Sunday, 12 April 2020 00:00

“ከወረርሽኝ ያዳነ፣ ኢኮኖሚን ያልናደ” መፍትሔ!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

          - እንደ በሽታ ወረርሽኝ - የኢኮኖሚ ቀውስም ለኢትዮጵያ በጣም አደገኛ ነው፡፡
         - በ60ዎቹ ዓ.ም በተፈጠረው የነዳጅ ቀውስ ላይ፣ ድርቅና ረሃብ ተደርቦ፣ ስንት ጥፋት አስከተለ? ስንቱን መከራ አባባሰ?
         - የ77 ዓ.ም ረሃብ ብዙዎችን ቀጥፎ፣ የ82 ድርቅ ታከለበት፡፡ ችግር ከፋ፡፡ አገር ተሰንጥቃ ወደብ አልባ ሆነች፡፡
        - በ2007/8 የእህል ምርት በ4% ስለቀነሰ፤ 20ሚ ሰው ተራበ፡፡ የፖለቲካ ቀውስ ተባባሰ፡፡ ወደ ትርምስ አፋፍ ተደረሰ፡፡
             
           የኢትዮጵያ ሁኔታ፤ እስካሁን ደህና ይመስላል፡፡ ለእርሻ ከሚጠቅም የበልግ ዝናብ ጋር፤ ሞቃትና ፀሐያማ የአየር ሁኔታው አጋዥ ከሆነልን፤ ዶ/ር ዐቢይ እንዳሉት፣ በታሪክ የሚወደስ አኩሪ ስኬትን መቀዳጀት፣ የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው፡፡
በዝንጋታ አለመፍዘዝ፣ በጭፍን ይሉኝታ አለመደንዘዝ…እናም፣ የአቅማችን ያህል፣ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የጥንቃቄ ጥረት ማድረግ ይገባናል፡፡ አለመፍዘዝና አለመደንዘዝ ብቻ ሳይሆን፣ አለመቃዠትና አለመደናበርም ያስፈልጋል፡፡
“ከወረርሽኝ ያዳነ፣ ኢኮኖሚን ያልናደ” ተብሎ የሚወደስ መፍትሔ የሚገኘው በዚህ መንገድ ነው፡፡
ከቫይረስና ከበሽታ ወረርሽኝ ለማምለጥ፣ በጭፍን ኩረጃ መደናበር፤ ደካማውን ኢኮኖሚ ማድቀቅ፤ መዘዙ ለዘንድሮ ብቻ ሳይሆን፣ ለበርካታ አመታት የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ጉሮሮን ይዘጋል፤ የነገ የኑሮ ገመድን ይበጥሳል፡፡ ህይወትንና አገርን ያሳጣል፡፡
የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ለድሃ አገራት እጅግ አደገኛ በሽታ እንደሆነ፣ ከአገራችን የቅርብ ጊዜ ታሪክ መማር እንችላለን፡፡  
በ1965 እና 66 ዓ.ም፤ ከነዳጅ ገበያ መዘጋት ጋር ተያይዞ በተከሰተው አለማቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ ላይ፣ ድርቅ እና ረሃብ ተደርቦበት፣ የኢትዮጵያ ችግሮች ተባብሰው፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ መከራዋ ለስንት ዓመታት እንደተዘመተ አስታውሱ፡፡
በ1977 ዓ.ም ድርቅና ረሃብም፤ ብዙ ሰው አልቋል፡፡ መዘዙ ግን ከዚህም አልፏል፡፡ ኢኮኖሚዋና ፖለቲካዋ ክፉኛ ከመቃወሱ የተነሳ፣ አገራችን፣ ነባር ሕልውናዋን ጠብቃ ለመቀጠል አቅም አጥታ ተሰንጥቃለች፡፡ ወደብ አልባ ሆናለች፡፡
ሌላው ይቅርና፤ በ2007/8 ዓ.ም የተከሰተው ድርቅ፤ ጠቅላላ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ባያንኮታኩትም እንኳ፤ ስንቱን ችግር እንዳባባሰ መመልከት ይቻላል፡፡
የእህል ምርት በ4% ስለቀነሰ ብቻ፣ 20 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ለረሃብ ተጋልጠዋል፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን፣ የአገሪቱ የኑሮ ቅሬታ ተባብሶ፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ ምንኛ በፍጥነት እንደተስፋፋና እንደተወሳሰበ ልንዘነጋው አንችልም፡፡
በድርቁ ማግስት፣ አገሪቱን ወደ ትርምስ አፋፍ ያደረሳት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ፤ እስከ ቅርብ ወራት ድረስ፣ እለት ተእለት ኑሮን የሚያጐሳቁል የዘወትር ዜና ነበር፡፡
በሺ የሚቆጠሩ  ሰዎች፣ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በርካታ ሚሊዮን ዜጐች ከኑሮ ተነቅለው ተሰደዋል፡፡
ግን አደጋው ከዚህም የከፋ ሊሆን ይችል እንደነበር አይካድም፡፡ ህዝብን በጅምላ ከሚጨርስ፣ አገርንም በትርምስ ከሚያፈርስ ከባድ አደጋ ነው ለጥቂት የተረፍነው፡፡
ሌሎች በርካታ አገራት አልተረፉም፡፡ ከሶማሊያ እስከ ሶሪያ፣ ከየመን እስከ ሊቢያ፣ ከማጡ ወደ ረመጡ ገብተዋል፡፡
በአጭሩ፣ በነባር ድህነት ላይ ትንሽ የኢኮኖሚ ችግር ሲጨመርበት፣ እንደ ኢትዮጵያ ለመሳሰሉ አገራት፣ “ጊዜያዊና አላፊ ችግር” አይሆንላቸውም፡፡
እናም፤ የበሽታ ወረርሽኝ፣ ለኢትዮጵያ ድርብ አደጋ ነው፡፡
በህመም ህይወትን ይቀጥፋል፡፡ ኢኮኖሚን አድቅቆ ለረሃብ፣ ለባሰ እልቂትና ለትርምስ ያጋልጣል፡፡
በሽታውን ስንከላከል፣ ኢኮኖሚን በሚገድል መንገድ ሳይሆን፣ ኢኮኖሚን በሚያድን መንገድ ይሁን፡፡ ደግሞም ይቻላል፡፡ እስካሁንም፣ ከጥቂት አነስተኛ ስህተቶች በስተቀር፣ ዋና ዋናዎቹ የጥንቃቄ ጥረቶች ትክክለኛና ውጤታማ እንደሆኑ እያየን ነው፡፡
ከበሽታ የሚታደጉ፣ ኢኮኖሚን የማይገድሉ እንደነዚህ አይነት ጥረቶች ላይ፣ በጥንቃቄና በጥበብ፣ በብልሃትና በትጋት እንበርታ፡፡



---------------------------------------

Read 2608 times