Monday, 06 April 2020 00:00

‹‹ከኮሮና ሊታደገን የሚችለው ማህበረሰባዊ ዲሲፕሊን ብቻ ነው››

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

       - ተቋማችን ‹‹የኮሮና መድሃኒት ሰው ነው›› የሚል ንቅናቄ ጀምሯል
        - መንግሥት ሥራው በሽታውን መዋጋት ብቻ ነው መሆን ያለበት
        - ከፍተኛ የመከላከያና የህክምና መስጫ ቁሳቁስ ችግር አለ


           በሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ የሚመራው ‹‹የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ›› ከምሁራን፣ ታዋቂ ሰዎችና ባለሀብቶች የተውጣጣ የበጎ ፈቃደኞች ቡድን ከሰሞኑ ያቋቋመ ሲሆን ዓላማውም የኮሮና ወረርሽኝን ለመግታት በሚደረገው አገራዊ ርብርብ የበኩሉን ለመወጣት ነው፡፡ እንዴት? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ከአቶ ኦባንግ ሜቶ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡


        የበጎ ፈቃደኞች ቡድኑን ማቋቋም ያስፈለገው ለምንድን ነው?
ኮሮና በአለም ላይ የመጣ ችግር ነው:: ችግሩ በቻይና ከተከሰተና መስፋፋት ከጀመረ በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም እኔም ሆንኩ ሌሎች በይፋ ጠይቀን ነበር፡፡ በወቅቱ ግን ማንም በሽታው እኛ ጋ ይደርሳል ብሎ ያሰበ አይመስለኝም:: ግን ዛሬ የአለምን ታሪክ እየለወጠ ያለ ወረርሽኝ ሆኗል፡፡ ከዚህ የምንማረው፤ እኛም አለም በሽታውን ለመከላከል ከሄደበት ርቀት አንፃር፣ የራሳችንን መንገድ መፈለግ እንዳለብን ነው፡፡ ኮሮናን የሚገድለው ሰው ነው፡፡ እሱም የሚገድለው ሰውን ነው፡፡ ስለዚህ ኮሮናን ለመግደል የኛ እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው፡፡ የኛ የመከላከል መንገድ ባህላችንንና ትስስራችንን ያገናዘበ መሆን አለበት፡፡
የበሽታውን ሥርጭት ለመከላከል ምን ለማድረግ አቅዳችኋል?
አንደኛ፤ ሁላችንም እንደ ሰው በአንድ አመለካከት መቆም አለብን፡፡ ኮሮና አላማ የሚያደርገው ሰውን እንጂ ብሔርን አይደለም፡፡ ስለዚህ ጉዳዩን በፖለቲካ መነጽር ሳንመለከት እንደ ሰው ራሳችንንም ሌላውንም ማዳን አለብን፡፡ ኮሮና ብሔር፣ ሃይማኖት፣ ስልጣን፣ ቀለም ወዘተ አይለይም:: ስለዚህ እኛም ኮሮናን ለመከላከል ስንቆም እንደ ሰው መሆን አለበት፡፡ ከጤና ሚኒስትር ጋር ተገናኝተን ተነጋግረን ነበር፡፡ ሚኒስትሯ የሚሰሩት ሥራ የሚደነቅ ነው፡፡ ነገር ግን የሳቸው ብቻ በቂ አይሆንም፡፡ ሌላ ደጋፊ አካል መኖር አለበት፡፡ የሃይማኖት አባቶች፣ ሽማግሌዎች፣ ባለሀብቶች፣ ምሁራን፣ የአገር መከላከያና ደህንነት ሀይሎችን ያካተተ ተቋም ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ጠንካራ ሀይል በመፍጠር  የተቀናጀ ስራ መስራት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል፤ ይሄን ወረርሽኝ እንደ ሰው መግታት የምንችለው ጠንካራ ሥነ ሥርዓት (ዲስፕሊን) ስንከተል ነው:: ቻይናውያን ይሄን በሽታ የተቋቋሙት ጠንካራ ማህበረሰባዊ ዲስፕሊን ስላላቸው ነው፡፡ በተቃራኒው አሜሪካ በከፍተኛ መጠን እየተጠቃች ያለችው ማህበረሰባዊ ዲስፕሊን ስለሌላት ነው፡፡ ስለዚህ እኛም የቻይናን ዲስፕሊን እንደ መልካም ትምህርት ወስደን መተግበር አለብን፡፡ ‹‹ራስን መጠበቅ ሌላውንም ማዳን ነው›› የሚል ሥነ ሥርዓታዊ የጋራ አመለካከት ያስፈልገናል፡፡ የኛም ተቋም ‹‹የኮሮና መድሃኒት ሰው ነው›› የሚል ንቅናቄ ጀምሯል፡፡ ሰው ሆነን ነው ኮሮናን መቋቋም የምንችለው፡፡ ሰው መሆን ለራስ ክብር ሰጥቶ ሌላውንም ማክበር፤ ሕይወቱን መጠበቅ ነው፡፡ አሁን የኛ በሽታውን የመቋቋሚያ ትልቁ ሀብት ገንዘብ ሳይሆን ሥነ ሥርዓታችን ነው፡፡ ዲስፕሊን ነው ከዚህ ወረርሽኝ ሊታደገን የሚችለው፡፡
ተቋማችሁ በኮሮና ጉዳይ ላይ ምን ሊሰራ ነው ያሰበው?
በዕቅዶቻችን ላይ ከጤና ሚኒስቴርና ከሰላም ሚኒስቴር ጋር ተወያይተንበታል:: እነሱም ሀሳቡን ደግፈውታል፡፡ ሀሳባችን፤ አንድ ትልቅ የድጋፍ ማዕከል ማቋቋም ነው፤ በየክፍለ ከተማዎቹም ቅርንጫፍ ማዕከላት ይኖሩታል፤ ከዚያም ወረድ ብሎ ንኡስ ቅርንጫፎች ተከፍተው፣ ገቢያቸው አነስተኛ የሆኑ ሰዎች በራቸውን ዘግተው ሲቀመጡ፣ ድጋፍ የሚያገኙበትን መንገድ ለመዘርጋት ነው፡፡ ሃብታም አገሮች ገንዘብ ስላላቸው እንቅስቃሴ ቢገታ እንኳን ሱፐር ማርኬት ሄደው የሚፈልጉትን ይሸምታሉ፡፡ የኛ አገር ሁኔታ ግን እንደዚህ አይነት ዕድል የሚሰጥ አይደለም፡፡ አብዛኛው ማህበረሰብ ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ ነው፡፡ በርካታ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ለምነው የሚያድሩ፣ በቀን ገቢ ኑሮአቸውን የሚመሩ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ወገኖች አንድ ቀን እንቅስቃሴ ቢዘጋ ጉሮሯቸው አብሮ ይዘጋል፡፡ አሜሪካ ሕዝቧን ለመርዳት እኮ ትሪሊዮን ዶላር መድባለች:: እኛ እንዲህ ማድረግ እንችላለን? ከየትስ ነው የምናመጣው? እኛ እንዲህ ያለ አቅም የለንም፡፡ ስለዚህ በእያንዳንዱ ክፍለ ከተማ የተለያዩ ማዕከሎች ተቋቁመው፣ ሰዎች ያላቸውን የሚረዱበት፣ ያ እርዳታ ደግሞ ለአቅመ ደካሞች በሥርዓት የሚደርስበት አሰራር ከወዲሁ መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ የኛ ተቋሞ ይሄን ሥርዓት ለመዘርጋት ነው ያቀደው፡፡ ከአዲስ አበባ ባሻገርም ክልሎች ይህ አይነቱን ሥርዓት እንዲዘረጉ ምክረ ሃሳብ አቅርበናል፡፡ ለዚህ ድጋፍ ከአገር ውስጥም ከውጭም እርዳታዎችን ማሰባሰብ ያስፈልጋል፡፡ በዋናነት ሀብት ያለው በእጃችን ነው፡፡ ድሆች ያሉንን ያህል ሀብታሞችም አሉን፡፡ ዋናው ህብረት፣ ደግነት፣ ሰውነት፣ መተሳሰብ ነው፡፡ ሰው እንሁን፤ ሰው ስንሆን ብዙ ነገር ይገለፅልናል፡፡
ድጋፍ የምታሰባስቡት ከየትና እንዴት ነው?
ያሰብነው እንደ አንድ ትልቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ ከሌሎች ጋር ትስስር የሚያደርግ ፕሮጀክት ነው፡፡ አሁን ተሰሚነት ካላቸው ሰዎች ጋር ተሰባስበን ስራውን ጀምረናል፡፡ ፕሮጀክቱ በዋናነት አንድ የድጋፍ ማዕከል ለማቋቋም ነው፡፡ ያ የድጋፍ ማዕከል ስለ ኮሮና ያስተምራል፣ ይመክራል፤ መንግሥት ወረርሽኙን ለመከላከል በሚወስዳቸው እርምጃዎች፣ ተጎጂ የሚሆኑት ሕይወታቸው እንዳይናጋ ይደግፋል፡፡ እኔ ከጤና ሚኒስቴር በተረዳሁት መሰረት፤ ብዙ ያልተሟሉ ነገሮች አሉ፡፡ የህክምና መስጫ ቁሳቁስ የለም:: ለምሣሌ ለህክምናው እስከ 3 መቶ ሺህ ቬንቲሌተር ያስፈልጋል፤ ነገር ግን በመላ ሀገሪቱ ያለው ቬንቲሌተር 270 ብቻ ነው፡፡ ስለ መሳሪያው የሚያውቁ በርካታ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ለእነሱ ይሄንን ማሳወቅ በራሱ መፍትሔ ሊያመጣ ይችላል፡፡
በተረፈ ግን አቅማችን ውስን ነው፤ ስለዚህ ማህበራዊ ርቀትና ራስን መጠበቅ ላይ አተኩረን ማስተማር ወሳኝ ነው፡፡ አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች፤ ኮሮናን አጣጥለው የሚናገሩት ነገር ስህተት መሆኑን አስረግጦ መግለጽ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ‹‹ኮሮናን ዶግ አመድ አደርጋለሁ›› እያሉ ህዝብን በሚያሳስቱ ወገኖች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድም ይገባል፡፡ እኛ ድጋፍ በማሰባሰብ ጥሩ ልምድ አለን፡፡ ለ16 ዓመታት የሠራንበት ዘርፍ ነው፡፡ ይሄን ልምድ ተጠቅመን አንድም ሰው በኮሮና እንዳይሞት ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ ሰውን እጃችሁን ታጠቡ ካልን፣ ውሃ ያለማቋረጥ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ከፍተኛ ክትትልና ሥራ ማከናወን ይጠበቅብናል፡፡  
የኛም እንቅስቃሴ እነዚህን ሁሉ እየተከታተለ ለሚመለከታቸው አካላት መጠቆምን ይጨምራል፡፡ የድጋፍ ምንጫችሁ ለተባለው በርካታ ድጋፍ ሰጪ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች አሉ፤ በሀገር ውስጥም በውጪም፡፡ እነዚህ ባለሃብቶች ሰውን ለማትረፍ እንኳን ገንዘባቸውን ህይወታቸውንም ይሰጣሉ፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ አሁን ሁላችንም እንደ ወርቅ በእሣት የምንፈተንበት ጉዳይ ነው የገጠመን፡፡ ሠውነታችን የሚፈተንበት ወቅት ነው፡፡ ሰው መሆናችንን የምናሳይበት አጋጣሚ ነው፡፡ ቻይና በራሷ መንገድ፣ አሜሪካም በራሷ መንገድ በሽታውን ለማቋቋም እንደጣሩት ሁሉ፤ እኛም እንደ ኢትዮጵያዊ  ይሄን ችግር መወጣት ይኖርብናል፡፡  
በሽታው ከአዲስ አበባ ውጪ እንዳይሰራጭ ምን መደረግ አለበት?
እኛ ያሰብነው ከአዲስ አበባ ወዴትም የሚሄድ ነገር እንዲዘጋ ነው፡፡ ከተዘጋ በሽታው ወደ ክልሎች አይሰራጭም፡፡ ችግሩ ገጠር አካባቢ እንዳይደርስ ግን እያንዳንዱ ክልል በትጋት መስራት አለበት፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ፣ ከከተማ ወደ ገጠር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መገታት አለባቸው፡፡ እኛም በየቦታው ባሉን አባላት መልዕክታችንን እናስተላልፋለን፤ ድጋፍም እናደርጋለን፡፡
ይሄን ወረርሽኝ ለመቋቋም በመንግስት በኩል ምን ተጨማሪ ተግባር መከናወን ይኖርበታል?
አሁንም ግንዛቤ የመስጠት ስራ ነው ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት፡፡ አቅማችን የሚፈቅደው በግንዛቤ ላይ መስራት ነው፡፡ በመንግስት በኩል ዋና ተጠባቂ ስራ ግንዛቤ መስጠት ነው፡፡ የሚተላለፉ መልዕክቶች ደግሞ ሰዎች በሚገባቸው ቋንቋ መሆን አለባቸው፡፡ መልዕክቶቹ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መድረስ አለባቸው፡፡ በዚህ ረገድ ገና ብዙ መሰራት ይኖርበታል፡፡
ኮሮና ቫይረስን በተመለከተ የተሳሳቱ መረጃዎች በስፋት ተሰራጭተዋል፡፡ በኮሮና ዙሪያ መረጃ ከአንድ ማዕከል ብቻ ነው መውጣት ያለበት፡፡ የግንዛቤ ትምህርቱም ከአንድ ማዕከል ነው ወጥቶ መሠራጨት ያለበት፡፡ መንግስት በጠንካራ ስነስርአት የሚመራ የመረጃና የግንዛቤ ፍሰት ሊኖረው ይገባል፡፡ ሰዎች ከቤት አትውጡ ሲባሉ፤ ከእያንዳንዱ ቤት ኃላፊነት ወስዶ ነገሩን የሚቆጣጠር ሰው መሰየም ያስፈልጋል:: አባወራው ሊሆን ይችላል፣ ጐረቤትም ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ተወካዮች ብቻ እየወጡ የምግብና የውሃ ፍላጐትን ገዝተው ማሟላት ቢችሉ ጥሩ ነው፡፡ ነገሩ የፕሮቶኮልና የማስመሰል አይነት ከሆነ ግን ልፋታችን ሁሉ ዋጋ ቢስ ነው የሚሆነው፡፡ መንግስት አሁን ሌላ ምንም ስራ ሊኖረው አይገባም፡፡ ስራው በሽታውን መዋጋት ብቻ ነው መሆን ያለበት፡፡  

Read 2798 times Last modified on Saturday, 04 April 2020 13:04