Saturday, 04 April 2020 11:49

ዘመን ባንክ በአበባ ምርት ለተሰማሩ ደንበኞቹ የብድር ወለድ ሰረዘ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

  - የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት ለሚደረገው ጥረት 5.ሚ.ብር ለግሷል
   - የኮሮና ቫይረስን ተጋፍጠው እያከሙ ላሉ የጤና ባለሙያዎች የሚውል ገንዘብ እየሰበሰበ ነው
               
            ዘመን ባንክ በኮቪድ 19ን ወረርሽኝ ምክንያት የምርትና የመላክ ችግር ላይ ለወደቁና ከፍተኛ ኪሳራ ላደረሰባቸው አበባ አምራችና ላኪ ደንበኞቹ ለ3 ወር የሚቆይ የብድር ወለድ መሰረዙን አስታወቀ፡፡ ባንኩ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ሥርጭት ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የ5 ሚ ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ገንዘቡን ሰኞ ለብሄራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ብሄራዊ ኮሚቴ እንደሚያስረክብ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ዘበነ ገልጸዋል፡፡
ባንኩ ትላንት መጋቢት 25 ቀን 2012 ዓ.ም ረፋድ ላይ በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው የአበባ አምራች ዘርፍ ካለው ልዩ ባህሪና የሚያመርተው ምርት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ለውጭ ገበያ በተለይም ለአውሮፓ የሚቀርብ በመሆኑና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ገበያው ሙሉ በሙሉ በመቋረጡ ሁኔታዎች ድረስ እስከሚሻሻሉ በዚህ ዘርፍ ላይ የሚደርሰውን ከፍተኛ ጉዳትና ኪሳራ ባንካቸው በመገንዘቡ የወለድ ስረዛውን ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ የብድር ወለዱ ስረዛ ለሶስት ወራት ማለትም ለኤፕሪል 2 እስከ ጁን 30 2020 ዓ.ም እንደሚዘልቅም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ያጠቃውና እስካሁንም 50 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ሕይወት የነጠቀው ይሄው ወረርሽኝ በአገራችንም ማርች 14 ቀን የመጀመሪያው ተጠቂ ከተገኘ በኋላ መንግሥት ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ ለመቆጣጠርና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱን ለመቀነስ እየወሰደ ያለውን የተለያየ እርምጃ ያደነቁት የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ የግሉ ዘርፍም ከመንግሥት ጎን ሆኖ ወረርሽኙን ለመከላከል የበኩሉን በማድረግ ለሚደረገው ጥረት ባንካቸው የ5.ሚ ብር ድጋፍ ማድረጉንና ገንዘቡን የፊታችን ሰኞ መጋቢት 28 ቀን 2012 ዓ.ም ለብሄራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ እንደሚያስረክቡ ተናግረዋል፡፡
የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኮቪድ 19 ወረርሽኝን በመጋፈጥ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን አሳልፈው ሰጥተው በሕክምና ስራ ላይ ለተሰማሩ የጤና ባለሙያዎች ያላቸውን ክብርና አድናቆት ከገለፁ በኋላ እነዚህን የጤና ባለሙያዎች ለማገዝና አስፈላጊው ነገር እንዲሟላላቸው ለማድረግ በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ የተሰማሩ የባንኩ ደንበኞች ከጊዜ ማራዘም ጋር በተያያዘ የሚከፍሉትን የአገልግሎት ክፍያ 75 በመቶ በመሰረዝና ቀሪውን 25 በመቶ በመሰብሰብ ለጤና ባለሙያዎች ድጋፍ እንዲውል መደረጉን አብራርተው እስካሁንም ወደ 800 ሺህ ብር መሰብሰቡንና ተሰብስቦ ሲያልቅ ለጤና ሚኒስቴር እንደሚያስረክብ ተናግረዋል፡፡
ስራ አስፈፃሚው አያይዘውም ባንኩ እንደ ተቋም ካደረገው ልገሳ በተጨማሪ ከ900 በላይ የሆኑ ሰራተኞቹን በማስተባበር የገቢ ማሰባሰብ ስራ እየከወነ መሆኑንና ከዚህም እስከ ግማሽ ሚ.ብር ለዚሁ ጉዳይ ወደ ተዘጋጀው ሂሳብ ገቢ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
በሽታውን ከመከላከል አንፃር ባንኮቸው ነፍሰ ጡር ሴቶችን፣ ዕድሜያቸው ከ55 ዓመት በላይ የሆኑትን፣ እንዲሁም ቀደም ሲል የጤና ችግር ያለባቸውን ሰራተኞቹን እረፍት ላይ ሆነው እንዲቆዩ ማድረጉንና በማረፋቸው የሚቀርባቸው አንድም ጥቅማ ጥቅም እንደማይኖር አስታውሰው በስራ ላይ ለሚገኙ ሰራተኞችም ተራርቀው እንዲሰሩ በማድረግ አስፈላጊ የንጽህና መጠበቂያና መከላከያ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ደንበኞችም በአብዛኛው የኢንተርኔት የባንክ አገልግሎትን በብዛት እንዲጠቀሙና ብር የግድ ማውጣት ሲፈልጉ በኢቲኤም ማሽኖች አማካኝነት እስከ 12 ሺህ ብር ድረስ ማውጣት የሚያስችል አሰራር መመቻቸቱም ተገልጿል፡፡
ወረርሽኙን ተከትሎ በገበያው ውስጥ የገንዘብ እጥረት እንዳይፈጠር መንግሥት ባንኮች ገዝተውት ከነበረው የብሄራዊ ባንክ ቢል ውስጥ ግምታቸው 15 ቢ. የሚያወጡ ሰነዶችን ብሄራዊ ባንክ መልሶ በመግዛት ባንኮች የገንዘብ እጥረት እንዳያጋጥማቸው ያደረገውን ጥረት አድንቀው ዘመን ባንክ የችግሩን መጠንና ስፋት እያየ በጣም ለሚጎዱ ዘርፎች ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚያደርግ ዋና ሥራ አስፈፃሚው አስታውቀዋል፡፡

Read 9325 times