Saturday, 11 April 2020 14:01

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፓርላማ በአብላጫ ድምጽ ጸደቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

    በኮማንድ ፖስት ሳይሆን በሚኒስትሮች ም/ቤት ይመራል
           አዋጁ የኮሮና ስርጭትን ለመግታት ብቻ እንዲያገለግል ተጠይቋል  
 
      ትናንት በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለ5 ወራት እንዲፀና የፀደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ የሰብአዊ መብት በማይጥስ መልኩ በጥንቃቄ እንዲተገበር የተጠየቀ  ሲሆን መንግስት በበኩሉ፤ "አዋጁ የኮሮናን ስርጭት ለመግታት አላማ ብቻ ይውላል፤ የሰብአዊ መብቶችም በጥብቅ የተጠበቁ ይሆናሉ" ብሏል፡፡
አዋጁ ያስፈለገው አሁን ባለው የቫይረሱ የስርጭት ሁኔታ በመደበኛ ህጐችና አሠራሮች መከላከል የማይቻልበት ሁኔታ በመፈጠሩ መሆኑን ያብራሩት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ አዋጁ ለታለመለት አላማ እንደሚውል አስታውቀዋል፡፡ ፡
ሀገሪቱ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 93 ስር እንድትተዳደር የሚያደርገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ በቀጣይ ዝርዝር መመሪያዎች እንደየ አካባቢዎች፣ከተሞችና ክልሎች ሁኔታ የሚወጡ ይሆናል ተብሏል፡፡
አዋጁ በዋናነት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጐች ወረርሽኙን ለማስተዳደር ከሚወሰዱ እርምጃዎች ጋር ተያይዞ መሠረታዊ የመኖሪያ ሁኔታቸው እንዳይናጋ ለመከላከል መታቀዱንም ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር በጉዳዩ ላይ የተወያዩ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
በአዋጁ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የፌደራል ዋና ጠቅላይ አቃቤ ህግ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ አዋጁ በዋናነት መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል አስፈላጊ እርምጃ በሚካሄድበት ጊዜ የተሻለ ነፃነትና አቅም እንዲኖረው ያስችለዋል ብለዋል፡፡
አክለውም፤በመንግስት ስልጣን ላይ ገደብ የሚያበጁ እንደ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ያሉት ለጊዜው ተፈፃሚነታቸው ቀርቶ ዋናው ትኩረት ወረርሽኙን መከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎች መወሰድ ላይ ይሆናል ብለዋል፡፡ በቀጣይም እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ስራ አስፈፃሚው መመሪያዎችን በማውጣት አዋጁን ያስፈጽማል፤ ኮማንድ ፖስት አይቋቋምም ብለዋል ወ/ሮ አዳነች፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው፤ ይህ አዋጅ ለታለመለት አላማ ብቻ እንዲውል የጠየቁ ሲሆን አዋጁ መውጣቱን ደግፈዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ የአቋም መግለጫ ያወጣው ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ፤ አዋጁ በትክክል እንዲፈፀም መንግስት ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪክ ማህበራትና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጋር ተባብሮ እንዲሠራ ጠይቋል፡፡  
ብየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ልዩ ስብሰባ፤ ለኮቪድ -19 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አባላትን ለመሰየም የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ በአብላጫ ድምፅ አጸደቀ።
ምክር ቤቱ በልዩ ስብሰባው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትና የጉዳትን መጠን ተከታትሎ በየጊዜው ለምክር ቤቱ ሪፖርት የሚያቀርብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አባላትን የሰየመው ከምክርቤቱ አባላት መካከል ነው።

Read 11943 times