Saturday, 28 March 2020 16:02

“ሳዳም ሁሴን ባለውለታዬ ነው”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ከሰፊው የሙያ መስክ የተመረጠ በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ዘመን ተሻጋሪ ባለ ታሪክ፣ በአርዓያነትና መልካም ስነ ምግባሩ የቤቶቻችንን የሚያማምሩ የግድግዳ ጌጦች ያክል የምናውቀውና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በግል ህይወታችን ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ ስመ ጥር ጋዜጠኛ፤ አለምነህ ዋሴ፡፡
ብዙዎችን በተንቀለቀለ ኢትዮጵያዊነት ስሜት አስተዋውቆናል፤ የተባ ብዕር ባለቤትና አንደበተ ርቱዕ ተወዳጅ የሬዲዮ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ለቁጥር የሚያታክቱ አጓጊ የዜና እወጃዎችን አውጇል፡፡ በአቀራረቡም አድማጭን እያስደመመ፣ እጃችንን በአፋችን ላይ አስጭኗል፡፡ የወርቃማው ድምጽ ባለቤት አለምነህ ዋሴ፡፡
ፈረንሳይ ለጋሴዮን  ተወልዶ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በህዝባዊ ሰራዊት እና ሚያዚያ 23፣ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በኮከበጽባህ እና እንጦጦ አጠናቋል:: በሂሳብ ሙያ አያያዝ (አካውንቲንግ) ዲፕሎማ አግኝቷል፡፡
የአለምነህ የጋዜጠኝነት ፍላጎትና ልምድ የጀመረው አግዳሚ ወንበር ላይ ቆሞ በአማርኛና እንግሊዝኛ ጋዜጦች ያሸበረቀውን የቤታቸውን ማስዋቢያ ጮክ ብሎ በማንበብ እንደሆነ ይናገራል:: ታዲያ ይህ የጋዜጣ ንባብ በየቀኑና በየሰዓቱ የሚከውነው ጉዳይ ሆነ፡፡ ሁሉንም አንብቦ አብዛኞቹን ሸመደዳቸው፣ እንግዳ ቤታቸውን በሚጎበኝ ጊዜም አለምነህ በዜና ማንበብ ይቀበላቸዋል፡፡ ለሚመጣው እንግዳ ሁሉ ጮክ ብሎ ጋዜጣውን ያነብላቸዋል:: ትኩረቱንም ሲያገኝ ደስ እያለው መጣ፡፡ (ርእዮት፣ ቴዎድሮስ ጸጋዬ)
ጎረቤቱ ሃምሳ አለቃ መርሻ ውድነህ ጆሯቸውን ወደ ግድግዳው አስጠግተው ሁሌም ይሰሙት ነበር፡፡ በተለይም ‹‹ወታደር እና እርምጃ››ን ሲያነብ እጅጉን ይመሰጡ ነበር፡፡ በደንብ እየተከታተሉም አስተያየት ይሰጡት ጀመር፡፡
በኢትዮጵያ ሬዲዮ ጥር 1 ቀን 1979 ዓ.ም ቅጥር ፈጸመ፡፡ ያኔ ገና የ20 ዓመት ወጣት ነበር፡፡ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ከመቀጠሩ በፊት ሃምሳ አለቃ መርሻ ውድነህ የመጀመሪያው አድማጬ ናቸው ይላል፡፡ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ሬዲዮ ለመቀጠርም የእሳቸው ሚና ከፍተኛ ነበር:: ባለውለታው ናቸው፡፡ ያበረታቱታል:: መንገዱን አሳይተውታል፡፡
ሬዲዮ ማዳመጥና ዜናዎችን መከታተል ከስራውና ትምህርቱ ባልተናነሰ መደበኛ ስራው ነበር፡፡ ‹‹አንድ ቀን የኛ ሬዲዮ ተሰበረና የጎረቤት ግድግዳ ላይ ተጠግቼ ዜናዎችን እሰማ ነበር፡። የወጋየሁ ትረካ ደግሞ ለኔ ልዩ ቦታ ነበረው፡፡››
በኢትዮጵያ ሬዲዮ ስራ እንደጀመረም በጉጉትና በስስት የሚያዳምጣቸውን ጋዜጠኞች በአካል ለማግኘት ቻለ፡፡ የነበረውን ስሜት ይናገራል፤ ‹‹አቡነ ጴጥሮስ ኢትዮጵያ ሬዲዮ እንደገባሁ ከአንጋፋው ጋዜጠኛ ዳሪዮስ ሞዲ ጋር ተቀመጥኩ፤ ግን ደግሞ ደነገጥኩ፡፡ ምክንያቱም በአካል እንኳን አገኛቸዋለሁ አላልኩም፤ እንኳን አብሬ ቁጭ ልል። በሰርቪስ ወደ ቤትም ስንሄድ አብረን ተቀመጥን፡። በእኔና በእሱ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው ብዬ ራሴን ጠየኩ፡፡ የደሞዝ ብቻ፡፡ አንጋፎችን ማክበር ላይ ገና እንደሆንን ተሰማኝ፤ አዘንኩ፤ የእኔም እጣ ፈንታ እንደዚህ ይሆን? አልኩ፡፡ ወጋየሁ ንጋቱ ፍቅር እስከ መቃብርን ከ1 ዓመት በላይ ተርኮ እና ህይወት ሰጥቶ የተከፈለው 1000 ብር ብቻ ነበር፡፡ ይሄንን ስሰማ ደግሞ ይበልጥ አፈርኩ፡፡
ይሄንን ሁሉ  የታዘበው አለምነህ፤ እነዚህን ሰዎች ከልቡ ቢያደንቃቸውም ሙያውን ግን አልወደደውም፡፡ እነዛ በክብርና በስስት የሚሰማቸው ጋዜጠኞች የተሰጣቸው ክብር አነሰበት፡፡
በኢትዮጵያ ሬዲዬ በአስገምጋሜ ድምጹ የብዙዎችን ቀልብ እየሳበ ተወዳጅ እየሆነ መጣ፡፡ የተለያዩ የውጭ ሃገራት ሚዲያዎችንም ጎን ለጎን ያዳምጥ ነበር:: በተለይም በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ይበልጥ በፍቅር የወደቁለትና ብቃቱን ያሳየበት ደግሞ የአሜሪካና የኢራቅ ጦርነት ነበር፡፡ ይህንን የጦርነት ዘገባ በብዙ ተጨንቆና አንብቦ በደንብ ይሰራው ነበር:: አጫጭር ቃላትንና የጦርነቱን ድርጊት በሚገልጹ ሃረጎች፣ የሁለቱን ሀገራት ጦርነት ለኢትዮጵያውያን እንዲሰሙት ብቻ ሳይሆን እንዲያዩት አደረገ፡፡ የጦር ሃይሎችን ፕሮግራም መስማት ደግሞ ይበልጥ ለዚህ እንደረዳው ይገልጻል፡፡ ጦርነቱንም እንደ ድራማ በየቀኑ ሰዎች ተጋፍተው እንዲሰሙት አደረገ፡፡  እሱም እንዲህ አለ፤ ‹‹ሳዳም ሁሴን ባለውለታዬ ነው፡፡››
በጣም የሚገርመው ደግሞ ጓደኞቹ የሳዳም ሁሴንን ውለታ ለአለምነህ ዋሴ ታዋቂ መሆን እንዲህ ይገልጹልኝ ነበር ይላል ‹‹አቶ ዋሴ ወለዱህ እንጂ ምን አደረጉልህ? አለምነህ ሳዳም ሁሴን ብትባል ይሻላል” ይሉኝ ነበር፡፡
የእንጀራው በር ከፋች ሳዳም ሁሴን እንደሆነ ደጋግሞ ይናገራል፡፡ በዚህ ሁኔታም እውቅናን ያተረፈው አለምነህ፤ ወደ ህይወቱም አዲስ ነገር ይዞለት መጣ:: ይህም የኢትዮጵያ ሬዲዮ ግቢ አለምነህ ዋሴን በሚፈልጉ ባለሀብቶች ተሞላ:: ማስታወቂያዎችንም እንዲያነብላቸው ሁሉም ተሽቀዳደሙት፡፡ አሁን አለምነህ ህይወቱ በሙያው ብቻ ሳይሆን ገንዘብም ማግኘት ጀመረ፡፡ እጆቹ በርካታ ብሮችን መቁጠር ጀመሩ፡፡     
(ከግዛቸው አሻግሬ “የጋዜጠኞች ወግ” መጽሐፍ፤2012)


Read 2435 times