Saturday, 04 April 2020 11:47

የአየር መንገድ ሠራተኛ የመቀነስ እርምጃ ተቃውሞ ገጥሞታል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

     የሠራተኞች ማህበር ሊቀመንበር መብታችንን ለማስከበር ትግላችን ይቀጥላል ብለዋል

           የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተወሰደውን እርምጃ ተከትሎ ገቢው መቀነሱን ያስታወቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የኮንትራት ሠራተኞችን ቀንሷል፤ የአየር መንገድ የሠራተኞች መሠረታዊ ማህበር በበኩሉ እርምጃውን ተቃውሞታል፡፡
የሠራተኛ ማህበሩ ሊቀ መንበር ‹‹የአየር መንገዱን ስም አጥፍተዋል፣ ሰራተኞችን በቡድን አደራጅተዋል›› በሚል ምክንያት ከስራቸው እንደተባረሩም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የአየር መንገዱ መሠረታዊ የሠራተኞች ማህበር ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫው፤ ‹‹እየተደረገ ያለው ቅነሳ ወቅቱን ያላገናዘበ፣ መሠረታዊ የሠራተኞች መብትን የጣሰ ነው›› ሲል ወቅሷል፡፡
አየር መንገዱ መንገደኞችን ማጓጓዝ ቢያቆምም ጭነት እያመላለሰ መሆኑን የጠቆመው ማህበሩ፤ ከዚህም አንፃር ሁሉንም ሠራተኞች ይዞ ማቆየት የሚያስችል ገቢ እያገኘ በመሆኑ ቅነሳው ተገቢ አይደለም ሲል ተቃውሞታል፡፡ የጥገና ክፍሉም የውጭ ሀገር አውሮፕላኖችን እየጠገነ ገቢ በማግኘት ላይ ነው ሲል አክሏል፡፡
አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ገንዘብ የሚከፍላቸውን የውጭ ሀገር ዜጐች ይዞ እየቀጠለ ኢትዮጵያውያንን ማባረሩም ተገቢ አይደለም ያለው ማህበሩ፤ በዚህ የችግር ወቅት ትርፍን ኢላማ አድርጐ መንቀሳቀሱ ለዜጐች ህልውና አለመጨነቁን አመላካች ነው ብሏል፡፡
50 ኢትዮጵያውያን ሠራተኞችን ከማስወጣት 1 የውጭ ሀገር ዜጋ ተቀጣሪን መቀነስ ይቀል ነበር ያለው ማህበሩ፤ አየር መንገዱ ለዜጐች የሰጠው ግምት አስተዛዛቢ ነው ብሏል፡፡
በአጠቃላይ በአየር መንገዱ ማናጅመንት በኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ላይ የተወሰደው የሰራተኞች የቅነሳ እርምጃ ኢ-ሰብአዊ ተግባራት ጐልተው የታዩበት ነው የሚለው መግለጫው፤ መንግስት ጣልቃ ገብቶ ለችግሩ እልባት እንዲያበጅ ጠይቋል፡፡  
በአየር መንገዱ ውስጥ በርካታ ሠራተኞች የኢትዮጵያ ሠራተኛና አሠሪ ህግ ከሚፈቅደው ውጪ በኮንትራት ብቻ ለረጅም አመታት እንዲሠሩ ይደረጋል የሚሉት ካፒቴን የሺዋስ፤ ሆስተሶች፣ ቴክኒሻኖች፣ የቲኬት ቢሮ ሠራተኞችን ጨምሮ በርካቶች ያለ አግባብ በኮንትራት ነው አላቂ ላልሆነ ስራ እንዲሠሩ የሚደረጉት ይላሉ፡፡
ይህም ሠራተኛው እንደ ቋሚ ሠራተኛ መብቱን እንዳይጠይቅ ለማድረግ ታቅዶ መሆኑን የሚያስረዱት ካፒቴን የሺዋስ፤ አሁን ሰራተኞችን የቀነሰበት አግባብም ከህግ ውጪ በሆነ አሠራር ነው ይላሉ፡፡
የሰራተኛ ማህበሩ ሊቀመንበር ካፒቴን የሺዋስ፤ ከተባረሩት ሠራተኞች መካከል መሆናቸውን ጠቁመው፤ የተባረሩበት ምክንያትም ‹‹ሠራተኞች በቡድን በማደራጀት፣ የአየር መንገዱን ስም አጠልሽተዋል›› በሚል መሆኑን ከአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
‹‹ይሁን እንጂ እኔ በህገወጥ መንገድ ነው ከስራዬ የተባረርኩት፤ አሁንም የማህበሩ አመራር ሆኜ ለሠራተኞች መብት መታገሌን እቀጥላለሁ፡፡ በቀጣይም መንግስት ጣልቃ ገብቶ ጉዳዩን የማያስተካክል ከሆነ ተከታታይ ሰላማዊ ሠልፎችን እናደርጋለን፤ በተለያዩ አግባቦች መብታችንን ለማስከበር እንታገላለን፤ ድርጅቱ የግለሰብ ሳይሆን የህዝብ ነው፤ ይሄ መታወቅ አለበት›› ብለዋል፡፡
በአየር መንገዱና በመሠረታዊ የሠራተኛ ማህበሩ መካከል የተፈጠረውን ችግርም የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ከፌዴሬሽንና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እንዲያውቁት መደረጉንም ካፒቴን የሺዋስ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አየር መንገዱን ማኔጅመንት ለማነጋገር ሞክረን ጥረት ጥያቄያችንን በኢ-ሜይል አቅርቡ በተባልነው መሰረት ብናቀርብም ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ጊዜ ድረስ ምላሽ ባለማግኘታችን ሃሳባቸውን ልናካትት አልቻልንም፡፡

Read 9347 times