Saturday, 04 April 2020 12:40

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(10 votes)

  ግብፅና ኮሮና፣ የፍርሀት ድምር

በድሐ መንደሬ
ይኸ ስውር ሌባ፣ ግሽበት ባራቆታት
ድርቅ ባሸማቀቃት
አንበጣ ባሰጋት
‹ዘቅዝቀህ ስቀለው›
‹መጤውን አስወጣው›
መባል ተጀምሮ በተፎከረባት
ያዲስ አለም ማርያም የእንጦጦዋ አዛኝት
የቁስቋሟ ቤዛ የግሸኗ እመቤት
ባለችበት አገር ባለችበት ምድር
የሴትን ልጅ ማገት፣ እናትን ማሸበር
ባገሬ ተሰምቶ
በወንዜ ተስፋፍቶ
ቀን በቀን ሳቃትት
ወጥሮኝ ፍርሀት
ተከትሎኝ ድብርት
ሆነና ነገሩ አንድ ሲሉት ሁለት
ሁለት ሲሉት ሦስት
ተስፋዬ በምለው
ፀሐዬ በምለው
በሕዳሴው ጉዳይ ግብፅ ያዘች ሽለላ
ሕዳሴ አይቀጥልም አይሞላም ብላ
ትራምፕ የሚባልን ደፋር አስከትላ
እንደገና ደግሞ ኮረና መጣና
በድሐ አገሬ ላይ ጉልበቱን አጠና
ይህን ጊዜ ታዲያ
ሲስፋፋ ኮሮና፣ ግብፅ ስትንጣጣ
የናንተን ባላውቅም
ያ ሁሉ ድብርቴ ከልቤ ውስጥ ወጣ
የፍራቴ ድምር ተስፋ ሆኖ መጣ።
ወዲያዉኑ ታየኝ
ያ ያድዋ መንፈስ
ያብቹ መደመር
ወንድማማችነት
ፍጹም መደጋገፍ
ፍጹም መተሳሰብ
ፍጹም መተዛዘን
አንዱ ላንዱ ማሰብ ባገሬ ሲመጣ።

Read 2920 times