Print this page
Saturday, 04 April 2020 12:31

“አሰ ብ፤ ቀይ ባሕርና ወደባችን በዚያን ጊዜ”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   ቅኝት፡- በታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ ር)
የመጽሐፉ ርዕስ፡- አሰብ፤ ቀይ ባሕርና ወደባችን በዚያን ጊዜ
ደራሲ፡- ዮሐንስ ተፈራ
የአራተኛ ዘመነ ኅትመት፡- 2012 ዓ.ም
መካነ ኅትመት፡- ኦስሎ ኖርዌይ
የገጽ ብዛት፡- 418
የመጽሐፉ ዋጋ፡- 200 ብር


             መጽሐፉ ጥሩ የቋንቋና የቃላት ፍሰት አለው::  የምስጋናና የመግቢያ ትንታኔን ሳይጨምር   18 ምዕራፎችና 418 ገጾች ያሉት ነው፡፡ በምዕራፍ አንድ፡- ከቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ ስለምትገኘው የአሰብ ወደብ ገጽታ፣ ስለ አሰብ ባላባቶች፣ ስለ አፋር ሕዝብ፣ ስለ አሁኑ የኢትዮጵያ አፋሮች የክልል ሁኔታ፣ ስለ አፋሮች ጥንተ ታሪክ፣ ስለ አፋሮችና ኢትዮጵያዊነታቸው፣ ደንከል፣ አዳልና አፋር ስለ ሚባሉት ስያሜዎች፣ ስለ አፋሮች የባህል መድኃኒት፣ የባሕር ንግድ በአፋር እንዴት እንደነበር፣ ስለ አልዩ አምባ ምንነት፣ ስለ አፋሮች ብሔር ዘለል ጋብቻ፣ …ይነግረናል፡፡ በሀብትና በሥልጣን ምክንያት በአፋሮች መኻል ልዩነት እንደሌለም ደራሲው ዮሐንስ ያወሳናል፡፡ ግመል ለአፋሮች የበረሃ ጓደኛቸውና መርከባቸው እንደሆነም ያስታውሰናል፡፡ በምዕራፍ ሁለት አሰብ በፌዴሬሽን፤ በአውራጃና በራስ ገዝ አስተዳደር እንዴት ትተዳደር እንደነበር፤ በምዕራፍ አምስትና ስድስት፡- ደራሲው እንዴት ለመጀመሪያና ሁለተኛ ጊዜ ወደ አሰብ እንደሄደ፤ ስለ ሶቪየት ሩሲያ ካምፕ፤ በምዕራፍ ሰባት ስለ አሰብ ከተማ ማኅበራዊ ኑሮ፤ ምዕራፍ ስምንት፡- አሰብ የባሕር በርና ወደብ ሆና ለኢትዮጵያ እንዴት ታገለግል እንደነበር ያስገነዝበናል፡፡
በተጨማሪ በምዕራፍ ዘጠኝ፡- ስለ ሐሌብና ስለ ጢኦ ወደብ፤ በምዕራፍ ዐሥርና አሥራ አንድ፡- ስለ አሰብና የደርግ ፖለቲካ እንዲሁም ስለ መጨረሻው የመፈናቀል ሳምንት፤ በምዕራፍ አሥራ ሁለት፡- ስለ ምጽዋ ኮከብ መርከብ፤ በምዕራፍ አሥራ ሦስት፡- በባሕሩና በወደቡ ላይ ስለተሰማሩ ዋና ዋና ድርጅቶችና መሥሪያ ቤቶች ደራሲው ይነግረናል፡፡ በምዕራፍ አሥራ ዐራት ለዐፋር ሕዝብ የወንጌል ስርጭት እንዴት እንደ ነበር፤ በምዕራፍ አሥራ አምስት፡- ስለ ኢትዮጵያና ኤርትራ አንድነትና ልዩነት፤ የግል ሐሳቡን ሲያቀብለን በተቀሩት ምዕራፎቹ የኤርትራ ተወላጆች በኢትዮጵያ ላይ ስላላቸው አስተሳሰብና በእኛ በኩል መስተካከል ስላለባቸው ስሕተቶችና ስለቀድሞው የአሰብ ነዋሪዎች ማኅበር ይተርክልናል፡፡
የመጽሐፉ አጠቃላይ ጭብጥ  አሰብ  ወደ ዛሬይቱ ኤርትራ ከመጠቃለሏ በፊት የኢትዮጵያ በነበረችበት ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ለወደቡና ለከተማው እድገት ስላደረጉት አስተዋጽኦና አዘጋጁ በወቅቱ የአሰብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንባታ ውስጥ ስለነበረው ተሳትፎና የወጣትነት ዘመኑን ከሚወደውና ከሚያከብረው የአፋርና የኤርትራ  ማኅበረሰብ ጋር እንዴት እንዳሳለፈ፤ የወደቡ ሥራ አስኪያጆች ጥረት ምን ይመስል እንደነበር ማለፊያ በሆነ አተራረክ ያስቃኘናል፡፡
አቶ ዮሐንስ  የአሰብ ወደብ ሠራተኛ ከነበረበት ከመስከረም ወር 1969 ዓ.ም ጀምሮ በሻዕቢያና በሕወሐት የተባበረ ክንድ አሰብ እስከ ተደመሰሰችበትና እስከ ተፈናቀለበት ግንቦት 1983 ድረስ በዐይኑ ስላየው፤ በጆሮውም ስለሰማውና ልዩ ልዩ የታሪክ መጻሕፍትንና ሰነዶችን አንብቦ ከተረዳው ጭብጥ በመነሣት፣ አሰብ እንዳስፈላጊ ከተማና ወደብ ከመታወቋ በፊት ጥቂት የኢትዮጵያ የአንካላ ጎሳ አፋሮች የሚኖሩባት የበረሀ መንደር እንደነበረች፤ ከ1889 ወዲህ ደግሞ ሐሰን ኢብራሂም የተባለ ያካባቢው ገዥ፣ ከኢጣሊያው ቄስ ጁሴፔ ሳፔቶ ጋር  ባደረገው ስምምነት ሩባቲኖ ለተባለ የኢጣሊያ መርከብ ኩባንያ በ8100 ማሪያ ትሬዛ ገንዘብ አሰብን እንዴት እንደሸጣት፣ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አሰብ ለባብኤል መንደብና ለዐረቢያ ካላት ወሰንተኛነት የተነሣ ጠቃሚ ወደብ እየሆነች ስለመምጣቷ ያስረዳናል፡፡
ዶክተር ያዕቆብ ወልደ ማርያምም ቀደም ሲል “አሰብ የማነች»? በሚል ጽሑፍ ይሄን ጉዳይ ያስነበቡን ሲሆን ደራሲው ግን ሌሎች ምንጮችን በዋቢነት ሲጠቅስ፣ ከጉዳዩ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለውን ይህን መጽሐፍ በምንጭነት ለምን እንዳልተጠቀመበት ግልጽ አይደለም፡፡ ስለ አሰብ ተጽፈው የምናገኛቸው መጻሕፍት ብዙዎች ሲሆኑ ሁሉንም በተቻለው መጠን አሟጦ ቢጠቀምባቸው ብዙ መረጃዎችን ያጋራን ነበር፡፡ ይህም ሆኖ መጽሐፉ ለሦስተኛ ጊዜ መታተሙ በአንባብያን ዘንድ ተፈላጊ መሆኑንና በታሪክ መረጃነቱ ጠቃሚ ሰነድ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ መሬቱን ገለባ ያድርግላቸውና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ፤ የአሰብ ወደብ ለኢትዮጵያ እንደማይጠቅም በማውሳት «ግመሎቻቸውን (የኤርትራ ሰዎች ለማለት ነው) ውኃ ያጠጡበት፤ አንፈልገውም» ብለው ፌዘኛ ንግግር በተናገሩ ጊዜ መሰሎቻቸው ሲሥቁ፣ በርካታ ብዕረኞች አሰብን አስመልክቶ ጠንካራ የተቃውሞ ጽሑፎችን በግል ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ያወጡ ነበር፡፡ ምክንያቱም የአሰብ ወደብ ከግመል መጠጫነት ባለፈ በዓለም አቀፍ ወደብነቱ ለኢትዮጵያና ለመላው ዓለም ጭምር የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጠቀሜታ ስላለው ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢም  «ትንቅንቅ» በተሰኘ የሥነ ግጥም መድበሉ (1993፤265) አሰብ በኢትዮጵያ መንግሥት የፖለቲካ  ውሳኔና ፊርማ በሔደች ጊዜ ቅሬታውን፡-
«አይኖርም ነበረ አስችሎት አሉላ፤
ያሳደጋት አሰብ ከእጁ ተነጥላ፡፡
በጉልበት ተነጥቃ ያሳደጋት ልጁ፤
አይኖርም ነበረ አሉላ በደጁ፡፡
ከደጋማው ሀገር ማኽዳና ጉሎ፤
የወደብ ግርግር ባለበት ቃተሎ፤
አይፈርምም ነበር አሰብ ትሒድ ብሎ»… በሚል ግጥም ማሳተሙ  ይታወሳል፡፡
በዘመኑም ስለ አሰብም ሆነ ስለ ኤርትራ የሚፅፍም ሆነ የሚናገር ትምክህተኛ፣ የለየለት ጦረኛ፣ ነፍጠኛ፣ ጽልመተኛ፣ ያለፈውን ሥርዓት ናፋቂ፣ ደርግ -ኢሠፓ በሚል በኢሕአዴግ ካድሬዎች የስድብ ውርጅብኝ ይወርድበት ነበር፡፡ አቶ ዮሐንስ ግን ስለ አሰብ  የጻፈው የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ ተለያይቶ መቅረትን አይፈልግምና በአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂና በዶክተር ዐቢይ አህመድ መልካም ፈቃድ አሥመራና አዲስ አበባ ላይ ፍቅር ተርፎ በፈሰሰበት ሰዓት ላይ በመሆኑ ይመሰገንበታል እንጂ አይወቀስበትም፡፡ አቶ ዮሐንስ በትጋቱ በአዘጋጀው መጽሐፍ የሚያሳየን ስለ አፋር ሕዝብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወቱ፣ ስለተከበረው የባህል ዕሴቱ፣ ስለ ኢትዮጵያዊነቱና ደግነቱ፣ ስለ ቋንቋው፣ ስለ ጋብቻው፣ ስለ ግመሉ፣ ስለ መረጃ ልውውጡ፣ …በአሰብ ከተማ በኢትዮጵያ መንግሥት ተሠርተው ስለነበሩት ዘመናውያን የወደብ ሕንጻዎች፣ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ መኖሪያ ቤቶችና አፓርትማዎች፣ በአማንያን ሀብትና ንብረት ስለተገነቡት አብያተ ክርስቲያናት፣ ቤተመስጊዶች፣ ስለ ልዩ ልዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ በከተማዋ ውስጥ ይኖሩ ስለነበሩት 40 ሺህ ያህል ዜጎች፣ በከተማዋ ውስጥ ይኖሩ ስለነበሩ ታላላቅ ሰዎችና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ስለ ጓደኞቹ፣ ስለ ግዙፉ ነዳጅ ማጣሪያ… ነው፡፡
ወደቡ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጡና ታሪካዊ ሀብትነቱ  የኢትዮጵያ  ቢሆንም አቶ ዮሐንስ ይገባናል የሚል  አቋም አላንጸባረቀም:: በመሠረቱማ የዛሬን አያድርገውና  እንደነ ዓጼ ዐምደ ጽዮን፤ ዓጼ ዘርአ ያዕቆብ፤ እንደነ ዓጼ ወናግ ሰገድ (ልብነ ድንግል)፤ እንደነ ዓፄ ሠርፀ ድንግል፣ እንደነ ዓጼ አድያም ሰገድ ኢያሱ፣ እንደነ ዓጼ ቴዎድሮስ፣ ዓፄ ዮሐንስ… የመሳሰሉ ነገሥታት ከጠረፍ እስከ ጠረፍ እየዘመቱና ከውጭ ወራሪዎች ማለት ከቱርክና ከመሐዲስቶች፣ ከግብጾች፣ ከጣሊያኖች ጋር እየተዋጉ የሀገሪቱን አንድነት አስጠብቀውና እንደነ አዶሊስ፣ ዘይላ፣ ምጽዋ፣ አሰብ፣ ጂቡቲ፣ በርበራና ሐርጌሳ የመሳሰሉ ወደቦቻቸውን አስከብረው ለትውልዱ ቢያስተላልፉም እንደ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ኢጣሊያ የመሳሰሉ ተኩላዎች በኢትዮጵያውያን ላይ በፈጠሩት የልዩነት መንፈስ ያሁኑ የተፈጥሮ ወደቦቻችንን እንድናጣና ኢትዮጵያን ጨምሮ በኢኮኖሚ የደከሙ ትናንሽ መንግሥታት (ሶማሊያ፣ ጂቡቲ፣ ኤርትራ) እንዲፈጠሩ ተጽዕኖ ፈጥረውብናል፡፡ እናም ቀደም ሲል በመንግሥትነት የማይታወቁትና የኢትዮጵያ አካል የነበሩት ሶማሊያ፣ ጂቡቲና ኤርትራ ሥጋቸው ሳስቶ፣ አጠገባቸው በሚገኝ በውኃ ሀብት ተማምነውና በወደቦቹ በበለጠ መጠቀም ያለብን እኛ ነን ብለው ከኢትዮጵያውያን እህት ወንድሞቻቸው በመለየት የራሳቸውን መንገድ መርጠዋል:: ግን ኢትዮጵያ በመንግሥት አወቃቀሯና በኢኮኖሚ አደረጃጀቷ ልዕለ ኃያል ብትሆን ኖሮ፣  እንኳን የገዛ ልጆቿ ኤርትራ፣ ጂቡቲና ሶማሊያ  ይቅሩና ጐረቤቶቿ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ዑጋንዳና ግብጽ አብረንሽ ተዋሕደንሽ እንኑር፣ አብረን እንብላ፣ አብረን እንጠጣ፣ በኅብረት እንደግ ይሏት ነበር፡፡
ስለዚህ በአቶ ዮሐንስ ላይ እንደደረሰው ሰው ከኖረበት፣ ካደገበት፣ እትብቱ ከተቀበረበትና ከሚወደው ቀበሌ በድንገት ውጣ ተብሎ ሲፈናቀል የሚሰማው ስሜት ዘለዓለማዊ እንጂ  በቶሎ ሊረሳ የሚችል ወቅታዊ ጉዳይ አይሆንም፡፡ ዛሬም ቢሆን በመኻል ኢትዮጵያና በሀገሪቱ ጫፍ የሚገኙ የአንዳንድ ክልል ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች የእኛ ክልል በነዳጅ፣ በወርቅ በአልማዝና በተፈጥሮ ሀብት ክምችት የበለጸገ ነውና መጤዎች ውጡልን፣ ከኢትዮጵያ እንገነጠላለን፣ እንደ ወፍ በርረን እንሄዳለን፤ በኢትዮጵያም ውስጥ ስንበደል በብሔራዊ ጭቆና ስንረገጥ ኖረናልና ነፃ መውጣት አለብን እያሉ የሚያስፈራሩት፣ የሚያሟርቱትና ሕዝቡንም የሚያሰቃዩት ኢትዮጵያ በፌዴራሊዝም ሰበብ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አቅሟ፤ የደኅንነትና የአንድነት ጉልበቷ የላላ ስለመሰላቸው ነው፡፡     
ድምጻዊው የክብር ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ፡-
«ዑዑታ አያስከፋም ሲለዩ ተዋድዶ፤
ከዚህ የበለጠ ከየት ይምጣ መርዶ»
ብሎ እንዳቀነቀነው… በአሁኑ ሰዓት በኖርዌይ ኦስሎ ከተማ የሚኖረው አቶ ዮሐንስ፤ የመንግሥት ሠራተኛ ሆኖ ከኖረባት ከአሰብ ተፈናቅሎና በየመን በኩል  ወደ ሰው አገር ተሰድዶ ለ27 ዓመታት ያህል ቢኖርም፣ የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈባት አሰብ በፍጹም ልትረሳው ስላልቻለች የትዝታውን ቅባት ያፈሰሰበትን መጽሐፍ ጽፎ አሰብን እነሆ በረከት ብሎናል:: በደራሲ ዮሐንስ ብዕር በተለይ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና ከደርግ ዘመነ መንግሥት ወዲህ አሰብ በአምስት ወረዳዎች ተከፋፍላና ራስገዝ ሆና ከመንደርነት ወደ ዘመናዊ ከተማነት እንዴት እንደተለወጠችና እንዳደገች፣ የወደቡና የሠራተኛው ታሪክ፣ የሥራ ኃላፊዎች ትጋት፣ ስለንግድ መርከቦች ማለት ስለ ባልደርዚያ፣ ስለ ግርማዊነታቸው የጦር መርከብ፣ ስለምጽዋ ኮከብ መርከብ፣ ስለ ንጋት፣ ስለ ንግሥተ ሳባ፣ ስለ ላሊበላ፣ ስለ ጣና ሐይቅ፣ ስለ አብዮትና ስለ ነጻነት የኢትዮጵያ መርከቦች፣ በከተማዋ ይኖሩ ስለነበሩ ታላላቅ ሰዎች፣ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና ሊቀ መንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የአሰብ ከተማን በየዘመናቸው ሲጎበኙ የነበረው ፌስታ ምን ይመስል እንደነበር  በፎቶግራፍ ጭምር በተጠናከረ ማስረጃና አይረሴነት ባለው አተራረኩ ያስቃኘናል፡፡ በአጠቃላይ መጽሐፉ በታሪክ ሰነድነት ጭምር የሚፈለግና በምንጭነትም የሚጠቀስ ሲሆን ቀሪውን ይዘት ከመጽሐፉ ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 2715 times
Administrator

Latest from Administrator