ከዚያስ?
እንግዲህ፣ በመርከብም ሆነ በአሳ ነባሪ አማካኝነት፣ በዛሬዋ ኢራቅ ውስጥ ወደምትገኘው የነኔዌ ከተማ ዘንድ ደርሷል። ነዋሪዎቹን ማስጠንቀቅና መዓት ይመጣባችኋል ብሎ ትንቢት ማውራት ባይፈልግም፤... ተናገረ። “በአርባ ቀን መዓት ይወርድባችኋል” ብሎ አስጠነቀቃቸው። መንገዳችሁን አስተካክሉ ብሎ መከራቸው።   
ነነዌ ዝነኛ ከተማ ናት። ነበረች - በጊዜዋ። “እጅጉን የገነነች ከተማ” ተብላለች - የዮናስ ትንቢት ላይ። 120ሺ ሕዝብ የሰፈረባት፤ “ወደረ የለሽ” የሚል ማዕረግ የተሰጠው ባለ 80 ክፍል ቤተ መንግስት የተገነባባት፤ ወረራዎችን ለመከላከል 12 ኪሎሜትር የግንብ አጥር የቀሰረች፤... ከአራቱም አቅጣጫ የንግድ መተላለፊያና መናሃሪያ የሆነች ድንቅ ከተማ ናት።
የቱን ያህል እንደበለፀገችና እንደሰለጠነች ለመገመት ከፈለጋችሁ፣ የከተማዋን ውኃ ማየት ነው። ከ50 ኪሎሜትር ርቀት፣ ወንዞችን በመገደብና ቦዮችን በመዘርጋት ነው፤ ከተማዋ ውኃ የምታገኘው። አዋቂዎችና ጥበበኛ ባለሙያዎች ነበሯት ማለት ነው - እውቀትና ትምህርት የተከበረባት፣ የግዙፍ ቤተመጻህፍት ባለቤት የሆነች ከተማ ናትና። በታታሪነት የሚሰሩና የሚያመርቱ፣ በንግድና በግብይት ኑሯቸውን የሚያሻሽሉ፣ ብዙ ነዋሪዎች ነበሯት ማለት ነው። ብልፅግናው እንዲሁ በከንቱ የመጣ አይደለም። ከእውቀትና ከትምህርት፣ ከሙያና ከትጋት፣ ከብቃትና ከስነምግባር፣ ከመልካምናትና ከቅዱስ ሰብእና፣ ከመልካም ባሕል ጋር እንጂ።
ይሄ የዛሬ 2700 ዓመት ገደማ ነው - ዋና ከተማ የሆነችበት ዘመን። ሰፋፊ አውራ ጎዳናዎችና ያማሩ አደባባዮች በተሰሩላት ከተማ ነው፣ ወደር የለሹ ቤተመንግት የተገነባው። አምስት የእግርኳስ ሜዳዎችን ይሸፍናል - ስፋቱ። ርዝመቱና ወርዱ፣ 190 ሜትር በ180 ሜትር ገደማ ነው። ባማረው የቤተመንግስት ግንብ ዙሪያ፣ በርካታ ከብረትና ከድንጋይ የተቀረጹ የጥበብ ሥራዎች ተደርደረዋል። በመዳብ በተለበጡት በሮችም፣ በቅርጻ ቅርጽ ጥበብ የተዋቡ ናቸው።
የአዳራሾችና መኝታ ቤቶች፣ ቢሮዎችና የእንግዳ መቀበያ፣ መዝገብ ቤት እና መጋዘኖችን ጨምሮ 80 ክፍሎች በተገነቡለት ቤተመንግስት፤ ትልቅ ቤተመጻሕፍት ይዟል። ቢያንስ ቢያንስ በ20ሺ ግዙፍ ሰነዶች የተደራጀው ቤተመጻሕፍት፣ የሂሳብ፣ የሳይንስ፣ የሃይማኖት፣ የአስተዳደር፣ የመማሪያና የጥበብ ጽሑፎችን ያካትታል።
እንደ ዘመኑ ድንቅ ከተሞች ሁሉ፣ ነነዌም፣ ግዙፍ መንፈሳዊ ስፍራ ነበራት - ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ።
የዛሬ 4000 ዓመት ገደማ “ኡር” የተሰኘችው ዋና ከተማ፣ 65 ሜትር በ45 ሜትር ወለል ላይ የተመሰረተና ሽቅብ እንደፒራሚድ የተገነባ ሕንፃ ሰርታለች። በሦስት እርከኖች የተከፈለው የሕንፃው ቁመት፣ አንደኛውን ለመዝለቅ፣ 100 ደረጃዎችን መራመድ ያስፈልጋል።  ይሄ 15 ሜትር ቁመት አለው። በዚህ የመጀመሪያ እርከን ላይ ነው፤ ሌሎች ሁለት እርከኖች የሚጨመሩበት።
የሜሶፖታሚያ (የአካድ፣ የሱመር እና የአሦር) ከተሞች ጉደኛ ናቸው። ግን ባቢሎንን የሚስተካከል የለም።
ከተማዋን ለመጠበቅ በተገነባው አጥር ዙሪያ ካሉት በሮች መካከል አንዱን ብቻ መመልከት ይቻላል። በሩ ሕንፃ ነው ማለት ይቻላል። ቁመቱ 24 ሜትር ይደርሳል። የተገነባው፣ ወደ መሬት ስር 20 ሜትር ተቆፍሮ በተገነባ መሰረት ላይ ነው።
በእውቀትና በአእምሮ፣ በጽሑፍና በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በስራ እጅጉን በስኬት የተራመዱ አስገራሚ ሰዎች የነበሩበት ዘመን ነው።
ከጊዜ በኋላ ግን፣ እንዳልነበሩ ሆነው ጠፍተዋል።
አዎ፤ በዮናስ ትረካ ውስጥ፣ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ መንገዳቸውን ስላስተካከሉ፣ ከመዓት ተርፈዋል። ግን ብዙም ሳይቆይ፣ ድንቋ ከተማ ነነዌ፣ በውድቀት ጠፍታለች። ከሷ የሚበልጡት እነባቢሎንም ጠፍተዋል። ለምን?
በስልጣኔ እስከ ታላቂቱ ባቢሎን፣ ከእውቀት እስከ ሰማይ ጠቀስ
የኢራቅ ምድር፣ በዛሬዋ ባግዳድ እና በዛሬዋ ሞሱል ዙሪያ ያለው ምድር፣ በሁለት ታላላቅ ወንዞች የተከበበ ለም መሬት ነበር ያኔ። ግን ድንጋይ እንደልብ አይገኝም።
አፈር፣ ውሃ እና እሳት በብልሃት በማቀናጀት፣ አፈርን በውሃ ተለውሶ በሳጥን ቅርፅ ሲጠፈጠፍ፣ ከዚያም በእቶን ሲጠበስ በእሳት ሲተኮስ... እንደ ጥርብ ድንጋይ ይሆናል። ሸክላ ተፈጠረ። “ሰው ሰራሽ ድንጋይ” ብለን ልንጠራው እንችላለን።
ይሄ ውጤት፣ ከሰማይ የሚዘንብ ሲሳይ አይደለም። ከእውቀት ነው የሚነጨው። የነገሮችን ምንነት ከማገናዘብ፣... የአፈር፣ የውሃ፣ የእሳት ምንነትንድ ከማወቅ ነው የሚነሳው። በምንነታቸው መሰረት፣ በልዩ ዘዴ ሲቀናጁ፣... የሸክላ ቴክኖሎጂ ተፈጠረ። እሺ፣ ሰው ሰራሽ ድንጋር ለመፍጠር ቻለ እንበል!... ጥሩ። ግን ምን ትርጉም አለው? ምን ይፈይዳል? ያ ሁሉ ውጣውረድና ጥረታ ግረት፣ ለምን አስፈለገ? ምን ለማትረፍ? ለምን አላማ?
መጠለያ፣ መኖሪያና መተዳደሪያ ለመስራት፣  ለማሻሻል፣ ለማሟላት፤...  ቤት ለመስራት፣ መንገድ ለመጥረግና ለማንጠፍ፣ የውሃ ግድብ ለመገንባት፣ የመስኖ ካናል ለመዘርጋት፣...
የእውቀት፣ የፈጠራ፣ የጥረት ዋጋ የሚመዘነው፣ ፋይዳውም የሚሰፈረው፣ ለኑሮ በሚያበረክተው ውጤት ነው። ኑሮን ለማሻሻልና ለማበልፀግ በሚያበረክተው ውጤት ነው የሚለካው። እውቀትና ኑሮ፣ አእምሮና አካል ስምም ሆነዋል ማለት ነው።
ግን፣ የአእምሮና የአካል መስማማት፣ የአስተዋይነትና የጥረት መሰናኘት፣ የእውቀትና የምርት ስኬት መጣጣም ብቻ በቂ አይደለም።
በዚያው ልክ፣ “አካላዊ የኑሮ ብልፅግና ከመንፈሳዊ እርካታ ጋር”፤... “አእምሯዊ የእውቀት ብስለትም፣ በግል ብቃት ላይ ከተመሰረተው የእኔነት ክብር ጋር” ሲዋሃዱ ነው፣ ሕይወትን በምልዓት ማጣጣም የሚቻለው።
ኑሮው እንዲሻሻል፣ የምርት ስኬትንና ብልፅግናን ይሻል። ማንነቱም፣ በብቃት እና በጀግንነት ባሕርይ መታነፅን ይጠይቃል። ሰብእናው በእኔነት ክብርና በእርካታ የሕይወትን ጣዕም ማጣጣምን ይሻል። በየጊዜውም፤ የሌሎች ሰዎችን ብቃትና ጀግንነት በማየት፣ መንፈሱን ማደስ ያስፈልገዋል። ቀላል ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።
የስፖርት ውድድሮችን በፍቅር የምንመለከተው፣ ኦሎምፒክን በጉጉት የምንጠብቀው፣ በሌላ ምክንያት አይደለም - ብቃትን በእውን ለማየት፣ የጀግኖችን ስኬት በአይናችን ለመመስከር ነው።
የባቢሎን ሰዎችም፣ በመኖሪያ ቤት ብቻ የታጨቀች ከተማን አልገነቡም። ከመኖሪያ ቤት ጎን ለጎን፣ ብቃትን አጉልቶ የሚያሳይ፣ የእኔነት ክብርንም አግዝፎ የሚመሰክር፣ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ ለመገንባት ነበር የተነሱት። ስም የሚያስጠራ፣ እርስበርስም የሚያስተሳስርና የሚያሰባስብ ሰማይ ጠቀስ ህንፃ፣ እንገነባለን ብለዋል።
እርስ በርስ የሚያግባባቸው፣ እርስ በርስ የሚያስማማቸውና እርስ በርስ በየሚያቀራርባቸው ነገር ምንድነው?
እውቀትና ሙያ ያግባባቸዋል - አእምሮ አላቸው። በዚህ እውቀትም ሸክላ ፈጥረዋል። ዘዘ
ኑሮን የማሻሻልና የማበልፀግ አላማ ያስማማቸዋል። ከተማ እንገነባለን ብለዋል።
ብቃትን በእጅጉ የማድነቅና የማክበር ሰብእናም ያቀራርባቸዋል። ይህንን የሚመሰክር ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ ይገነባሉ። መግባቢያ ቋንቋ!
ሁሉንም የባቢሎን ነዋሪዎች በጅምላ መፈረጅ የለብንም። ይልቅስ፣... የእውቀት፣ የሥራ እና የጀግንነት ባለቤት የሆኑትን የባቢሎን ሰዎች፣ እንመልከት።
መግባቢያ ቋንቋቸው፤ ጭፍን እምነትና ጭፍን ስሜት አይደለም። መግባባት የቻሉት፣ በእውነታ ላይ እና በአእምሮ ላይ የተመሰረተ፣ የጠራ የነጠረ እውቀትን ስለያዙ ነው። “ኑ፥ ጡብ እንሥራ፥ በእሳትም እንተኵሰው ተባባሉ። ጡቡም እንደ ድንጋይ ሆነላቸው።” የተስማሙትስ እንዴት ነው?
ኑሮን የማሻሻልና የማበልፀግ የየግል አላማቸው ነው፣ ያስማማቸው። “ኑ፤ ለራሳችን ከተማ እንስራ” ተባባሉ።
ተባብለው አልቀሩም። ወደ ጥረት፣ ወደ ተግባር ተሸጋግረዋል። “ይህንንም ማድረግ ጀመሩ” ተብሎ ተጽፏልና። “አላማቸውን መተግበር ጀመሩ” እንደማለት ነው።
የተቀራረቡትስ በምን ሳቢያ ይሆን?
ብቃትን ስለሚያፈቅሩ፤ ጀግንነትን ስለሚያደንቁ ነው የተቀራረቡት። ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ መስራት የመሩትም፤ ይህንኑን አጉልተው ለማሳየት ነው - ለብቃት ያላቸውን ፍቅር፣ ለጀግንነት ያላቸውን ክብር ለመግለፅ፣ ለማወደስ ነው ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ የሚገነቡት። መንፈሳዊ ተቋማት ናቸው ማለት ይቻላል። በዘመናው ገፅታቸው ደግሞ፤ ከግዙፍ ትያትር ቤቶች እና ከመዝናኛ ስቴዲየሞች ጋር ልናመሳስላቸው እንችላለን።
ከእንግዲህ የሚያስቆማቸው የለም!
እውቀትንና ስራን፤ እውነትንና አላማን ከእኔነታቸው ጋር አዋህደው፤ ድንቅ የብቃትና የጀግንነት ሰብዕናን ተቀዳጅተዋል። “ከአንግዲህ፣ የሰቡትን ለመስራት፣ ለማሳካት አይሳናቸውም” የተባለላቸውም በዚህ ምክንያት ይመስላል።
ሥማቸውን የሚያስጠራ ሰማይ ጠቀሱ ሕንፃም... ይህንን ቅዱስና ድንቅ ሰብዕናቸውን ይመሰክራል። የብቃት ቤተመቅደስ ልንለው እንችላለን። ብቃትን የተጎናፀፉ ጀግኖች የሚወደሱበት፣ የጀብድ ታሪካቸው እየተወሳ ምስክርነት የሚተረክበት፤ ሕፃን አዋቂው ሁሉ ለላቀ ብቃት የሚነሳሳበት፣ መንፈሱን የሚያነቃቃበት ስፍራ ነው። የብቃት ሙዚዬም ብለንም ልንጠራው እንችላለን - ለምሳሌ የሳይንስ ጠበብቶች፣ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች፣ በምርታማነት የመጠቁ የቢዝነስ ጌቶች፣... የኦሎምፒክ ባለድል አትሌቶችንም ጭምር፣ በየመስኩ ባለ ስኬትና ባለ ብቃት ጀግኖች፣ በድምቀት የሚዘከሩበት ነው። ገድላቸውንም አጉልቶ የሚያሳይ ስፍራ።
ዋና አገልግሎቱ መንፈስን ማደስ ነው። በአንዳች የሙያ አይነት፣ እውቀትን ማስጨበጥ አይደለም - ዋና አላማው። ሁሉም ሰው፣ እንደዝንባሌው በየመረጠው ሙያ፣ ለላቀ ብቃትና ጀግንነት እንዲነሳሳ መንፈሱን ማበርታት ነው፤ የሰማይ ጠቀሱ ሕንፃ አላማ። የእለት ምግብ የሚፈበረክበት ወይም ሌሊቱን የሚያስጠልል ማደሪያና መኖሪያ ቤት አይደለም። ይልቅስ፤ ምግብና መጠለያን ጨምሮ፣ ጠቃሚ ነገሮችን ሁሉ እውን ማድረግ እንደሚቻል የሚያሳይ፣ የጀግኖችን አርአያነት እየመሰከረ፣ ውስጣዊ ብርታትን ማስታጠቅ፣ ውስጣዊ ኃይልን ማቀጣጠል ነው የመንፈሳዊው ሕንፃ አገልግሎት። “ይቻላል” የሚለውን መልእክት በእውን የሚያሳይል ነውና።
“እግዚአብሔርም፣ የአዳም ልጆች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ። እግዚአብሔርም አለ። ...አሁንም ያሰቡትን ሁሉ ለመሥራት አይሳናቸውም”
አዎ፤ አይሳናቸውም።
ታዲያ ለምን፣ የሚያግባባ ቋንቋ አጥተው ተደናቆሩ? ለምንስ፣ የሚያስማማ አላማ ርቋቸው ተበታተኑ? ለምንስ፣ የሚያቀራርባቸው ሰማይ ጠቀስ ሕንፃውን ትተው ባከኑ?
(www.addis admass news.com 08
May 2017)

Read 5239 times