Saturday, 04 April 2020 11:19

ዓለም በ75 አመታት ታሪኳ እጅግ የከፋው ፈተና ገጥሟታል

Written by 
Rate this item
(5 votes)

    ኮሮና ከ1,040,000 በላይ ሰዎችን አጥቅቶ፣ ከ56,000 በላይ ገድሏል

                ማንም ከጉዳይ አልጻፈውም ነበር…
ቻይና “ውሃን በተባለችው ግዛቴ አንድ ያልተለመደ ጉንፋን ነገር ገጠመኝ” ብላ ስትናገር፣ አዲሱን አመት 2020 ሊቀበሉ የሰዓታት ዕድሜ የቀራቸው የተቀረው አለም ፈረንጆች በዋዜማ ሽር ጉድ ተጠምደው ነበር፡፡ አውሮፓና አሜሪካ በአዲስ አመት ፈንጠዝያ ያሳለፉት አንድ ሳምንት፣ ለቻይና የግራ መጋባትና የገጠማትን አንዳች እንቆቅልሽን ለመፍታት ደፋ ቀና የማለት ነበሩ፡፡
በአዲሱ አመት 11ኛው ቀን ላይ…
ቻይና ኮሮና የተሰኘው አዲስ ቫይረስ የ61 አመት የእድሜ ባለጸጋ ዜጋዋን ለሞት እንደዳረገባት ይፋ አደረገች፡፡ በነጋታው ደግሞ የአለም የጤና ድርጅት ቫይረሱ ወደ ታይላንድ መሻገሩን አረጋግጫለሁ አለ፡፡ ከሶስት ቀናት በኋላ፣ የጃፓን የጤና ሚኒስቴር ቻይና ደርሶ የመጣ አንድ ዜጋው ቫይረሱ እንዳለበት ማረጋጋጡን አስታወቀ፡፡ በቀጣዩ ቀን ቻይና ሁለተኛው ዜጋዋ በቫይረሱ ለሞት መዳረጉን አስታወቀች፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን፣ አለም ለቻይናም ከወደ ቻይና ለተነሳው አዲስ ነገርም ጆሮ አልሰጠም ነበር፡፡
ቀናት ሲፈራረቁ፣ ሳምንታት ሲቆጠሩ ጉዳዩ የተቀረው አለም እምብዛም ትኩረት ያልሰጠውና ከቁብ ያልቆጠረው የቻይና እና የቻይና ጉዳይ ብቻ ሆኖ ነበር የዘለቀው፡፡
የአዲሱ የፈረንጆች አመት 2020 የመጀመሪያው ወር ሊጠናቀቅ የሶስት ቀናት ዕድሜ ብቻ ሲቀረው፣ ቻይና ኮሮና የሚባለው አዲስ ቫይረስ 56 ዜጎቿን በሞት እንደነጠቃትና ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑትንም እንዳጠቃባት ይፋ አደረገች፡፡ በዚያው ዕለት አሜሪካ፣ ታይዋን፣ ታይላንድ እና ደቡብ ኮርያ ኮሮና ወደ ግዛታቸው መግባቱን አስታወቁ፡፡
በወሩ የመጨረሻ ዕለት…
ቻይና በቫይረሱ የተጠቁ ዜጎቿ ቁጥር ከ11 ሺህ 800 ማለፉንና 259 ሰዎችም ለሞት መዳረጋቸውን በጭንቀትና በድንጋጤ ውስጥ ሆና ለአለም ስትናገር፣ ህንድ፣ ፊሊፒንስ፣ ሩስያ፣ ስፔን፣ ስዊድንና እንግሊዝ በበኩላቸው አንድ አንድ ዜጎቻቸው በኮሮና ቫይረስ እንደተጠቁባቸው ሲያስታውቁ፤ የአለም የጤና ድርጅት በበኩሉ ኮሮና አለማቀፍ የጤና ችግር መሆኑን በይፋ አወጀ፡፡
ከቻይና ተነስቶ ወደ ሌሎች በርካታ አገራት መስፋፋቱን የቀጠለውና ከአውስትራሊያ እስከ ካናዳ፣ ከጀርመን እስከ ሲንጋፖር፣ ከተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እስከ ቬትናም መገስገሱን የቀጠለው ኮሮና፣ ቀስ በቀስ ግን አለም እንደወትሮው ጆሮውን የሚነፍገውና ችላ ብሎ የሚያልፈው ተራ የአንድ አገርና የአንድ ህዝብ ጉዳይ እንዳልሆነ ታወቀ፡፡
ወረርሽኙ ውቅያኖስ እየተሻገረ ወሰን ድንበር ሳያግደው አገራትን ሲያዳርስ፣ የሚያጠቃቸውና ለሞት የሚዳርጋቸው ሰዎች ቁጥርም እያደር ሲያሻቅብ፣ አለማችን ደንገጥ ብላ ቆም አለችና ትኩረቷን ሁሉ ለድፍን አንድ ወር ችላ ብላው የነበረው ኮሮና ላይ አደረገች፡፡
ኮሮና እንደ ሰደድ እሳት አለምን ከዳር እስከዳር ሊያዳርስ በፍጥነት መገስገሱን ተያያዘው፡፡ ድሃና ሃብታም ብሎ ሳይለይ፣ ዘርና ቀለም ሳይመርጥ የአገራትን በር ሳያንኳኳ ተሰውሮ መግባቱንና በርካቶችን አልጋ ላይ ማዋሉን፣ ብዙዎችን ወደ መቃብር ማውረዱን ገፋበት፡፡
አለም ከዳር እስከዳር ባጥለቀለቃት የጥፋት ማዕበል ክፉኛ ተመታች፡፡ መሽቶ በነጋ ቁጥር፣ የባሰ ጥፋትና የከፋ አደጋ እንጂ የመጽናናት ዕድል የሚሰጥ ይህ ነው የሚባል በጎ ነገር ሳይሰማ ከመቼውም የከፉ ጥቁር ወራት ተፈራረቁ፡፡
አለም ድንገት በተከሰተባት የጥፋት ማዕበል መናጧን፣ ሃያላን ሳይቀሩ በማይችሉት የመከራ ጎርፍ መብረክረካቸውን፣ እልፎች ከመጣው ጥፋት ለማምለጥ በሮቻቸውን ዘግተው ሲጨነቁ ውለው ማደራቸውን ቀጠሉ - መላው አለም ሊገታው አቅም ባጣለት የመከራ ዶፍ ክፉኛ ተፈተነ፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኮሮና ቫይረስ እስከ አርብ ተሲያት ድረስ በአለም ዙሪያ በሚገኙ 204 አገራትና ግዛቶች ውስጥ ከ1,040,000 በላይ ሰዎችን ያጠቃ ሲሆን፣ ቫይረሱ ለህልፈተ ህይወት የዳረጋቸው ሰዎች ቁጥርም ከ56,000 ማለፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሳምንቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎቿ በቫይረሱ በተጠቁባትና ለሞት በተዳረጉባት አሜሪካ የተጠቂዎች ቁጥር አርብ ተሲያት ላይ ከ245,442 ማለፉ፣ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ6,098 በላይ መድረሱ የተዘገበ ሲሆን፣ አሜሪካ በአለማችን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው በቫይረሱ የተጠቃባት ቀዳሚዋ አገር መሆኗም ተነግሯል፡፡
ብዛት ያላቸው ሰዎች በቫይረሱ የተጠቃባቸው ተከታዮቹ ሁለት የአለማችን አገራት ከ117,710 በላይ ሰዎች የተጠቁባት ስፔን እና የተጠቂዎች ቁጥር ከ115,242 በላይ ያለፈባት ጣሊያን ሲሆኑ፣ ጀርመን በ85,063፣ ቻይና በ81,620፣ ፈረንሳይ በ59,105፣ ኢራን በ53,183፣ እንግሊዝ በ33,718፣ ስዊዘርላንድ በ19,145፣ ቱርክ በ18,135 ተጠቂዎች እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
ኮሮና ቫይረስ እስከ ትናንት ተሲያት 13,915 በላይ ሰዎችን የገደለባት ጣሊያን ከአለማችን አገራት መካከል ከፍተኛው ሞት የተመዘገበባት ቀዳሚዋ አገር ስትሆን፣ ስፔን በ10,935፣ አሜሪካ በ6,098፣ ፈረንሳይ በ5,387 እና ቻይና በ3,322 ሟቾች እንደሚከተሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከአፍሪካ እስከ አውሮፓ፣ ከእስያ እስከ አሜሪካ ከአህጉር እስከ አህጉር ከአገር እስከ አገር በሁሉም አቅጣጫ የኮሮና ወረርሽኝ የሚያስከትለው ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስና ጥፋት ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ የተጠቂዎችና የሟቾች መጠን በፍጥነት ማደጉን ተያይዞታል፤ ቁጥሮች በየሰከንዱና በየደቂቃው መቀያየራቸውን ቀጥለዋል፡፡
እየሆነ ያለው ሁሉ፣ እስካሁን ከሆነው ይልቅ ገና ወደፊት የሚሆነው እጅግ የከፋ እና የመረረ ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ኮሮና የጤና ጉዳይ ከመሆን አልፎ ከተሞችን በጠራራ ጸሃይ ዝምታ ውስጥ የቆለፈ፣ አደባባዮችንና ጎዳናዎችን በአስከሬን ክምር ያጣበበ፣ የአገራትን ኢኮኖሚ ክፉኛ ያሽመደመደ፣ ግዙፍ ኩባንያዎችን ያንገዳገደ፣ መንግስታትን ብርክ ያስያዘ በአጠቃላይም መላውን የሰው ልጅ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ውስጥ የከተተ የህልውና ጉዳይ ሆኗል፡፡
“አለማችን ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ ገጥሟት በማያውቅ እጅግ የከፋ ቀውስ እየተፈተነች ነው!...” ነበር ያሉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የኮሮና ቫይረስን ወረርሽኝ አስመልክተው ከቀናት በፊት ባደረጉት ንግግር፡፡
ጉዳዩ ክፉኛ እንዳሳሰባቸው የሚገልጹት ጉቴሬዝ እንደሚሉት፣ አስከፊው የኮሮና ወረርሽኝ እያደረሰ ያለው የጤና እና የኢኮኖሚ ቀውስ አንዳች መላ እስካልተገኘለት ድረስ አለማችንን ወደከፋ አለመረጋጋት፣ ብጥብጥና ግጭት እንዳያስገባት ያሰጋል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት በበኩሉ በሳምንቱ መገባደጃ ባወጣው መግለጫ እንዳለው በጥቂት ቀናት ውስጥ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ከ1 ሚሊዮን የሟቾች ቁጥር ደግሞ ከ50 ሺህ እንደሚያልፍ እና ወረርሽኙ በአለማችን እያደረሰ ያለው ጥፋት ተባብሶ እንደሚቀጥል ያለውን ስጋት ገልጧል፡፡
ኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን ለሞት ይዳርግባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁት አገራት አንዷ በሆነችው አሜሪካ፣ በዚህ አመት ብቻ በኮሮና ሳቢያ ከ100 ሺህ እስከ 240 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ለሞት ይዳረጋሉ ተብሎ መገመቱን የዘገበው ደግሞ ሲኤንቢሲ ኒውስ ነው፡፡
አሜሪካ የአንደኛው የአለም ጦርነትና የቬትናም ጦርነቶችን ጨምሮ በተለያዩ ታላላቅ ጦርነቶች ካጣቻቸው ሰዎች በላይ ቁጥር ያላቸውን ዜጎቿን በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ልታጣ እንደምትችል መነገሩን ነው ዘገባው የገለጸው፡፡
የአፍሪካ ነገር
ኮሮና ከአለም ዘግይቶ ይጎብኛት እንጂ፣ እንዲህ እንደዋዛ በአጭር ጊዜና በመጠነኛ ጥፋት በቀላሉ ይምራታል፣ በቶሎም ታገግማለች ተብላ በማትገመተው አፍሪካ በአንድ እጅ ጣቶች ከሚቆጠሩ አገራት በስተቀር ሁሉም አገራት የቫይረሱን ገፈት መቅመሳቸውን ተያይዘውታል፡፡
እስከ አርብ ተሲያት ድረስ ኮሮና ቫይረስ ከኮሞሮስ፣ ሌሴቶ፣ ሳኦ ቶሜና ፕሪንሲፔ እና ደቡብ ሱዳን በስተቀር በ50ዎቹ የአፍሪካ አገራት በድምሩ ከ7 ሺህ 100 በላይ ሰዎችን ማጥቃቱንና ከ284 በላይ የሚሆኑትንም ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን ኦልአፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
በደቡብ አፍሪካ ከ1ሺህ 462፣ በአልጀሪያ ከ986፣ በግብጽ ከ865 በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በርካታ የአፍሪካ አገራት ቫይረሱን ለመግታት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና የእንቅስቃሴ ገደብ አንስቶ የተቻላቸውን ሁሉ ርብርብ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡
ዜጎቻቸውን ከቤት እንዳይወጡ ከከለከሉ የአፍሪካ አገራት መካከል የሚጠቀሱት ዚምባዌና ናይጀሪያ በእንቅስቃሴ ገደብ ሳቢያ ለከፋ ሁኔታ እንዳይጋለጡ በመስጋት በአስር ሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ለድሃ ዜጎቻቸው ገንዘብ ለመደጎም ማቀዳቸው የተነገረ ሲሆን፣ የሩዋንዳ መንግስትም ምግብን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ መጀመሩ ተዘግቧል፡፡
ግብጽ እና ናይጀሪያ ሁሉንም አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎቻቸውን አገልግሎት አቋርጠው እንዲዘጉ ያደረጉ ሲሆን፣ በርካታ አገራት ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብና የስራ ማቆም እርምጃ መውሰዳቸው ተነግሯል፡፡
የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን አፍሪካ ከኮሮና ቀውስ ለማገገም እንድትችል የ100 ቢሊዮን ዶላር ያህል የኢኮኖሚ ማገገሚያ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ያስታወቀ ሲሆን፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ በአህጉሪቱ የኮሮና ቫይረስን ለመግታት ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መደገፊያ የ2 ሚሊዮን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ለመስጠት መወሰኑ ተነግሯል፡፡
በአነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት በኮሮና መከላከልና ህክምና ዙሪያ የተፋጠኑ ምርምሮችን የማከናወን አላማን ያነገበና በ30 አገራት ውስጥ ከሚገኙ ከ70 በላይ ተቋማት የተውጣጡ ሳይንቲስቶች፣ የህክምና ባለሙያዎች፣ ለጋሾችና ፖሊሲ አውጪዎች በአባልነት የተካተቱበት አዲስ አለማቀፍ ጥምረት መቋቋሙም ተሰምቷል፡፡
ኮቪድ-19 ክሊኒካል ሪሰርች ኩዋሌሽን የተባለው ይህ ጥምረት በተለይም ኮሮና ከፍተኛ ጥፋት ሊያስከትልባቸው በሚችልባቸው ይህ ነው የሚባል የጤና መሰረተ ልማት ባልተሟላባቸውና የፋይናንስ እጥረት ባለባቸው ድሃ አገራት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ሲሆን፣ የአፍሪካ የላቲን አሜሪካ፣ የምስራቅ አውሮፓና አንዳንድ የእስያ አገራት እየተስፋፋ ለመጣው የኮሮና ወረርሽኝ በቂ ምላሽ እንዲሰጡ ለማስቻል አለማቀፍ የምርምር ትብብሮች በማስፈለጋቸው በአፋጣኝ ወደ ስራ እንደሚገባ ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የከፋው ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ አለማችን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ እየገጠማት እንደሚገኝ እየተነገረ ሲሆን፣ የኢኮኖሚ ቀውሱ ባደጉም ሆነ ባላደጉ አገራት ላይ ለአመታት የማይሽር ስር የሰደደ ጠባሳ እንደሚያሳርፍ ተዘግቧል፡፡ ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ አለማችን በአመቱ ባለፉት አስርት አመታት ያልታየ የ2.4 በመቶ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ እድገት እንደምታስመዘግብ ይጠበቃል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በመላው አለም ከ25 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከስራ ገበታቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ ባሳለፍነው ሳምንት በሰጠው መግለጫ ያስታወቀ ሲሆን፣ በወረርሽኙ ክፉኛ በተመታችው ስፔን ዜጎችን ከቫይረሱ ለመከላከል በሚል በተወሰዱ ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደቦችና የስራ ማቆም እርምጃዎች 900 ሺህ ያህል የአገሪቱ ዜጎች ለስራ አጥነነት አንደተዳረጉ ተነግሯል፡፡ በእንግሊዝ 25 በመቶ ያህል ኩባንያዎች ሰራተኞቻቸውን መቀነሳቸውም ተዘግቧል፡፡
ከ100 በላይ የሚሆኑ አገራት የጉዞ እገዳ መጣላቸውንና ታላላቅ አየር መንገዶች ሳይቀሩ በረራዎቻቸውን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ማቋረጣቸውን ተከትሎ የአቪየሽን ኢንዱስትሪው ክፉኛ መመታቱን የዘገበው ቢቢሲ፣ የእንግሊዙ ብሪትሽ ኤርላይንስ 80 በመቶ ያህል ሰራተኞችን ወይም 36 ሺህ ያህል ሰዎችን ከስራ ሊያሰናብት እንደሚችል ማስታወቁን አመልክቷል፡፡
ከአውሮፓ እስከ አሜሪካና እስያ አገራት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ መግባቱን የዘገበው ዘ ኢንዲፔንደንት በበኩሉ፣ ለአብነትም በቻይና የመኪኖች ሽያጭ ባለፈው ወር ብቻ በ86 በመቶ መቀነሱን አስታውሷል፡፡
የነዳጅ ዋጋ ባለፉት ሁለት ስርት አመታት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን በመቀጠል በበርሜል 23 ዶላር ያህል የደረሰ ሲሆን ይህም የነዳጅ አምራች አገራትን ኢኮኖሚ አደጋ ውስጥ መጣሉን ቀጥሏል፡፡
ታላላቅ የአለማችን የአክሲዮን ገበያዎች ባለፉት ሶስት አስርት አመታት አጋጥሟቸው የማያውቀው እጅግ ከፍተኛ የአክሲዮን ዋጋ ቅናሽ ታይቶባቸዋል፤ ኢንቬስተሮችና ኩባንያዎች ተደናግጠዋል፡፡
በርካታ የዓለማችን አገራት ብድርን በማበረታታት ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት በማሰብ የባንክ ወለድ መጠንን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስንና በትሪሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር የድጎማ በጀት ቢመድቡም ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ ለአመታት የሚዘልቅ ተጽዕኖ እንደሚኖረው እየተነገረ ነው፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም በበኩሉ ባለፈው ሰኞ ባወጣው ሪፖርቱ ድሃና ያላደጉ አገራት ኮሮና ቫይረስ ከሚያስከትልባቸው ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ለማገገም አመታትን እንደሚፈጅባቸው የገለጸ ሲሆን፣ በአገራቱ ግማሽ ያህሉ ህዝብ ከስራ እንደሚፈናቀልና ከ220 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያጣል ተብሎ እንደሚገመት አመልክቷል፡፡
ከፖለቲከኞች እና ዝነኞች መንደር
የቀድሞው የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኑር ሃሰን ሁሴን በተወለዱ በ83 አመታቸው ባለፈው ሃሙስ ማለዳ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በእግሊዝ መዲና ለንደን ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን ተከትሎ አገሪቱ የሶስት ቀናት ብሔራዊ ሃዘን ማወጇን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው ቤሩት ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው የቆዩት በሊባኖስ የፊሊፒንስ አምባሳደር በርናርዲታ ካታላ ባለፈው ሃሙስ ከዚህ አለም በሞት መለየታቸው የተነገረ ሲሆን፣ የኮንጎ የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ዮምቢ ኦፓንጎም ፓሪስ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ሲታከሙ ቆይተው ባለፈው ረቡዕ መሞታቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የእስራኤል የጤና ሚኒስትር ኮቭ ሊዝማንና ባለቤታቸው፣ የስፔን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ካርሜን ካልቮ እና የቡርኪናፋሶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልፋ ቤሪም ከሰሞኑ በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸው ከተነገረላቸው የአለማችን ፖለቲከኞችና ታዋቂ ሰዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የኮሮና ተጠቂ ሐኪሞች ተበራክተዋል
በስፔን ዜጎችን በመርዳት ላይ እያሉ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ የህክምና ባለሙያዎች ቁጥር ከ12 ሺህ 298 በላይ መድረሱ የተዘገበ ሲሆን፣ በቫይረሱ ከተጠቁት ዜጎች ሀኪሞች 15 በመቶ ያህሉን እንደሚይዙ ተነግሯል፡፡
በፖርቹጋል 853፣ በቻይና ከ3 ሺህ በላይ፣ በጣሊያን ከ6 ሺህ በላይ ዶክተሮችና ሌሎች የህክምና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸውም ተዘግቧል፡፡
በአሜሪካዋ ማሳቹሴትስ ብቻ ከ515 በላይ የህክምና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸውን ቦስተን ዴይሊ ድረገጽ ከሰሞኑ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡
የአሜሪካ ክብረወሰኖች - በጠመንጃ ግዢ እና በስራ አጥነት
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ብዙዎች ባልጠበቁት መልኩ አቅሟን ተፈታትኖ እያንገዳገዳት ባለችው አሜሪካ ከሰሞኑ ሁለት ትኩረትን የሚስቡ ከፍተኛ ቁጥሮች ተመዝግበዋል - ከስራ አጥነትነት እና ከጦር መሳሪያዎች ግዢ ጋር በተያያዘ፡፡
የአገሪቱ የሰራተኞች ቢሮ ከትናንት በስቲያ ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ሲኤንቢሲ ኒውስ እንደዘገበው፣ በአሜሪካ በሳምንቱ 6.6 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ስራ አጥ ነን ድጋፍ ይገባናል ብለው ያመለከቱ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር ባለፉት 40 አመታት የአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ 3.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የስራ አጥነት ማመልከቻ ማስገባታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ በሁለቱ ሳምንታት ያመለከቱት ሰዎች ቁጥርም ከ10 ሚሊዮን እንደሚበልጥም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በአሜሪካ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋቱን ተከትሎ ባለፉት 20 አመታት ተመዝግቦ የማያውቅ ከፍተኛ የጦር መሳሪያዎች ሽያጭ መከናወኑን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፣ ባለፈው መጋቢት ወር ውስጥ ብቻ ከ2.4 ሚሊዮን በላይ የጦር መሳሪያ ግዢዎች መፈጸማቸውን ከአገሪቱ መንግስት ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ አብራርቷል፡፡
በአሜሪካ ካሊፎርኒያን ጨምሮ በተለያዩ ግዛቶች የመሳሪያ መሸጫ መደብሮች በገዢዎች ተጨናንቀው መሰንበታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ 1.2 ሚሊዮን ያህሉ መሳሪያ ግዢዎች የተከናወኑት በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ እንደነበርና መጋቢት 20 ቀን ብቻ ከ210 ሺህ በላይ የጦር መሳሪያዎች ግዢ መፈጸሙንም አመልክቷል፡፡

121 አገራት ደ/ኮርያን እየተማጸኑ ነው
የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በመላው አለም መስፋፋቱንና የመመርመሪያ መሳሪያ እጥረት መከሰቱን ተከትሎ፣ ከ100 በላይ የሚሆኑ አገራት ደ/ ኮርያ መሳሪያውን እንድትሰጣቸው እየተማጸኑ እንደሚገኙ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
መሳሪያውን በብዛት በማምረት ላይ ለምትገኘው ደቡብ ኮርያ እነማን ጥያቄውን እንዳቀረቡላትና ለእነማን እንደምትረዳ የታወቀ ነገር ባይኖርም አሜሪካ ባለፈው ሳምንት ጥያቄ ማቅረቧንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

ስለኮሮና ማውራት ያሳስራል፤ ከቤት መውጣት ያስገድላል
ቫይረሱ ወደ ግዛቴ ድርሽ አላለም ብለው ማስተባበሉን የቀጠለው የቱርኬሚኒስታን መንግስት “ኮሮና” የሚለውን ቃል ሲጠሩና ስለቫይረሱ ተሰብስበው ሲያወሩና ሲወያዩ ያገኛቸውን እንዲሁም ለጥንቃቄ ብለው የፊት ጭምብል ያጠለቁ ዜጎችን እንደሚያስር አስጠንቅቋል፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሁሉም ሚዲያዎች በዘገባዎቻቸው “ኮሮና” የሚል ቃል እንዳይጠቀሙና ዜጎችም በየመንገዱ ይህንን ቃል እንዳይጠሩ ጥብቅ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን የዘገበው አርኤስኤፍ፣ ፖሊስም ኮሮናን ለመከላከል የፊት ጭምብል አድርገው የተገኙ ወይም ስለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሲወያዩ ያገኛቸውን ዜጎች ማሰር መጀመሩንም ገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ የፊሊፒንሱ ፕሬዚዳንት ሮዲሪጎ ዱቴሬ ኮሮናን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚል የታወጀውን የአንድ ወር ከቤት ያለመውጣት ገደብ ጥሰው ከቤታቸው ወጥተው የተገኙ ወይም ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገውን ርብርብ በማንኛውም መንገድ ሲያደናቅፉ የተገኙ ዜጎችን ያለምንም ማመንታት ተኩሰው እንዲገድሉ ለአገሪቱ የፖሊስና የጦር ሃይል አባላት ቀጭን ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
“አደገኛ ወቅት ላይ ነንና፣ ስርዓታችሁን ጠብቃችሁ መንግስት የሚላችሁን ብቻ አድርጉ!... በጤና ባለሙያዎችና በዶክተሮች ላይ ማንኛውንም አይነት ጉዳት ማድረስ ትልቅ ወንጀል መሆኑን አውቃችሁ ተጠንቀቁ!... ለፖሊስና ለወታደሩ የማስተላልፈው ትዕዛዝ አጭርና ግልጽ ነው - ችግር ሲፈጥር እና የገዛ ህይወቱን አደጋ ውስጥ ሲከትት ያገኛችሁትን ሰው ሁሉ ተኩሳችሁ ግደሉት!...” ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ረቡዕ በቴሌቪዥን ባስተላለፉት ማስጠንቀቂያ፡፡

“ነጻ ነኝ!...” የምትለዋ ሰ/ ኮርያ የሚያምናት አጥታለች
ኮሮና ቫይረስ በመላው አለም በሚገኙ 204 አገራትና ግዛቶች ውስጥ ተከስቶ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ባጠቃበት በዚህ የቀውስ ወቅት፣ “ቫይረሱ ድንበሬን አልፎ አልገባም አንድም ዜጋዬ በቫይረሱ አልተጠቃም” ብላ መከራከሯን የቀጠለችው የሰሜን ኮርያ ጉዳይ አሁንም ማነጋገሩን ቀጥሏል፡፡
የኪም ጁንግ ኡን መንግስት ወረርሽኙ በአለም ዙሪያ ከመስፋፋቱ ቀደም ብሎ ድንበሮቼን ከመዝጋትና በረራዎቼን ከማቋረጥ ባሻገር በርካታ እርምጃዎችን መውሰዴና ጥንቃቄዎችን ማድረጌ ለኮሮና አላጋለጠኝም፣ ዛሬም ከቫይረሱ ነጻ ነኝ ይበል እንጂ፣ አሜሪካን ጨምሮ በርካታ አገራት፣ መገናኛ ብዙሃንና ፖለቲከኞች ግን አንባገነኑን መንግስት ነጭ ውሸት እየዋሸ ነው እንጂ ብዙ ዜጎቹ ተጠቅተውበታል በማለት ይናገራሉ፡፡
በደቡብ ኮሪያ የአሜሪካ ጦር አዛዥ ጄኔራል ሮበርት አብራምስ ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት ሰሜን ኮርያ አንድም ሰው በኮሮና ቫይረስ አልተጠቃብኝም ማለቷ ፍጹም ቅጥፈት እንደሆነ በመግለጽ፣ ጦሩ ባገኘው መረጃ ኮሮና ሰሜን ኮርያ መግባቱንና ሰዎችን ማጥቃቱን ለማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል።
ሰሜን ኮርያ በቂ የጤና መሰረተ ልማት እንዳላት አገሪቱ ጥሩ በሚባል ሁኔታ ኮሮናን ለመከላከል ዝግጅት ስታደርግ መቆየቷን ያስታወሰው የጠቆመው የቢቢሲ ዘገባ፣ የአገሪቱ መንግስት ቫይረሱን ለመከላከል ብዙ ርቀት ስለሄደና ኮሮና አልተዳፈረኝም በማለት ፕሮፖጋንዳ ሲነዛ ስለቆየ ቫይረሱ ወደ አገሪቱ መግባቱን ማመን እንደ ሽንፈት አድርጎ ስለሚቆጥረው ነው ለማመን ያልፈለገው መባሉንም አመልክቷል፡፡
ከ193 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት መካከል እስከ ትናንት ተሲያት ድረስ በቫይረሱ እንዳልተጠቁ የሚናገሩ አገራት 19 መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ እምብዛም ከማይታወቁት ከእነዚህ አገራት መካከል ኪሪባቲ፣ የማርሻል ደሴቶች፣ ሜክሮኒሺያ፣ ናዉሩ፣ ፓላዉ፣ ሳሞዋ፣ ሳዎ ቶሜና ፕሪንሲፔ፣ ቶንጋ፣ ቱቫሉ፣ ቫኑዋቱና የመን እንደሚገኙበትም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 15347 times