Saturday, 11 April 2020 14:01

ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት በኮሮና ምክንያት ለከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ ይዳረጋሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 “1አፍሪካ ችግሩን ለመቋቋም ከ1 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ያስፈልጋታል”

               ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የሰሃራ በታች የአፍሪካ ሀገራት ባለፉት 25 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት የአለም ባንክ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ባወጣው ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
በመላው አፍሪካ ቀስ በቀስ እያሻቀበ በሚገኘው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት አገራቱ ወሳኝ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ካላደረጉና አለማቀፍ ድጋፍ ካላገኙ በስተቀር ለተወሳሰበ ማህበራዊ ቀውስ ሊዳረጉ እንደሚችሉ የአለም ባንክ ስጋቱን ገልጿል፡፡
ከሰሀራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ባለፈው አመት ካስመዘገቡት የኢኮኖሚ እድገት ዘንድሮ በ5.1 በመቶ እንደሚያሽቆለቁል የጠቆመው ሪፖርቱ፤ የንግድ ልውውጦች መቀዛቀዝንና የንግድ ግንኙነቶች መቋረጥን ተከትሎ እስከ 79 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያጡም ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
“የኮሮና ወረርሽኝ በአጠቃላይ በመላው አለም የከፋ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያደረሰ ቢሆንም በአፍሪካ ሀገራት ላይ የሚያሳድረው ጉዳት ግን ለንጽጽር የሚቀርብ አይደለም ብለዋል - የአለም ባንክ የአፍሪካ ተጠሪ ምክትል ፕሬዚዳንት ሃፊዝ ጋኒየም ሪፖርቱን አስመልክቶ ለሮይተርስ በሰጡት ቃል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ተጽእኖ ከሚያሳድርባቸው የኢኮኖሚ አውታሮች መካከል የቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሽ ሲሆን ከዘርፉ ላይ የሚደርሰው ጉዳት እስከ 24 ሚሊዮን የሚደርሱ አፍሪካውያንን ከስራ ውጪ የሚያደርግ መሆኑን ሪፖርቱ ጠቁሞ፤ በዚህም ሳቢያ ሃገራቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ድርቅ እንዲመቱ ያደርጋል ብሏል፡፡
አፍሪካ ከቻይናና ከቀረው አለም ጋር የምታደርገው የንግድ ግንኙነት መስተጓጐሉን ተከትሎ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ የሚደርስባት ሲሆን በተለይ ዋነኛ የቻይና ነዳጅ አቅራቢ የሆኑት ናይጀሪያንና አንጐላ በእጅጉ ለጉዳት እንደሚዳረጉ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ደግሞ ወትሮም ያለባቸው የፍላጐትና አቅርቦት አለመጣጣም ተባብሶ ለማህበራዊ ቀውስ ሊዳረጉ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡
የበሽታው ስርጭት ይበልጥ የሚስፋፋና በፍጥነት መቆጣጠር የማይቻል ከሆነም ሀገራቱ ለምግብ እጥረትና ቀውስ ሊጋለጡ ይችላሉ ያለው የዓለም ባንክ፤ ከውጭ ሀገራት ምግብ ገዝተው ወደ ሀገራቸው ለማስገባትም ችግር ይገጥማቸዋል ብሏል፡፡ ሀገራቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሚያስከትለውን መጠነ ሰፊ ችግር ተቋቁመው እንዲያልፉ ቻይና፣ አሜሪካና ሌሎች አበዳሪ ሀገራት የገቡበትን አጣብቂኝ ተገንዝበው የብድር ወለድ ስረዛ እንዲያደርጉና ብድራቸውን የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላቸው ባንኩ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
በተጨማሪም፤ የአፍሪካ ፖሊሲ አውጪዎች፤ በዚህ ወቅት የዜጎቻቸውን ህይወት ማቆየት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ አተኩረው እንዲሠሩ፣ የጤና አገልግሎት የሚጠናከርበትን መንገድ እንዲያመለክቱና ምግብ ለዜጐች ተደራሽ የሚሆንበትን አቅጣጫ እንዲተልሙ አሳስቧል የአለም ባንክ፡፡
መንግስታትም ለዜጐቻቸው ከወዲሁ ምግብ እንዲያድሉ፣ ገንዘብ እንዲሰጡና የተለያዩ ድጋፎችን በተለይ ቋሚ ስራ ለሌላቸው ዜጐች እንዲያደርጉ የአለም ባንክ መክሯል፡፡
የአለም ገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) በበኩሉ፤ የኮሮና ወረርሽኝ ተከትሎ አፍሪካ ችግሩን ለመቋቋም ከ1 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት አስታውቋል፡፡
ከአስሩ የአለም ፈጣን ኢኮኖሚ ባለቤቶች መካከል 6ቱ የአፍሪካ ሀገራት እንደነበሩ የጠቆመው የገንዘብ ድርጅቱ፤ የኮሮና ወረርሽኝ እነዚህን የእድገት ግስጋሴዎች ወደኋላ የሚጎትት ሆኗል ብሏል - በመግለጫው፡፡
ሀገራቱ በአሁኑ ወቅት የዜጐቻቸውን ህይወት መታደግ ላይ ማተኮር እንዳለባቸውም አይኤምኤፍ መክሯል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ በአገሪቱ መከሰቱን ተከትሎ እያስከተለ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት ጥናት እያደረገ መሆኑን ለአዲስ አድማስ የገለፁ ምንጮችን፤ እስካሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ550 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኪሣራ እንዳጋጠመውና የኢትዮጵያ አበባ ላኪዎች ማህበር ደግሞ 25 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማጣቱን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ አበባ ላኪዎች ማህበር ባወጣው መረጃ መሠረት፤ ቀደም ሲል በትንሹ በቀን 240 ቶን አበባ ወደተለያዩ የውጭ ሀገራት ይላክ የነበረ ሲሆን አለም በኮሮና ወረርሽኝ መጠቃቱን ተከትሎ በቀን ከ40 እስከ 50 ቶን አበባ ብቻ ወደ ውጪ እየተላከ መሆኑን ገልጿል፡፡


Read 11525 times