Saturday, 04 April 2020 11:59

ኮቪድ-19… አበስኩ ገበርኩ! - (ወግ)

Written by  በኃይለገብርኤል እንደሻው
Rate this item
(2 votes)

     “-ሰዎቹ ግን ምን ነካቸው! ለምን የሞት ነጋዴ ይሆናሉ! ሲሆን በዚህ ወቅትም አልነበር ትብብራቸውን ለወገኖቻቸው ማሳየት የሚገባቸው! አበስኩ ገበርኩ! ድሮ… የፊደል ዘሮችን በወጉ ያልለዩት እናቶቻችን እንዲህ ነበር እንዴ ያኖሩን? … የለም! ያን ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ጭካኔ ላለመኖሩ እኔው ራሴ ምስክር ነኝ፡፡-
                  
             ኮቪድ-19… ምን ዓይነት መከራ ነው ‘ባካችሁ! …ጥቁር ሞት፣ ስፓኒሽ ፍሉ (የሕዳር በሽታ)፣ ፈንጣጣ፣ ኩፍኝ፣ የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ)፣ ትክትክ፣ ንዳድ፣ ተስቦ፣ ቸነፈር… ኤች. አይ. ቪ.-ኤድስ፣ ኢቦላ፣ ኮሌራ፣ ሳርስ፤ አሁን ደሞ ኮሮና! …“ሃጢያታችን በዝቶ’ኮ ነው!” ብለዋል አሉ አብዬ ጉተማ:: እውነታቸውን ነው!
በነገራችን ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ በተለያዩ ወቅቶች በዓለማችን ተከስተው የነበሩ ከባባድ ወረርሽኞች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈት ዳርገዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1330 ተከስቶ የነበረውና ‘ጥቁሩ ሞት’ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ታላቁ ወረርሽኝ፤ ከ75 እስከ 200 ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ቅርጥፍጥፍ አድርጎ በልቷል ይባላል፡፡ ይሄን ያስነበበን ‘ሆሞ ዴኡስ’ የተሰኘው የዩቫል ኖህ ሃራሪ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ የበሽታውን ምንጭ በደፈናው ምሥራቅ ወይም ማዕከላዊ እስያ ሲል ነው የሚገልፀው፡፡ ‘ሁዋይ ኔሽንሽ ፌይል’ የተሰኘው መጽሐፍ ግን የ‘ጥቁር ሞት’ በሽታ ምንጭ ቻይና ናት ሲል ጽፏል:: በዓይጥ ተሸካሚነት በቁንጫ በኩል ይተላለፍ የነበረ ገዳይ በሽታ ነው ብሏል፡፡  
ሌላው ትልቁ ወረርሽኝ ደሞ ስፓኒሽ ፍሉ ወይም በእኛ አጠራር የሕዳር በሽታ እየተባለ የሚጠራው ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከ50 እስከ 100 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንደበላ ነው የሚነገርለት፤ ይሄ ታሪካዊ የከባድ ሚዛን ወረርሺኝ፡፡ በጨዋታችን ላይ አንደኛው የዓለም ጦርነት እ.ኤ.አ. ከ1914 እስከ 1918 ሲካሄድ፣ ሞቱ የተባሉት ሰዎች በአራት ዓመታት ውስጥ 40 ሚሊዮን ናቸው ይባላል፡፡
አሁን በቀጥታ ወደ ሰሞኑ አደገኛ ወረርሺኝ፣ ኮቪድ-19! …ይሄ በሽታ በቃኝ አያቅም እንዴ! በነገራችን ላይ፣ በእኛ፣ በኢትዮጵያውያን በኩል እየታየ ያለው ቸልተኝነት፣ በሽታውን ወደ ራስ የመጋበዝ ያህል ሆኖ ነው የሚሰማኝ፡፡ ይሄ አካሄድ ከእኛ በብዙ እጥፍ ለተሻለችው ለጥሊያንም እንዳልበጃት እያየንና እየሰማን ነው፡፡ አካላዊ ርቀታችንን በመጠበቅ ስርጭቱን ለመቆጣጠር የበኩላችንን ማድረግ የእያንዳንዳችን ግዴታ ነው:: በየቴሌቪዥኑ እየታዩ ያሉ ድርጊቶችም ቢሆኑ፣ ከመሰራጨታቸው በፊት ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ ተጠጋግቶ እጅን መተጣጠብ ወይም አንዱ ለሌላው ውሃ እያፈሰሰ ማስታጠብ… የመከባበር ባህላችን ቢሆንም… ድርጊቱ በራሱ ለበሽታው ስርጭት እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ያስተዋልን አይመስልም፡፡ ሰዉ በየግሉ ራቅ ብለው ወደ ሚቀመጡ ጀሪካኖች በመሄድ፣ እጆቹን በሳሙና ሙልጭ አድርጎ ቢታጠብ ነው የሚመከረው፡፡
…እስኪ ለማንኛውም ያንን የእጅ መታጠቢያ ከመድሃኒት ቤት ልግዛና በኪሴ ልያዝ… አሁን ‘ለታ አንዲት ብልቃጥ ‘ሳኒታይዘር’ በ50 ብር ሸጡልኝ፡፡ ልብ አድርጉ… 50 ብር ነው ያልኳችሁ! በፊት‘ኮ ያች የብልቃጥ የእጅ ማፅጃ 20 ብር ነበረች! ‘አበስኩ ገበርኩ’ አሉ ብርቅዬ! …(ብርቅነሽ አበበ ያሳደጉን የሰፈር እናታችን ናቸው፡፡) ‘ምን መዓት መጣብን… የምን መንሰፍሰፍ ነው’ ለማለት የሚጠቀሙበት የመገረም ወይም የመደነቅ አባባላቸው ነው:: …ለማንኛውም ያች ያልኳችሁ የብልቃጥ መታጠቢያ ሶስት ቀናትም አልቆየች፡፡ (ልጁ ሳኒታይዘር ከመድሃኒት ቤት ገዝቶ ሲወጣ፣ ‹ወንድም፣ በብልቃጡ ክዳን በየቀኑ ስንት ጠብታ ነው የምጠጣው› ብሎ ጠየቀኝ፣ ያልከኝ የሰፈሬ ልጅ፤ እግዚአብሔር ይይልህ ከማለት ውጭ  ምንም አልል!)
ያችን የገዛኋትን ሳኒታይዘር በቁጥ ቁጥ በየሰዓቱ መዳፌ ላይ ስጨምቃት… ያንን ያየ ሰው ደሞ ለኔም እያለ እጁን ሲዘረጋልኝ፣ እኔም ጠብ ሳደርግ ጨረስኳት፡፡ መቼስ እምቢ አይባል! ባይሆን የእነሱስ ከበሽታው መጠበቅ የኔም አይደል! …የእነሱ ቫይረስ ወደ እኔ እንዳይመጣስ ማድረግ ያለብኝ ትንሹ ነገር ይሄም አይደል! በቃ ይለቅ! ሌላ እገዛለሁ፡፡ …እና አሁንም ወደ መድሀኒት ቤት እየሄድኩ ነው፡፡
“ሳኒታይዘር አላችሁ?” ባንክ ቤት አጠገብ ያለችው ፋርማሲ ውስጥ የምትሰራውን አንዲት ወጣት ሴት ልጅ ጠየኳት፡፡
“አለ!” አለችኝ፣ በፊት ሽፋን በታፈነ ድምፅ፡፡
“ስንት ነው?”
“75 ብር፡፡” አጠገቧ የመስታወቱ ባልኮኒ ላይ ከተገጠገጡት በርከት ያሉ ጠርሙሶች መካከል የጥፍር ቀለም ብልቃጥ የምታክለውን መዝዛ አቀበለችኝ፡፡ አገላብጬ አየኋት፡፡ አበስኩ ገበርኩ! …“ይችማ ፊት 22 ብርም አልነበር የምትሸጠው!” አልኩ በገረሜታ፡፡ መልስ የሰጠኝ ሰው አልነበረም:: …ቤት ያሉት ሰዎቼ ትዝ አሉኝና፣ “አራት ጨምሪልኝ” አልኳት፤ ልጂቱን፡፡ በመገረም አስተዋለችኝና አምስቱንም ብልቃጦች በላስቲክ ከረጢት ጠቅልላ ሰጠችኝ:: አትራፊ ነጋዴ መስያት ይሆን! ከወደ ጥግ በኩል ደረቱን የነፋ ጎረምሳ ገንዘብ ተቀባይ፤ የመስታወት አጥር ውስጥ እንደ አንበሳ ተቆልሏል፡፡ አራት አዳዲስ የመቶ ብር ኖቶችን ከደረት ኪሴ ውስጥ መዥረጥ አደረኩና በመስታወቱ ቀዳዳ በኩል አቀበልኩት፡፡
“ደረሰኝ እፈልጋለሁ” አልኩ፣ ወደ ቁጣ በሚጠጋ ቃና፡፡
ጎረምሳው ምንም ሳይናገር የገንዘብ ማሽኑን ጠቅ ጠቅ አደረገና ጉርድ ደረሰኙን ከ25 ብር መልስ ጋር አጣብቆ አቀበለኝ፡፡ እያጉረመረምኩ ወጥቼ ሄድኩ፡፡ ‘እነዚህን ነበር ወደ ህግ መውሰድ’ ስል በውስጤ ተነጫነጭኩ፡፡
ሰዎቹ ግን ምን ነካቸው! ለምን የሞት ነጋዴ ይሆናሉ! ሲሆን በዚህ ወቅትም አልነበር ትብብራቸውን ለወገኖቻቸው ማሳየት የሚገባቸው! አበስኩ ገበርኩ! ድሮ… የፊደል ዘሮችን በወጉ ያልለዩት እናቶቻችን እንዲህ ነበር እንዴ ያኖሩን? … የለም! ያን ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ጭካኔ ላለመኖሩ እኔው ራሴ ምስክር ነኝ:: ያን ጊዜማ ጓሮ ያፈራው የእፅዋት መድሃኒት ሁሉ በነፃ ይሰጥ ነበር፡፡ ማፅናናት ካልተለየው እናታዊ ምክራቸው ጋር እየጨመቁ ይሰጡን የነበረውን መድሃኒት ውጠሽ ነው አዳሜ ሁላ እዚህ የደረስሺው፡፡ (ቀሺም ሁላ!!) ዳማ ከሴ በድንጋይ ሙቀጫ ተጨቅጭቆ ወይም በእናቶች መዳፍ ተዳምጦ፣ “ባቦል ቡና ጠጡት” ተብለሽ ነው ሁልሽም ያደግሽው፡፡
ነጭ ሽንኩርት የመሰለ ቢጫ ንፍጣችንን ሳይጠየፉ ካፍንጫችን ላይ በባዶ እጃቸው የጠረጉልን፣ ሰንሰል በጥሰው ቂጣችንን ያበሱልን እናቶች ናቸው እዚህ ያደረሱን:: ከእናታችን ማሕፀን ስንወጣ በነጭ ጨርቅ ለተቀበሉን፣ በጣታቸው ጥሬ ቅቤ ላዋጡን፣ ቅጫማችንን አራግፈው ቆሮቆራችንን በግራዋ ላከሙልን፣ ሙጃሌያችንን በመርፌ ቁልፍ ፈንቅለው ላወጡልን፣ እንቅፋት ያጎነውን የእግር ጣታችንን በምጣድ ማሰሻ ለተኮሱልንና በዶሮ ስብ አስረው ላከሙልን፣ የጥርሳችንን ጠዝጣሽ ሕመም በጣዝማ ማር ለፈወሱልንና ሃገራችንንና ልጆቻችንን ሰላም አድርግልን ብለው ዘወትር ለሚፀሉይልንና ፈጣሪያችንን ለሚማፀኑልን አዛውንት የመንደር እናቶቻችን ነው፣ አንዲት ጠውላጋ ሎሚ በአምስት ብር… አንድ ኪሎ ነጭ ሽንኩርት በ180 ብር ካልሸጥን ብለን ቡራ ከረዩ የምንለው! ‘አበስኩ ገበርኩ’ ማለት አሁን ነው!
ቁርጠት ሲያመን ስር ምሰው እንድናኝክ ላደረጉን የሰፈር አዛውንት አባቶቻችንና ሃገራችንን ከወራሪ ጠላት በደማቸውና ባጥንታቸው ለጠበቁልን ደሃ ወገኖቻችን ነው፣ ፌጦ በውድ ዋጋ ካልሆነ አንሸጥላችሁም የምንለው! ፊደል ያስቆጠረንን የዕውቀት አባታችንን ነው፣ ለአንዲት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ብጣሽ ጨርቅ የጡረታ ደሞዙን የሚያህል ገንዘብ ካልሰጠኸን አንሸጥልህም የምንል! በርግጥም ማፈሪያ ዜጎች እየሆንን ነው!
ይኸን ይመስላል ያለንበት ዘመን! በርግጥም ዛሬ ዛሬ መተዛዘንና መተሳሰብ የቀረ ይመስላል፡፡ …ሳኒታይዘሯን በገዛኋት ማግስት ቢሮ እንዳለሁ ያችን ደረሰኝ በኪሴ ውስጥ ከብር ጋር ተጣጥፋ ሳገኛት አገላብጬ አየኋት፡፡ የሸቀጡ ስም ‘ሳኒታይዘር’ መባል ሲገባው በምትኩ በ‘ኤስ’ የሚጀምር ሌላ የመድሃኒት ስም ተፅፎበታል፡፡ …አበስኩ ገበርኩ!
ከሳምንት በኋላ እዛች መድሃኒት ቤት አጠገብ ወዳለው ባንክ ሳመራ፣ የዛች የአጎራባቿ መድሀኒት ቤት በር በጠራራ ፀሐይ ተከርችሞ አየሁ፡፡
“ምን ሆኖ ነው የተዘጋው?” ስል ጠየኩት በረጅም መዳበሻ ይፈትሸኝ የነበረውን ወጣት የባንክ ቤት ሰራተኛ፣ በአገጬ ወደ መድሃኒት ቤቷ እያመለከትኩት፡፡
“ባለቤቱ በሰሞኑ በሽታ ታሞ ነው ይላሉ” ሲል፣ የምንግዴ መለሰልኝ፡፡
“ምን!?” በድንጋጤ መልሼ ጠየኩት፡፡
አፉን በጨርቅ የሸበበው ጥበቃ፣ ትኩር ብሎ ካየኝ በኋላ፣ “ምን ነው ጌታው? …ታውቀው ኖሯል እንዴ?” ሲል ጠየቀኝ፡፡
“እየነገርከኝ ያለኸው ስለዚያ ከውስጥ ይሰራ ስለነበረው አጭር፣ ወፍራም ወጣት ነው?” ሌላ ጥያቄ አስከተልኩበት፡፡
“አዎን፡፡ …ካሸር ሁኖ ብሩን ሲያግበሰብስ የነበረውን ኮበሌ ነው፡፡”
“አበስኩ ገበርኩ! … ምነው!” የእኔ የመገረም ምክንያቱ በቅርቡ በዚያች መድሃኒት ቤት የተዋለብኝ የገበያ ሸፍጥ እንደሆነ ልቤ ያውቀዋል፡፡
ወደ ባንኩ ጎራ ያልኩበትን ጉዳዬን ተኩሼ ስወጣ ባካባቢው ወደተቀመጠ የውሃ ጀሪካን ተጠጋሁና ብር የነካኩ እጆቼን ፍትግ… ፍትግትግ አድርጌ ታጠብኩ፡፡ ይሄን ሳደርግ ግን ደጃፏ ወደተከረቸመው መድሃኒት ቤት አተኩሬ እየተመለከትኩ ነበር፡፡ ‘ብር ቢከመር ከሞት አያድን…’ የሚል ድምፅ በውስጤ አስተጋባ:: ከየቦታው የሚሰበሰበው ብር፣ በብዙ የእጅ ንክኪዎች ስለሚሽከረከር፣ ለበሽታው ከሚያጋልጡ መንገዶች መካከል ነው መባሉን በተግባር የተገነዘብኩ ያህል ሆኖ ተሰማኝ፡፡ በየባንክ ደጃፎች የእጆቻችሁን ታጠቡ ግዳጅም ለዚህ ማሳያ ሳይሆን ይቀራል! …‘አቦ፣ በዚያ ወጣት ነጋዴ ላይ ገዳፋ ሆንኩበት ይሆን እንዴ!’ ሥራው ያውጣው እንግዲህ፡፡ ፈጣሪ ምህረቱን ያውርድልን፡፡ እኛም እንጠንቀቅ፡፡  



Read 1826 times