Tuesday, 07 April 2020 21:12

ታዋቂ ኢትዮጵያውያን - ስለ ኮሮና፣ ጥንቃቄውና ተግዳሮቱ ይናገራሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

መላውን ዓለም እያስጨነቀ ያለው ኮሮና ቫይረስ በአገራችን መከሰቱን ተከትሎ የወረርሽኙን ስርጭት ለመቀነስ መንግስት፣ የግል ተቋማትና በጎ ፈቃደኞች ለሕዝቡ ግንዛቤ በማስጨበጥና በመቀስቀስ እዲሁም ድጋፍ ማሰባሰብ ከፍተኛ እያደረገ ይገኛሉ፡፡ ለመሆኑ ታዋቂ ሰዎችና በጎ ፈቃደኞች እኒህን በጐ ተግባራት ሲፈጽሙ የራሳቸውን ደህንነት በምን መልኩ እየጠበቁ ነው? ምን ያህልስ ይጠነቃሉ በሚሉና ህብረተሰቡ በሚያደርገው ጥንቃቄ ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ታዋቂ ግለሰቦችን አነጋግራ አስተያየታቸውን አጠናቅራለች፡፡

(ያሬድ ሹመቴ፣ የፊልም ባለሙያና በጎ ፈቃደኛ)


‹‹ላለፉት ሁለት ሳምንታት ራሴን ከቤተሰቤ አገልያለሁ››
፣ኮሮና ቫይረስ በአገራችን ተከስቷል፤  እንደሚታወቀው ዓለምን እያመሰም ነው:: ነገር ግን እኛ አገር ከተባባሰ ከሌላው ዓለም የበለጠ ጥፋት ያደርሳል፡፡ ይሄ ከአኗኗራችን ከባህላችንና ከድህነታችን ጋር የሚገናኝ ነው:: ስለዚህ “ጥምረት ለሰብዓዊነት ድጋፍ” የተሰኘው ህብረታችን ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ በሚደረገው የእንቅስቃሴ ገደብ፣ ሰው በርሃብ እንዳይሞት ጥንቃቄና ቅድመ ዝግጅት ያስፈገዋል፡፡ ከዚህ በፊት በዓለም ላይ ብዙ ችግርና መከራዎች በሰው ልጅ ላይ ሲደርሱ ኖረዋል፡፡ ለምሳሌ የዛሬ 100 አመት፣ በዓለም ላይ ወረርሽኝ ሆኖ የተከሰተው ስፓኒሽ ፍሉ (በኢትዮጵያ የህዳር በሽታ ይባላል፡፡)  በርካታ ጥፋት አድርሶ አልፏል። ይህ በሽታ ከመቶ አመት በፊት ሲከሰት የዓለም ሕዝብ ብዛት 1. 2 ቢሊዮን ነበር፡፡ አሁን ከ7 ቢሊዮን ተሻግሯል:: የዛን ጊዜ ግማሽ የሚሆነውን የዓለም ሕዝብ (500 ሚ.) ሕዝብ ሲያጠቃ፤ የ50 ሚሊዮን ሰዎችን ሕይወት ነጥቋል፡፡ ከዓለም ሕዝብ 10 በመቶውን ሕይወት አጥፍቷል ማለት ነው፡፡ በአገራችንም በተለያየ ጊዜ የተለያየ ወረርሽኝ ተከስቷል፡፡ በአፍሪካም ደረጃ ኢቦላ ቫይረስን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ግን በመላው ዓለም ብዙ ጥፋት እያደረሰ ነው:: ዞሮ ዞሮ የእኛንም አገር በር አንኳኩቷል፡፡ በዓለም ላይ የተከሰቱትን ወረርሽኞች የተሻገሩት ደግሞ በቂ ዝግጅት ቀድመው ያደረጉ አገራት ናቸው:: እኛም ለዚሁ እየተዘጋጀን ነው፡፡ በርካታ የምግብ እህል እየሰበሰብን ነው፡፡ እህልም ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል በኩል 0102 (ዞሮ አንድ ዜሮ ሁለት) በሚል አጭር የባንክ ቁጥር ከፍተን፣ ገንዘብ እየገባ ነው፡፡ ባለፉት 10 ቀናት ወደ 1 ሚ.ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወደ ሂሳብ ቁጥሩ ገብቷል፡፡ እንግዲህ በአገር ፍቅር ቴአትር ግቢ ውስጥ ችግሮች ሲከሰቱ በርካታ ድጋፎችን ይሄ ጥምረት ይሰባስባል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ድጋፍ የማሰባስብባቸው ማዕከላት ብሎ ከሚጠቅሳቸው የአገር ፍቅር ቴአትር አንዱ መሆኑን ደጋግሞ ጠቅሷል፡፡
አሁን እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶችና ድጋፍ የማሰባሰብ ስራዎች ከሚያስፈልገው አንጻር 10 በመቶ እንኳን አይሞሉም፡፡ እኛ ብቻ ሳንሆን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚደረገውና በእነታማኝ በየነ ግሎባል አሊያንስ የሚከናወነውንም እንቅስቃሴ ጨምሮ ማለቴ ነው፡፡ አሁን ካለው ተጨባጭ ችግር አኳያ በጣም ትንሽ ነው:: ነገር ግን የምንችለውን ዝግጅት እያደረግን ነው:: በዚህ በአገር ፍቅር የሰብዓዊ ድጋፍ ጥምረት እስካሁን ወደ 3ሚ. የሚያወጣ የምግብ እህልና ልዩ ልዩ የንጽህና መጠበቂያ እቃዎችን ሰብስቧል:: በለንደን የሚገኙ ግለሰብ የግማሽ ሚ.ብር ዕቃ ገዝተው ሊልኩልን በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ እሱ ሲመጣ 3.5 ሚ የሚገመት ይሆናል ማለት ነው:: አሁን ከተማ አስተዳደሩም የሰብዓዊ ድጋፍ ጥምረትም ሌላውም የሚሰበሰበው ጠቅላላ ኤግዚቢሽን ማዕከል በሚገኘው ዋናው ቋት ይገባል፡፡ እኛም ከስር ከስር እየላክን ነው፡፡
የሰብዓዊ ድጋፍ ጥምረት በውስጡ ‹‹ኬር ኤንድ ሼር››፣ ‹‹ቅድሚያ ለሰብአዊነት››፣ ‹‹ጉዞ አድዋ››፣ ‹‹ሰው ለሰው›› ስብስብ፣ አገር ፍቅር ቴአትርና ቀይ መስቀል የተጣመሩበት ነው:: እነዚህ በጋራ ነው የአገር ፍቅሩን የማሰባሰብ ስራ የሚሰሩት፡፡ ጥምረቱን ወደ አገር ፍቅር ማህበርነት የማሳደግና አገር ችግር ላይ ስትወድቅ ቀድሞ የሚደርስ ጠንካራ ተቋም ለማድረግም እቅድ ተይዟል፡፡
ሌላው በዚህ ችግር ላይ ግንባር ቀደም ተሰላፊ የሆኑ በጎ ፈቃደኞች፣ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ሥራቸውን ሲያከናውኑ ራሳቸውን ይጠብቃሉ ወይ? ለተባለው የግድ መጠበቅ አለባቸው፤ አለብን፡፡ ለሌላውም ማሰብና መጠንቀቅ ስላለብን፡፡ ለምሳሌ እኛ አገር ፍቅር ውስጥ የምንሰራ ድጋፍ አሰባሳቢ በጎ ፈቃደኞች፤ በተቻለ አቅም የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘሮችን፣ አልኮል፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛና ጓንቶችን እንጠቀማለን፡፡ ለድጋፍ ለሚመጡትም  አልኮልም ሳኒታየዘርም በመስጠት  እጃቸውን እንዲያፀዱ እናደርጋለን:: ወደ ግሌ ስመጣ ላለፉት 10 ቀናት  ከቤተሰቤ ተገልያለሁ፡፡ ስራ ውዬ ወደ ቤተሰቤ አልሄድም፤ ከሰው ጋር ቅርርብም አካላዊ ንክኪም ሆነ መጨባበጥ የለኝም፡፡ ይህንን የድጋፍ ማሰባሰብ ስራ ሰርቼ እስካጠናቅቅ ወደ ቤተሰቤ አልሄድም:: በዚህ መልኩ ራሴን በመጠበቅ ነው ለሌላው መድረስ የምችለው፡፡ ሀኪሞችም ከፍተኛ የመንግሥት ሃላፊዎችም ታዋቂ ሰዎችም ሆኑ በጎ ፈቃደኞች በዚህ መልኩ በመጠንቀቅ፣ ለሰፊው ማህበረሰብ ምሳሌ መሆንና ማስተማር አለባቸው የሚል መልዕክት አለኝ፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ወረርሽኝ ተፈጥሮን ለማስተካከልም የራሱ በጎ ጎን ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ የካርቦን ልቀት ተስተካክሏል፣ የኦዞን መሸንቆር እያገገመ ነው፣ ምክንያቱም ፋብሪካም መኪናም ስላቆመ ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ችግር ተረጋግተንና ተደጋግፈን ካለፍን፣ መጪው ጊዜ የተሻለ አየር የምንተነፍስበት ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ እስከ ዛሬ ተፈጥሮን የሚጎዳ ቴክኖሎጂ ስንሰራ ነው የኖርነውና፡፡  አሁን ላይ መጠጥና ሱሰኝነትም ቀንሷል፡፡ ይህንን ሁሉ በበጎ ጎኑ ካየነው፣ ችግሩን ተሻግረን መልካም ቀን እናያለን፡፡

Read 1137 times