Saturday, 11 April 2020 13:38

ስለ ኮሮና ቫይረስ የተሳሳቱ መረጃዎች?!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   የቫይረስ ምርመራን አስመልክቶ በደቡብ አፍሪካ የተሰራጨው አሳሳች ቪዲዮ

         በደቡብ አፍሪካ የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ መሳሪያዎች በቫይረሱ የተበከሉ መሆናቸውን የሚገልጽ የቪዲዮ መረጃ በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት ተሰራጭቶ ነበር፡፡ በቪዲዮው ላይ አንድ ሰው፣ ደቡብ አፍሪካውያን የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እንዳያደርጉ ጥሪ ያቀርባል፡፡ (ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው የሚያረጋግጠውን ምርመራ ማለት ነው፡፡)
“በምንም ዓይነት ሁኔታ ምርመራ እንዲያደርጉላችሁ አትፍቀዱ፡፡ መሳሪያው በኮቪድ-19 ሊበከል የሚችልበት ዕድል አለ” ይላል፤ ሰውየው በቪዲዮው ባሰራጨው መልዕክት፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰዎች እነዚህ መሳሪያዎች ቫይረሱን ለማሰራጨት ዓላማ እየዋሉ እንደሆነ   እየተናገሩ ነው የሚለው ሰውየው፤በእንግሊዝ የመመርመሪያ መሳሪያዎቹ በቫይረሱ ተበክለው መገኘታቸውን የሚጠቁሙ ሪፖርቶችንም ያጣቅሳል፡፡  
የኢስተርን ኬፕ የጤና ቢሮ፤ ሰውየው ያሰራጨው መረጃ መሰረተ-ቢስ ነው ብሏል፡፡
“የመመርመሪያ መሳሪያዎቹ በቫይረሱ ያልተበከሉ መሆናቸውን እያስታወቅን፤ የተበከሉ የመመርመሪያ መሳሪያዎችን በሰዎች ላይ በመጠቀም ህይወታቸውን ፈጽሞ ለአደጋ እንደማናጋልጥም በአጽንኦት ልንገልጽ እንወዳለን” ሲሉ የጤና ቢሮው ቃል አቀባይ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል፡፡ ይህን የተሳሳተ መረጃ ያሰራጨው ሰውዬም፤ የማታ ማታ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ፍ/ቤት ቀርቧል፡፡
ክትባቶች በአፍሪካውያን ላይ እየተሞከሩ አይደለም አፍሪካውያን አዲስ የኮሮና ቫይረስ ክትባት መሞከሪያ ሊሆኑ ነው የሚል መረጃ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ተሰራጭቶ ነበር፡፡ ሆኖም ይሄ ከእውነት የራቀ ነው - ለኮቪድ 19 የተሰራ ክትባት የሌለ ሲሆን የተወሰኑ ሙከራዎች ብቻ ናቸው እየተደረጉ ያሉት፤ ከእነዚህም ውስጥ አንዳቸውም ደግሞ በአፍሪካ አገራት ውስጥ የሚከናወኑ አይደሉም::
አፕሪል 1 የሁለት ፈረንሳይ ሳይንቲስቶች ቃለ መጠይቅ በኢንተርኔት ላይ በስፋት መሰራጨቱን ተከትሎ፤ ይሄ ጉዳይ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ዳግም ቁጣ ያስነሳ ሲሆን እኒህ ሳይንቲስቶች የኮሮና ክትባት በአፍሪካውያን ላይ ይሞከር ብለዋል በሚል ተወግዘዋል፡፡ ከሳይንቲስቶቹ አንዱ፤ “የሳንባ ምች ክትባት ኮሮና ቫይረስን በመከላከል ረገድ ውጤታማ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ “የፊት ጭንብል፣ ፈዋሽ መድሃኒትና አርቴፊሻል የመተንፈሽያ መሳሪያዎች በሌሉባት” አፍሪካ ሙከራ ቢደረግ ሲል ይጠይቃል፡፡
ይሄ አስተያየት ከፍተኛ ነቀፌታ የተሰነዘረበት ሲሆን ከእነዚህም መካከል የዓለም ጤና ድርጅት እንዲሁም ሁለት  ክዋክብት የአፍሪካ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ይገኙባቸዋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም፤ “አፍሪካ አሁንም ወደፊትም የክትባት መሞከሪያ አትሆንም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል ሳይንቲስቶቹ የተናገሩት ሀሳብ ተዛብቶ መቅረቡን ገልፀዋል፡፡ በቃለ መጠየቁ ላይ ሳይንቲስቶቹ የክትባት ሙከራው መጀመሪያ በአፍሪካ ላይ መደረግ አለበት አላሉም - ተመሳሳይ ጥናት እዚያም መካሄድ እንዳለበት ነው የገለፁት፡፡
ጥቁር የቆዳ ቀለም ኮቪድ - 19 ቫይረስን አይቋቋምም
የቆዳ ቀለምንና በሽታውን መቋቋምን አስመልክቶ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሀሳቦች ሲሰራጩ ቆይተዋል፡፡ ማርች 13 ቀን 2020 ዓ.ም የኬንያ የጤና ሚኒስትር “ጥቁር ቆዳ ያላቸው ሰዎች ኮሮና ቫይረስ አይዛቸውም” የሚለውን አሉባልታ ውድቅ አድርገውታል፡፡
 “ይሄንን ሀሳብ የሚደግፍ አንድም ማስረጃ የለም፤ እንዲያውም በእርግጠኝነት የምናውቀው ጥቁር የሰውነት ቆዳ ያላቸው ሰዎች በቫይረሱ እንደሚያዙ ነው፡፡” ብለዋል፤አንድ የህክምና ባለሙያ፡፡
ከአዘጋጁ፡-
ቢቢሲ ሌሎችም በአፍሪካ ሲሰራጩ ነበሩ ያላቸውን የተሳሳቱ መረጃዎች አስነብቧል:: በኮሮና ዙሪያ የሚያዋጣው፤ መረጃዎችን ከተዓማኒ ምንጮች ብቻ መውሰድ ነው፡፡


Read 1424 times