Saturday, 04 April 2020 13:02

ሼህ አልአሙዲ የትም ቢሆኑ፣ ከኢትዮጵያ አልራቁም፡፡

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(4 votes)

   ሼህ መሐመድ አልአሙዲ፤ እስከዛሬ ለብዙ ሺ ኢትዮጵያውያን፣ የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡ በቀጥታና በተዘዋዋሪ፣ መቶ ሺ ኢትዮጵያውያን በስራ ራሳቸውን ችለው  መተዳደሪያ ገቢ አግኝተዋል ከነቤተሰባቸው፣ በርካታ መቶ ሺ ሰዎች ሰርቶ የመኖር የክብር ኑሮ ተጐናጽፈዋል ማለት ነው፡፡ በርካታ አምራች ፋብሪካዎችንና ቢዝነሶችን በማቋቋም፣ የአገራችን የኢኮኖሚ አቅም እንዲያድግ፣ ሼህ አልአሙዲ አቻ የሌለው ብዙ ቁም ነገር ሰርተዋል፡፡ አምስት ድርጅቶች የነበሩት የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕን ብቻ ብናይ፣ ዛሬ ከ25 በላይ ድርጅቶችን ያቀፈ ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም ሆኗል፡፡
ሼህ መሐመድ አልአሙዲ፣ በችግርና በፈተና ጊዜ፣ ለአገራቸው “ፈጥኖ ደራሽ” እንደሆኑም፣ በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ የውለታቸው ብዛት ለቁጥር ያስቸግራል የሚባለው፤ በእርግጥም ብዙ ስለሆነ እንጂ በማጋነን አይደለም፡፡ ሰሞኑን እንኳ፤ የበሽታ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቋቋም የሚውል 120ሚ ብር አበርክተዋል፡፡
ለሆስፒታል፣ ለትምህርት፣ ለስፖርት፣ ለኪነጥበብና ለሌሎች መስኮች፣ በየጊዜው የድጋፍ ጥሪ ሲቀርብ፣ የሼክ አልአሙዲ ድጋፍ ቀድሞ እንደሚደርስ ነው ሁሌም የሚጠበቀው፡፡ ነገር ግን፣ ከተጠበቀው በላይ አብዝተው ነው የሚለግሱት፡፡ በምግብ እጥረት የተጐዱትን ለመርዳትስ፣ ደራሽ አለኝታ ያልሆኑበት ጊዜ መቼ ነው? የኢትዮጵያን ክብር ከፍ ለማድረግ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ አለማቀፍ ጉባኤዎችን በስኬት ለማከናወን በሚደረግ ጥረትም፣ ሼህ አልአሙዲ እንደራሳቸው ጉዳይ ሲሰሩ ነው የኖሩት፡፡ የአገርን ችግር የሚያቃልል፣ ክብሯን የሚያጠብቅ ድጋፍ እንዲሰጡና ኃላፊነት እንዲሸከሙ ጥሪ ሲቀርብላቸው፤ ከተጠየቁት በላይ እጥፍ ድርብ ይደግፋሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ደግሞ፣ እስኪጠየቁ ድረስ ሳይጠብቁ፣ ለአገር ይበጃል ብለው የሚያስቡትን በልባዊ ፍቅር ይሰራሉ፡፡  
ይሄም ብቻ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ የወደፊት ታሪክ እንዲፈካና ብሩህ እንዲሆን፣ የወደፊት የአገር ጉዞ በብልጽግና ጐዳና እንዲገሰግስ፣ ሼህ አልአሙዲ በአርቆ አሳቢነት፣ ሳያሰልሱ በመስራትም ቀዳሚ ናቸው፡፡ ወደፊት ከኢትዮጵያ የእድገት ታሪክ ጋር አብሮ የሚወሳ ተግባራቸው፤ ለአገራቸው ያላቸውን ወደር የለሽ ፍቅር፣ ብሩህ ተስፋና ምኞትን ያሳያል፡፡
ሼህ አልአሙዲ፣ ካሁን በፊት ከፍተኛ ስጦታ በማበርከትና ቦንድ በመግዛት ድጋፋቸውን እንደገለፁት ሁሉ፣ እንደገና በቅርቡ፣ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ተጨማሪ ከፍተኛ ገንዘብ ሰጥተዋል፡፡
ጐበዝ ተማሪዎችን በመርዳት፣ ለህዋ ምርምርና ለሳተላይት ማዕከል ትልቁን ገንዘብ በማበርከት፣ ሼህ አልአሙዲ አገራቸውን ሲደግፉ፤ በማግስቱ ተዓምረኛ ለውጥና ውዳሴ ያስገኛል ብለው አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን የወደፊት ጉዞ ለማቃናትና ለማሳመር ግን ይረዳል፡፡ ለሚቀጥሉት አመታት ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም የሚፈጥር የህዳሴ ግድብን በመደገፍም፣ የኢትዮጵያ የወደፊት ታሪክ የብልጽግና ታሪክ እንዲሆን ሰርተዋል፤ እየሰሩም ነው፡፡
ለድል ጊዜም ሆነ ለፈተና፣ ለአጣዳፊ ችግርም ሆነ ለዘላቂ የስኬት ታሪክ፣ ሼክ አላሙዲ፣ ከአገራችን ጐን አልተለዩም፡፡
“እኔም ችግር ገጥሞኛል”፣ “እኔም ፈተና ላይ ነኝ” ብለው፣ ለአገራቸው ከማሰብና ከመስራት፣ ስንዝር ታህል ወደኋላ አለማለታቸውን ስናይ፣ የአገር ፍቅራቸው እጅግ ጥልቅ፣ ሃሳባቸውም ሰፊ፣ ራዕያቸውም ብሩህ እንደሆነ ለመረዳት አይከብድም፡፡
በአጠቃላይ፣ ሼህ መሐመድ አልአሙዲ ለአገራቸው ያከናወኑት እልፍ ተግባር፣ በጣም የሚደነቅ፣ የሚመሰገን፣ በአርአያነትም ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ለዘመናት በክብር የሚዘልቅ ትልቅና ልዩ ተግባር ነው ማለት ይቻላል፡፡
ማመስገን ለራስ ነው፡፡
በእርግጥም፣ በፍቅርና በሙሉ ልብ የሚሰራ ሰው፤ ተግባሩን ያስቀድማል እንጂ፣ ምስጋናን እና አድናቆትን አገኛለሁ ብሎ አይሰራም፡፡
እናም፣ ምስጋና ማቅረብ፣ አድናቆትንና ክብርን…መግለጽ፣ ከሁሉም በፊት ለራስ ነው፡፡ የመቶ ሺዎችን ህይወት የሚያሻሽልና የስራ እድሎችን በብዛት የሚፈጥር ሰው፣ ከሁሉም በላይ ሊደነቅና ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ እርዳታ ከመስጠት በእጅጉ ይልቃል፡፡ አዎ፤ ከአጣዳፊ አደጋና ፈተና የሚታደግ እርዳታ በጣም ይመሰገናል፡፡ ግን ጊዜያዊ ነው፡፡ የስራ እድሎችን በሰፊው መፍጠር ነው ዘላቂው የተባረከ ተግባር፡፡
በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች፣ በተረጂነት ሳይሆን፣ በስራ ራሳቸውን ችለው፣ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን የሚስተዳደሩት ሰፊ የስራ እድልን መፍጠር፣ በእጅጉ ያስመሰግናል፡፡ ለምን? የሰውን ኑሮ ለሚያሻሽል ጥሩ ተግባር ትልቅ ዋጋ የመስጠት ጉዳይ ነው፡፡
አገርን ከበሽታ ወረርሽኝ ለመታደግ፣ በፈተና ጊዜ መደገፍም፣ ትልቅ ውለታ ነው፡፡ ይህን የምንለው፣ ድጋፍ ሰጪዎችን ለመጥቀም አይደለም፡፡ ቅንነት ለራስ ነው፡፡ ውለታ ቢስ አለመሆን ነው፡፡
እንደ ህዳሴ ግድብ የመሳሰሉ ታሪካዊ ስራዎች ደግሞ አሉ፡፡ ስራዎቹን ማሳካት፣ እንዲሳኩም መደገፍ፣ ታሪክን መስራት ነው፡፡ እዚህ ላይ፣ የሼህ አልአሙዲ ድጋፍ ምን ያህል ትልቅ እንደሆነ አስቡት፡፡ የአገር ብልጽግና እውን እንዲሆን፣ በብሩህ ራዕይና በአርቆ አሳቢነት የሚከናወኑ እንዲህ አይነት ተግባራት የተባረኩ ናቸው የሚባለው፤ ለአገር ብልጽግና ሊኖረን ከሚገባ መልካም ምኞትና ክብር የተነሳ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ረቡዕ እለት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሁለት አበይት ጉዳዮችን አጉልተው አንስተዋል፡፡ በሁለቱም ጉዳዮች ላይ፣ በጥንቃቄና በአላማ ጽናት እንድንተጋ ጠ/ሚ ዐቢይ ማሳሰባቸው አለምክንያት አይደለም፡፡ የበሽታ ወረርሽኝን ለመከላከልና የህዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ… በሌላ አነጋገር፣ አጣዳፊ ፈተናዎችን ለማሸነፍና ዘላቂ የብልጽግና ራዕይን ለማሳካት፣ በጥንቃቄ ተግተን መስራት እንዳለብን ነው የተናገሩት፡፡
አገርንና ዜጐችን፤ ዛሬ ከአደጋ ለማትረፍ፣ ለነገም… የተሻለ ኑሮ ለመፍጠር፣ ድንቅ ታሪክንም ለመስራት መትጋት ነው፤ የአገር ፍቅር፡፡ የዜግነት ፍቅር፡፡
በዚህ በዚህ፣ ሼህ አልአሙዲ ቀዳሚ ተጠቃሽ፣ ባለውለታና አርአያ ናቸው፡፡ ባሉበት ስፍራ ሁሉ፣ ሃሳባቸው ከኢትዮጵያ ጋር እንደሆነው ሁሉ፤ ኢትዮጵያም ውለታ መላሽ ብትሆን እንዴት መልካም ነበር? የአገር ድህነት ይጐዳል፣ ያስጠቃል፡፡
ቢሆንም ግን፣ ጠ/ሚ ዐቢይ፣ ካሁን በፊት በተግባር እንዳሳዩን፣ ኢትዮጵያ ባላት አቅም ሁሉ ለዜጐችዋና ለወዳጆችዋ አለኝታ ለመሆን መጣር እንዳለባትና እንደምትችል ጥሩ ትምህርት አግኝተናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ከእስርና ከችግር ለማላቀቅ፤ ብዙ ሰርተው ብዙ እንደተሳካላቸው አይተናል፡፡ በሼህ አልአሙዲ ጉዳይ ላይም በተደጋጋሚ ጥረው፣ የተወሰነ ውጤት አግኝተዋል፡፡
ነገር ግን፣ ጥረታቸው እንደማይቋረጥም ቃል ገብተዋል፡፡ የሼህ አልአሙዲ ጉዳይ ለኢትዮጵያ  ትልቅ ትርጉም እንዳለው የሳዑዲ መንግስት ተገንዝቦ፤ በተሟላ መፍትሔ በዚህ ፈታኝ ጊዜ ኢትዮጵያን እንዲተባበር፣ ጠ/ሚ ዐቢይ የሚያደርጉት ጥረትም ቶሎ እንዲሳካ ምኞታችን ነው፡፡     

Read 1851 times