Print this page
Saturday, 04 April 2020 11:29

ጡት አስጥል ብለው ቢልኩት ሲጠባ ተገኘ!

Written by 
Rate this item
(10 votes)

           ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ባል ሚስቱ ድርስ እርጉዝ ሆና ሳለ፣ በየማታው ይጨቀጭቃት ነበር፡፡
ሚስት - አንተ ሰውዬ ለምን ቃልህን አታከብርም? ትላለች፡፡
ባል - የምን ቃል?
ሚስት - ጭራሽ የገባኸውንም ቃል ረስተኸዋል?
ባል - አልረሳሁትም፡፡
ሚስት - ታዲያ ምነው ዕቃውን አላመጣህም?
ባል - የምን ዕቃ?
ሚስት - ነጋ ጠባ ከሥራ ስትመጣ ምን ይታይሃል?
ባል - አንቺና እርግዝናሽ
ሚስት - እና እኔንና እርግዝናዬን የሚመለከት ምንም ትዝ አይልህም?
ባል - ይለኛል፡፡
ሚስት - ምን?
ባል - ልጅ፡፡
ሚስት - እና ስለ ልጁ ቃል አልገባህም?
ባል - ገብቻለሁ፡፡
ሚስት - እና የታል ዕቃው?
ባል - የምኑ ዕቃ?
ሚስት ትናደድና፤ አልጋው ነዋ!
ባል - ኦ! እሱንማ እንዴት እረሳዋለሁ?
ሚስት - ታዲያ ምን ሆነ?
ባል - የውልሽ የሆነው እንደዚህ ነው፡፡ ለአንድ ዐረብ፣ ለልጃችን ያን አልጋ እንዲሰራልን የአናጢነቱን፣ የእጁን ዋጋ፣ ገንዘብ ሰጠሁት፡፡
ሚስት - ገንዘቡን ይዞ ጠፋ እንዳትለኝ?
ባል - በጭራሽ፡፡ ያን ያህል ባለጌ አይደለም!
ሚስት - ከዛ ምን ሆነ እሺ?
ባል - ባየው አይሰራውም፡፡ ባየው አይሰራውም፡፡
ሚስት - ‹‹እና?››
ባል - ‹‹ብመላለስም አልሰራውም››፡፡
በዚህ ሁኔታ ሚስትየው በየማታው እንደወተወተችው ልጁ ተወለደ፡፡ ከዚያም ውሎ አድሮ፣
ልጁ አደገና ለአካለ መጠን ደርሶ አገባ፡፡
ሚስቱ አረገዘች!
ልጅ አባቱን፡--
‹‹አልጋ የት ላሰራ፣ አባዬ?›› ብሎ ጠየቀው፡፡
አባትየውም፤
‹‹የዛሬ ሃያ ዓመት የከፈልኩት አንድ ዐረብ አናጢ አለ፡፡ ሂድና ስሜን ጠቅሰህ ጠይቀው›› አለው፡፡
ልጅየውም  እንደተባለው ወደ ዐረቡ ሄዶ፤
‹‹አባቴ የዛሬ ሃያ ዓመት የከፈለበት አልጋ አንተ ዘንድ አለ፡፡ እሱን ልወስድ ነው የመጣሁት›› አለው፡፡ ዐረቡም በጣም በንዴት፤
‹‹እናንተ ሰዎች አታጣድፉኝ፡፡ እኔ ጥድፍ ጥድፍ ማለት አልወድም! ካልፈለጋችሁ ይሄው ገንዘቡ መውሰድ ትችላላችሁ!›› አለና ገንዘቡን ከኮሞዲኖው አወጣ!
ብዙ ባለሙያዎች ሥራን በሰዓቱ አይሰሩም፡፡ አለመስራታቸው ሳያንስ ጭራሽ መቅጣት ይዳዳቸዋል፡፡ ብዙ ባለሥራዎች ደግሞ ባለሙያዎቹን በአግባቡ አይቆጣጠሯቸውም፡፡ በማህል ሥራው ገደል ይገባል፡፡ ከላይ ያየነው ዐረብ በትክክል አልጋውን ሰርቶ ማስረከብ ሳይሆን በትክክል ገንዘቡን ኮመዲናው ውስጥ ቆልፎ ማስቀመጡን ስኬታማ አድርጎ ራሱን እንዲያይ እንደገፋፋው ተመልክተናል፡፡ በአገራችን ከመንግሥት ጀምሮ ታችኛው እርከን ላይ ያሉ ሰራተኞች ድረስ፣ ዋናውን ጉዳይ በሰዓቱ መፈፀምን እንደ መሰረታዊ ግዴታቸው አድርገው ደንገጥም አይሉለትም! ጭራሽ ዳተኝነታቸውን ለትውልድ ማስተላለፍ ይቃጣቸዋል፡፡ ምናልባትም በዚሁ ሁኔታ ለብዙ ዘመን መክረምን ይኩራሩበታል! ከዚህ ይሰውረን ማለት ነው!
የአንድ አገር አስተዳደራዊ ሥርዓት መረጋጋት መገለጫዎች ከሆኑት ነገሮች አንዱ ሕዝብ መንግሥት የሚለውን መስማቱና መተግበሩ ነው፡፡ ይህንንም አንዱ ማሳያ መንግሥትን ማመኑና መቀበሉ፣ የሚለውንም መስማቱ ነው፡፡ መንግሥት ማናቸውንም ዓይነት ሀይል ሳይጠቀም ከሕዝብ ጋር ግብብነት መፍጠሩ የሰላምና መረጋጋት መኖር ምልክት ነው፡፡ ሕዝብ መመሪያ አልቀበልም፣ የምታዘዘውን አልፈጽምም፣ አርግ የተባልኩትንም አላረግም የሚልበት ደረጃ ላይ ሲደርስ የሚጠቅመውን አዋጅም ሳይቀር ላለመስማት ጆሮ ዳባ ልበስ ይላል፡፡
‹‹አሁን የት ይገኛል ቢፈልጉ ዞሮ
መስማት ከማይፈልግ የባሰ ደንቆሮ›› በሚለው የደራሲ ከበደ ሚካኤል ማዕቀፍ ውስጥ እስከ መግባት ይደረሳል፡፡
 ያ ደግሞ ደግ አይደለም፡፡ የሰሞኑን የኮሮና ቫይረስ አደጋ ብናየው፣ ከመንግሥት የሚሰጠውን መመሪያ አልቀበልም ቢል፤ ቢተው ጎጂ እምቢታ በሆነ ነበር፡፡ ያ ሆኖ ቢሆን ኖሮ፣ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት  ሰፍቶ ሕዝብ ባለቀ ነበር፡፡ ለመቆጣጠር ፈፅሞ የማይቻልበት ሁኔታ ውስጥም በተገባ ነበር፡፡ ሕዝብን የማንቃት፣ የማሳወቅ፣ የማደራጀት፣ የህክምና እርዳታ እንዲያገኝ የማድረግ ጥረትና ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ በእንዲህ ያለው የአደጋ ጊዜ አንድም ‹‹ከአያያዝ ይቀደዳል››ን፣ አንድም ‹‹ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ››፣ የሚለውን ማገናዘብ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ጥንቃቄ የዕለት የሰርክ መመሪያ መሆን ያለበት ጊዜ ነው፡፡ ዛሬ መንግሥት የሚለውን ማዳመጥ ሀኪም የሚለንን ከማዳመጥ እኩል ነው፡፡ ዛሬ ራስን ማዳን አገርን ማዳን ነው፡፡ በየሚዲያው የሚሰጠውን ምክር መቀበልና መተግበር ሕይወትን የመታደግ ቅዱስ እርምጃ ነው! ተቋማትም ምክሩን ማሰራጨት ብቻ ሳይሆን በሚቻለው መንገድ ሁሉ የገንዘብ፣ የቁሳቁስ፣ የቦታ፣ የህክምና ዕቃዎች ድጋፍ በማድረግ፣ በሁሉም ረገድ የመረባረብ እገዛቸው እጅግ አስፈላጊ የሆነበት ወቅት ነው፡፡ ታዋቂው የመረዳዳት ባህላችን የሚፈለግበት ወሳኝ ጊዜ ነው፡፡ ያለ መጨባበጥ፣ ከቤት ያለ መውጣት፣ ከሥራ የመቅረት፣ የማህበራዊ መራራቅ ተግባርን ከልብና ከዕውቀት ሥራ ላይ ማዋል ይጠበቅብናል፡፡ በአንፃሩ ሁኔታዎችን ለመበዝበዣ የሚጠቀሙ ስግብግብ ነጋዴዎችን መዋጋት ተገቢ ነው! መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሕዝብም ሊዋጋቸው ግድ ነው! በኃላፊነት የተመደቡና የተሰማሩ ሰዎች ሁኔታውን ለግል ጉዳይ ካዋሉት ‹‹ጡት አስጥል ብለው ቢልኩት ሲጠባ ተገኘ›› ነውና ያስጠይቃል፡፡ እንጠንቀቅ፡፡ ክፉ ጊዜን በጥንቃቄና በሰብዕና እንለፍ!  


Read 15789 times
Administrator

Latest from Administrator