Saturday, 11 April 2020 13:45

ከበረራ ነፃ የሆነ ሰማይ - ከኮቪድ-19 በኋላ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(6 votes)

       ከአንድ ሚሊዮን ስድስት መቶ ሺ በላይ የዓለማችን ሕዝቦች ያጠቃውና መቶ ሺዎችን ለሞት የዳረገው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ አራተኛ ወሩን ይዟል፡፡ በሽታው መላውን የአለም አገራትን ለማዳረስ የወሰደበት ጊዜም እጅግ በጣም አጭር ነው፡፡ የወረርሽኙን ስርጭት መስፋፋት ተከትሎ አየር መንገዶች በረራዎቻቸውን ለማቋረጥ ቢገደዱም የቫይረሱን ስርጭት ሊያቆሙት አልተቻላቸውም፡፡ ይልቁንም የአለም አገራት የአየር በረራዎቻቸውን ማቆማቸው ተከትሎ የመቶ ቢሊዮኖች ዶላር ኪሳራ ደርሶባቸዋል።
በዓለም ዙሪያ ባለፉት 3 ወራት ብቻ የበረራ ኢንዱስትሪው 252 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ የደረሰበት ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ፤ 550 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማጣቱን አስታውቋል፡፡ ከ101 ዓመታት በፊት (እ.ኤ.አ በየካቲት ወር 1919) የተጀመረውን ዓለም አቀፍ በረራ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የገታው ሲሆን እንዲህ ያለው የበረራ መቋረጥ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት እንኳን እንዳላጋጠመ “ፍላይት ራዳር 24” የተሰኘው ድረገጹ አመልክቷል፡፡
የድረገጹ ይፋ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በዓለም ዙሪያ ከሃያ አምስት ሺ የሚበልጡ የንግድ አውሮፕላኖች የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፤ በየዕለቱም ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጡ ተሳፋሪዎችን ያጓጉዛሉ፡፡ በሌላ አነጋገር ከዓለማችን አጠቃላይ ሕዝብ 0.1 በመቶ ያህሉ በየቀኑ በአውሮፕላን ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ይንቀሳቀሳል ማለት ነው፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ የአየር ትራንስፖርት እንቅስቃሴ በእጅጉ መቀነሱን የገለፀው ድረ ገፁ፤ በአሁኑ ወቅት በአለም ዙሪያ የበረራ እንቅስቃሴዎች ከቀድሞው ከነበረው 80 በመቶ ያህል ቀንሰዋል ብሏል፡፡ አሐዙ በአንዳንድ አካባቢዎች ወደ 90 በመቶ ያህል እንደሚደርስም ጠቁሟል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ሰሞኑን እንደተናገሩት፤ አየር መንገዱ ከሚንቀሳቀስባቸው 110 መዳረሻዎች ውስጥ በአሁኑ ወቅት እየተንቀሳቀስ የሚገኘው በአስራ ዘጠኙ ብቻ ነው፡፡ በኮሮና ሳቢያ ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ (550 ሚሊዮን ዶላር ገደማ) ኪሳራ እንደገጠመው የገለፀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የኮንትራት ተቀጣሪ ሰራተኞቹን የግዳጅ እረፍት እንዲወጡ ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚሁ መሰረትም የበረራ አስተናጋጆች፣ የምግብ ዝግጅት ባለሙያዎችና የትኬት ሽያጭ ሰራተኞች ለሶስት ወራት ያለ ደመወዝ የግዳጅ እረፍት እንዲወጡ ደብዳቤ ደርሷቸዋል፡፡
የጀርመን አየር መንገድ ሉፍታንዛ ከረቡዕ አንስቶ እስከ ነገ አፕሪል 12 ድረስ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጋቸው፤ በረራዎች ሙሉ በሙሉ የሰረዘ መሆኑን ያሳወቀ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ወደ ፍራንክፈርት በየዕለቱ የሚያደርጋቸውን በረራዎች አሁንም እንደ ቀጠለ ነው፡፡ የሉፍታንዛ አየር መንገድ ኃላፊን ካስተን ሸፓር ጠቅሶ ዶችቬሌ እንደ ዘገበው፤ “ዓለማችን ከኮሮና ቫይረስ ቀውስ በኋላ ሌላ አለም ትሆናለች፤ በተለይ የአየር መንገዱ ዘርፍ የተለየ አለም ይሆናል፡፡ በአሁኑ ወቅት በረራቸውን እንዲያቋርጡ ከተገደዱት የዓለም አየር መንገዶች መካከል የትኞቹ ጨርሶ ከገበያ እንደሚወጡና የትኞቹ ደግሞ መቆየት እንደሚችሉ የሚያውቅ ሰው የለም፤ ብለዋል፡፡
እንደ አለም አቀፉ የአቪዬሽን ማህበር (IATA) መረጃ በ2019 ሩብ ዓመት ከ7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ትርፍ የተገኘ ቢሆንም በዚሁ ተመሳሳይ ወቅት በ2020 ሩብ ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ በጠቅላላው የ39 ቢ.ዶላር ኪሳራ ይደርስበታል፡፡
አውሮፕላኖች ከበረራ ውጪ ሆነው አገልግሎት መስጠት ቢያቆሙም ከፍተኛ ወጪ ማስወጣታቸው አይቀሬ ጉዳይ ነው ያለው የ“ፍላይት ራዳር 24” መረጃ፤ የኢንሹራንስ ክፍያዎች፣ የደመወዝ ክፍያዎች እንዲሁም ለአውሮፕላን ጥገና የሚዳርጉ ወጪዎች ሁሉ ወጪውን ያንሩታል፤ አንድ አውሮፕላን ለሰባት ቀናት የማይበር ከሆነ ለመብረር እስኪሰናዳ ብቻ 60 የሥራ ሰዓቶች የሚጠይቅ ተጨማሪ ሥራ እንደሚኖርበት ይኸው መረጃ ያመለክታል:: አውሮፕላኖቹ መቆም ከጀመሩ በኋላ እንደየ አውሮፕላኖቹ አምራች ድርጅቶች ደረጃ በየሰባት፣ በየአስራ አምስት ቀናትና በየወሩ ፍተሻ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ አውሮፕላኖቹ በቆሙባቸው ቦታዎች የሞተር ፍተሻ ይደረጋል:: ጎሚዎቻቸው ጠፍጣፋ ቦታዎችን እንዳይፈጥሩ እያንዳንዱ አውሮፕላን በየሳምንቱ ወደ ኋላና ወደፊት መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡ ለሶስት ወራት የቆመ አውሮፕላን፤ በሦስት ወር አንድ ጊዜ ወደ ሰማይ መብረር ይኖርበታል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ሁሉ ከፍተኛ ወጪዎችን የሚያስከትሉ ናቸው ብሏል “ፍላይት ራዳር 24” በዘገባው፡፡
“ፍላይት ራዳር 24” ድረ - ገፁ፤ በዓለም ዙሪያ ያሉ በረራዎችን ለማየት የሚያስችል ድረገጽ ሲሆን የአውሮፕላን ምልክቶችን በመጫን፤ በዚያ ቅፅበት እየበረረ ስላለው አውሮፕላን መረጃ ለማግኘት የሚያስችልም ነው፡፡
ድረገጹ ከኮረና ወረርሽኝ በፊት በሰማይ ላይ የተጨናነቁ የአየር ትራፊኮችን ለማየት ያስችል ነበር፤ አሁን ግን በአየር ላይ የሚታዩት እጅግ ጥቂት አውሮፕላኖች ሲሆኑ አብዛኛዎቹም የዕቃ ማመላለሻ በረራዎች ናቸው፡፡  

Read 11531 times